FAQ

የሥላሴ ሥነ አመክንዮአዊ ችግር(LPT)

የሥላሴ አስተምህሮ በተለያዩ ሰዎች በተለያዩ ዘመናትም ትችት ሲደርስበት መስማት የተለመደ ነው። ይህንንም ትምህርት በሰዎች አእምሮ ዘንድ ፈጽሞ መረዳት የማይቻልና በተለይም “አምላክ/God/” የሚለውን ቃል በተለያዩ አይነት በመጠቀም በሥነ አመክንዮ ዘንድ መሠረታዊ ችግር እንዳለበት ለማሳየት ይሞክራሉ። ሙግቱ እንዲህ ይቀርባል፦ 1) ክርስቲያኖች አብ አምላክ ነው፣ ወልድ አምላክ ነው፣ መንፈስ ቅዱስ አምላክ ነው ይላሉ። 2) ነገር ግን “አምላክ” የሚለው ቃል በአንድ ጊዜ አብን፣ ወልድን እንዲሁም መንፈስን የሚያመለክት ከሆነ አንድን ምንነት ያለውን አምላክ በቋሚነት ሊያመለክት አይችልም። 3) ስለዚህ ይህ አስተምህሮው ከአመክንዮአዊ ወጥነት ይልቅ አሻሚ የሆነ ግራ አጋቢ ትርጉም ላይ እንዲሆን ያደርገዋል። መልስ ይህ ሙግት መሠረት ያደረገው እኛን(ክርስቲያኖችን) “አምላክ” የሚለውን ቃል የተለያዩ አካላትን በተለያየ መንገድ መገለጫ እንደሆነ በማመልከት እንደምንል አድርጎ ሙጉቱን በሥሑት ነጥቦች ላይ ገንብቶ የጀመረ ነው። ማለትም “አምላክ” አብን በአንድ መንገድ፣ ወልድን በሌላ ፣ እንዲሁም መንፈስ ቅዱስን በሌላ እንደማለት ነው። ነገር ግን ይህ አይነቱ መረዳት በሥላሴ የአምላክነት ባሕርይ ወይም “ግጻዌ መለኮት” መረዳት ውስጥ የማያታወቅ ነው። ታዲያ አምላክ ማለት ግን በኑባሬው ያለማቋረጥ አንድ፣ የማይከፋፈል መለኮታዊ ማንነትን የሚያመለክት መለኮታዊ ባህርይ የሚል ቃል ነው። ስለዚህ ክርስቲያኖች “አብ አምላክ ነው”፣ “ወልድ አምላክ ነው” እንዲሁም “መንፈስ አምላክ ነው” ሲሉ የአምላክነት ባህርይን ያለውን አካላቶቹ አሏቸው በዚህም እያንዳንዱ አካል ያንን የመለኮትነትን ባህርይ ሙሉ በሙሉ ይጋራሉ ማለታቸው ነው። ይህም አንድ አምላክ ብቻ አለ ሲባል፣ አንድ ምንነት እንዳለ እያረጋገጡ ነው። አንዱ አምላክ በሦስት አካል የተገለጠ ነው ሲሉ ደግሞ አንድ አምላክ በአካል ሦስት ነው እያሉ ነው። አብ፣ ወልድ እና መንፈስ አንድ አምላክ ናቸው ሲሉ እያንዳንዱ አካል መለኮታዊ ባህርይ እንዳለው እያስረገጡ ነው። ስለዚህ፣ ከላይ በሥላሴ ላይ በተነሳው የሶስቱ ነጥብ ሙግቶች፣ “አምላክ” የሚለውን ቃል ውይይት ከመገባቱ በፊት ከተብራራ፣ የሚመጣውን የትኛውንም ጥያቄ ይመልሳል ማለት ነው።

የሥላሴ ሥነ አመክንዮአዊ ችግር(LPT) Read More »

