Blog & Articles

የህፃናት ጥምቀት | Infant Baptism

ክፍል ፩ በወንድም ዮሃንስ ብዙ ሰዎች የህፃናት ጥምቀትን አስተምህሮ ለመቀበል የሚከብዳቸውና በተደጋጋሚም የሚጠይቁት ነገር ቢኖር እንዴት ህፃናት ማመን ይችላሉ? የሚለው ነው። በእርግጥ በጠቅላላ ይህንን አስተምህሮ የማያምኑ ሁሉ ቀዳሚ ምክንያታቸው “ህፃናት ማመን አይችሉም” የሚል ነው። መቼም ሁላችንም እንደምንስማማው ሰው ለመዳን የእግዚአብሔርን ቃል ሰምቶ ማመን አለበት። መጽሐፍ ቅዱስ ሰው ለመዳን ማመን እንዳለበት መሐከለኛ አስተምህሮው አድርጎ የሚያስቀምጠው ነገር ነው። ነገር ግን አንድ የምናውቀው ነገር ህፃናት ወንጌልን ብንሰብክላቸው ሰምተው ከዛም አሰላስለው የተነገራቸውን ተረድተውት ፤ በተገለጠም መልኩ እምነታቸውን አያሳዩም ወይም አይናገሩም። ስለዚህም ብዙዎች ከዚህ ተነስተው ህፃናት ሊያምኑ አይችሉም ብለው በማመን እነሱን ማጥመቅ ይከለክላሉ። በአጭሩ የዚህ አይነቱ አስተሳሰብ ስህተት የሚጀምረው ራሳቸው ጥያቄ አድርገው ከሚያቀርቡት ከእምነት ምንነት ነው። እምነትን በትክክል በመረዳት ብቻ ይህን አረዳድ ማስካከል ይቻላል። እንግዲህ እምነት ማለት ሰዎች ከእግዚአብሔር በነፃ የቀረበላቸውን የተጨረሰና የተጠናቀቀ ድህነት የሚቀበሉበት እጅ ነው።(ይህንን በሌላ ጽሑፍ የእምነት ብቻ አስተምህሮና የቅዱሳት ሚሥጢራት አስተምህሮ ንፅፅር በስፋት አብራርቼ አስቀምጣለሁ።) በታሪካዊው ፕሮቴስታንቱ አስተምህሮ መሠረት እውነተኛ አዳኝ እምነት በሶስት መሠረታዊ ነገሮች ላይ የሚመሠረት ወይም የሚተረጎም ነው። እነርሱም እውቀት ፣ ፍቅር እና መደገፍ (Trust) ናቸው። አንድ ሰው ለማመን የሚታመንበት ነገር ሊቀርብለት እርሱንም በሆነ መልኩ ሊያውቅ፣ ሊረዳ ወይም ሊያስተውል ይገባል። በመቀጠልም ይህ አዳኝ እምነት በፍቅር የሚሰራ ነው። ማለትም ከፍቅር ባህሪ ጋር የተጋመደና የፍቅር ድርጊቶችንም የሚያፈልቅ ነው። ሶስተኛውና ትልቅ ዋጋ ያለው ደግሞ(Definitional Aspect) ደግሞ መደገፍ(Trust) ነው። ይህም ማለት እምነት በአማኙ ደካማነት ፣ አለመቻልና ባዶነት ላይ ተመስርቶ የሚታመነው አካል ባለው ጥንካሬ፣ ችሎታ፣ አቅምና ብርታት ላይ ራስን መጣልና መደገፍ ነው። ከዚህ የመደገፍ(Trust) ትርጉሙ አንፃር እምነት ሙሉ ለሙሉ ተቀባይ ነው እንጂ ሰጪ አይደለም ማለት ነው። እምነት የሚያድነውም በዚህ በተቀባይ ባህሪው ብቻ ነው። ይህንን እውነተኛ እምነት/Fides Directa/ ብለን እንጠራዋለን። እምነትን በዚህ መልኩ ከተረጎምነው ሌላው መረዳት ያለብን አንድ ልዩነት/Distiniction/ አለ። እርሱም Councious Faith እና Uncouncious Faith ናቸው። እንተርጉማቸው። Conscious Faith/አስተውሎታዊ እምነት/፦ ይህም አማኙ በውል ተረድቶትና አውቆት የሚይዘው እምነት ነው። ይህም አንድ ሰው ስለ እምነቱ ያለውን ጥልቅ የሆነ አመክንዮአዊ ምልከታና ምክንያታዊ ግንዛቤን ያካትታል። Unconscious Faith/ደመ-ነፍሳዊ እምነት/፦ ይህም በአንድ ሰው ውስጥ ያለ ነገር ግን ገና በንቃት ወይም በዕውቀት ያልተገለጠ የእምነት ዓይነት ነው። ይህም ስለ እምነት ያለን አመክንዮአዊ ትንታኔ ወይም ምክንያታዊ መረዳትን አይዝም። እነዚህን ሁለት ልዩ ባህርያት/Distinictions/ ህፃናቱ ጋር ሳንሄድ ከትላልቅ ሰዎች በመነሳት መረዳት እንችላለን። ለመጀመሪያው የእምነት አይነት ምንም የራቀ ማስረጃም አያስፈልግም። ለምሳሌ ይህን ጽሑፍ የምታነቡት አንባቢያን ለአፍታ ወደራሳችሁ ዞር ብላችሁ ስለእምነታችሁ ካስተዋላችሁ ካደረጋችሁ እርሱ በቂ ማስረጃ ይሆናችኋል። ሁለተኛውን የእምነት አይነት ግን አቅርበንም፣ አርቀንም በተለያዩ መንገዶች ልንመለከተው እንችላለን። ከቅርቡ ለመነሳት ያህል ለምሳሌ በቀን ውሏችን ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ትኩረታችንን በሚወስዱ ስራና የተለያዩ ድርጊቶች በተወጠርንበት ሰአት አስተንትኖታዊ እምነት/ Councious Faith/ አይኖረንም። በዚህ ውስጥ የትኛውም ከራሳችን ውጪ ሙሉ ትኩረታችንን የሚወስዱ ድርጊቶች ሙሉ ለሙሉ ሊካተቱ ይችላሉ። ይህ የዕለት ተዕለት ኑሮዋችን ውስጥ የሚከናወን ከመሆኑ አንፃር ቀላሉና ቅርቡ ምሳሌ ይሆናል። ምናልባት ሰፋ አድርገን ከሩቁ ካየነው ደግሞ እውነተኛ እምነት የነበራቸውና የዳኑ ነገር ግን በአደጋ ምክንያት ራሳቸውን የሳቱ ወይም ሲብስ ኮማ ውስጥ የገቡ ሰዎችን መጥቀስ እንችላለን። በእርግጥ እዛም ሳይደርስ ሁላችንንም የሚያካትት ሙሉ ለሙሉ የፍቃድም/Will/ ሆነ የነቃ የአእምሯዊ ህላዌን/Intellect Conciousness/ የምናጣበት እጅግ ቅርብ የሆነውን የሌሊት እንቅልፍ በምሳሌነት ማንሳት እንችላለን። በእነዚህ ሁሉ ውስጥ ግን ምንም እንኳ አስተንትኖታዊ እምነት/ Councious Faith/ ባይኖረንም ግን እምነታችንም አይጠፋም። በአጭሩ እነዚህ ከላይ ያሉት ሁሉ ሰው የፍቃዱም ሆነ የመረዳቱ ችሎታዎች ሙሉ ለሙሉ ተግባራቸውን በንቃት በማይሰሩበት በዛ ሁኔታ ውስጥ ቢሆንም ግን እውነተኛ እምነት መኖርና መቀጠል መቻሉን የሚያስረግጡ ናቸው። ወደ መጀመሪያው ጥያቄ ስንመለስ ቀድመን መረዳት ያለብን ነገር “ህፃናት ማመን አይችሉም!” የሚሉ ወንድሞች በዚህ አገላለፃቸው በጭራሽ ህፃናት የማመን አቅምና ችሎታ የላቸውም(Capacity to Believe) እያሉን አይደለም። ምክንያቱም እነዚህ ክሂሎች ግዴታዊ ባህሪያት በማንኛውም ሰው ውስጥ የሚቀመጡ ሰው ሰው ለመሆኑ በባህሪያዊ ግዴታ የሚይዛቸው(Intrinsic Property) ናቸውና። ስለዚህ በብቸኝነት ለእውነተኛ እምነት እና ግዴታዊ ውሳኝ ቅድመ ሁኔታ አድርገው የሚያስገቡት ከላይ የተቀመጠውን አስተውሎታዊ እምነትን(Conscious Faith) ነው። እርሱም በቀጣይነት ያለንበትን ሁኔታ በመመርመር እና ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ማስጨበጥ ነው። ነገር ግን ከላይ ከተቀመጡት ሁለቱ ልየነቶች የምንረዳው ለእውነተኛ እምነት (Fides Directa) አስተውሎታዊ እምነትን(Conscious Faith) በጭራሽ ውሳኝ ቅድመ-ሁኔታ(necessary condition) ሊሆን እንደማይችል ነው። ይህ ካልሆነ ግን በUnconscious Faith/ደመ-ነፍሳዊ እምነት/ ስር በተዘረዘሩት ምሳሌዎች ውስጥ ያሉ አማኝ ሰዎችን በጠቅላላ ወደ ኢ-አማኒነት እየገለበጥን ልናስቀምጣቸው እንገደዳለን። ምክንያቱም ይህን አመለካከት እንደ ቅድመ-ሁኔታ ካደረግው ከእርሱ የወጣውን እምነትም ሙሉ ለሙሉ ስለሚጠፋ። ከዚህ ቀጥሎ መጨመር የሚያስፈልገን ነጥብ በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት ያለውን አንድ መፅሀፍ ቅዱሳዊ እውነት ነው። እርሱም እምነት ራሱ የእግዚአብሄር ስጦታ መሆኑ ነው። መፅሐፍ ቅዱስ መንፈስቅዱስ በሚሰጠው የቃሉ ብርሀን እና እርሱም ይዞት በሚመጣው ፀጋ እምነትን በነፍሳችን ውስጥ እንደሚፈጥር መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምረናል። እዚህ ላይ መሳሳት የሌለብን ይህ ማለት እግዜር ነው የሚያምንልን ማለት አይደለም። አማኞቹ እኛ ነን። ነገር ግን የምናምንበትን ልብ እንዲያምን የሚቀርፀውም ሆነ የምናምንበትን ያንን የእምነት ይዘት(content) የሚያቀርብልን መንፈስቅዱስ ነው ማለት ነው። መንፈስ ቅዱስ ይህንን ስራ እንዳይሰራ በብቸኝነት የሚከለክለው ነገር ደግሞ ተቃውሞና እምቢታ(Will full Rejection) ብቻ ነው። ህፃናት ግን መንግስተ ሰማይ የተወከለባቸው ፤ እኛንም እንኳን መንግስቱን ለመምሰል ወደ ኋላ ተመልሰን እነርሱን እንድንመስላቸው የተነገረላቸው ናቸው። መቼም ምሰሉ የተባልነው ቁመታቸውን አይደለም። ይህም ራሳቸውን አዋርደው የተሰጣቸውን ሁሉ ያለተቃውሞ የሚቀበሉ መሆናቸውን እርሱም እምነታቸውን(Fides Directa) እንጂ! ስለዚህ መንፈስቅዱስ ልክ በእኛ ውስጥ እምነትን እንደሚሰራ በእነርሱም ውስጥ ሊሰራ የማይችልበት ምንም ምክንያት የለም ማለት ነው። የእግዚአብሔር ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ።

