atheist

ኑ መጽሐፍ ቅዱስን እንተዋወቀው

ሰላም። በመጀመሪያ ከእኛ ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብ ዝግጁና ፍቃደኛ በመሆናችሁ እግዚአብሔርን እናመሰግናለን። ምናልባት ይህን በእጃችሁ ያለውን መጽሐፍ አዲስ እና እንግዳ ሆኖባችሁ ይሆናል። ዛሬ በዚህ ጽሑፍም በእጃችሁ የሚገኘው መጽሐፍ ቅዱስ የሚለው መጽሐፍ ምንድነው የሚለውን በአጭሩ የምንተዋወቅ ይሆናል። ክርስቲያኖች 66ቁጥሮች ርዝማኔ ያላቸው መጻሕፍ አላቸው። እነዚህም መጻሕፍትበሁለት ክፍል ይቀመጣሉ። እነርሱም ብሉይ ኪዳን እና አዲስ ኪዳን በማለት ይከፈላሉ። ብሉይ ኪዳን 39 አዲስ ኪዳን ደግሞ 27 መጻሕፍትን ይዘዋል። መጽሐፍ ቅዱስ የሚለው ቃል የእንግሊዝኛው አቻ ትርጉም “ባይብል” የሚለው “ቢብሊያ” ከሚለው የጽርእ(የግሪክ) ቃል የመጣ ሲሆን “መጻሕፍት” ማለት ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በአንድ ግለሰብ እንዲሁም በጥቂት ዓመታት ውስጥ የተጻፈ መጽሐፍ ሳይሆን፣ በብዙ መቶ ዘመናት ውስጥ በተለያዩ ቋንቋዎች ከ40 በላይ ጸሐፊያን ያሉትና በ1500 ዓመታት ውስጥ የተጻፉ የተለያዩ መጻሕፍት ስብስብ ነው፡፡ በእርሱም ውስጥ እግዚአብሔር በቀጥታ ከህዝቡ ጋር ይነጋገራል፣ በሌላ ጊዜ ደግሞ በቅዱሳን ሰዎች ሐሳብና ቃል አማካኝነት ሲናገር፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ በዘመን መጨረሻ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ተግልጦ ተናግሮናል። በመጽሐፍ ቅዱስ ምሑራን የጊዜ አመዳደብ መሰረት የመጀመርያው ክፍል ከክርስቶስ ልደት በፊት በ1400 ዓ.ዓ. አካባቢ እንደሆነና የመጨረሻው ደግሞ ከክርስቶስ ልደት በኋላ በ90 ዓ.ም. አካባቢ እንደተጻፈ ይታመናል። መጽሐፍ ቅዱስን ስናነብ ማወቅ ካሉብን ልዩ ሁኔታዎች መካከል መጽሐፍ ቅዱስ እንደ ቁርአን እና ሌሎች አይነት መገለጥ እንዳልሆነ ነው። ይህን ለመረዳት ጳውሎስ ለመንፈሳዊ ልጁ ለጢሞቴዎስ በላከው 2ኛ ጢሞቴዎስ 3፥16-17 እንዲህ ሲል ይናገራል፦ “የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ፥ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል።” በዚህ ክፍል ላይ ጳውሎስ የእግዚአብሔርን ቃል፣θεόπνευστος “ቴኦፕኔውስቶስ” መሆኑን ሲናገር የቃሉ ፍቺ θεό “ቴኦ” ማለት “እግዚአብሔር” እና πνευστος “ፕኔውስቶስ” ማለትም “መንፈስ” ከሚሉ ሁለት የጽርእ ቃል የተገኘ ነው፤ በአንድ ላይ ሲነበቡም “እስትንፋሰ እግዚአብሔር” የሚል ነው። ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስ ሁሉ በእግዚአብሔር መንፈስ እስትንፋስ የተጻፈ ነው፤ የሰዎችን ልብ ሁሉ የሚቀይር እንዲሁም በእምነት የሚያነብ የእርሱን ድምፅ ይሰማል። በግልጽ ልብና አእምሮ ካነበብነው፣ እግዚአብሔር እኛ በማናቀው መንገድ ሲናገረን እንገኛለን። ስለዚህ ይህ የያዛችሁት መጽሐፍ ሌሎች ጋር እንዳለ አይነት መጽሐፍ እንዳልሆነ በእነዚህ መንገዶች ትረዳላችሁ። የመጻሕፍቱ ዝርዝር # መደቦች የመጽሐፍቱ ብዛት መጻሕፍቱ 1 የሙሴ ሕግ (ፔንታቱክ) 5 ዘፍጥረት – ዘዳግም 2 የታሪክ መጻሕፍት 12 እያሱ – አስቴር 3 ቅኔ/ግጥም 5 እዮብ – መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን 4 አበይት ነብያት 5 ኢሳይያስ – ዳንኤል 5 ደቂቅ ነብያት 12 ሆሴዕ – ሚልኪያ       ➡ አጠቃላይ ብሉይ ኪዳን 39 6 ወንጌላት 4 ማቴዎስ – ዮሐንስ 7 የታሪክ መጽሐፍ 1 ሐዋርያት ሥራ 8 የጳውሎስ መልእክታት 13 ሮሜ – ፊልሞና 9 አጠቃላይ መልእክታት 8 ዕብራውያን – ይሁዳ 10 ራዕይ(አቡቀለምሲስ) 1 ራዕይ ➡ አጠቃላይ አዲስ ኪዳን 27 ➡ ጠቅላላ ድምር 66 መጽሐፍ ቅዱስ በአጭሩ የመጽሐፉ ዋና ዋና መልእክቶች፦ በኦሪት ዘፍጥረት ምዕራፍ 1 ላይ ዓለምን የፈጠረ እግዚአብሔር እንደሆነ ገልጾ በማሳየት ይጀምራል። በዚህም እግዚአብሔርም ፍጥረታትን በስድስት ቀን እንደፈጠረ በሰባተኛው ቀን እንዳጠናቀቀ እንመለከታለን። በዚህም ውስጥ “ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር” በማለት ሰው የሚለውን ከፍጥረቱ ሁሉ መካከል ልዩ አድርጎ እንደሰራው፣ ስማቸውንም አዳም እና ሔዋን እንደነበሩ እንመለከታልን። በዚህም የፍጥረት መጽሐፍ ላይ የምንረዳው የዓለማትና የእኛ ሠሪ አንዱ እግዚአብሔር ብቻ እንደሆነ አስተዋውቆ ይጀምራል። ነገር ግን ብዙም ሳይቆይ በቅድስና የተመሰገነውን አምላክ አዳምና ሔዋን ኃጢአት ሰርተው እንዳሳዘኑት በዚህም ከእግዚአብሔርም ጋር የነበራቸው ግንኙነት ሲያጡ እንመለከታለን። ከዚያም እግዚአብሔርም በሙሴ በማስነሳት(ዘፀአት 7) በእርሱ በኩል አሥርቱን ትእዛዛት(በዘፀአት 20) እንዴት እንደሰጣቸው እንመለከታለን። በታሪክ መጻሕፍት ውስጥ የኪዳኑ ሕዝብ ኪዳን ከሌላቸው ጣኦት አምላኪያን ጋር የነበራቸውን ውጣ ውረድና የእግዚአብሔርን ፍቅሩ ጽድቁን ባደረጉት የቁጣው ፀሐይ ደግሞ ባልፈለጉት ላይ እንደወጣች በሰፊው ተከትቦ እናገኛለን። በእያንዳንዱ ታሪኮችን ውስጥ የምንገነዘበው ነገር እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ያለው የታመነ ፍቅሩ ነው፤ እርሱም በደንዳናው ሕዝበ እስራኤል ላይ ምን ያህል ታጋሽ የሆነ ፍቅር እንዳለው በስፊው ተቀምጦልናል። ለምሳሌ፦ እንደ ኖኅ፣ አብርሃም፣ ሙሴ፣ ኢዮብ፣ ዳዊት እና ሌሎች ያሉ የተወሰኑ ሰዎችን በልዩ መንገድ ጠርቶ ይህ ኃያል አምላክ በየዘመናቱ ፍቅሩን ሲገልጥ እናገኘዋለን። እነዚያ የመረጣቸው የኪዳኑ ሕዝብ በኋላም ከአመጻቸው የተነሳ ለእግዚአብሔር ሕግ መታዘዝ እንዳቃታቸው ስለዚህም እግዚአብሔር በመጨረሻው ዘመን የሰው ልጆች ያፈረሱትን የድሮውን ኪዳን ለመፈጸም እና አዲስን ኪዳን ከህዝቡ ጋር ለማቆም አንድያ ልጁን የላከው። ይህ አዲሱ ኪዳን ግን በደካማ የሰው ልጆች ሥራና ታዛዥነት ላይ የተመሰረተ ሳይሆን፣ በሰማያዊው አዳኝ፣ በዘላለማዊው ቃል በሆነው በመሲሕ ላይ ነው። ይህ መሲሕ በብሉይ ኪዳን ዘመን ጌታችን ኢየሱስ ከድንግል ከመወለዱ ከ700 ዓመት በፊት በነብዩ ኢሳይያስ ላይ ተነግሮለታል። አሁን የትንቢቱ ፍጻሜው ቀረበና እርሱ ራሱ በትልቁ የሮም ግዛት እጅጉን ደሳሳና አናሳ በሆነች ቤት የተወለደ ሆኖ መጣ።(ዮሐንስ 1፥14) አዎን ከላይ እንዳልነው እግዚአብሔር ኃያልና የከበረ ነው፣ ነገር ግን እርሱን እንድናውቀው ግን የባሪያን መልክ ያዘ።(ፊልጵስዩስ 2) የክርስቶስን ሕይወትና አገልግሎት ስናነብ ሳለ በአእምሯችን ሥሑት ትርጓሜ እንዳይፈጠር ሥነመለኮታችንን የተቃኘ መሆን አለበት። በዚህም የሚያግዟችሁን ጥሩ መጋቢያን መፈለግ ጥሩ ነው። አንዳንድ መናፍቃን አምላክ አይደለም ይልቅ ሰው ብቻ ነበር በማለት ሊያስቱ ይሞክሩ ይሆናል። በዚህም ትምህርት ንፋስ ተውስደን “ኢየሱስ ሰው ብቻ ነበር” ካልን፣ ሙሉ በሙሉ እንስታለን። “ሰው አይደለም አምላክ ብቻ ነበር” ካልንም ሰውነቱን ክደናልና ከሃዲያን እንባላለን። የነገረ ክርስቶስ ጥናት ስፊ ውቂያኖስ ነው። ይህንንም ሐሳብ መምህራን ሲገልጡ “…ጥናቱም ልክ ቀጭን ምላጭ ላይ እንደመራመድ ማለት ነው። በግራ ብንወድቅ አውጣኬ አለ። በቀኝ የወደቅን የሆንን ከሆነ ድግሞ ንስጥሮስ አለ…” በማለት ያስቀምጣሉ። ታዲያ ነገረ ክርስቶሳችን ጥናቱ ያልተቃኘ ከሆነ መርማሪው እንዳይወድቅ ይፍራ። ጥሩ አንባቢ ክርስቲያን ግን በቀጭኗ ምላጭ ላይ በቀስታ ይራመዳል። ስለዚህ በዚህን መጽሐፍ ቅዱስን ጥናት ወቅት አውዱን ያልሳተ ትርጓሜ መጠቀም፣ ተዓማኒ የሚባሉ ማብራሪያውችን ማገላበጥ፣ ታሪካዊ፣ ስዋሰዋዊ እና ቁማዊን ትርጉም ምን እንደሆነ ከሥሩ ማጥናት እጅጉን ያስፈልጋል።  ማጠቃለያ በመጨረሻም አንድ ሰው ለምን ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር መተዋወቁ ለሕይወቱ ምን ይጠቅመዋል? ያለ እንደሆነ አንደኛ፦ ኢየሱስ አምላኩና ጌታው እንደሆነ እንደሞተ እና በሦስተኛው ቀን ከሙታን እንደተነሳ ያምናል። ሁለተኛ፦ ክርስቶስ በከፈለው የቤዛነት ሥራ በኩል ብቻ የዘላለም ሕይወት አለህ ስለሚለው ነው። ሦስተኛ ፦ ሰው በሕግ ሥራ ፈጽሞ ሊጸድቅ ስለማይችል፣ በዚህም የተከፈለለትን የእዳ ክፍያ በክርስቶስ አምኖ ተስፋውንም በአለቱ ላይ ስለሚተክል ነው።(ሐዋ 4፥12) ስለዚህ አሁን ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ያልተዋወቃችሁ ወገኖች ይህንን ታላቅ መጽሐፍ አግኝታችሁ ታነቡት ዘንድ እናበረታታችኋለን። በቃሉ ውስጥ የተገለጠውን እግዚአብሔርን ፊት ለፊት የምናይበት ሕያው መስታወት ቅዱስ ቃሉ ብቻ በመሆኑ በውጤቱ ክርስቶስ ኢየሱስን በማመን የሚገኘውን የዘላለምን ሕይወት እንደምታገኙ ባለ ሙሉ ተስፋዎች ነን፡፡

