July 2026

የዘመኑ ሕሙም ኅሊና እና የቅድስና ጥሪ

በወንድም ምናሴ የምንኖርበት ዘመን ዕብደት የነገሠበት፣ ነውር የተወደሰበት፣ ርኲሰትም የገነነበት ነዉ። አግድም አደግነት እንደ ሥልጡንነት ሲቈጠር፣ ዋልጌነትም እንደ ትልቅ ጀብድ የክብር ኒሻን ሲያሸልም እያየን አለን። ይህ የዕሳቤ መገለባበጥ ኤሪክ ፍሮም (Erich Fromm) ‘The Sane Society’ በተሰኘው መጽሐፉ የሣለውን አስፈሪ ሥዕል ያስታውሰናል። ፍሮም እንዳለው፣ “አንድ ማኅበረሰብ በአጠቃላይ ጤናማነቱን አጥቶ ሊያብድ ይችላል፤ ነገር ግን አብዛኛው ሰዉ በዚያ ዕብደት ውስጥ አብሮ ስለሚሳተፍና ተመሳሳይ ነውር ስለሚፈጽም ብቻ፣ ያንን የጋራ ዕብደት ‘ጤናማነትና ሥልጣኔ’ ብሎ መፈረጅ ይጀምራል።”እኛም ልክ እንደዚሁ በፍሮም እንደተገለጸው የታመመ ማኅበረሰብ፣ የዘመኑን መበላሸትና የጋራ ውድቀት ለመሸፈን የባሕርይ መለኪያዎቻችንን አዛብተናል። ኀጢአትን በትክክለኛ ስሙ መጥራት ትተን፣ በሥነ ልቦናዊና በዘመናዊ ቅጽል ስሞች ማንቆለጳጰስ ከጀመርን ይኸው ስንት ዘመን ተቈጠረ?! ነገረ ቅድስና ከሌላ ዓለም እንደመጣ ባዕድ ፍጥረት (Alien) ጥጒን እንዲይዝ ተደርጓል፤ ባይተዋር ሆኗል። “ቤት ያጣው ቤተኛ” መባል የነበረበት ከየምስባኮቻችን እና ከዕለት ተዕለት ምልልሳችን እንደ ውሃ ሽታ ተንኖ የጠፋዉ የቅድስና አስተምህሮ እና ኑሮ እንጂ የሙዚቃና ሙዚቀኛነት ጒዳይስ አልነበረም። ለመሆኑ ግን፣ በዚኽ በርኲሰት ውቅያኖስ በተጥለቀለቀ፣ በፍትወት አምቡላ ሰክሮ ጥምብ ርኲሱ በወጣ ዘመን በቅድስና እግዚአብሔርን አስከብሮ መኖር ይቻላል? ሰዉ ኀጢአትን እንደ ውሃ በሚጨልጥበት፣ እንደ ምድጃ እሳት በሚሞቅበትስ ዘመን ነቀፋ በሌለበት የሕይወት ዘይቤ መገለጥ ፍቁድ (የተፈቀደ) ነውን? የቅድስና ሕይወት በታሪክ መስኮት አጮልቀን የምናየው የድሮ ዘመን ትዝታ፣ ወይም በመስተዋት ተጠብቆ እንደሚቀመጥ ጥንታዊ ቅርስ በሩቅ የምንጐበኘው ቅሪተ አካል አይደለም። ቅድስና በአፍ የሚነገር ገድል፣ በጥራዝ የሚሰነድ ትርክት ከመሆን በዘለለ በተጨባጭ ኑሮ የሚገለጥ አይደለም ያለው ማነው? ቅዱሱ መጽሐፍ የነገረን “የመለኮቱ ኀይል እግዚአብሔርን ለመምሰልና ለእውነተኛ መንፈሳዊነት የሚያስፈልገንን ሁሉ እንደሰጠን ነዉ” (2ኛጴጥ1፣12)። በቅድስና መኖር የሚያስችል የእግዚአብሔር ጸጋ ተሰጥቶናል። ቅድስና በዘመን ጅረትና በሰዎች ኑረት ውስጥ እንደ ውሃ ቅርጽ አልቦነትን ገንዘቡ አድርጐ፣ ዘመኑን በመምሰል አልተጓዘም። ቅድስና መለኮታዊው የእግዚአብሔር ፍጽምና መገለጫ ነውና ከዘመኑ ጋር አብሮ ሊዘምን፣ ሊሻሻል አሊያም ሊለወጥ በፍጹም አይችልም። ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንደተናገረው፦ “ሰዎች ክብርን ውርደት፣ ውርደትንም ክብር አድርገው ሊጠሩት ይችላሉ። ነገር ግን የእውነተኛ ክብርና ውርደት መለያው የሰዎች አስተያየት ሳይሆን የእግዚአብሔር ቃል ነው”። በመሆኑም፣ ክብርና ውርደት ቦታ የተለዋወጡ የመሰለን ለእኛ ለምድራውያኑ እንጂ፣ እንከን አልቦ በሆነው ሰማያዊው ዓለም አሁንም የክብር ሚዛን አልተዘናበለም፤ የውርደትም ትርጒም አልተቀየረም። ክብር የቅድስና መዳረሻ፣ ውርደትም የርኲሰት መጨረሻ ነውና። እግዚአብሔር አብ በውድ ልጁ ደም መፍሰስና በሥጋው መቆረስ የዋጀን፣ በመንፈስ ቅዱስም ማኅተም ያተመን ለታላቅ ሰማያዊ ዓላማ ስላጨን ነው። ያ የታጨንለት ክቡር ዓላማም ‘ቅድስና’ ይባላል። ይኽም፦ ‘ለርኲሰት ሳይሆን እግዚአብሔር በቅድስና ጠርቶናልና’ (1ኛ ተሰ. 4፣7) ተብሎ እንደተጻፈው ነው። ይኽ ክቡር ጥሪ በክቡር አንድያ ልጁ አማካኝነት በታላቅ ክብር ቀርቦልናል። የተጠራነው ለቅድስና ነው፤ የምንኖረውም በቅድስና። ጠሪው ቅዱስ፣ ጥሪውም ቅዱስ ነው፤ ተጠሪዎቹም ቅዱሳን ይሆኑ ዘንድ የተለዩ ናቸው። ቅድስና የመዳናችን ግብ፣ የነፃነታችን አርማ፣ የናዝራዊነታችንም ማኅተም ነው። ቅድስና በፍጹም ደስታ ለእግዚአብሔር መለየት ነው፤ ቅድስና የክርስቶስ ኅሩያን ሕይወት ነውና። በብሉይ ኪዳን ‘የኪዳኑ ሕዝብ’ የተባሉት እስራኤላውያን ለእግዚአብሔር የተለዩ መሆናቸው ይታወቅ ዘንድ፣ ያሕዌ ለአባታቸው ለአብርሃም የሰጠውን የግዝረት ሥርዓት እንደ ቃል ኪዳን ማኅተምና እንደ አይሁድኅነት መስፈርት አጽንተው ጠበቁት። በዚኽም ሥርዓተ ግዝረት ቁልፈታቸውን በማስወገድ፣ የእግዚአብሔር ሕዝብ ከአኅዛብ ወገን ተለይተው የታወቁ ሆኑ፤ ሥርዓቱም የታሪክን ሰንሰለት ተሻግሮ ከትውልድ ወደ ትውልድ ዘለቀ። ጥንታዊው የቤተክርስቲያን አባት ቅዱስ ዩስጢኖስ ይህንን የታሪክና የመንፈስ ትሥሥር ሲያብራራ፦ “ይህ የሥጋ ግዝረት እግዚአብሔር የአብርሃምን ዘር ከአኅዛብ ወገን ለይቶ ለመጠበቅና የራሱ የኪዳን ሕዝብ አድርጐ ለማተም የሰጣቸው ምልክት ነበር፤ ይህም ውጫዊ መለያ እውነተኛውና መንፈሳዊው ግዝረት ከኀጢአትና ከዓለም ክፋት ተለይቶ በቅድስና መኖር መሆኑን የሚያሳይ ጥላ ነው” ይላል። ይኽም የሚያመለክተን