የህፃናት ጥምቀት | Infant Baptism Read More »

የሥላሴ ሥነ አመክንዮአዊ ችግር(LPT)

የሥላሴ አስተምህሮ በተለያዩ ሰዎች በተለያዩ ዘመናትም ትችት ሲደርስበት መስማት የተለመደ ነው። ይህንንም ትምህርት በሰዎች አእምሮ ዘንድ ፈጽሞ መረዳት የማይቻልና በተለይም “አምላክ/God/” የሚለውን ቃል በተለያዩ አይነት በመጠቀም በሥነ አመክንዮ ዘንድ መሠረታዊ ችግር እንዳለበት ለማሳየት ይሞክራሉ። ሙግቱ እንዲህ ይቀርባል፦ 1) ክርስቲያኖች አብ አምላክ ነው፣ ወልድ አምላክ ነው፣ መንፈስ ቅዱስ አምላክ ነው ይላሉ። 2) ነገር ግን “አምላክ” የሚለው ቃል በአንድ ጊዜ አብን፣ ወልድን እንዲሁም መንፈስን የሚያመለክት ከሆነ አንድን ምንነት ያለውን አምላክ በቋሚነት ሊያመለክት አይችልም። 3) ስለዚህ ይህ አስተምህሮው ከአመክንዮአዊ ወጥነት ይልቅ አሻሚ የሆነ ግራ አጋቢ ትርጉም ላይ እንዲሆን ያደርገዋል። መልስ ይህ ሙግት መሠረት ያደረገው እኛን(ክርስቲያኖችን) “አምላክ” የሚለውን ቃል የተለያዩ አካላትን በተለያየ መንገድ መገለጫ እንደሆነ በማመልከት እንደምንል አድርጎ ሙጉቱን በሥሑት ነጥቦች ላይ ገንብቶ የጀመረ ነው። ማለትም “አምላክ” አብን በአንድ መንገድ፣ ወልድን በሌላ ፣ እንዲሁም መንፈስ ቅዱስን በሌላ እንደማለት ነው። ነገር ግን ይህ አይነቱ መረዳት በሥላሴ የአምላክነት ባሕርይ ወይም “ግጻዌ መለኮት” መረዳት ውስጥ የማያታወቅ ነው። ታዲያ አምላክ ማለት ግን በኑባሬው ያለማቋረጥ አንድ፣ የማይከፋፈል መለኮታዊ ማንነትን የሚያመለክት መለኮታዊ ባህርይ የሚል ቃል ነው። ስለዚህ ክርስቲያኖች “አብ አምላክ ነው”፣ “ወልድ አምላክ ነው” እንዲሁም “መንፈስ አምላክ ነው” ሲሉ የአምላክነት ባህርይን ያለውን አካላቶቹ አሏቸው በዚህም እያንዳንዱ አካል ያንን የመለኮትነትን ባህርይ ሙሉ በሙሉ ይጋራሉ ማለታቸው ነው። ይህም አንድ አምላክ ብቻ አለ ሲባል፣ አንድ ምንነት እንዳለ እያረጋገጡ ነው። አንዱ አምላክ በሦስት አካል የተገለጠ ነው ሲሉ ደግሞ አንድ አምላክ በአካል ሦስት ነው እያሉ ነው። አብ፣ ወልድ እና መንፈስ አንድ አምላክ ናቸው ሲሉ እያንዳንዱ አካል መለኮታዊ ባህርይ እንዳለው እያስረገጡ ነው። ስለዚህ፣ ከላይ በሥላሴ ላይ በተነሳው የሶስቱ ነጥብ ሙግቶች፣ “አምላክ” የሚለውን ቃል ውይይት ከመገባቱ በፊት ከተብራራ፣ የሚመጣውን የትኛውንም ጥያቄ ይመልሳል ማለት ነው።

የሥላሴ ሥነ አመክንዮአዊ ችግር(LPT) Read More »

ኑ መጽሐፍ ቅዱስን እንተዋወቀው

ሰላም። በመጀመሪያ ከእኛ ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብ ዝግጁና ፍቃደኛ በመሆናችሁ እግዚአብሔርን እናመሰግናለን። ምናልባት ይህን በእጃችሁ ያለውን መጽሐፍ አዲስ እና እንግዳ ሆኖባችሁ ይሆናል። ዛሬ በዚህ ጽሑፍም በእጃችሁ የሚገኘው መጽሐፍ ቅዱስ የሚለው መጽሐፍ ምንድነው የሚለውን በአጭሩ የምንተዋወቅ ይሆናል። ክርስቲያኖች 66ቁጥሮች ርዝማኔ ያላቸው መጻሕፍ አላቸው። እነዚህም መጻሕፍትበሁለት ክፍል ይቀመጣሉ። እነርሱም ብሉይ ኪዳን እና አዲስ ኪዳን በማለት ይከፈላሉ። ብሉይ ኪዳን 39 አዲስ ኪዳን ደግሞ 27 መጻሕፍትን ይዘዋል። መጽሐፍ ቅዱስ የሚለው ቃል የእንግሊዝኛው አቻ ትርጉም “ባይብል” የሚለው “ቢብሊያ” ከሚለው የጽርእ(የግሪክ) ቃል የመጣ ሲሆን “መጻሕፍት” ማለት ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በአንድ ግለሰብ እንዲሁም በጥቂት ዓመታት ውስጥ የተጻፈ መጽሐፍ ሳይሆን፣ በብዙ መቶ ዘመናት ውስጥ በተለያዩ ቋንቋዎች ከ40 በላይ ጸሐፊያን ያሉትና በ1500 ዓመታት ውስጥ የተጻፉ የተለያዩ መጻሕፍት ስብስብ ነው፡፡ በእርሱም ውስጥ እግዚአብሔር በቀጥታ ከህዝቡ ጋር ይነጋገራል፣ በሌላ ጊዜ ደግሞ በቅዱሳን ሰዎች ሐሳብና ቃል አማካኝነት ሲናገር፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ በዘመን መጨረሻ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ተግልጦ ተናግሮናል። በመጽሐፍ ቅዱስ ምሑራን የጊዜ አመዳደብ መሰረት የመጀመርያው ክፍል ከክርስቶስ ልደት በፊት በ1400 ዓ.ዓ. አካባቢ እንደሆነና የመጨረሻው ደግሞ ከክርስቶስ ልደት በኋላ በ90 ዓ.ም. አካባቢ እንደተጻፈ ይታመናል። መጽሐፍ ቅዱስን ስናነብ ማወቅ ካሉብን ልዩ ሁኔታዎች መካከል መጽሐፍ ቅዱስ እንደ ቁርአን እና ሌሎች አይነት መገለጥ እንዳልሆነ ነው። ይህን ለመረዳት ጳውሎስ ለመንፈሳዊ ልጁ ለጢሞቴዎስ በላከው 2ኛ ጢሞቴዎስ 3፥16-17 እንዲህ ሲል ይናገራል፦ “የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ፥ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል።” በዚህ ክፍል ላይ ጳውሎስ የእግዚአብሔርን ቃል፣θεόπνευστος “ቴኦፕኔውስቶስ” መሆኑን ሲናገር የቃሉ ፍቺ θεό “ቴኦ” ማለት “እግዚአብሔር” እና πνευστος “ፕኔውስቶስ” ማለትም “መንፈስ” ከሚሉ ሁለት የጽርእ ቃል የተገኘ ነው፤ በአንድ ላይ ሲነበቡም “እስትንፋሰ እግዚአብሔር” የሚል ነው። ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስ ሁሉ በእግዚአብሔር መንፈስ እስትንፋስ የተጻፈ ነው፤ የሰዎችን ልብ ሁሉ የሚቀይር እንዲሁም በእምነት የሚያነብ የእርሱን ድምፅ ይሰማል። በግልጽ ልብና አእምሮ ካነበብነው፣ እግዚአብሔር እኛ በማናቀው መንገድ ሲናገረን እንገኛለን። ስለዚህ ይህ የያዛችሁት መጽሐፍ ሌሎች ጋር እንዳለ አይነት መጽሐፍ እንዳልሆነ በእነዚህ መንገዶች ትረዳላችሁ። የመጻሕፍቱ ዝርዝር # መደቦች የመጽሐፍቱ ብዛት መጻሕፍቱ 1 የሙሴ ሕግ (ፔንታቱክ) 5 ዘፍጥረት – ዘዳግም 2 የታሪክ መጻሕፍት 12 እያሱ – አስቴር 3 ቅኔ/ግጥም 5 እዮብ – መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን 4 አበይት ነብያት 5 ኢሳይያስ – ዳንኤል 5 ደቂቅ ነብያት 12 ሆሴዕ – ሚልኪያ       ➡ አጠቃላይ ብሉይ ኪዳን 39 6 ወንጌላት 4 ማቴዎስ – ዮሐንስ 7 የታሪክ መጽሐፍ 1 ሐዋርያት ሥራ 8 የጳውሎስ መልእክታት 13 ሮሜ – ፊልሞና 9 አጠቃላይ መልእክታት 8 ዕብራውያን – ይሁዳ 10 ራዕይ(አቡቀለምሲስ) 1 ራዕይ ➡ አጠቃላይ አዲስ ኪዳን 27 ➡ ጠቅላላ ድምር 66 መጽሐፍ ቅዱስ በአጭሩ የመጽሐፉ ዋና ዋና መልእክቶች፦ በኦሪት ዘፍጥረት ምዕራፍ 1 ላይ ዓለምን የፈጠረ እግዚአብሔር እንደሆነ ገልጾ በማሳየት ይጀምራል። በዚህም እግዚአብሔርም ፍጥረታትን በስድስት ቀን እንደፈጠረ በሰባተኛው ቀን እንዳጠናቀቀ እንመለከታለን። በዚህም ውስጥ “ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር” በማለት ሰው የሚለውን ከፍጥረቱ ሁሉ መካከል ልዩ አድርጎ እንደሰራው፣ ስማቸውንም