ኑ መጽሐፍ ቅዱስን እንተዋወቀው

ሰላም። በመጀመሪያ ከእኛ ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብ ዝግጁና ፍቃደኛ በመሆናችሁ እግዚአብሔርን እናመሰግናለን። ምናልባት ይህን በእጃችሁ ያለውን መጽሐፍ አዲስ እና እንግዳ ሆኖባችሁ ይሆናል። ዛሬ በዚህ ጽሑፍም በእጃችሁ የሚገኘው መጽሐፍ ቅዱስ የሚለው መጽሐፍ ምንድነው የሚለውን በአጭሩ የምንተዋወቅ ይሆናል። ክርስቲያኖች 66ቁጥሮች ርዝማኔ ያላቸው መጻሕፍ አላቸው። እነዚህም መጻሕፍትበሁለት ክፍል ይቀመጣሉ። እነርሱም ብሉይ ኪዳን እና አዲስ ኪዳን በማለት ይከፈላሉ። ብሉይ ኪዳን 39 አዲስ ኪዳን ደግሞ 27 መጻሕፍትን ይዘዋል። መጽሐፍ ቅዱስ የሚለው ቃል የእንግሊዝኛው አቻ ትርጉም “ባይብል” የሚለው “ቢብሊያ” ከሚለው የጽርእ(የግሪክ) ቃል የመጣ ሲሆን “መጻሕፍት” ማለት ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በአንድ ግለሰብ እንዲሁም በጥቂት ዓመታት ውስጥ የተጻፈ መጽሐፍ ሳይሆን፣ በብዙ መቶ ዘመናት ውስጥ በተለያዩ ቋንቋዎች ከ40 በላይ ጸሐፊያን ያሉትና በ1500 ዓመታት ውስጥ የተጻፉ የተለያዩ መጻሕፍት ስብስብ ነው፡፡ በእርሱም ውስጥ እግዚአብሔር በቀጥታ ከህዝቡ ጋር ይነጋገራል፣ በሌላ ጊዜ ደግሞ በቅዱሳን ሰዎች ሐሳብና ቃል አማካኝነት ሲናገር፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ በዘመን መጨረሻ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ተግልጦ ተናግሮናል። በመጽሐፍ ቅዱስ ምሑራን የጊዜ አመዳደብ መሰረት የመጀመርያው ክፍል ከክርስቶስ ልደት በፊት በ1400 ዓ.ዓ. አካባቢ እንደሆነና የመጨረሻው ደግሞ ከክርስቶስ ልደት በኋላ በ90 ዓ.ም. አካባቢ እንደተጻፈ ይታመናል። መጽሐፍ ቅዱስን ስናነብ ማወቅ ካሉብን ልዩ ሁኔታዎች መካከል መጽሐፍ ቅዱስ እንደ ቁርአን እና ሌሎች አይነት መገለጥ እንዳልሆነ ነው። ይህን ለመረዳት ጳውሎስ ለመንፈሳዊ ልጁ ለጢሞቴዎስ በላከው 2ኛ ጢሞቴዎስ 3፥16-17 እንዲህ ሲል ይናገራል፦ “የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ፥ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል።” በዚህ ክፍል ላይ ጳውሎስ የእግዚአብሔርን ቃል፣θεόπνευστος “ቴኦፕኔውስቶስ” መሆኑን ሲናገር የቃሉ ፍቺ θεό “ቴኦ” ማለት “እግዚአብሔር” እና πνευστος “ፕኔውስቶስ” ማለትም “መንፈስ” ከሚሉ ሁለት የጽርእ ቃል የተገኘ ነው፤ በአንድ ላይ ሲነበቡም “እስትንፋሰ እግዚአብሔር” የሚል ነው። ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስ ሁሉ በእግዚአብሔር መንፈስ እስትንፋስ የተጻፈ ነው፤ የሰዎችን ልብ ሁሉ የሚቀይር እንዲሁም በእምነት የሚያነብ የእርሱን ድምፅ ይሰማል። በግልጽ ልብና አእምሮ ካነበብነው፣ እግዚአብሔር እኛ በማናቀው መንገድ ሲናገረን እንገኛለን። ስለዚህ ይህ የያዛችሁት መጽሐፍ ሌሎች ጋር እንዳለ አይነት መጽሐፍ እንዳልሆነ በእነዚህ መንገዶች ትረዳላችሁ። የመጻሕፍቱ ዝርዝር # መደቦች የመጽሐፍቱ ብዛት መጻሕፍቱ 1 የሙሴ ሕግ (ፔንታቱክ) 5 ዘፍጥረት – ዘዳግም 2 የታሪክ መጻሕፍት 12 እያሱ – አስቴር 3 ቅኔ/ግጥም 5 እዮብ – መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን 4 አበይት ነብያት 5 ኢሳይያስ – ዳንኤል 5 ደቂቅ ነብያት 12 ሆሴዕ – ሚልኪያ       ➡ አጠቃላይ ብሉይ ኪዳን 39 6 ወንጌላት 4 ማቴዎስ – ዮሐንስ 7 የታሪክ መጽሐፍ 1 ሐዋርያት ሥራ 8 የጳውሎስ መልእክታት 13 ሮሜ – ፊልሞና 9 አጠቃላይ መልእክታት 8 ዕብራውያን – ይሁዳ 10 ራዕይ(አቡቀለምሲስ) 1 ራዕይ ➡ አጠቃላይ አዲስ ኪዳን 27 ➡ ጠቅላላ ድምር 66 መጽሐፍ ቅዱስ በአጭሩ የመጽሐፉ ዋና ዋና መልእክቶች፦ በኦሪት ዘፍጥረት ምዕራፍ 1 ላይ ዓለምን የፈጠረ እግዚአብሔር እንደሆነ ገልጾ በማሳየት ይጀምራል። በዚህም እግዚአብሔርም ፍጥረታትን በስድስት ቀን እንደፈጠረ በሰባተኛው ቀን እንዳጠናቀቀ እንመለከታለን። በዚህም ውስጥ “ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር” በማለት ሰው የሚለውን ከፍጥረቱ ሁሉ መካከል ልዩ አድርጎ እንደሰራው፣ ስማቸውንም አዳም እና ሔዋን እንደነበሩ እንመለከታልን። በዚህም የፍጥረት መጽሐፍ ላይ የምንረዳው የዓለማትና የእኛ ሠሪ አንዱ እግዚአብሔር ብቻ እንደሆነ አስተዋውቆ ይጀምራል። ነገር ግን ብዙም ሳይቆይ በቅድስና የተመሰገነውን አምላክ አዳምና ሔዋን ኃጢአት ሰርተው እንዳሳዘኑት በዚህም ከእግዚአብሔርም ጋር የነበራቸው ግንኙነት ሲያጡ እንመለከታለን። ከዚያም እግዚአብሔርም በሙሴ በማስነሳት(ዘፀአት 7) በእርሱ በኩል አሥርቱን ትእዛዛት(በዘፀአት 20) እንዴት እንደሰጣቸው እንመለከታለን። በታሪክ መጻሕፍት ውስጥ የኪዳኑ ሕዝብ ኪዳን ከሌላቸው ጣኦት አምላኪያን ጋር የነበራቸውን ውጣ ውረድና የእግዚአብሔርን ፍቅሩ ጽድቁን ባደረጉት የቁጣው ፀሐይ ደግሞ ባልፈለጉት ላይ እንደወጣች በሰፊው ተከትቦ እናገኛለን። በእያንዳንዱ ታሪኮችን ውስጥ የምንገነዘበው ነገር እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ያለው የታመነ ፍቅሩ ነው፤ እርሱም በደንዳናው ሕዝበ እስራኤል ላይ ምን ያህል ታጋሽ የሆነ ፍቅር እንዳለው በስፊው ተቀምጦልናል። ለምሳሌ፦ እንደ ኖኅ፣ አብርሃም፣ ሙሴ፣ ኢዮብ፣ ዳዊት እና ሌሎች ያሉ የተወሰኑ ሰዎችን በልዩ መንገድ ጠርቶ ይህ ኃያል አምላክ በየዘመናቱ ፍቅሩን ሲገልጥ እናገኘዋለን። እነዚያ የመረጣቸው የኪዳኑ ሕዝብ በኋላም ከአመጻቸው የተነሳ ለእግዚአብሔር ሕግ መታዘዝ እንዳቃታቸው ስለዚህም እግዚአብሔር በመጨረሻው ዘመን የሰው ልጆች ያፈረሱትን የድሮውን ኪዳን ለመፈጸም እና