ቅድስና የሕዝበ እግዚአብሔር የመኖሪያ ፈቃድና የዜግነት መታወቂያ መሆኑን ነው። በሐዲስ ኪዳን በክርስቶስ ክቡር ደም ለተዋጀን ለእኛ ቅድስና ዐይነተኛ መታወቂያችን ነው፤ ይልቁንም ደግሞ ወሲባዊ ንጽሕናችን። ቅድስና የማይዳስሰዉና የማይለውጠው የማንነታችን ክፍል የለም፤ ቅድስና ሁለንተናዊ የሕይወት መዓዛ ነውና። ነገር ግን ወሲባዊ ቅድስና ላይ ለየት ባለ መልኲ ልናተኲር የሚገባን፣ ወሲባዊ ርኲሰት የእግዚአብሔር ማደሪያና የክርስቶስ ቤተ መቅደስ በሆንነው በማንነታችን ላይ የተቃጣ አውዳሚ መቅሰፍት በመሆኑ ነው። ቅዱስ ቃሉ በግልጽ እንደሚነግረን፦ ‟ዝሙትን የሚሠራ በገዛ ሥጋው ላይ ኀጢአትን ይሠራል„ (1ኛ ቆሮ. 6፣18)። ይኽ በደል የክርስቶስን መቅደስ የሚያፈርስ ብቻ ሳይሆን፣ በውስጣችን ያደረውን ቅዱስ መንፈስ የሚያሳዝን የድፍረት ተግባር ነው። ዝሙት—በአጥፍቶ ጠፊ አካል ላይ እንደተጠመደ ፈንጂ፣ ራስን በቁም አፈንድቶ የሚያጠፋና ለሌላውም የመጥፊያ ምክንያት ለመሆን የሚዳርግ ነው። ወሲባዊ ቅድስናን መጠበቅ የክርስቶስ ሕያው ቤተ መቅደስ የሆነውን እኛነታችንን መጠበቅ ነውና መጽሐፍ ቅዱሳዊውን የነገረ ወሲብ ትምህርት አድምተን ልንማር እና አኗኗራችንንም ከተማርነው እውነት አንጻር ልንቃኝ ያስፈልጋል ። በወሲባዊ ቅድስና መመላለሳችን እግዚአብሔርን ማወቃችን የሚለካበት ሚዛን፣ የመንገዱ ሰዎች የመሆናችንም ማረጋገጫ ቱምቢ ነዉ። ወሲባዊ ርኲሰት እግዚአብሔርን የማያውቁ አኅዛብ የኑሮ ሥርዓት እና የሕይወት ዘይቤ ነዉ። “የአማኙ የኑሮ ዘይቤ ለእግዚአብሔር ባሕርይ የሚደረግ ምላሽ ነው። ጴጥሮስም፣ ዳሩ ግን እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ’ ተብሎ ስለ ተጻፈ፣ የጠራችሁ ቅዱስ እንደሆነ እናንተ ደግሞ በኑሮአችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ” ብሎአል (1ኛ ጴጥ 1፣1516)። ክርስቲያኖች ቅዱሳን መሆን ያለባቸው ለምንድን ነው? ምክንያቱም እግዚአብሔር ቅዱስ ነዉ። ሌላ ምክንያት አልተሰጠም። አያስፈልግምና። “እግዚአብሔር ‟ቅዱሳን ሁኑ„ ሲለን፣ ከርሱ ጋር ወዳለው ኅብረትና ደስታ እየጋበዘን ነው። ቅድስና ከደስታ የሚለይ አድካሚ ሥራ አይደለም፤ ይልቁኑ በእግዚአብሔር ፊት የመኖር እና የርሱን ሰላም የመለማመድ ውጤት ነው። ወንጌል የሚቀድሰን በጸጋው ተቀብሎን ለፍቅሩ ምላሽ የምንሰጥበትን አዲስ ልብ በመስጠት ነው። የወሲባዊ ቅድስና ደማቁ መርሕም ይኽ ነው፦ በቅድስና የከበረውን እግዚአብሔርን በማወቅ፣ በቅዱስ መንፈሱ እየተመራንና በጸጋው አስቻይነት ላይ ተመርኲዘን፣ ወሲባዊ ንጽሕናችንን በመጠበቅ ለቅድስና ሕይወት እንትጋ የሚል ነው።