አዳም እና ሔዋን እንደነበሩ እንመለከታልን። በዚህም የፍጥረት መጽሐፍ ላይ የምንረዳው የዓለማትና የእኛ ሠሪ አንዱ እግዚአብሔር ብቻ እንደሆነ አስተዋውቆ ይጀምራል። ነገር ግን ብዙም ሳይቆይ በቅድስና የተመሰገነውን አምላክ አዳምና ሔዋን ኃጢአት ሰርተው እንዳሳዘኑት በዚህም ከእግዚአብሔርም ጋር የነበራቸው ግንኙነት ሲያጡ እንመለከታለን። ከዚያም እግዚአብሔርም በሙሴ በማስነሳት(ዘፀአት 7) በእርሱ በኩል አሥርቱን ትእዛዛት(በዘፀአት 20) እንዴት እንደሰጣቸው እንመለከታለን። በታሪክ መጻሕፍት ውስጥ የኪዳኑ ሕዝብ ኪዳን ከሌላቸው ጣኦት አምላኪያን ጋር የነበራቸውን ውጣ ውረድና የእግዚአብሔርን ፍቅሩ ጽድቁን ባደረጉት የቁጣው ፀሐይ ደግሞ ባልፈለጉት ላይ እንደወጣች በሰፊው ተከትቦ እናገኛለን። በእያንዳንዱ ታሪኮችን ውስጥ የምንገነዘበው ነገር እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ያለው የታመነ ፍቅሩ ነው፤ እርሱም በደንዳናው ሕዝበ እስራኤል ላይ ምን ያህል ታጋሽ የሆነ ፍቅር እንዳለው በስፊው ተቀምጦልናል። ለምሳሌ፦ እንደ ኖኅ፣ አብርሃም፣ ሙሴ፣ ኢዮብ፣ ዳዊት እና ሌሎች ያሉ የተወሰኑ ሰዎችን በልዩ መንገድ ጠርቶ ይህ ኃያል አምላክ በየዘመናቱ ፍቅሩን ሲገልጥ እናገኘዋለን። እነዚያ የመረጣቸው የኪዳኑ ሕዝብ በኋላም ከአመጻቸው የተነሳ ለእግዚአብሔር ሕግ መታዘዝ እንዳቃታቸው ስለዚህም እግዚአብሔር በመጨረሻው ዘመን የሰው ልጆች ያፈረሱትን የድሮውን ኪዳን ለመፈጸም እና አዲስን ኪዳን ከህዝቡ ጋር ለማቆም አንድያ ልጁን የላከው። ይህ አዲሱ ኪዳን ግን በደካማ የሰው ልጆች ሥራና ታዛዥነት ላይ የተመሰረተ ሳይሆን፣ በሰማያዊው አዳኝ፣ በዘላለማዊው ቃል በሆነው በመሲሕ ላይ ነው። ይህ መሲሕ በብሉይ ኪዳን ዘመን ጌታችን ኢየሱስ ከድንግል ከመወለዱ ከ700 ዓመት በፊት በነብዩ ኢሳይያስ ላይ ተነግሮለታል። አሁን የትንቢቱ ፍጻሜው ቀረበና እርሱ ራሱ በትልቁ የሮም ግዛት እጅጉን ደሳሳና አናሳ በሆነች ቤት የተወለደ ሆኖ መጣ።(ዮሐንስ 1፥14) አዎን ከላይ እንዳልነው እግዚአብሔር ኃያልና የከበረ ነው፣ ነገር ግን እርሱን እንድናውቀው ግን የባሪያን መልክ ያዘ።(ፊልጵስዩስ 2) የክርስቶስን ሕይወትና አገልግሎት ስናነብ ሳለ በአእምሯችን ሥሑት ትርጓሜ እንዳይፈጠር ሥነመለኮታችንን የተቃኘ መሆን አለበት። በዚህም የሚያግዟችሁን ጥሩ መጋቢያን መፈለግ ጥሩ ነው። አንዳንድ መናፍቃን አምላክ አይደለም ይልቅ ሰው ብቻ ነበር በማለት ሊያስቱ ይሞክሩ ይሆናል። በዚህም ትምህርት ንፋስ ተውስደን “ኢየሱስ ሰው ብቻ ነበር” ካልን፣ ሙሉ በሙሉ እንስታለን። “ሰው አይደለም አምላክ ብቻ ነበር” ካልንም ሰውነቱን ክደናልና ከሃዲያን እንባላለን። የነገረ ክርስቶስ ጥናት ስፊ ውቂያኖስ ነው። ይህንንም ሐሳብ መምህራን ሲገልጡ “…ጥናቱም ልክ ቀጭን ምላጭ ላይ እንደመራመድ ማለት ነው። በግራ ብንወድቅ አውጣኬ አለ። በቀኝ የወደቅን የሆንን ከሆነ ድግሞ ንስጥሮስ አለ…” በማለት ያስቀምጣሉ። ታዲያ ነገረ ክርስቶሳችን ጥናቱ ያልተቃኘ ከሆነ መርማሪው እንዳይወድቅ ይፍራ። ጥሩ አንባቢ ክርስቲያን ግን በቀጭኗ ምላጭ ላይ በቀስታ ይራመዳል። ስለዚህ በዚህን መጽሐፍ ቅዱስን ጥናት ወቅት አውዱን ያልሳተ ትርጓሜ መጠቀም፣ ተዓማኒ የሚባሉ ማብራሪያውችን ማገላበጥ፣ ታሪካዊ፣ ስዋሰዋዊ እና ቁማዊን ትርጉም ምን እንደሆነ ከሥሩ ማጥናት እጅጉን ያስፈልጋል።  ማጠቃለያ በመጨረሻም አንድ ሰው ለምን ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር መተዋወቁ ለሕይወቱ ምን ይጠቅመዋል? ያለ እንደሆነ አንደኛ፦ ኢየሱስ አምላኩና ጌታው እንደሆነ እንደሞተ እና በሦስተኛው ቀን ከሙታን እንደተነሳ ያምናል። ሁለተኛ፦ ክርስቶስ በከፈለው የቤዛነት ሥራ በኩል ብቻ የዘላለም ሕይወት አለህ ስለሚለው ነው። ሦስተኛ ፦ ሰው በሕግ ሥራ ፈጽሞ ሊጸድቅ ስለማይችል፣ በዚህም የተከፈለለትን የእዳ ክፍያ በክርስቶስ አምኖ ተስፋውንም በአለቱ ላይ ስለሚተክል ነው።(ሐዋ 4፥12) ስለዚህ አሁን ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ያልተዋወቃችሁ ወገኖች ይህንን ታላቅ መጽሐፍ አግኝታችሁ ታነቡት ዘንድ እናበረታታችኋለን። በቃሉ ውስጥ የተገለጠውን እግዚአብሔርን ፊት ለፊት የምናይበት ሕያው መስታወት ቅዱስ ቃሉ ብቻ በመሆኑ በውጤቱ ክርስቶስ ኢየሱስን በማመን የሚገኘውን የዘላለምን ሕይወት እንደምታገኙ ባለ ሙሉ ተስፋዎች ነን፡፡