አዲስን ኪዳን ከህዝቡ ጋር ለማቆም አንድያ ልጁን የላከው። ይህ አዲሱ ኪዳን ግን በደካማ የሰው ልጆች ሥራና ታዛዥነት ላይ የተመሰረተ ሳይሆን፣ በሰማያዊው አዳኝ፣ በዘላለማዊው ቃል በሆነው በመሲሕ ላይ ነው። ይህ መሲሕ በብሉይ ኪዳን ዘመን ጌታችን ኢየሱስ ከድንግል ከመወለዱ ከ700 ዓመት በፊት በነብዩ ኢሳይያስ ላይ ተነግሮለታል። አሁን የትንቢቱ ፍጻሜው ቀረበና እርሱ ራሱ በትልቁ የሮም ግዛት እጅጉን ደሳሳና አናሳ በሆነች ቤት የተወለደ ሆኖ መጣ።(ዮሐንስ 1፥14) አዎን ከላይ እንዳልነው እግዚአብሔር ኃያልና የከበረ ነው፣ ነገር ግን እርሱን እንድናውቀው ግን የባሪያን መልክ ያዘ።(ፊልጵስዩስ 2) የክርስቶስን ሕይወትና አገልግሎት ስናነብ ሳለ በአእምሯችን ሥሑት ትርጓሜ እንዳይፈጠር ሥነመለኮታችንን የተቃኘ መሆን አለበት። በዚህም የሚያግዟችሁን ጥሩ መጋቢያን መፈለግ ጥሩ ነው። አንዳንድ መናፍቃን አምላክ አይደለም ይልቅ ሰው ብቻ ነበር በማለት ሊያስቱ ይሞክሩ ይሆናል። በዚህም ትምህርት ንፋስ ተውስደን “ኢየሱስ ሰው ብቻ ነበር” ካልን፣ ሙሉ በሙሉ እንስታለን። “ሰው አይደለም አምላክ ብቻ ነበር” ካልንም ሰውነቱን ክደናልና ከሃዲያን እንባላለን። የነገረ ክርስቶስ ጥናት ስፊ ውቂያኖስ ነው። ይህንንም ሐሳብ መምህራን ሲገልጡ “…ጥናቱም ልክ ቀጭን ምላጭ ላይ እንደመራመድ ማለት ነው። በግራ ብንወድቅ አውጣኬ አለ። በቀኝ የወደቅን የሆንን ከሆነ ድግሞ ንስጥሮስ አለ…” በማለት ያስቀምጣሉ። ታዲያ ነገረ ክርስቶሳችን ጥናቱ ያልተቃኘ ከሆነ መርማሪው እንዳይወድቅ ይፍራ። ጥሩ አንባቢ ክርስቲያን ግን በቀጭኗ ምላጭ ላይ በቀስታ ይራመዳል። ስለዚህ በዚህን መጽሐፍ ቅዱስን ጥናት ወቅት አውዱን ያልሳተ ትርጓሜ መጠቀም፣ ተዓማኒ የሚባሉ ማብራሪያውችን ማገላበጥ፣ ታሪካዊ፣ ስዋሰዋዊ እና ቁማዊን ትርጉም ምን እንደሆነ ከሥሩ ማጥናት እጅጉን ያስፈልጋል።  ማጠቃለያ በመጨረሻም አንድ ሰው ለምን ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር መተዋወቁ ለሕይወቱ ምን ይጠቅመዋል? ያለ እንደሆነ አንደኛ፦ ኢየሱስ አምላኩና ጌታው እንደሆነ እንደሞተ እና በሦስተኛው ቀን ከሙታን እንደተነሳ ያምናል። ሁለተኛ፦ ክርስቶስ በከፈለው የቤዛነት ሥራ በኩል ብቻ የዘላለም ሕይወት አለህ ስለሚለው ነው። ሦስተኛ ፦ ሰው በሕግ ሥራ ፈጽሞ ሊጸድቅ ስለማይችል፣ በዚህም የተከፈለለትን የእዳ ክፍያ በክርስቶስ አምኖ ተስፋውንም በአለቱ ላይ ስለሚተክል ነው።(ሐዋ 4፥12) ስለዚህ አሁን ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ያልተዋወቃችሁ ወገኖች ይህንን ታላቅ መጽሐፍ አግኝታችሁ ታነቡት ዘንድ እናበረታታችኋለን። በቃሉ ውስጥ የተገለጠውን እግዚአብሔርን ፊት ለፊት የምናይበት ሕያው መስታወት ቅዱስ ቃሉ ብቻ በመሆኑ በውጤቱ ክርስቶስ ኢየሱስን በማመን የሚገኘውን የዘላለምን ሕይወት እንደምታገኙ ባለ ሙሉ ተስፋዎች ነን፡፡