ቅድስና ከፍቅር የሚመነጭ፣ በትህትና የሚጠበቅ፣ በመታዘዝ የሚቀጥል ሕይወትነዉ። የቅድስና ምንጩ ፍቅረ እግዚአብሔር ነዉ። የቅድስና መጠበቂያ ዐጥሩ ትሕትና ነዉ። የቅድስና ሕይወት አስቀጣይ ሞተሩ ቃሉን መታዘዝ ነዉ። ምክንያቱም፦ “እግዚአብሔርን መውደድ የቅድስና መጀመሪያ እንደሆነ ሁሉ፣ በትሕትና ራስን ዝቅ ማድረግና ለቃሉ መታዘዝ ደግሞ ያቺን የተቀደሰች ነፍስ ከጥፋት ቀስቶች የሚጠብቃትና ወደ ፍጽምና የሚያደርሳት የማይናወጥ መሠረት ነውና። በጸጋው ያግዘን!1

የዘመኑ ሕሙም ኅሊና እና የቅድስና ጥሪ Read More »

አርጌንስ እና የአዲስ ኪዳን ጥንታዊ ቅጂዎች

ጽሑፍ፦ Samuel Greenትርጉም፦ David Yeshua ይህ መጣጥፍ፣ በሊቁ አርጌንስ ድርሳን ውስጥ ስለ አዲስ ኪዳን የሰፈረውን ንግግር መሠረት በማድረግ የሚያብራራ እና በሙስሊሞች መካከል ለሚደረገው ውይይት እንዴት በጥቅም ላይ መዋል እንዳለበት የሚተነትን ነው። ከሙስሊም ወገኖች ጋር በሚደረጉ ውይይቶች መካከል የአዲስ ኪዳን ቅጂ ተዓማኒነት በተደጋጋሚ የሚነሳ ጉዳይ ሲሆን፣ አንዳንድ ሙስሊሞች የአዲስ ኪዳን ጽሑፍ ተዓማኒ አለመሆኑን ለማስረዳት የአርጌንስን ጽሑፍ በማስረጃነት ያቀርባሉ። በዚህም ጽሑፍ የእስክንድሪያው አርጌንስን(ከ184 – 253 ዓ.ም) የኖረ የቤተክርስቲያን ሊቅ ሲሆን እውን ስለ አዲስ ኪዳን ጥንታዊያን ቅጂች የተዛባ ምልከታን ያምናልን? የሚለውን በመተንተን የማስቀምጥ ይሆናል። የሊቁ ጽሑፍ እንዲህ ይነበባል፦ “The differences among the manuscripts [of the Gospels] have become great, either through the negligence of the copyists or through the perverse audacity of others; they either neglect to check over what they have transcribed, or, in the process of checking, they lengthen or shorten, as they please.”1 “በእደ ክታባት ገልባጮች ቸልተኝነት አልያም በሌሎች እኩይ አላማ የተነሳ በወንጌላት እደ ክታባት ቅጂዎች መካከል ያለውን ልዩነት እጅግ የጎላ መሆን