ኑ መጽሐፍ ቅዱስን እንተዋወቀው Read More »

የማርቆስ እና እስረኛው ታሪክ

በሰሞኑን በተነሳው በቻርሊ ከርክ ሕልፈት ምክንያት ሁለት ጽንፍ ጎራዎችን እንመለከታለን። አንዱ ጎራ በዚህ ሀሳቡ አልስማማውም ሲል ይኼኛው አይደለም እንዲያማ አይባልም በዚህ ሀሳቡ እጋራዋለሁ በማለት ሲወያዩ ስመለከት ነበር። በእርግጥ ቻርሊን በአንዳንድ ሀሳቦቹ ባልስማማም ነገር ግን በወጣቱ ዘንድ ያለውን ተጽዕኖ እና ወደ ኋላ ገሸሽ በማይለው አቋሙ ሁሌ የማደንቀው ሰው ነው። በሳልና አዕምሮውን የሚጠቀም፣ በልቡን የማያምንበት ከሆነ የማያደርግ ነበር። በኋላ በተለያዩ ገጾች የሚጻፉትንና ደጋግመው የሚመጡትን የተለያዩ ጽሑፎችና የምስል ቪዲዮዎችን ለመመልከት ሞክሬ ነበር። በእርሱም ህልፈት ምክንያት ብዙዎች ከኢ-አማንያን ወደ ክርስትና እንደመጡና ቤተክርስቲያንን ሥፍራ አጣን እስከማለት ደርሰው እንደተገኙ እንመለከታለን። ይኼንን ታሪክ ስመለከት በሞቱ ብዙዎችን መጥራቱን ሳስብ የማርቆስና የእስረኛው ታሪክ ጋር ከዚህ ቀደም ፊልጵስዩስን በማጠናበት ጊዜ ከጻፍኩት ጽሑፍ ጋር የቻርሊ ከርክ ታሪክ ተመሳሰለብኝ። የማርቆስ እና የእስረኛው ታሪክ በፊልጵስዩስ 1፥21 ላይ የተመሠረተ አፈ-ታሪክ ነው። ከታሪኩ በፊት ቃሉ እንዲህ ይነበባል፦ “ለእኔ ሕይወት ክርስቶስ፥ ሞትም ጥቅም ነውና።”  — ፊልጵስዩስ 1፥21 ማርቆስ በፊልጵስዩስ የሚኖር ወጣት ለእምነቱ ታጋይ ሰው ነበር። ማርቆስ በክርስትና ምክንያት ዘወትር በሮማውያን እና በቅርብ ወዳጆቹ መገለል ከዛም ታልፎ መከራ በገጠመው ቁጥር ኹል ጊዜ ወደ እስር ቤት ይሄዳል። በዛም እስር ቤት በእምነቱ ጽኑ የሚባለውን ጳውሎስን እንዲጎበኝ ይሄድ ነበር። የእስር ቤቱ ጨለማ ክፍል ሁልጊዜ ለማርቆስ አስጨናቂው መንገዱ ነበር፣ ነገር ግን ጳውሎስ በዚያ ውስጥ ሁልጊዜ ደስታ የተሞላበት ዓይን ነበረው። አንድ ምሽት ላይ እንደተለመደው ለጉብኝት በሚሄድበት ጊዜ ማርቆስ ስለ ጳውሎስ ከሚደርስበት መከራ መደሰት ምክንያቱ ምን እንደሆነ እንዲህ ሲል ጠየቀው፦ «ጳውሎስ፣ ነገ ሊገደሉህ ሲሆን እንዴት እንደዚህ ፊትህ ላይ ደስታ ይታያል? ሞትን አትፍራም?» ይለዋል ጳውሎስም ከትከሻው ላይ እጁን አሳረፈ እና እንዲህ አለ፦ «ማርቆስ፣ ከክርስቶስ ውጪ በዚህ ዓለም ሳለህ ጥሩ ሆነ መጥፎ የሚባል ነገር የለም። ለእኔ ሕይወት ክርስቶስ፥ ሞትም ጥቅም ነውና። ባለሁበት ዘመን ሁሉ ክርስቶስን እናገራለሁ፤ በዚህም የክርስቶስ አካል ፍጹማን ይሆኑ ዘንድ በመከራዬ ሁሉ አጽናናለሁ። በዚህስ ብሞት ግን፣ ከእርሱ ጋር እኖራለሁ። እኔ እንዴት እጎዳለሁ?» በማለት መለሰለት። ማርቆስ ተደነቀ። «እንግዲህ… በኑሮህም በሞትም ክርስቶስ ድሌ ነው የምትለኝ?» አለ። ጳውሎስም፦ «አዎን። ይህች ዓለምን እንዳልመስል በደማስቆ መንገድ ላይ ሕይወትና አገልግሎትን ሰጥቶኛል። በዛም በተቀበልኩት ሕይወት ሞት ወደ እኔ ቢመጣ አልሰጋም ምክንያቱም የምቀምሰው ጽዋ ክርስቶስን ራሱን ይሰጠኛል። ስለዚህ አንዳችም አልሰጋም።» በማለት መለሰለት። እነዚህ ቃላት በእሥረኛ ጠያቂው በማርቆስ ልብ ውስጥ በጽኑ ጠነከሩ። ከብዙ ዓመታት በኋላ፣ በፊልጵስዩስ ላይ ስደትና መከራ በክርስቲያኖች ላይ መጣ። በዛም መከራ ውስጥ ማርቆስ የጳውሎስን ቃል በልቡ አሰበ። በዚያም ሸንጎ ተይዞ ስለ እምነቱ ሞት ቅጣትን በማርቆስ ላይ ሊያደርሱበት በተሰለፉ ጊዜ፣ ቆመና እንዲህ ብሎ ቃሉን ተናገረ፦ «በህይወት መኖሬ በክርስቶስ ውስጥ አገልግሎት እና ፍሬያማ ሥራዬ ነው። ሞት ቢመጣ ደግሞ ከክርስቶስ ጋር መኖርን የሚሰጠኝ ሕያው ድልድይ ነው። ለእኔም ይህ ደግሞ የተሻለ ነው አላቸው።…» አጠገቡ የነበሩት፣ ሊገድሉት ከሚፈልጉት መካከልም አንዳንዶች የማርቆስን እምነት ምንኛ ነው? በማለት እርስ በእርሳቸው አንጎራጎሩ። ዳግመኛም ማርቆስ የመጨረሻ የክህደት ቃልህን አስፍርና ተናገር ባሉት ጊዜ « ለእኔ ሕይወት ክርስቶስ፥ ሞትም ጥቅም ነውና…» በማለት አጠናቀቀ ንግግሩን። የማርቆስም ሞት በፊልጵስዩስ ቤተክርስቲያንም በዙሪያዋ ባሉት ሁሉ ላይ ብዙዎች ጋር ደረሰ። ብዙዎች በጽናት ተመሰረቱ፣ በዛችም ከተማ ወንጌሉ ብዙዎችን እየለወጠ ሄደ። ይሄን እምነት መርሕ አድርገው የቤተክርስቲያን አባቶች ብዙዎች እንደ ሻማ ቀልጠውበታል። ለዚህም ነው ጠርጡልያንም ሲናገር The blood of the Martyrs is the seed of the Church(የሰማዕታት ደም የቤተክርስቲያን ዘር ነው) ያለው። በአጭሩ የቻርሊ ከርክ ፖለቲካ አቋም ምንድነው? የሚል ትርጉም ሳይሆን ጽሑፉ ትኩረት የሚሰጠው በእርሱ ህልፈት ምክንያት የመጣውን ሰዎች ባሰብን ቁጥር እግዚአብሔር በቃሉ ሞትም ጥቅማችን እንደሆነ የሚነግረን። በዚህ ዘመንስ እንደ እንቁ የምናያቸውን ምሑራንን ለማጥፋት ብዙዎች የሚያቅዱት። በዚህ ሁሉ ግን እግዚአብሔር ጽኑ እምነት ሰጥቷቸው የክርስቶስን ወንጌል ለማገልገል የተሰጡ ስንቶች ይሆኑ? እንጃ፤ ለእኛ ግን እግዚአብሔር በዚህ ጽኑ እምነት ይባርከንም።

የማርቆስ እና እስረኛው ታሪክ Read More »

ንጉሥ ሄነሪ ስምንተኛ እና የአንግሊካን ቤተክርስቲያን?

ክፍል አንድ አብዛኛውን ጊዜ በአንግሊካን ቤተ ክርስቲያን ላይ ከሚነሱ ትችቶች መካከል ትልቁን ሥፍራ የሚይዘው የንጉሥ ሄነሪ ስምንተኛ(Henry VIII) ትዳር መፍረስ ምክንያት የእንግሊዝ ቤተክርስቲያን በዛ መንሥኤ የተጀመረች አድርጎ መሞገት ነው። ይሄ ደሞ የቤተ ክርስቲያንቱን ታሪክና አስተምህሮን በአግባቡ ካለማወቅ የሚነሳ ትችት ተደርጎ በብዙ ምሑራን ዘንድ የሚወሰድ ነው። ከክርስትና ውጭ ያሉ ሃይማኖታዊ ድርጅቶች(ሙስሊሞች፣ አርዮሳውያን፣ ሰባልዮሳውያን…) ክርስትና የጀመረው በንጉሥ ቆሰንጠንጢኖስ ነው ከሚል የአፈ ታሪክ የማይለይ ሙግትና በብዙ የተወሳሰበውን የታሪክ፣ የፖለቲካ እና የሥነ መለኮት እይታን ለማቅለል የሚሞከር ከንቱ ትግል ነው በማለት መግለጽ ይቻላል። በዚህ ጽሑፍ ደግሞ ከመጀመሪያው የንጉሥ ሄነሪ ስምንተኛ እና የንግሥት ካትሪን ትዳር ለመመልከት እንሞክራለን። የንጉሥ ሄነሪ ስምንተኛ ታላቅ ወንድም የነበረው አርተር በ1501 ካትሪንን አገባ። አምስት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በሕመም ምክንያት ይሞታል። ያገባትም የ16 ዓመቷ ልጃገረድ ንግሥት ካትሪን ባልቴት ትሆናለች። የንግሥት ካትሪንንና የልዑል አርተር ጋብቻ በስፔንና እና በእንግሊዝ መሃል ጥሩ የሆነ ፖለቲካዊ ግንኙነት ፈጥሮ ነበር። ንጉሥ ሄነሪ ስምንተኛም ይህን ፖለቲካዊ ግንኙነት እንዲቀር ስላልፈለገ ካትሪንን ያገባታል። እንደ ብዙዎች ምልከታ መሠረት ዘንድ ይህ ትዳር የተሳካ አልነበረም ይባላል። ወቅቱም የህፃናት ሞት ከፍተኛ  የነበረበት ጊዜ ስለነበር ከወለዳቸው ሦስት ወንዶችና ሶስት ሴቶች ልጆች መሀል 1 ልዕልት ማርያም (Mary I “Bloody Mary”) ነበር የተረፈችው።(ስለ Mary በክፍል ሁለት በስፋት እንመለከታለን።) በዚህ ትዳር ውስጥ የሚተካውን ወንድ ልጅ በማጣቱ በትዳሩ ላይ ጥያቄ ማንሳት ጀመረ። ለዚህም ይሆነው ዘንድ በኦሪት ዘሌዋውያን 20:21፦ “ ‘ማንኛውም ሰው የወንድሙን ሚስት ቢያገባ አድራጎቱ ርኩሰት ነው፤ ወንድሙን አዋርዷልና፣ ያለ ልጅም ይቀራሉ። በሚለው ቃል ላይ በመመስረት የወንድሙን ሚስት በማግባቱ እንደተረገመና ትክክለኛ ጋብቻ እንዳልሆነ በ1527 ዓ.ም ለሮማን ካቶሊክ ቤተክርስቲያን እና ለፖፕ ቀለሜንጦስ ሁለተኛ በጥያቄ መልክ ማቅረብ ጀመረ። እዚህ ታሪክ ላይ ልብ ልንለው የሚገባን ነገር ቢኖር በአንግሊካን ቤተክርስቲያን ሆነ በሮማን ካቶሊክ ፍቺ እንደማይፈቀድ ነው። ነገር ግን የንጉሡ ሄነሪ ስምንተኛ ጥያቄ የፍቺ ጥያቄ ብቻ አልነበረም ጋብቻው መጀመርያውኑ ትክክለኛ ጋብቻ ነው ወይ የሚል ነው ።(annulment ‘a legal procedure within secular and religious legal systems for declaring a marriage null and void’) በዚህም የጋብቻውን ትክክለኛነት ጠይቆ ትክክለኛ አለመሆኑ በሮማን ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያኗ ህግ ከተረጋገጠ ጋብቻው መጀመሪያውኑ ትክክለኛ አይደለም ተብሎ ሊወሰንለት ይችላል። ለዚህም በተለያዩ ጊዜያቶች በሮማን ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ይህ ስርዐት ሲተገበር ታይቷል። ለምሳሌ ታዋቂው አሜሪካዊው ፖለቲከኛ ቴድ ኬኔዲ(Ted Kennedy) በጋብቻው ወቅት ታማኝ አለመሆኑን አምኖ የሃያ አራት ዓመት ጋብቻውን በሮማን ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ፊት ትክክለኛ ጋብቻ እንዳልነበር ተቆጥሮለት ተለያይተዋል። ሌላኛው ደግሞ ዮሴፍ ኬኔዲ  ሁለተኛ(Joseph Kennedy II, 2007 እ.ኤ.አ) እና ታዋቂው ፈረንሳያዊው ገዥ ናፖሊዮ ቦናፓርቲ እና የንጉሥ ኤድዊግ(Eadwig 959 እ.ኤ.አ አካባቢ) ለዚህ ታሪክ ተጠቃሽ ናቸው። ነገሩን ለየት የሚያደርገው ደግሞ በዚህ ዘመን እንደሚታወቀው አይነት ፍቺ በመካከለኛው ዘመን በነበሩት ሰዎች ዘንድ አልነበረም። የጋብቻን ትክክለኛነት ማረጋገጥ እና በመጀመሪያውኑ ጋብቻ እንዳልነበር ማስመስከር (Annulment / Declaration of Nullity) የተለመደ ነበር። በዚህም ዘመንም የሮማን ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በህግዋ ውስጥ ይህ ጋብቻ ነው ለመባል ማሟላት ያለበትን ነገሮች በዝርዝር ተቀምጧል።(the code of canon of law 1095-1107) ለምሳሌ ያህል ሁለቱም ተገቢዎች በፈቃዳቸው መሆን አለበት ቤተሰብ(የደም ዝምድና) ያላቸው መሆን የለባቸውም። ማንኛውም ክህነት የተቀበለ መሆን የለበትም (ቄስ ,ጳጳስ)  የመሳሰሉትን ህጎች የያዘ ነው። ስለዚህ የንጉሥ ሄነሪ ስምንተኛ ጥያቄም ከዚህ የተለየ አልነበረም። ለጋብቻው ትክክለኛ አለመሆን እንደ ምክንያት አድርጎ ያስቀመጠው ነገር፦ የወንድሙን ሚስት ማግባት ትክክለኛ ጋብቻ አይደለም በመፅሐፍ ቅዱስ ህግ ጋር ይጋጫል። የወንድሙን ሚስት በፖፕ ጁሊየስ ሁለተኛ ፈቃድ(papal Dispensation) ማግባቱ ትክክል አይደለም። ንግሥናውን የሚተካ ወንድ ልጅ አለማግኘቱን እንደ እርግማን ይቆጥረው ነበር። እነዚህን እንደ ምክንያት አድርጎ በማቅረብ ለፖፕ ቀለሜንጦስ ሁለተኛ ጥያቄውን አቀረበ ነገር ግን የጠበቀው መልስ በተቃራኒ ሆኖ ይህን ሊፈቅድለት አልወደደም። ምክንያቶቹም ተብለው የሚነሱት፦ አንደኛ፦ የንጉሥ ሄነሪ ሚስት ካትሪን በጊዜ ኃያል የሚባለው የሮማን ገዢ የሆነው የስፔን ንጉሥ የቻርለስ አምስተኛ አክስት(Holy roman Empire) ስለ ነበረች ነበር።