የሥላሴ አስተምህሮ በተለያዩ ሰዎች በተለያዩ ዘመናትም ትችት ሲደርስበት መስማት የተለመደ ነው። ይህንንም ትምህርት በሰዎች አእምሮ ዘንድ ፈጽሞ መረዳት የማይቻልና በተለይም “አምላክ/God/” የሚለውን ቃል በተለያዩ አይነት በመጠቀም በሥነ አመክንዮ ዘንድ መሠረታዊ ችግር እንዳለበት ለማሳየት ይሞክራሉ። ሙግቱ እንዲህ ይቀርባል፦
1) ክርስቲያኖች አብ አምላክ ነው፣ ወልድ አምላክ ነው፣ መንፈስ ቅዱስ አምላክ ነው ይላሉ።
2) ነገር ግን “አምላክ” የሚለው ቃል በአንድ ጊዜ አብን፣ ወልድን እንዲሁም መንፈስን የሚያመለክት ከሆነ አንድን ምንነት ያለውን አምላክ በቋሚነት ሊያመለክት አይችልም።
3) ስለዚህ ይህ አስተምህሮው ከአመክንዮአዊ ወጥነት ይልቅ አሻሚ የሆነ ግራ አጋቢ ትርጉም ላይ እንዲሆን ያደርገዋል።
መልስ
ይህ ሙግት መሠረት ያደረገው እኛን(ክርስቲያኖችን) “አምላክ” የሚለውን ቃል የተለያዩ አካላትን በተለያየ መንገድ መገለጫ እንደሆነ በማመልከት እንደምንል አድርጎ ሙጉቱን በሥሑት ነጥቦች ላይ ገንብቶ የጀመረ ነው። ማለትም “አምላክ” አብን በአንድ መንገድ፣ ወልድን በሌላ ፣ እንዲሁም መንፈስ ቅዱስን በሌላ እንደማለት ነው። ነገር ግን ይህ አይነቱ መረዳት በሥላሴ የአምላክነት ባሕርይ ወይም “ግጻዌ መለኮት” መረዳት ውስጥ የማያታወቅ ነው። ታዲያ አምላክ ማለት ግን በኑባሬው ያለማቋረጥ አንድ፣ የማይከፋፈል መለኮታዊ ማንነትን የሚያመለክት መለኮታዊ ባህርይ የሚል ቃል ነው። ስለዚህ ክርስቲያኖች “አብ አምላክ ነው”፣ “ወልድ አምላክ ነው” እንዲሁም “መንፈስ አምላክ ነው” ሲሉ የአምላክነት ባህርይን ያለውን አካላቶቹ አሏቸው በዚህም እያንዳንዱ አካል ያንን የመለኮትነትን ባህርይ ሙሉ በሙሉ ይጋራሉ ማለታቸው ነው። ይህም አንድ አምላክ ብቻ አለ ሲባል፣ አንድ ምንነት እንዳለ እያረጋገጡ ነው። አንዱ አምላክ በሦስት አካል የተገለጠ ነው ሲሉ ደግሞ አንድ አምላክ በአካል ሦስት ነው እያሉ ነው። አብ፣ ወልድ እና መንፈስ አንድ አምላክ ናቸው ሲሉ እያንዳንዱ አካል መለኮታዊ ባህርይ እንዳለው እያስረገጡ ነው። ስለዚህ፣ ከላይ በሥላሴ ላይ በተነሳው የሶስቱ ነጥብ ሙግቶች፣ “አምላክ” የሚለውን ቃል ውይይት ከመገባቱ በፊት ከተብራራ፣ የሚመጣውን የትኛውንም ጥያቄ ይመልሳል ማለት ነው።


