ክፍል አንድ
አብዛኛውን ጊዜ በአንግሊካን ቤተ ክርስቲያን ላይ ከሚነሱ ትችቶች መካከል ትልቁን ሥፍራ የሚይዘው የንጉሥ ሄነሪ ስምንተኛ(Henry VIII) ትዳር መፍረስ ምክንያት የእንግሊዝ ቤተክርስቲያን በዛ መንሥኤ የተጀመረች አድርጎ መሞገት ነው። ይሄ ደሞ የቤተ ክርስቲያንቱን ታሪክና አስተምህሮን በአግባቡ ካለማወቅ የሚነሳ ትችት ተደርጎ በብዙ ምሑራን ዘንድ የሚወሰድ ነው። ከክርስትና ውጭ ያሉ ሃይማኖታዊ ድርጅቶች(ሙስሊሞች፣ አርዮሳውያን፣ ሰባልዮሳውያን…) ክርስትና የጀመረው በንጉሥ ቆሰንጠንጢኖስ ነው ከሚል የአፈ ታሪክ የማይለይ ሙግትና በብዙ የተወሳሰበውን የታሪክ፣ የፖለቲካ እና የሥነ መለኮት እይታን ለማቅለል የሚሞከር ከንቱ ትግል ነው በማለት መግለጽ ይቻላል።
በዚህ ጽሑፍ ደግሞ ከመጀመሪያው የንጉሥ ሄነሪ ስምንተኛ እና የንግሥት ካትሪን ትዳር ለመመልከት እንሞክራለን። የንጉሥ ሄነሪ ስምንተኛ ታላቅ ወንድም የነበረው አርተር በ1501 ካትሪንን አገባ። አምስት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በሕመም ምክንያት ይሞታል። ያገባትም የ16 ዓመቷ ልጃገረድ ንግሥት ካትሪን ባልቴት ትሆናለች። የንግሥት ካትሪንንና የልዑል አርተር ጋብቻ በስፔንና እና በእንግሊዝ መሃል ጥሩ የሆነ ፖለቲካዊ ግንኙነት ፈጥሮ ነበር። ንጉሥ ሄነሪ ስምንተኛም ይህን ፖለቲካዊ ግንኙነት እንዲቀር ስላልፈለገ ካትሪንን ያገባታል። እንደ ብዙዎች ምልከታ መሠረት ዘንድ ይህ ትዳር የተሳካ አልነበረም ይባላል። ወቅቱም የህፃናት ሞት ከፍተኛ የነበረበት ጊዜ ስለነበር ከወለዳቸው ሦስት ወንዶችና ሶስት ሴቶች ልጆች መሀል 1 ልዕልት ማርያም (Mary I “Bloody Mary”) ነበር የተረፈችው።(ስለ Mary በክፍል ሁለት በስፋት እንመለከታለን።) በዚህ ትዳር ውስጥ የሚተካውን ወንድ ልጅ በማጣቱ በትዳሩ ላይ ጥያቄ ማንሳት ጀመረ።
ለዚህም ይሆነው ዘንድ በኦሪት ዘሌዋውያን 20:21፦
“ ‘ማንኛውም ሰው የወንድሙን ሚስት ቢያገባ አድራጎቱ ርኩሰት ነው፤ ወንድሙን አዋርዷልና፣ ያለ ልጅም ይቀራሉ።
በሚለው ቃል ላይ በመመስረት የወንድሙን ሚስት በማግባቱ እንደተረገመና ትክክለኛ ጋብቻ እንዳልሆነ በ1527 ዓ.ም ለሮማን ካቶሊክ ቤተክርስቲያን እና ለፖፕ ቀለሜንጦስ ሁለተኛ በጥያቄ መልክ ማቅረብ ጀመረ። እዚህ ታሪክ ላይ ልብ ልንለው የሚገባን ነገር ቢኖር በአንግሊካን ቤተክርስቲያን ሆነ በሮማን ካቶሊክ ፍቺ እንደማይፈቀድ ነው። ነገር ግን የንጉሡ ሄነሪ ስምንተኛ ጥያቄ የፍቺ ጥያቄ ብቻ አልነበረም ጋብቻው መጀመርያውኑ ትክክለኛ ጋብቻ ነው ወይ የሚል ነው ።(annulment ‘a legal procedure within secular and religious legal systems for declaring a marriage null and void’) በዚህም የጋብቻውን ትክክለኛነት ጠይቆ ትክክለኛ አለመሆኑ በሮማን ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያኗ ህግ ከተረጋገጠ ጋብቻው መጀመሪያውኑ ትክክለኛ አይደለም ተብሎ ሊወሰንለት ይችላል። ለዚህም በተለያዩ ጊዜያቶች በሮማን ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ይህ ስርዐት ሲተገበር ታይቷል። ለምሳሌ ታዋቂው አሜሪካዊው ፖለቲከኛ ቴድ ኬኔዲ(Ted Kennedy) በጋብቻው ወቅት ታማኝ አለመሆኑን አምኖ የሃያ አራት ዓመት ጋብቻውን በሮማን ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ፊት ትክክለኛ ጋብቻ እንዳልነበር ተቆጥሮለት ተለያይተዋል። ሌላኛው ደግሞ ዮሴፍ ኬኔዲ ሁለተኛ(Joseph Kennedy II, 2007 እ.ኤ.አ) እና ታዋቂው ፈረንሳያዊው ገዥ ናፖሊዮ ቦናፓርቲ እና የንጉሥ ኤድዊግ(Eadwig 959 እ.ኤ.አ አካባቢ) ለዚህ ታሪክ ተጠቃሽ ናቸው።
ነገሩን ለየት የሚያደርገው ደግሞ በዚህ ዘመን እንደሚታወቀው አይነት ፍቺ በመካከለኛው ዘመን በነበሩት ሰዎች ዘንድ አልነበረም። የጋብቻን ትክክለኛነት ማረጋገጥ እና በመጀመሪያውኑ ጋብቻ እንዳልነበር ማስመስከር (Annulment / Declaration of Nullity) የተለመደ ነበር። በዚህም ዘመንም የሮማን ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በህግዋ ውስጥ ይህ ጋብቻ ነው ለመባል ማሟላት ያለበትን ነገሮች በዝርዝር ተቀምጧል።(the code of canon of law 1095-1107) ለምሳሌ ያህል ሁለቱም ተገቢዎች በፈቃዳቸው መሆን አለበት ቤተሰብ(የደም ዝምድና) ያላቸው መሆን የለባቸውም። ማንኛውም ክህነት የተቀበለ መሆን የለበትም (ቄስ ,ጳጳስ) የመሳሰሉትን ህጎች የያዘ ነው። ስለዚህ የንጉሥ ሄነሪ ስምንተኛ ጥያቄም ከዚህ የተለየ አልነበረም።
ለጋብቻው ትክክለኛ አለመሆን እንደ ምክንያት አድርጎ ያስቀመጠው ነገር፦
የወንድሙን ሚስት ማግባት ትክክለኛ ጋብቻ አይደለም በመፅሐፍ ቅዱስ ህግ ጋር ይጋጫል።
የወንድሙን ሚስት በፖፕ ጁሊየስ ሁለተኛ ፈቃድ(papal Dispensation) ማግባቱ ትክክል አይደለም።
ንግሥናውን የሚተካ ወንድ ልጅ አለማግኘቱን እንደ እርግማን ይቆጥረው ነበር።
እነዚህን እንደ ምክንያት አድርጎ በማቅረብ ለፖፕ ቀለሜንጦስ ሁለተኛ ጥያቄውን አቀረበ ነገር ግን የጠበቀው መልስ በተቃራኒ ሆኖ ይህን ሊፈቅድለት አልወደደም። ምክንያቶቹም ተብለው የሚነሱት፦
አንደኛ፦ የንጉሥ ሄነሪ ሚስት ካትሪን በጊዜ ኃያል የሚባለው የሮማን ገዢ የሆነው የስፔን ንጉሥ የቻርለስ አምስተኛ አክስት(Holy roman Empire) ስለ ነበረች ነበር።
ንጉሥ ሄነሪ ጥያቄውን ባቀረበበት በ1527 በዛው ዓመት በቁጥር ከሃያ ሺ የሚበዙ ደሞዝ ያልተከፈላቸው ወታደሮች(አስራ አራት ሺህ የሚሆኑ ጀርመናዊ ሉተራውያን ወታደሮች እና ስድስት ሺህ ስፔናውያን እና ጣሊያንናዊ ወታደሮች) ንቅናቄ የሮማን አገዛዝና ያደከመ፣ ከሃምሳ አምስት ሺህ ወደ አስር ሺህ የሮም ህዝቡ ቁጥር የቀነሰበት፣ እስከ ሁለት መቶ የሚሆኑት ወታደሮች ፖፑን ለመጠበቅ የሞቱበት፣ ፖፑም በአማፅያኑ እጅ ገብቶ በእስር የነበረበት ጊዜና መንበረ ጴጥሮስ በትልቅ ሀዘን ውስጥ የሆነበትም ጊዜ ነበር። ከዚህም ክስተት(the sack of Rome 1527) ዘጠኝ ወር ያህል ፖፑ ታግተው ከቆዩ በኃላም ከገበሬዎች ጋር በመመሳሰል ያመለጡበት ጊዜ ነበር። በዚህ መሐልም ግን የንጉሥ ሄነሪ የጋብቻ ጥያቄ አልተመለሰም ነበር። ጋብቻውን ትክክለኛ አይደለም ቢሉ በዚያን ጊዜ የሮማን ንጉሥ የነበረው ቻርለስ አምስተኛ ስለሚያስተዳድሩአቸው ከእርሱ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ስለሚያሻክር ፈርተውም ነበር።
ሁለተኛው፦ ምክንያት ንጉሥ ሄነሪና ካትሪንን ያጋባው የቀድሞ ፖፕ ጁሊየን ሁለተኛ ስለነበር የእሱን ስልጣን መቃወም ስላልነበረበት ነበር።
ሦስተኛው፦ ምክንያት ደግሞ ካትሪን ከአርተር (ከንጉሥ ሄነሪ ወንድም) ጋር በጫጉላ ወቅት ስጋዊ ተራክቦ አልነበረንም ማለቷ ነው። ጋብቻ የሚፈፀመው በስጋዊ ተራክቦ ነው ተብሎ ስለሚታመንም ካትሪን የመጀመሪያ ጋብቻዋ ወቅት ስጋዊ ተራክቦ ካልነበር ከንጉሥ ሄነሪ ያላት ጋብቻ ትክክለኛ ይሆናል። ሆኖም እርሱዋ ይህንን ብትልም የልዑል አርተር የቅርብ ጓደኞች ግን ከእርሷ በተቃራኒ ቆመው ነበር የተናገሩት።
በዚህ ምክንያት ለንጉሥ ሄነሪ አለመፈቀዱ ንጉሡን አስቆጥቶታል። ስለዚህም በ1534 ዓ.ም እራሱን በእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን ዋና የቤተ ክርስቲያን የበላይ ሃላፊ አድርጎ በመሾም ከፖፕ ቀለሜንጦስ ሁለተኛ ቤተ ክርስቲያኒቱን ለያት። ንጉሡ ራሱን የቤተክርስቲያን የበላይ አድርጎ በሾመበት ወቅት ብዙ ቢሾፖች ዲያቆናቶች እና መነኩሴ በመቃወማቸው ምክንያት በእምነታቸው ሰማዕታት ሆነዋል። በ1538 ዓ.ም ፖፕ ጳውሎስ ሶስተኛ ከሮማን ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን አወገዘው(excommunicate) ተደረገ።
ከዚያም በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለ ከአርክ ቢሾፕ ቶማስ ክራመር ጋር በመሆን ደግሞ ጋብቻ ትክክለኛ እንዳልሆነ አጸደቀ። ግን ብዙም ሳይቆይ ደግሞ በ1533 አናን አገባ። የሄነሪ ጋብቻ ታሪክ በዚህ አያበቃም እስከ ዘመኑ መጨረሻ ድረስ ስድስት ሚስቶች በተለያዩ ምክንያቶች ነበሩት። ቢሆንም ዘሩን የሚተካ ልጅ ከኤድዋርድ ውጭ አላገኘም ነበር። ኤድዋርድን ቢተካውም ስድስት አመት ከገዛ በኋላ በ15 ዓመቱ በህመም ሞቷል። በዚህ ሁሉ ታሪክ በስተ መጨረሻም ግን ልንረዳው የሚገባው የእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን በንጉሥ ሄነሪ ጊዜ ፕሮቴስታንት እንዳልነበረችና ሄነሪ ካቶሊክ እንደ ነበር። ሉተርንም የሚቃወም ጽሑፍ “ሰባቱ ቅዱስ ምስጥራት መከላከያ”(Defense of the Seven Sacraments/Assertio Septem Sacramentorum) በማለት ጽፎ የነበር መሆኑን ማወቅ አለብን። በዚያም ከፖፕ ሊዮ ኤክስ በ1521 ዓ.