ንጉሥ ሄነሪ ጥያቄውን ባቀረበበት በ1527 በዛው ዓመት በቁጥር ከሃያ ሺ የሚበዙ ደሞዝ ያልተከፈላቸው ወታደሮች(አስራ አራት ሺህ የሚሆኑ ጀርመናዊ ሉተራውያን ወታደሮች እና ስድስት ሺህ ስፔናውያን እና ጣሊያንናዊ ወታደሮች) ንቅናቄ የሮማን አገዛዝና ያደከመ፣ ከሃምሳ አምስት ሺህ ወደ አስር ሺህ የሮም ህዝቡ ቁጥር የቀነሰበት፣ እስከ ሁለት መቶ የሚሆኑት ወታደሮች ፖፑን ለመጠበቅ የሞቱበት፣ ፖፑም በአማፅያኑ እጅ ገብቶ በእስር የነበረበት ጊዜና መንበረ ጴጥሮስ በትልቅ ሀዘን ውስጥ የሆነበትም ጊዜ ነበር። ከዚህም ክስተት(the sack of Rome 1527) ዘጠኝ ወር ያህል ፖፑ ታግተው ከቆዩ በኃላም ከገበሬዎች ጋር በመመሳሰል ያመለጡበት ጊዜ ነበር። በዚህ መሐልም ግን የንጉሥ ሄነሪ የጋብቻ ጥያቄ አልተመለሰም ነበር። ጋብቻውን ትክክለኛ አይደለም ቢሉ በዚያን ጊዜ የሮማን ንጉሥ የነበረው ቻርለስ አምስተኛ ስለሚያስተዳድሩአቸው ከእርሱ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ስለሚያሻክር ፈርተውም ነበር። ሁለተኛው፦ ምክንያት ንጉሥ ሄነሪና ካትሪንን ያጋባው የቀድሞ ፖፕ ጁሊየን ሁለተኛ ስለነበር የእሱን ስልጣን መቃወም ስላልነበረበት ነበር። ሦስተኛው፦ ምክንያት ደግሞ ካትሪን ከአርተር (ከንጉሥ ሄነሪ ወንድም) ጋር በጫጉላ ወቅት ስጋዊ ተራክቦ አልነበረንም ማለቷ ነው። ጋብቻ የሚፈፀመው በስጋዊ ተራክቦ ነው ተብሎ ስለሚታመንም ካትሪን የመጀመሪያ ጋብቻዋ ወቅት ስጋዊ ተራክቦ ካልነበር ከንጉሥ ሄነሪ ያላት ጋብቻ ትክክለኛ ይሆናል። ሆኖም እርሱዋ ይህንን ብትልም የልዑል አርተር የቅርብ ጓደኞች ግን ከእርሷ በተቃራኒ ቆመው ነበር የተናገሩት። በዚህ ምክንያት ለንጉሥ ሄነሪ አለመፈቀዱ ንጉሡን አስቆጥቶታል። ስለዚህም በ1534 ዓ.ም እራሱን በእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን ዋና የቤተ ክርስቲያን የበላይ ሃላፊ አድርጎ በመሾም ከፖፕ ቀለሜንጦስ ሁለተኛ ቤተ ክርስቲያኒቱን ለያት። ንጉሡ ራሱን የቤተክርስቲያን የበላይ አድርጎ በሾመበት ወቅት ብዙ ቢሾፖች ዲያቆናቶች እና መነኩሴ በመቃወማቸው ምክንያት በእምነታቸው ሰማዕታት ሆነዋል። በ1538 ዓ.ም ፖፕ ጳውሎስ ሶስተኛ ከሮማን ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን አወገዘው(excommunicate) ተደረገ። ከዚያም በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለ ከአርክ ቢሾፕ ቶማስ ክራመር ጋር በመሆን ደግሞ ጋብቻ ትክክለኛ እንዳልሆነ አጸደቀ። ግን ብዙም ሳይቆይ ደግሞ በ1533 አናን አገባ። የሄነሪ ጋብቻ ታሪክ በዚህ አያበቃም እስከ ዘመኑ መጨረሻ ድረስ ስድስት ሚስቶች በተለያዩ ምክንያቶች ነበሩት። ቢሆንም ዘሩን የሚተካ ልጅ ከኤድዋርድ ውጭ አላገኘም ነበር። ኤድዋርድን ቢተካውም ስድስት አመት ከገዛ በኋላ በ15 ዓመቱ በህመም ሞቷል። በዚህ ሁሉ ታሪክ በስተ መጨረሻም ግን ልንረዳው የሚገባው የእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን በንጉሥ ሄነሪ ጊዜ ፕሮቴስታንት እንዳልነበረችና ሄነሪ ካቶሊክ እንደ ነበር። ሉተርንም የሚቃወም ጽሑፍ “ሰባቱ ቅዱስ ምስጥራት መከላከያ”(Defense of the Seven Sacraments/Assertio Septem Sacramentorum) በማለት ጽፎ የነበር መሆኑን ማወቅ አለብን። በዚያም ከፖፕ ሊዮ ኤክስ በ1521 ዓ.ም “የእምነት ጠባቂ”(“Defender of the Faith”) የሚል ስም ተሰጥቶት ነበር። በዚህም ካቶሊክ ሆኖ ነበርም የሞተው። በንጉሥ ሄነሪ ጊዜ በአንግሊካን ቤተ ክርስቲያን ንግሡ መጥቶ የአስተምህሮ ለውጥ በምንም አይነት መልኩ አላደረገም ነበር። ስለዚህ አንግሊካን ቤተ ክርሰቲያን በንጉሡ ተመሥርታለች የሚለው አስተምህሮ በዚህ ውድቅ ይሆናል። ነገር ግን የአንግሊካን ቤተክርስቲያን በ597 ዓ.ም በፖፕ ጎርጎርዮስ አማካኝነት የካቲቤሪውን ቅዱስ አውግስጢኖስ ወደ እንግሊዝ በመላክ ወደ ሮም ቤተክርስቲያን ውስጥ ተጠቅልላ ባካተተቻት ከአንድ ሺህ ዓመታት በኃላ ቤተክርስቲያኒቱ ከሮም ውጭ ሆነች። ንጉሥ ሄነሪ የእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያንን ከሮማን ካቶሊክ እንደ ቀድሞዋ መለየቱ ለተሐድሶው የማይካድ ጥቅም ቢኖረውም ነገር ግን ያደረጋቸው ነገሮች እና ሕይወቱ ሙሉውን የአንግሊካን ቤተ ክርስቲያንን ታሪክ ለመግለጽ የማይችል መሆኑን መገንዘብ አለብን። ምክንያቱም የአንግሊካን ቤተ ክርስቲያንን ለመረዳት ከዚህም ያለፈ የተወሳሰበ የታሪክና የስነመለኮት ጥልቀት ውስጥ ዘልቆ መግባት አለብን። የአንግሊካን ቤተ ክርስቲያን መልክ ማቆጥቆጥ የተጀመረው በ1536 ዓም የአስር የሃይማኖት አንቀጾች (Ten Articles) (የካቶሊክ እምነት ያለው ትንሽ በተሃድሶ ሃሳብ ተጽዕኖ ያለበት) ከዚያም 1539 ዓም ስድስት የሃይማኖት አንቀጾች (six articles of faith) (አጥባቂ