ኑ መጽሐፍ ቅዱስን እንተዋወቀው Read More »

የባሕርዩ ምሳሌ?

በማህበራዊ ድህረገጽ ላይ ሲዘዋወሩ ከነበሩ ሙግቶች መካከል አንድ ጥያቄ ተቀምጦ ነበር። ይኼም ሙግት ኢየሱስ ፍጡር ነው ከሚል ከአንድ አርዮሳዊ በተለምዶ የይሖዋ ምሥክሮች ቤተ ጎራ የሚመደብ ነው። ኢየሱስ ፍጡር ነው ያለውም ከዚህ ጥቅስ የተነሳ ነበር ጥቅሱ እንዲህ ይነበባል፦ “እርሱም የክብሩ መንጸባረቅና የባሕርዩ ምሳሌ ሆኖ፥ ሁሉን በስልጣኑ ቃል እየደገፈ፥ ኃጢአታችንን በራሱ ካነጻ በኋላ በሰማያት በግርማው ቀኝ ተቀመጠ፤”  — ዕብራውያን 1፥3 ምሳሌ ሲባል ሰው በእግዚአብሔር ምሳሌ ተፈጥሯል እናም ኢየሱስ የእግዚአብሔር ምሳሌ ነው። ስለዚህ ፍጡር ነው የሚል ድምዳሜን አስቀምጦም ነበር። መልስ ምሳሌ የተባለበት ምክንያት ኢየሱስ በትክክል አብን የሚገልጥ መሆኑን ለማመልከት እንጂ ፍጡር መሆኑን ለማሳየት አይደለም፡፡ ኢየሱስ የእግዚአብሔር አብ ምሳሌ መኾኑ የተጠቀሰበት አምላክነቱን ለክርክር ሊቀርብ በማይችልበት ኹኔታ የሚገልጥ ሌላ ጥቅስ በዕብራውያን መልዕክት ውስጥ ይገኛል(ዕብራውያን 1፥2 ዕብራውያን 1፥8 እና ሌሎችም)። ከጠያቂያችን ጥቅስ ግን ተነስተን በአጭሩ መልስ እንስጥ፡- “እርሱም የክብሩ መንጸባረቅና የባሕርዩ ምሳሌ ሆኖ፥ ሁሉን በስልጣኑ ቃል እየደገፈ፥ ኃጢአታችንን በራሱ ካነጻ በኋላ በሰማያት በግርማው ቀኝ ተቀመጠ፤”  — ዕብራውያን 1፥3 “የባሕርዩ ምሳሌ” ተብሎ የተተረጎመው “ሁፖስታሴዎስ ካራክቴር” የሚል የግሪክ ሐረግ ሲሆን ካራክቴር የአንድን ነገር ትክክለኛ፣ ያልተሸራረፈ፣ ከዚያኛው አካል ያላነሰ፣ እኩል የሆነ ማንነት የሚያሳይ ነው፡፡ ይህ “ምሳሌ” ከዚያኛው አካል ጋር በኹሉም ረገድ ፍጹም ተመሳሳይ ነው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሚነግረን ወልድ ከአብ ልዩ መኾኑን፤ ነገር ግን ደግሞ ከአብ ጋር ፍጹም እኩል መኾኑን ከምንም ዓይነት ጥርጣሬ በፀዳ ኹኔታ የሚገልጥ ክፍል ነው፡፡[1] ስለዚህ ይሄ ክፍል ኢየሱስ ፍጡር ነው ተብሎ የቀረበው መለኮታዊ ባሕርዩን ገላጭ እና ይልቅም አምላክነቱን የሚያሳይ ሆኖ እናገኘዋለን። ማጣቀሻ [1] Vines Complete Expository Dictionary of Old and New Testament Words, Thomas Nelson Publishers, Nashville Camden New York, 1984, P. 319.

የባሕርዩ ምሳሌ? Read More »

