በወንድም ምናሴ
የምንኖርበት ዘመን ዕብደት የነገሠበት፣ ነውር የተወደሰበት፣ ርኲሰትም የገነነበት ነዉ። አግድም አደግነት እንደ ሥልጡንነት ሲቈጠር፣ ዋልጌነትም እንደ ትልቅ ጀብድ የክብር ኒሻን ሲያሸልም እያየን አለን። ይህ የዕሳቤ መገለባበጥ ኤሪክ ፍሮም (Erich Fromm) ‘The Sane Society’ በተሰኘው መጽሐፉ የሣለውን አስፈሪ ሥዕል ያስታውሰናል። ፍሮም እንዳለው፣ “አንድ ማኅበረሰብ በአጠቃላይ ጤናማነቱን አጥቶ ሊያብድ ይችላል፤ ነገር ግን አብዛኛው ሰዉ በዚያ ዕብደት ውስጥ አብሮ ስለሚሳተፍና ተመሳሳይ ነውር ስለሚፈጽም ብቻ፣ ያንን የጋራ ዕብደት ‘ጤናማነትና ሥልጣኔ’ ብሎ መፈረጅ ይጀምራል።”እኛም ልክ እንደዚሁ በፍሮም እንደተገለጸው የታመመ ማኅበረሰብ፣ የዘመኑን መበላሸትና የጋራ ውድቀት ለመሸፈን የባሕርይ መለኪያዎቻችንን አዛብተናል። ኀጢአትን በትክክለኛ ስሙ መጥራት ትተን፣ በሥነ ልቦናዊና በዘመናዊ ቅጽል ስሞች ማንቆለጳጰስ ከጀመርን ይኸው ስንት ዘመን ተቈጠረ?! ነገረ ቅድስና ከሌላ ዓለም እንደመጣ ባዕድ ፍጥረት (Alien) ጥጒን እንዲይዝ ተደርጓል፤ ባይተዋር ሆኗል። “ቤት ያጣው ቤተኛ” መባል የነበረበት ከየምስባኮቻችን እና ከዕለት ተዕለት ምልልሳችን እንደ ውሃ ሽታ ተንኖ የጠፋዉ የቅድስና አስተምህሮ እና ኑሮ እንጂ የሙዚቃና ሙዚቀኛነት ጒዳይስ አልነበረም። ለመሆኑ ግን፣ በዚኽ በርኲሰት ውቅያኖስ በተጥለቀለቀ፣ በፍትወት አምቡላ ሰክሮ ጥምብ ርኲሱ በወጣ ዘመን በቅድስና እግዚአብሔርን አስከብሮ መኖር ይቻላል? ሰዉ ኀጢአትን እንደ ውሃ በሚጨልጥበት፣ እንደ ምድጃ እሳት በሚሞቅበትስ ዘመን ነቀፋ በሌለበት የሕይወት ዘይቤ መገለጥ ፍቁድ (የተፈቀደ) ነውን? የቅድስና ሕይወት በታሪክ መስኮት አጮልቀን የምናየው የድሮ ዘመን ትዝታ፣ ወይም በመስተዋት ተጠብቆ እንደሚቀመጥ ጥንታዊ ቅርስ በሩቅ የምንጐበኘው ቅሪተ አካል አይደለም። ቅድስና በአፍ የሚነገር ገድል፣ በጥራዝ የሚሰነድ ትርክት ከመሆን በዘለለ በተጨባጭ ኑሮ የሚገለጥ አይደለም ያለው ማነው? ቅዱሱ መጽሐፍ የነገረን “የመለኮቱ ኀይል እግዚአብሔርን ለመምሰልና ለእውነተኛ መንፈሳዊነት የሚያስፈልገንን ሁሉ እንደሰጠን ነዉ” (2ኛጴጥ1፣12)። በቅድስና መኖር የሚያስችል የእግዚአብሔር ጸጋ ተሰጥቶናል። ቅድስና በዘመን ጅረትና በሰዎች ኑረት ውስጥ እንደ ውሃ ቅርጽ አልቦነትን ገንዘቡ አድርጐ፣ ዘመኑን በመምሰል አልተጓዘም። ቅድስና መለኮታዊው የእግዚአብሔር ፍጽምና መገለጫ ነውና ከዘመኑ ጋር አብሮ ሊዘምን፣ ሊሻሻል አሊያም ሊለወጥ በፍጹም አይችልም።