ም “የእምነት ጠባቂ”(“Defender of the Faith”) የሚል ስም ተሰጥቶት ነበር። በዚህም ካቶሊክ ሆኖ ነበርም የሞተው። በንጉሥ ሄነሪ ጊዜ በአንግሊካን ቤተ ክርስቲያን ንግሡ መጥቶ የአስተምህሮ ለውጥ በምንም አይነት መልኩ አላደረገም ነበር። ስለዚህ አንግሊካን ቤተ ክርሰቲያን በንጉሡ ተመሥርታለች የሚለው አስተምህሮ በዚህ ውድቅ ይሆናል።
ነገር ግን የአንግሊካን ቤተክርስቲያን በ597 ዓ.ም በፖፕ ጎርጎርዮስ አማካኝነት የካቲቤሪውን ቅዱስ አውግስጢኖስ ወደ እንግሊዝ በመላክ ወደ ሮም ቤተክርስቲያን ውስጥ ተጠቅልላ ባካተተቻት ከአንድ ሺህ ዓመታት በኃላ ቤተክርስቲያኒቱ ከሮም ውጭ ሆነች። ንጉሥ ሄነሪ የእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያንን ከሮማን ካቶሊክ እንደ ቀድሞዋ መለየቱ ለተሐድሶው የማይካድ ጥቅም ቢኖረውም ነገር ግን ያደረጋቸው ነገሮች እና ሕይወቱ ሙሉውን የአንግሊካን ቤተ ክርስቲያንን ታሪክ ለመግለጽ የማይችል መሆኑን መገንዘብ አለብን። ምክንያቱም የአንግሊካን ቤተ ክርስቲያንን ለመረዳት ከዚህም ያለፈ የተወሳሰበ የታሪክና የስነመለኮት ጥልቀት ውስጥ ዘልቆ መግባት አለብን። የአንግሊካን ቤተ ክርስቲያን መልክ ማቆጥቆጥ የተጀመረው በ1536 ዓም የአስር የሃይማኖት አንቀጾች (Ten Articles) (የካቶሊክ እምነት ያለው ትንሽ በተሃድሶ ሃሳብ ተጽዕኖ ያለበት) ከዚያም 1539 ዓም ስድስት የሃይማኖት አንቀጾች (six articles of faith) (አጥባቂ የካቶሊክ እምነት የያዘ) ጽሁፎቹ በሄነሪ አጽዳቂነት ቢጸሠፋም ትክክለኛው የአንግሊካን መልክ የያዘበት ዘመን በኤድዋርድ 6ኛ (1547-1553) እና በንግሥት ኤልሳቤጥ(1558-1603) የንግሥና ዘመን ነበር። በተጨማሪም የሰላሳ ዘጠኝ የሃይማኖት አንቀጾች (Thirty Nine Articles of Religion) እና በጸሎት መጽሐፉዋ(The Book of Common Prayer) ላይ የአንግሊካን ቤተ ክርስቲያን መልክ በትልቁ መሰረት ያደርጋል። ከእነዚህ መጽሐፍት ጋር ያልተዋወቃችሁ ሰዎች ታነቡት ዘንድ በእጅጉ እናበረታታችኋለን። ይቀጥላል።
ዋቢ ምንጮች
1] Weir, Alison. Henry VIII: The King and His Court. pp. 178-217.
2] Muhlbach, Louise. Henry VIII and His Court. pp. 53-68.
3] Guy, John. The Tudors: A Very Short Introduction. pp. 50-65.
4] Newcombe, D. G. Henry VIII and the English Reformation. pp. 35-51.
5] Bray, Gerald. Anglicanism: A Reformed Catholic Tradition. pp. 15-21.
6] Encyclopaedia Britannica. “Sack of Rome (1527).