ችሏል። የገለበጡትን ጊዜ ሰጥተው ለመርመር ቸል ይላሉ አልያም ደግሞ በሚመረምሩበት ወቅት እንደ ልባቸው ፈቃድ ያስረዝሙታል ወይም ያሳጥሩታል።” ከዚህ ከአርጌንስ ጽሑፍ በመነሳት ሙስሊም ወገኖች የአዲስ ኪዳን እደክታብ በሦስተኛው ክፍለ ዘመን ላይ ከባድ ችግሮች እንደነበሩበት እና በዚህም ምክንያት ዛሬ ላይ በእጃችን የሚገኙ ምንባባት ተዓማኒ እንዳልሆነ ይደመድማሉ፤ ጨመርም አድርገው ቁርዓን እንዲህ ዓይነት የጽሑፍ ግድፈቶች እንደሌሉበት ይደመድማሉ። አንድ ክርስቲያን ይህን የአርጌንስን አባባል እንዴት ሊረዳው ይገባል? ለዚህስ ሙግትና መልስ ለሚሻ ጥያቄ ምን ብሎ መመለስ አለበት? የሚለውን እኔ በሦስት የመልስ ነጥቦችን አስቀምጣለሁ። ነጥብ አንድ፦  ሊቁ አርጌንስ የአዲስ ኪዳንን ጽሑፍ ተዓማኒነትን በፍጹም አይክድም። ይልቅ በድርሳናቶቹ ሁሉ የአዲስ ኪዳን ምንባባትን በማጣመር የሚቀጥል ሲሆን፣ እንደ እስትንፋሰ እግዚአብሔር ቃሉን ይተማመንባቸዋል። ይህ ማለት፣ አርጌንስ አንዳንድ ሙስሊሞች ወደ ደረሱበት ዓይነት ድምዳሜ መሠረት በፍጹም አልደረሰም ማለት ነው። ነጥብ ሁለት፦ ችግሩ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ለማወቅ አርጌንስ ስለጠቀሳቸው የምንባባት ልዩነቶች (textual variants) አንዳንድ ምሳሌዎችን ማየት ያስፈልገናል። እነዚህ ምሳሌዎች ከሌሉ፣ በቀላሉ የተጋነነ ወይም ተገቢ ያልሆነ የተሳሳተ ግንዛቤ በሊቁ ላይ ሊፈጠርብን ይችላል። እንደ መልካም አጋጣሚ ሆኖ፣ እነዚህ ምሳሌዎች በቀላሉ ይገኛሉ፤ ምክንያቱም አርጌንስ ራሱ በድርሳኑ ውስጥ ጠቅሷቸዋል። ብሩስ ሜትዝገር (Bruce Metzger) የአርጌንስ ጽሑፎች በጥልቀት በመመርመር እነዚህን የጽሑፍ ልዩነቶች ሰብስቧቸዋል። የምርምሩም ውጤት ‘Explicit References in the Works of Origen to Variant Readings in New Testament Manuscripts’ በተሰኘው ጽሑፍ ላይ ታትሟል። በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ሜትዝገር አርጌንስ የጠቀሳቸውን 22 የጽሑፍ ልዩነቶች አቅርቦ ይወያይባቸዋል። ስለሆነም፣ አርጌንስ በትክክል ስለ ምን እየጻፈ እንደነበረ ማወቅ እንችላለን። አርጌንስ የጠቀሳቸው የ22ቱ ልዩነቶች ማጠቃለያ የሚከተለው ነው፦ መደምደሚያ ሐሳብ በሊቁ አርጌንስ ክታብ ውስጥ በጉልህ 22 የምንባብ ልዩነቶች ሰፍረዋል። ከእነዚህ ውስጥ በ20ቹ ላይ የታየው የእጅ ጽሑፎች ምንባባት ልዩነት በአጠቃላይ ከአንድ ቃል ጋር የተያያዙ ሲሆን፤ እርሱም ተመሳሳይ ትርጉም ያለው ሌላ ተመሳሳይ ቃል(synonym)፣ የተለየ የሰዋስው አወቃቀር፣ የተለየ ስም፣ የጎደለ ወይም የተጨመረ ቃል ተገኝቶ ሊሆን ይችላል። ጽሑፉ አንድ ዓይነት ሆኖ ሳለ፣ አርጌንስ አሁንም ጥያቄ የነበረበት ሁለት ምሳሌዎች ግን ነበሩበት። ይህም የሆነበት ምክንያት ሊቁ አርጌንስ ምሑርና ባለ ብዙ ቋንቋዎች ባለቤት እንደመሆኑ መጠን፣ የላቀ የጽሑፍ ጥራትና ወጥነትን ይፈልግ እንደነበረና ያንን ዓረፍተ ነገር የጻፈውም ለዚሁ እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም። በዚህም ሊቁ ከሰጣቸው ምሳሌዎች ውስጥ መረዳት የምንችለው፣ በአዲስ ኪዳን ጽሑፍ ላይ ምንም ዓይነት ጠንካራ የሚባል ችግር እንደሌለ ነው። ብዙውን ጊዜ ከአንድ ቃል ጋር የተያያዙ ጥቂት የጽሑፍ ልዩነቶች ያሉ ሲሆን፣ እነዚህንም ‘የምንባቤያዊ ሕየሳ’ (textual criticism) መስፈርትን በመጠቀም ለይቶ ማስተካከል ይቻላል። ስለሆነም፣ አርጌንስ አዲስ ኪዳንን በተመለከተ ችግሮች እንዳሉበት ያስቀምጣል ማለት እጅጉን ማጋነን ነው። የቀረበውም ማስረጃ ይህንንም በፍጹም አያሳይም። ሦስተኛውና የመጨረሻው ነጥቤ፦ የእስልምና ምሑራን ቁርዓንን በሚተረጉሙበት(በሚያብራሩበት) ጊዜ፣ ልክ እንደ ሊቁ አርጌንስ ሁሉ እነርሱም በቁርዓን ጽሑፍ ውስጥ ስላሉት የቅጂ ልዩነቶች(variants) ይወያያሉ። ለዚህም ሦስት ምሳሌዎች ላንሳ፦ አል-ጠበሪ እና ቁርዓን 2:2133፦ በዑስማን የተደነገገው(የተመደበው) መደበኛ የቁርዓን ጽሑፍ ‘የሰው ልጆች ሁሉ አንድ ማኅበረሰብ ነበሩ፤ ከዚያም አላህ ነቢያትን አስነሳ’ ይላል። ሆኖም በአብደላህ ኢብን መስዑድ የቁርዓን ቅጂ ላይ ‘የሰው ልጆች ሁሉ አንድ ማኅበረሰብ ነበሩ፤ ከዚያም ተለያዩ(ተጣሉ)፤ አላህም ነቢያትን አስነሳ’ የሚል ነበር። ሳሂህ አል-ቡኻሪ እና ቁርዓን 92:3 4፦ በዑስማን የተደነገገው መደበኛ የቁርዓን ጽሑፍ ‘ወንድና ሴትን በፈጠረው እምላለሁ’ ይላል። ሆኖም በአብደላህ ኢብን መስዑድ የቁርዓን ቅጂ ላይ ‘በወንዱና በሴቷ እምላለሁ’ የሚል ነበር። አብደላህ ዩሱፍ አሊ እና ቁርዓን 33:6 5፦ በዑስማን የተደነገገው መደበኛ የቁርዓን ጽሑፍ ‘ነቢዩ ለምእመናን ከነፍሶቻቸው ይልቅ ቅርብ ነው፤ ሚስቶቹም እናቶቻቸው ናቸው’ ይላል። ሆኖም በኡበይ ኢብን ካዕብ የቁርዓን ቅጂ ላይ ‘ነቢዩ ለምእመናን ከነፍሶቻቸው ይልቅ ቅርብ ነው፤ እርሱም ለእነርሱ አባት ነው፤ ሚስቶቹም እናቶቻቸው ናቸው’ የሚል ነበር። በታሪክ ሂደት ውስጥ በሙስሊሞች ዘንድ ለእነዚህ የጽሑፍ ልዩነቶች የተሰጡት ምላሾች የተለያዩ ነበሩ። በእስልምና የመጀመሪያዎቹ አሥርተ ዓመታት ውስጥ እነዚህ ልዩነቶች እንደ ችግር ይታዩ የነበረ ሲሆን፣ ሦስተኛው ከሊፋ ዑስማን አንድ ወጥ የሆነ መደበኛ የቁርዓን ቅጂ እንዲዘጋጅና ሌሎች የተለያዩ የእጅ ጽሑፎች በሙሉ እንዲቃጠሉ(እንዲጠፉ) አዟል።6 ሌሎች ሙስሊሞች ደግሞ እነዚህ የጽሑፍ ልዩነቶች ትክክለኛና ተዓማኒ (authentic) እስከሆኑ ድረስ የቁርዓኑ አካል አድርገው ይመለከቷቸዋል። ይህ ማለት ልዩነቶቹ መመዘንና መፈተሽ አለባቸው ማለት ነው። ይሁን እንጂ አብዛኞቹ ሙስሊሞች ስለነዚህ የጽሑፍ ልዩነቶች ግንዛቤ የላቸውም። ‘The Encyclopedia of the Quranic Readings with an Introduction to Readings and Famous Readers’ የተሰኘው ኢንሳይክሎፔዲያ የ10,243 የጽሑፍ ልዩነቶችን ዝርዝር መረጃ ይዟል።7 ማጠቃለያ ሊቁ አርጌንስ ስለ አዲስ ኪዳን ምንባባት ልዩነት የተናገረውን ንግግር አንዳንድ ጊዜ በሙስሊሞች ዘንድ አዲስ ኪዳን ከባድ ችግሮች እንዳሉበት ለማሳየት ጥቅም ላይ ይውላል። ነገር ግን ከላይ እንዳየነው ሊቁ በፍጹም ወደዚህ ድምዳሜ አልደረሰም፤ ከሰጣቸውም ምሳሌዎች መረዳት የሚቻለው አብዛኛውን ጊዜ ከአንድ ቃል ጋር የተያያዙ ጥቂት የጽሑፍ ልዩነቶች ብቻ መኖራቸውን ነው። እነዚህንም የምንባቤያዊ ሕየሳ(textual criticism) መሥፈርቶችን በመጠቀም ለይቶ ማስቀመጥ ይቻላል። በተጨማሪም ቁርዓን ራሱ የጽሑፍ ልዩነቶች ያሉበት መሆኑንና ሙስሊሞች ቀደም ሲልም የያዙት፣ አሁንም ድረስ እየያዙት ያለ ጉዳይ መሆኑን አይተናል። ስለሆነም ሙስሊሞች አርጌንስ አዲስ ኪዳንን ተዓማኒነት የጎደለው አድርጎ ያስብ ነበር የሚል የተሳሳተ ግንዛቤ ለመፍጠር መሞከር የለባቸውም፤ እንዲሁም ቁርዓን ከጽሑፍ ልዩነቶች የጸዳ ነው የሚል ስሜት ለመስጠትም መጣር የለባቸውም። [ማሳሰቢያ፦ ይህ የትርጉም ጽሑፍ በጸሐፊው ሙሉ ፍቃደኝነት የተተረጎመ መሆኑን እንገልጻለን።] ማጣቀሻዎች የጽሑፍ ምንጭ፦ https://www.answering-islam.org/authors/green/origen.html

አርጌንስ እና የአዲስ ኪዳን ጥንታዊ ቅጂዎች Read More »

Scroll to Top