መጽሐፍ ቅዱስ ብቻን እንጠያየቅ – ክፍል 2

ጥያቄ፦ እሺ ይሄን ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ያልከውን እንደ ሙግትህ ልቀበልህና መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ እየተባለ የተለያየ ሥነ-አፈታት ላይ የተለያየ ምልከታ ትደርሳላችሁ? ለዚህ ስነ አፈታት ዳኛችሁ ማነው? መልስ፦ በጣም ጥሩ ጥያቄ ነው። ይሄ እኮ ጥያቄ ቢነሳ በእናተም ዘንድ ያለ ነው።(ትውፊት ያላችሁ እናተም ይሄንን ተመሳሳይ ክሌም ማንሳት እንችላለን።) እኛ ነገሩን ሥነ መለኮታዊ ክፍፍሎሽ(Theological Triage) ብንሰራለት እንኳን። ወደፊት የማስረዳህ ይሆናል። አሁን ግን ወደ ጥያቄህ መልስ ልለፍልህ። ጥያቄ፦ እሺ መልስ፦ መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ እያላችሁ ሥነ አፈታት ላይ ብዙ ትለያያላችሁ። የሚል ጥያቄ ነው የተነሳው። ያው የሥነ-አፈታት መርሖ በመጽሐፍ ቅዱስ ብቻ መነጸር ሲታይ የራሱ የሆነ መንገድን አለው። ለሶላ ስክሪፕቹራ አማኝ መጠየቅ የሌለብህና ማሶገድ ያለብህ ጥያቄ፦ ስህተት1፦ እንደው ሰው እንደፈለገ እየፈታ እየተረጎመ መጠቀም አለበት የሚል እሳቤ አለው። ስህተት2፦ የመጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ችግር ይሄን ያስከትላል። ስህተት1 እና ስህተት2፦ የሁለታችሁ ዳኛችሁ ማነው ታዲያ? ለስህተት1 እና ለስህተት2 ድምዳሜህ ምላሻችን፦ መልስ፦ እነዚህ ነገሮች ለመጽሐፍ ቅዱስ ብቻ አማኝ ለሆነ ሰው የሚቀርብ ጥያቄ ነው ብዬ አላምንም።[እንዴት የሚለውን ወደ በኋላ እናየዋለን] ታዲያ ለዚህ መነሾ የመጀመሪያው መፍትሄ መርሕ የምንለው የሥነ አፈታት መርሖ በመባል ይታወቃል። ይህ ደግሞ አንደኛው መንገድ ነው(አውዳዊ ንባብ ንፅፅራዊ ምልከታ ነው።) ጥያቄ፦ ቆይ ቆይ ይህንን ታዲያ ሌላኛው ጎራም እነሱም ክሌም ያደርጉታል ግላዊነት አይደለም ወይ? መልስ1፦ ጥሩ ጥያቄ ነው። ግን የተሳሳትከው ነገር በተለይ በተለይ HGL(ጽሑፋዊ፣ ሰዋሰዋዊ እና ታሪካዊ ዳሰሳ) እንደነ ዲኤ ካርሰን የመሳሰሉ ምሑራን ይህ አይነቱ ትርጓሜ መጠቀም ይበልጥ ከግላዊነት ይልቅ ወደ ጽኑ ትርጓሜ እንደሚያመጣ ያስረዳሉ። ምክንያቱም ይሄ አይነቱ መንገድ ሥነ አፈታቱ በአውዱ ሲታይ፦ ➙ አውዳዊ ያልሆነው ተሟጋችህ ይወድቃል ➙ ከዛም ሻገር ስትል ሰዋሰዋዊ መንገድ በመጠቀም ታርመዋለህ፣ ➙ታሪካዊ መንገድን ትጠቀማለህ። ይሄ አይነቱ ሥነ አፈታት ለግላዊነት ወጥመድ ነው ማለት የማይቻልበትን መንገድ ቀጣይ ከማነሳቸው ካልኩህ ጋር አያይዤ አቀርባቸዋለሁ። መልስ 2፦ ሌላው በእነ R.C Sproul እና John Piper ተቀባይነት ያለው ሲሆን ይህህም መንፈሳዊውን ትርጓሜ ነው። ይሄ የሚወሰደው በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ነው። እንደ R.C Sproul እና John Piper አይነቱ የሚሉት መንፈስ ቅዱስ ለመጽሐፍ ቅዱስ ትርጓሜ እንዳንስት ትልቁን ሚና በአማኞች ዘንድ ከጥናት አንጻር እንደሚሰራ ይናገራሉ። ➙ ታሪካዊ የጉባኤዎች ውሳኔ እና መግለጫዎች ለሥነ አፈታት ቀጥተኛ ተዛምዶ ባይኖራቸውም(ማለትም በእነርሱ ተጠቅሞ በቀጥታ መተርጎምን ማድረግ ባይችሉም) በሉተራኑ ሥነመለኮቱ ላይ ባሉ እንደነ Robert Kolb እንደሚሉት ክሪዶች እና ኮንፌሽኖች ለመጽሐፍ ቅዱስ ስነ አፈታት አቅጣጫ ጠቋሚዎች ናቸው ይላሉ። ይህም ለቅዱሳት መጻሕፍት የበላይ ባለሥልጣንነት እንዲሁም በቂ እንደ መረታዊ አስተምህሮ ማለታችንም ነው። መልስ 3፦ በሥነ አፈታት ላይ ጥያቄህን በመራሕያነ ተሐድሶዎች በኩል ዘንድ የሚነሱ ሙግቶች ቢሆኑ ለምሳሌ፦ ካልቪኒዝም እና አርሜኒያን የሚል ቢሆን በቀላሉ ከትውፊት ጋር ካልሆነ የምትሉም ራሳችሁ ተከፋፍላችሁ ሳለና ወደ አበው ጎራ መካከል ጠጋ ስንል ራሱ ከሥነ አፈታት ጀምሮ ሁለት አይነት ቤተ እውቀቶች አሉ ብሎ ሀሳብህን መሞገት ይችላል። ምክንያቱም በእስክንድርያ ያለው ቤተ እውቀት እና አንጾኪያ ያለው ቤተ እውቀት መካከል የሥነ አፈታት ልዩነቶች ይስተውላሉ። የእስክንድርያው አመስጥሮታዊ ፍቺ(allegorical interpretation) ሲጠቀም የአንጾኪያው ደግሞ ቁማዊ(literal) ይጠቀማል። በተለይ በነገረ ክርስቶስ ዶክትሪን አንጻር ከተመለከትነው ጎራ መደብ ልዩነቶች ይስተዋላሉ(Hypostatic Union & two nature of Christ)። የእኛ ጥያቄ የሚሆነው ስለዚህ የትኛው የትምህርት ቤተ እውቀት መጽሐፍ ቅዱሳዊውን ስነ አፈታት ተጠቅሟል? የሚባል ጥያቄ ቢነሳ በቀላሉ የሚታለፍ አይደለም።[ማንሳትም እንችላለን ለማለት ነው] ስለዚህ መልስ1፣ መልስ2 እና መልስ3 ሲቀመጡ፦ ድምዳሜ 1፦ ከላይ እንዳልነው በእኛ ምሑራን ዘንድ የሚባለው የቅዱሳት መጽሐፍ ትርጓሜ ከማንኛውም ግላዊነት የጸዳ መሆን ይኖርበታል። ነገር ግን በቤተክርስቲያን ታሪክ ስንመለከተው ሁለቱ ቤተ እውቀቶች ተጽዕኖ ያሳደረባቸው የየራሳቸው ነገሮች አላቸው። የእስክንድርያው ቤተ እውቀት(Alexandria school) ለምሳሌ በፕላቶኒዝም በሃይል የተጠቃ ሆኖ እናየዋለን። ለዚህም የእስክንድርያው አርጌንስ ስለ ነብስ የሚያብራራው ከባሲል ቄሳርያው ሊለይ ይችላል(የተለየም ነው) አርጌንስ ስለ ነብስ ያለውን ቴዎሪ ለጥጦ ፕላቶኒክ በሆነ መልኩ መጽሐፍ ቅዱስን መፍታትን ሊያደርግ ይችላል። ይሄም ደሞ ምናልባት ወደ ስህተት ሊያመጣውም ይችላል(ስለ soul የሰጠውን ኮንሰፕሽን ስለምናውቀው) ስለዚህ ነው ያለንበት አካባቢ ያስተማሩን ሰዎች ወይም የግል ምልከታ በራሱ ለመጽሐፍ ቅዱስ ሥነ አፈታት መርህ ሆነው ይመጣሉ።[እንደውም የአበውን ሥልጣን ከመጽሐፍ ቅዱስ እኩል ካደረግነው ግላዊ ሥነ-አፈታት ሚነግስ አይደመስልህም?] ስለዚህ አንድ ትክክለኛ የሆነ የሥነ አፈታት መርሖ ያስፈልገናል። ይህም ሁሉም የሚዳኝበት HGL የምንለው መርህ ላይ አይመስልህም? ያው እንደ ጥያቄ ከተነሻ መወያየት እንችላለን ለማለት ነው። ድምዳሜ 2፦ ስለዚህ በሥርአት ከተጠናና ቋንቋውን እና ታሪካዊ አውዱ ከታየ ወደ ትክክለተኛው ሥነ አፈታት ይመራናል። መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ምንም እንኳን ግላዊን ትውውቅ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ያለንን ሕብረት ቢያበረታታም ከትርጓሜው እጅጉን ያርቀናል ማለት አይደለም። ስለዚህ በዶክትሪናል ነገሮች ሆኑ በአንዳንድ ውይይቶች ቤተክርስቲያን ውስጥ መታቀፍና ቅዱሳት መጻሕፍትን ለመተርጎም አማኞች ተጠያቂ ቢሆኑ የሚልን ነገርን መርሳት የለብንም። ይሄም ደሞ ግላዊነትን ይቀንሳል። በተለይ እንደ አማኝ አጥብቀን መያዝ ያለብን መንፈሳዊው ላይ ነው እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ለአማኞች የተላከው ለማስተማር ለማቅናት እና አቅጣጫን ለመስጠት እንደሆነ ሁሉ በጸሎት እና በትጋት በህብረትም ሆነ በግል በቤተ ክርስቲያን ጥላ ውስጥ የእግዚአብሔርን ቃል ማንበብ ጠቃሚ ነው እንላለን። ይህም የመጽሐፍ ቅዱስ ብቻ አስተምህሮን አይቃረንም።