ኑ መጽሐፍ ቅዱስን እንተዋወቀው Read More »

የነገረ ምክንያትነት ህግ(Law of Causality) – ክፍል 1

“ሰነፍ በልቡ፦ አምላክ የለም ይላል”  — መዝሙር 14፥1 የነገረ ምክንያትነት ህግ(Law of Causality) የፍልስፍና እና የሳይንሱ መሠረታዊ መርህ ሲሆን ማንኛውም ውጤት የራሱ የሆነ መንስኤያዊ እርሾ እንዳለው የሚያትት መርህ ነው። ምክንያትነት አመላካችነቱ የሆነ ነገር እንዲከሰት የሚያደርገውን ውጤት አዘል መንስኤን የሚያሳይ ነባቤ ቃል ነው። ክርስቲያናዊው የነገረ መለኮት እና የፍልስፍናው ሊቅ ዊሊያም ሌን ክሬግ ወደ ህላዌ የመጣ አካል ሁሉ ለመገኘቱ ምክንያት የሚሆን ከሳች ሐይል እንዳለ ይናገራል። በተጨማሪም ማንኛውም ነገር ከምንም እንደማይገኝ ይናገራል[1]፦ “ከምንም ምንም ነገር ሊከሰት አይችልም አልያም አንድ ነገር ከምንም ተነስቶ ህልው ሊሆን አይችልም” አንድ ነገር ከምንም ተነስቶ ሊከሰት ካልቻለ ለህልውናው መንስኤ የሆነ አንድ ምክንያት እንዳለ አመላካች ነው።[2] ነገር ግን ይህ አይነቱ ነባቤ ቃል የማይዋጥላቸው በፍልስፍናው አለም ያሉ ሳይንቲስቶች መኖራቸው የማይካድ ሐቅ ነው። ለምሳሌ ቴዎረቲካል ፊዚሽያኑ አሌክስ ቪሌንኪን ሁሉ አቀፉ ሕዋ በቅጽበታዊ(ድንገታዊ) ክሳቴው ከወናዊ ኳንተም (quantum vacuum) የመነጨ መሆኑ እና ይህም ደግሞ ሕዋ ከምንም ነገር ሊመጣ እንደሚችል የሚያሳይ ነው በማለት ይናገራል።[3] ይህንን ሐሳብ በመደገፍ ዴቪድ አልበርት ወናዊ ኳንተም (quantum vacuum) ነገሮች ከምንም መፈጠር እንደሚችሉ ያሳያል የሚል እምነት አለው።[4] በሌላ በኩል ደግሞ በሐይማኖታዊው ፍልስፍና የሚታወቀው ሪቻርድ ስዊንበርን አንድ ነገር ድንገት ያለ ምንም ምክንያት ህልውና አገኘ የሚለው ሙግት ሕጸጻዊ እና ኢ ምክንዮአዊ ሙግት ነው ሲል የእነ ዴቪድ አልበርት እና የአሌክስ ቪሌንኪንን እሳቤ ክፉኛ ይቃወማል።[5] በተለይ እውቁ እና በሳይንሱ አለም በክኑሳዊያን ተመራማሪዎች ትልቅ ተቀባይነት ያገኘው የታላቁ ፍንዳታ ቴዎሪ(Big Bang Theory) ሕዋ ኅሉቃዊ ጅማሮ(finite beginning) ያለው መሆኑን የሚያሳየውን መርህ ስንመለከት ይበልጡን አለም ካለመኖር ወደመኖር ያመጣት ከሳች ሐይል እንዳለ አመላካች ቴዎሪ ሁኖ እናገኘዋለን። ስለዚህ ሕዋ ያልነበረበት ካለ ለመገኘቱ ውጤት ከሳች አንድ ሐይል መኖሩን አንጡራዊ ቅድመ ሁኔታ ሁኖ እናገኘዋለን። ዊሊያም ሌን ክሬግ ይህ አይነቱ ከሳች አካል በአራት ወሳኝ ባህሪያተ ነጥቦች ይገልጹታል፥[6] 1) ጊዜአልቦ ማንነት(Timeless):- በታላቁ ፍንዳታ ቴዎሪ(Big Bang Theory) ጊዜ የሚባለው መስፈሪያ በራሱ ህላዌ ያገኘ በመሆኑ ጊዜን አስገኚው አካል ከጊዜ ውጭ ወይም ዘላለማዊ የሆነ ምንነት ነው 2) ኢ-ቁሳዊነት(Immaterial):- ቁሳዊ አካላት የተፈጠሩበት ምክንያት ስለሆነ ምክንያታዊው አካል ኢ-ቁሳዊነትን ባህሪዎት ገንዘቡ ያደረገ ነው 3) ልዕለ ሀይል ያለው(Powerful being):- ይህን ለቁጥር የማይመችን ፍጥረታዊው አለም ከዚህ አካል የተፈጠሩ እንደሆኑም መጠን ምክንያት እና ውጤት ከሳቹ አካል ወደር አልባ ሐይል ያለው መሆን አለበት 4) እኔ ባይ ቅዋሜ ማንነት ያለው(Personal):- የህዋ አስገኝ አካል እኔነት ያለው አካል መሆኑ መላው ፍጥረተ አለሙን ወደ መኖር ማምጣቱ ንቃተ ፈቃድ፣ እውቀት እና ስሜት ያለው አካል መሆኑን አመላካች ነው ይህን ያለንበትን ሕዋ ስናስብ ዝም ብሎ ድንገት የተከሰተ ሳይሆን ለመከሰቱ የሆነ አካል ከጀርባ እንዳለ የተፈጥሮውን አለም ባህሪዎት ስንመለከት የምንረዳው ጉዳይ ነው። ይህ ከሳች ሐይል ደግሞ ምንም ነገር(Nothing) ሊሆን ፈጽሞ አይችልም። የክኑሳዊው ሙግት ይሄንኑ የሚያስረዳ ነው፦ ስለዚህ፦ ሕዋ ከሳች ምክንያተ መንስኤ አለው ይህ የምንመለከተው አጽናፈ አለም በሆነ ጊዜ ህልው የሆነ እና ለመገኘቱ ጅማሮ ያለው ክስተት ነው። በሕዋ ውስጥ ያለ ማንኛውም ቁሳዊ አካል፣ ህያው ፍጥረት ሆነ ማንኛውም በዚህ ክበብ ውስጥ ያለ ክስተት ሁሉ ለመገኘቱ አስገኚ ምክንያት አለው። ለምሳሌ ዛፎችን ስንመለከት ለዛፎች መገኘት የዘሮች መተከል ወይም መዘራት እንደ ዋነኛ ከሳች ግብአት ነው። ይሄም ሐሳብ በፍልስፍናውም ምክንዮ ሆነ በሳይንሱ አለም ተቀባይነት አለው። ሌላው ሕዋ እራሱ ኅልቁ አላፊ ጊዜ ሊኖረው አይችልም። ምክንያቱም በእውናዊው አለም ፍጹም ኅልቁአዊ ኑባሬ (actual infinity) የሚባል ነገር እንደሌለ የሳይንሱ እና የፍልስፍናው አለም ያምናል። ክስተቶች ሁሉ ኅልቁ መሳፍርት ቢኖራቸው አጽናፈ አለሙ አሁን ያለበት ሁኔታ ላይ መድረስ እንደማይችል ይናገራሉ። በዚህ ምክንያት ሕዋ ወይም አጽናፈ አለም በሆነ ጊዜ የተከሰተ በመሆኑ ለክስተቱ ደግም ምክንያት የሌለው መንስኤያተ ምክንያት (uncaused cause) እንደሚኖረው አረጋጋጭ እውነታ ነው። እግዚአብሔር አምላክ ክስተቶች እና ለነገሮች ሁሉ ከሳች ምክንያት የሌለው መንስኤያተ ምክንያት (uncaused cause) ነው ስንል ከላይ እንደተመለከትነው ዘላለማዊ የሆነ፣ ቁሳዊ ያልሆነ፣ የማስገኘት ልዕለ ሐይልን የተጎናጸፈ እና እኔ ባይ ማንነታዊ ቅዋሜ ያለው አካል መሆኑን የሚገልጽ ነው። ሊቁ የኒሳው ጎርጎርዮስ ስለ እግዚአብሔር ዘላለማዊነት ሲናገር፦“የእግዚአብሔር መለኮታዊ ባህሪዎት ያልተፈጠረ እና ዘላለማዊ የሆነ፤ ምንጊዜም የነበረ፣ ያለና የሚኖር ጅማሬ እና ፍጻሜ የሌለው፤ በጊዜ እና በቦታ ያልተወሰነ፣ የማይለዋወጥ ሁልጊዜም ያው የሆነ አምላክ ነው። ስለዚህ እግዚአብሔር አምላክ የሌለበት ጊዜና ሁኔታ አለ ሊያስብለን የሚያስችል ምክንያት ፈጽሞ አይኖርም” ሊቁ አምላክ ዘላለማዊ እና ለጅማሮው መንስኤ የሌለው በጊዜ የማይወሰን መሆኑን ይናገራል። ቅዱሱም መጽሐፍ እንደሚናገረው ማንኛውም ነገር ከአለመኖር ወደ መኖር ከመምጣታቸው በፊት እግዚአብሔር አምላክ እንደነበር ይናገራል፦ “ተራሮች ሳይወለዱ፥ ምድርም ዓለምም ሳይሠሩ፥ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ አንተ ነህ።”  መዝሙር 90፥2 ስለዚህ እግዚአብሔር አምላክ ዘላለማዊ ከሆነ ከጊዜ ውጭ የሆነ እና ጊዜ የሚባለውን መስፈሪያ አስገኚ ነው። የነገረ ምክንያትነት ህግ(Law of Causality) በጊዜ ውስጥ የተገደበ ማንኛውም ነገር ለመገኘቱ ምክንያት አለው ስለሚል ፍጥረታዊው አለም ደግሞ ለመገኘቱ  ጅማሮ እና ከጀርባው ከሳች ምክንያታዊ ሐይል እንዳለው የሚያሳይ ነው። በሌላ በኩል ከጊዜ ውጭ የሆነው ከሳች ሐይል ግን ለመገኘቱ ምክንያት ሊኖረው ፈጽሞ አይችልም። ምክንያቱም ስለ ከሳቹ ሐይል ስናወራ ዘላለም የሚባለው ገደብ የለሽ ጊዜ ስለሚነሳ እና ከጊዜ ውጭ ስለሆነ ራሱ ምክንያት የሌለው መንስኤያተ ምክንያት(Uncaused Cause) ነው እንላለን። ይሄም ክኑሳዊው ሙግት ያረጋግጥልናል። ማጣቀሻዎች፦ [1] Craig, William Lane. The Kalam Cosmological Argument. Wipf and Stock Publishers, 2000. page 303[2] “ከምንም ነገር ምንም ሊከሰት አይችልም/ex nihilo nihil fit”[3] Alex Vilenkin (Many Worlds in One): Suggests that the universe could arise spontaneously from “nothing.” (Page 181-182)[4] David Albert (Quantum Mechanics and Experience): Critiques modern redefinitions of “nothing” in scientific contexts. (Page 142-144)[5] Swinburne, Richard, The Existence of God /Clarendon Press, 2004, Page 50-53, 138-140/[6] Craig, William Lane. The Kalam Cosmological Argument. Wipf and Stock Publishers, 2000, page 182,87,228

የነገረ ምክንያትነት ህግ(Law of Causality) – ክፍል 1 Read More »

Scroll to Top