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንደተናገረው፦ “ሰዎች ክብርን ውርደት፣ ውርደትንም ክብር አድርገው ሊጠሩት ይችላሉ። ነገር ግን የእውነተኛ ክብርና ውርደት መለያው የሰዎች አስተያየት ሳይሆን የእግዚአብሔር ቃል ነው”። በመሆኑም፣ ክብርና ውርደት ቦታ የተለዋወጡ የመሰለን ለእኛ ለምድራውያኑ እንጂ፣ እንከን አልቦ በሆነው ሰማያዊው ዓለም አሁንም የክብር ሚዛን አልተዘናበለም፤ የውርደትም ትርጒም አልተቀየረም። ክብር የቅድስና መዳረሻ፣ ውርደትም የርኲሰት መጨረሻ ነውና። እግዚአብሔር አብ በውድ ልጁ ደም መፍሰስና በሥጋው መቆረስ የዋጀን፣ በመንፈስ ቅዱስም ማኅተም ያተመን ለታላቅ ሰማያዊ ዓላማ ስላጨን ነው። ያ የታጨንለት ክቡር ዓላማም ‘ቅድስና’ ይባላል። ይኽም፦ ‘ለርኲሰት ሳይሆን እግዚአብሔር በቅድስና ጠርቶናልና’ (1ኛ ተሰ. 4፣7) ተብሎ እንደተጻፈው ነው። ይኽ ክቡር ጥሪ በክቡር አንድያ ልጁ አማካኝነት በታላቅ ክብር ቀርቦልናል። የተጠራነው ለቅድስና ነው፤ የምንኖረውም በቅድስና። ጠሪው ቅዱስ፣ ጥሪውም ቅዱስ ነው፤ ተጠሪዎቹም ቅዱሳን ይሆኑ ዘንድ የተለዩ ናቸው። ቅድስና የመዳናችን ግብ፣ የነፃነታችን አርማ፣ የናዝራዊነታችንም ማኅተም ነው። ቅድስና በፍጹም ደስታ ለእግዚአብሔር መለየት ነው፤ ቅድስና የክርስቶስ ኅሩያን ሕይወት ነውና።
በብሉይ ኪዳን ‘የኪዳኑ ሕዝብ’ የተባሉት እስራኤላውያን ለእግዚአብሔር የተለዩ መሆናቸው ይታወቅ ዘንድ፣ ያሕዌ ለአባታቸው ለአብርሃም የሰጠውን የግዝረት ሥርዓት እንደ ቃል ኪዳን ማኅተምና እንደ አይሁድኅነት መስፈርት አጽንተው ጠበቁት። በዚኽም ሥርዓተ ግዝረት ቁልፈታቸውን በማስወገድ፣ የእግዚአብሔር ሕዝብ ከአኅዛብ ወገን ተለይተው የታወቁ ሆኑ፤ ሥርዓቱም የታሪክን ሰንሰለት ተሻግሮ ከትውልድ ወደ ትውልድ ዘለቀ። ጥንታዊው የቤተክርስቲያን አባት ቅዱስ ዩስጢኖስ ይህንን የታሪክና የመንፈስ ትሥሥር ሲያብራራ፦ “ይህ የሥጋ ግዝረት እግዚአብሔር የአብርሃምን ዘር ከአኅዛብ ወገን ለይቶ ለመጠበቅና የራሱ የኪዳን ሕዝብ አድርጐ ለማተም የሰጣቸው ምልክት ነበር፤ ይህም ውጫዊ መለያ እውነተኛውና መንፈሳዊው ግዝረት ከኀጢአትና ከዓለም ክፋት ተለይቶ በቅድስና መኖር መሆኑን የሚያሳይ ጥላ ነው” ይላል። ይኽም የሚያመለክተን ቅድስና የሕዝበ እግዚአብሔር የመኖሪያ ፈቃድና የዜግነት መታወቂያ መሆኑን ነው። በሐዲስ ኪዳን በክርስቶስ ክቡር ደም ለተዋጀን ለእኛ ቅድስና ዐይነተኛ መታወቂያችን ነው፤ ይልቁንም ደግሞ ወሲባዊ ንጽሕናችን። ቅድስና የማይዳስሰዉና የማይለውጠው የማንነታችን ክፍል የለም፤ ቅድስና ሁለንተናዊ የሕይወት መዓዛ ነውና። ነገር ግን ወሲባዊ ቅድስና ላይ ለየት ባለ መልኲ ልናተኲር የሚገባን፣ ወሲባዊ ርኲሰት የእግዚአብሔር ማደሪያና የክርስቶስ ቤተ መቅደስ በሆንነው በማንነታችን ላይ የተቃጣ አውዳሚ መቅሰፍት በመሆኑ ነው። ቅዱስ ቃሉ በግልጽ እንደሚነግረን፦ ‟ዝሙትን የሚሠራ በገዛ ሥጋው ላይ ኀጢአትን ይሠራል„ (1ኛ ቆሮ. 6፣18)። ይኽ በደል የክርስቶስን መቅደስ የሚያፈርስ ብቻ ሳይሆን፣ በውስጣችን ያደረውን ቅዱስ መንፈስ የሚያሳዝን የድፍረት ተግባር ነው። ዝሙት—በአጥፍቶ ጠፊ አካል ላይ እንደተጠመደ ፈንጂ፣ ራስን በቁም አፈንድቶ የሚያጠፋና ለሌላውም የመጥፊያ ምክንያት ለመሆን የሚዳርግ ነው።
ወሲባዊ ቅድስናን መጠበቅ የክርስቶስ ሕያው ቤተ መቅደስ የሆነውን እኛነታችንን መጠበቅ ነውና መጽሐፍ ቅዱሳዊውን የነገረ ወሲብ ትምህርት አድምተን ልንማር እና አኗኗራችንንም ከተማርነው እውነት አንጻር ልንቃኝ ያስፈልጋል ። በወሲባዊ ቅድስና መመላለሳችን እግዚአብሔርን ማወቃችን የሚለካበት ሚዛን፣ የመንገዱ ሰዎች የመሆናችንም ማረጋገጫ ቱምቢ ነዉ። ወሲባዊ ርኲሰት እግዚአብሔርን የማያውቁ አኅዛብ የኑሮ ሥርዓት እና የሕይወት ዘይቤ ነዉ። “የአማኙ የኑሮ ዘይቤ ለእግዚአብሔር ባሕርይ የሚደረግ ምላሽ ነው። ጴጥሮስም፣ ዳሩ ግን እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ’ ተብሎ ስለ ተጻፈ፣ የጠራችሁ ቅዱስ እንደሆነ እናንተ ደግሞ በኑሮአችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ” ብሎአል (1ኛ ጴጥ 1፣1516)። ክርስቲያኖች ቅዱሳን መሆን ያለባቸው ለምንድን ነው? ምክንያቱም እግዚአብሔር ቅዱስ ነዉ። ሌላ ምክንያት አልተሰጠም። አያስፈልግምና። “እግዚአብሔር ‟ቅዱሳን ሁኑ„ ሲለን፣ ከርሱ ጋር ወዳለው ኅብረትና ደስታ እየጋበዘን ነው። ቅድስና ከደስታ የሚለይ አድካሚ ሥራ አይደለም፤ ይልቁኑ በእግዚአብሔር ፊት የመኖር እና የርሱን ሰላም የመለማመድ ውጤት ነው። ወንጌል የሚቀድሰን በጸጋው ተቀብሎን ለፍቅሩ ምላሽ የምንሰጥበትን አዲስ ልብ በመስጠት ነው። የወሲባዊ ቅድስና ደማቁ መርሕም ይኽ ነው፦ በቅድስና የከበረውን እግዚአብሔርን በማወቅ፣ በቅዱስ መንፈሱ እየተመራንና በጸጋው አስቻይነት ላይ ተመርኲዘን፣ ወሲባዊ ንጽሕናችንን በመጠበቅ ለቅድስና ሕይወት እንትጋ የሚል ነው።ቅድስና ከፍቅር የሚመነጭ፣ በትህትና የሚጠበቅ፣ በመታዘዝ የሚቀጥል ሕይወትነዉ። የቅድስና ምንጩ ፍቅረ እግዚአብሔር ነዉ። የቅድስና መጠበቂያ ዐጥሩ ትሕትና ነዉ። የቅድስና ሕይወት አስቀጣይ ሞተሩ ቃሉን መታዘዝ ነዉ። ምክንያቱም፦ “እግዚአብሔርን መውደድ የቅድስና መጀመሪያ እንደሆነ ሁሉ፣ በትሕትና ራስን ዝቅ ማድረግና ለቃሉ መታዘዝ ደግሞ ያቺን የተቀደሰች ነፍስ ከጥፋት ቀስቶች የሚጠብቃትና ወደ ፍጽምና የሚያደርሳት የማይናወጥ መሠረት ነውና።
በጸጋው ያግዘን!1
- ዐዲስ በሕትመት ላይ ካለ ከምናሴ ይርጉ ጐበና “የኅሩያን ሕይወት” መጽሐፍ መግቢያ የተወሰደ ↩︎