መጽሐፍ ቅዱስ ብቻን እንጠያየቅ – ክፍል 2 Read More »

መጽሐፍ ቅዱስ ብቻን እንጠያየቅ – ክፍል 1

ጥያቄ፦ መጽሐፍ ቅዱስ ብቻን(Sola Scriptura) ተቀብሎ መቀጠል የቤተክርስቲያን ሥልጣናዊነትን እና የአበውን ጽሑፍ ባለስልጣንነትን እንዳንቀበል ያደርጋል። አይደል? መልስ፦ ኧረ በፍፁም! ይህን እንድንል ትንሽ ክፍተት እንኳን አይሰጠንም። ምክንያቱም የመጽሐፍ ቅዱስ ብቻና አይሳሳቴው ባለስልጣን ነው የሚለው አስተምህሮ እነዚህን ጨምሮም ነው፦ ➙ ቤተክርስቲያን ባለስልጣን ነች። ➙ መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ስንልም የአበው ክታባት ባለስልጣን አድርገን ነው። ይህን ስንል ግን ሊሳሳት የማይችልና የሁሉ መመዘኛ ባለስልጣን የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ መሆኑን አምነን ነው። ለዚህም ነው አውግስጢኖስ እንዲህ በማለት የተናገረው፦ If you discover in my writing anything false or blameworthy, you may know that it is bedewed by a human cloud, and you may attribute that to me as truly my own.[1] ስለዚህ እነዚህ መጻሕፍት ማለትም የአበው ክታባት ሕጸጽ ከሌለባቸው (infallible & inerrant) ከሆኑ ከቅዱሳት መጻሕፍት ቀጥሎ ክብር የሚሰጣቸው መጽሐፍት ናቸው። ጥያቄ፦ ለዚህ ንግግርህ የአዲስ ኪዳን ድጋፋት አለህ? መልስ፦ አዎ። ጌታ ኢየሱስ ካደረገው እና ካስተማረው ማሳየትና መጥቀስ ችላለሁ። ለምሳሌ፦ ማቴዎስ 23¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯¹ በዚያን ጊዜ ኢየሱስ ለሕዝቡና ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ ብሎ ነገራቸው፦² ጻፎችና ፈሪሳውያን በሙሴ ወንበር ተቀምጠዋል። ጌታችን በማቴዎስ 23:2-3 በሙሴ ወንበር ላይ ስላሉ ጻፎችና ፈሪሳውያን ለተናገሩት ቃል ለቃላቸው መታዘዝ እንደሚገባ ያስተምራል።(ይሄም ደሞ በዘመኑ ሥልጣናዊ መሆናቸውን ያሳያል። ለዛም ሥልጣን መታዘዝ እንዳለብን ይናገራል።) ይህን አይተን ረሱ ጌታችን በማቴዎስ ምዕራፍ 15፥1-39 ላይ ጻፎች እና ፈሪሳውያን የደነገጓቸውን መመሪያዎች ከዋናው ከመጽሀፍ ቅዱስ ማዕከላዊ ትምህርት ጋር ስለተቃረኑ ይቃወማቸዋል።(ይህ ደሞ በመጀመሪያው ክፍለ ዘመናት ከመጽሐፍ ቅዱስ ሥልጣን በላይ የሆነ ግዛት እንዴሌለ ያሳየናል። መልሴን በአጭሩ ሳስቀምጠው፦ መነሻ1፦ ጻሕፍት እና ፈሪሳውያን ሥልጣናዊ ናቸው። መነሻ2፦ ይህ አንድ አካል ሥልጣን አለው ማለት ግን የግድ ሊሳሳት የማይችል ሥልጣን(ከመጽሐፍ ቅዱስ እኩል የሆነ) ነው ማለት ግን ፈጽሞ አይቻልም። ስለዚህ ድምዳሜ1፦ ስለዚህ ይህ ሥልጣናዊው አካል ራሱ በመጽሐፍ ቅዱስ ይመዘናል። ልክ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳደረገው። ድምዳሜ2፦ እነዚህ መዛኞቹ ጌታችንን ራሱ የጠየቁት እና የመዘኑት በመጽሐፍ ቅዱስ መሆኑ የሚያሳየው በዘመኑ በእነርሱ አስተሳሰብ መጽሐፍ ቅዱስ የበላይ ባለስልጣን መሆኑን ጥቂት የሚያሳይ ፍንጭ ነው። በዚህ ክፍል ግን ጌታችን የበላይ ባለስልጣን ያደረገው ራሱ በነብያቱ በኩል የተናገረውን የራሱን ቃል በሕዝቡ ዘንድ ነው። በመጨረሻም ድምዳሜ1 እና ድምዳሜ2፦ መጽሐፍ ቅዱስ የማይመዘን መመዘኛ ነው። ይህ ማለት ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ማለት ነው። አንተም ስትጠይቅ እኛ የምንለውን መጽሐፍ ቅዱስ ባለሥልጣን ነው ስንል ሌሎች ባለስልጣናንነታቸውን መካድ ማለት አይደለም። ይልቅ የማይመዘነው ብቸኛ የማይሳሳት መመዘኛ መጽሐፍ ቅዱስ ነው ማለት ነው። መልስ፦ እሺ። አሁን የእኛን እሳብ ተረዳህ? ጥያቄ፦ ይቀጥላል… ማጣቀሻ

መጽሐፍ ቅዱስ ብቻን እንጠያየቅ – ክፍል 1 Read More »

Scroll to Top