ንጉሥ ሄነሪ ስምንተኛ እና የአንግሊካን ቤተክርስቲያን? Read More »

“አንድ ታሪክ ላውጋችሁ”

ከአዲስ አበባ ወጣ ብላ በምትገኝ በአንዲት ገጠራማ አካባቢ የሚኖሩ አነስተኛ ማህበረሰብ ነበሩ። አብዛኛዎቹ የአውራጃው ነዋሪዎች ጣዖት አምላኪያን የነበሩና ስለ እግዚአብሔር መኖር የማያቁ የሆኑ እንደዋዛ የሚታለፉም አይደሉም። በዛ መካከል እውነትን የሚያቁ ጥቂት ክርስቲያኖች ግን አልጠፉም ነበር፡፡ ያው ጭስ ባለበት ጥቂትም ቢሆን እሳት አይጠፋም እንደሚባለው ተረቱ አንዳንድ ቦታዎች ላይ ሰፍረው ነበር።(ከዛ በፊት ሚሶናውያን በስፍራው ተልከው ወንጌልን ያደረሱ የነበሩ ይመስላል።) በጥልቀት በማህበረሰቡ ጫና ምክንያት ግን ወንጌልን ባለማድረሳቸው ብርቱ ክርስቲያን እንቁጠር ብንል እንደ ቦዘና ሽሮ ጥቂት ሥጋ ጣል ጣል ይመስል በትግል ነው የምናገኘው፡፡ (ያው ቦዘና ስለምወድ ምሳሌ ተጠቀምኳት፤ የምትወዱ ሰዎች ካላችሁ ከአፍቃሬ ነኝ ለማለት ነው)። በአንድ ወቅት እኒያ ወንጌልን የሰሙት ሰዎች ላልሰሙ ሰዎች ለማድረስ ለሁለት ተከፍለው ለጣዖት አምላኪውና አንዱ ወገን ደሞ አምላክ የለም(እግዚአብሔርን ለማያቀው) ተበታትነው በአንድነት ማሰራጨት ጀመሩ። በማህበረሰቡ መካከል በብዙ ታወቁ፣ ክርስትና ከዛች መንደር አልፎ ቀያቸውን ሙሉ አጥለቀለቀው፡፡ የዚህ ሁሉ ብርታትና የአንድነታቸው ምክንያት ለቤተክርስቲያን ቀናኢ ሀሳብ አለን ማለታቸውና አንዱ በአንዱ ስራ ጣልቃ ሳይገባ፣ ሳይንቅ፣ የሚሰራውን አገልግሎት ሳያሰናክልና ክፉ ሳያስብ አንድነትን ስለመረጠ ነበር። የሆነው ሁሉ ግን በአንዲት ክፉ ቀን ይሄ አንድነት ብዙ ርቀው እንዳይሄዱና ተሰናክለው እንዲወድቁ አደረጋቸው፡፡ የሰላሟ መንደርም ሁከት ተጀመረ። ለዚህ ሁሉ ጉስቁልና መንስኤ ክፋት ማሰባቸው ነበር። በተጨማሪም ሐዋርያው ጴጥሮስ በክታቡ እንዲህ ያለውን መዘንጋታቸው ነበር፦ “እግዚአብሔርንም በመምሰል የወንድማማችን መዋደድ፥ በወንድማማችም መዋደድ ፍቅርን ጨምሩ።” 2ኛ ጴጥሮስ 1፥7 እግዚአብሔርን ምሰሉ በተባሉበት ቦታ ይልቅ የራስን ፍላጎትን በሰዉ ዘንድ መሳላቸው፣ ከአሻጥር ይልቅ መዋደድን ሳሉ በተባሉበት ቦታ ላይ የእኔ ወንጌል በላጭ የእግዚአብሔሩ ሀሳብም በእኔ ተገልጧልና ፍቅር እኔ ጋር ነው፤ የእርሱ ወንጌል እንዲህ…በማለት ለማህበረሰቡ አልባሌ ስብከት ማሰማት ጀመሩ። ይሄ ነበር የውድቀታቸው ምክንያቱ፡፡ ታሪኩ በዚህ አላበቃም ቢያበቃማ ጥሩ ነበር፤ እነዚያ ወንጌል የሰሙ ያመልኩበትም የነበረችው ቤት በዚህ ሽኩቻ ወደቀች፣ የመንደሪቷ ቤተክርስቲያን ፖለቲካ ስለያዛት ተናደች፣ የአንዱን ግለሰብ ትችት ለገሃዱ ዓለም መናገር የሚያመጣውን ጦስ ስላልተገነዘቡ ጣዖት አምላኪያኑ ወደ እጣናቸውና ደም ማፍሰስ፤ አምላክ የለሾቹ ወደ ቁዘማቸው ገቡ፡፡ ይሄን ሁሉ ታሪክ ያነበብክ አንባቢዬ የነገሩ መጎሳቆል ለምን የሆነ ይመስልሃል? እንዲያ እንዲህ ብለህ ልታብራራ ከቻልክ ጥያቄው ላንተ በዝርዝር ከታች ላስቀምጥልህ፦  ➞ የክርስቲያኖቹ እንዲያ መሆን መንስኤው ምንስ ይሆን? ➞ በዚህስ ዘመን ምን እየሰማህ ይሆን? ➞ በዚህ ታሪክ ላይ ቀይራለሁ ብለህ ምታስበው ነገር ይኖር ይሆን? ኦኦኦ….ጥያቄማ አላብዛ ይቅር፤ ይሄ አጭር ማስታወሻዬ ጽሑፍ ለካ ብዙ ጥያቄ ያግዳል..! ጽሑፏም ጣፍጣ ለአንባቢያን በአጭሩ አትቀርብ ይሆን በሚል አሳጥሬዋለሁ፡፡ አድማጬና አንባቢዬ ሆይ..! ስትመልሳቸው ሐዋሪያው ጨምሩ ማለት ምን ማለት ይሆን? የምትለዋን ነገር ባትረሳት ጥሩ ነው፡፡ ጨረስኩ እያልኩ ቀጠልኩ አይደል ጨርሻለሁ።[2] 1] ሰሞናዊውን የክርስቲያን ማህበረሰብ ሁኔታ ስንመለከት ይሄ ታሪክ ለመጻፍ ተነሳሁ። ከእግዚአብሔር አገልጋይ ሆነው ግን በእግዚአብሔር ዓለም ውስጥ የሌለን ማንነት ለማሳየት፣ ለማጉላት መሞከራቸውን ሳይ እግዜሩ ይፋረድ አልኩና ይሄን አጭር ታሪክ በአጭር ማስታወሻዬ አካተትኩላችሁ። 2] በመጨረሻም ይሄን የጽሑፍ ልጥፍ ለማለት የፈለገውና የተነገረው ሳይገባህ ቅርጫፉን ይዘህ በደፈናው የምትቆጣ፣ ምዕመኑን ጨፍላቂና እብሪተኛ መጋቢ ሆይ….! ቤተክርስቲያን ላይ መንግስት ለመሆን የምታስቡም ጭምር ካላችሁ…! ይቺ አጭር ፖስት ለእናተ ትቀርብልኝ ዘንድ አሳሰብኩ። እግዚአብሔር በዚህ ዘመን ከምንሰማው ነገር ሁሉ ይጠብቀን። አሜን።

“አንድ ታሪክ ላውጋችሁ” Read More »

ይገርማል…ይደንቃል….!

ድንቅ ነው!! አምላክ ሥጋን ለብሶ ወደ ምድር መጣ የሃጥያት መከራችንንና የዲያቢሎስ የሹፈት ነጋሪት ዝም ለማስባልም ተገለጠ። ነገር ግን የእኛን መከታን ነፃ አውጪያችንን፦ በአክሊል ፋንታ የእሾህ ጉንጉን፣ በፍቅር ከማቀፍ ፋንታ ሰጠነው ጅራፍ፣ በእጆቻችን። እሱም አልበቃ ብሎ አዳኙን ራሱን ራስህን አድን አልነው፤ ሙሾ በሚመስል ቅላጼ እያላገድን አሾፍንበት፤ ከዛም ብሶ ሰቀልነውም በእንጨት በችንካር አድርገን። ይሄ ሁሉ ሆነና ጀንበርም ሳትጠልቅ፣ ፀሐይም ሳትገባ ሥራው ድንቅ ነው የሚል ድምጽ ሰማይ ምድር ሁሉ መወደስ ጀመረ። የጩኸቱ ድምድምታ ምን ይሆን? ብለን ተነሳን፤ እኛም ያኔ ጎኑን የተወጋው፣ እጆቹም ተቸነከሩ፣ ሄዷልና ሞቷል የተባለው አዳኙ ራሱ ያው መሢህ መሆኑን አወቅን። በፍርሃትም ያየነውን በመገረም ድንቅ ነው አልን። ከእላፋት ጋር አእላፋት ሆነን፥ ባሾፍንበት ከንፍራችን ከሙታን በኩር፣ የነገስታት ንጉስ፣ የጌቶች ጌታ፣ የምድር ሁሉ ባለቤት እርሱን አመሠገንን። ጨመር አድርገንም ተነስቷል በዚህ የለም መቃብሩ ባዶ ነው ተመልከቱ በዚህ የለም፤ በሚል ክብሩ ሁሉ በአርያም በምድር ይሁን ስንል ጣፋጭ መዓዛ ያለውን ዝማሬ ለታረደው በግ አቀረብን። ለአንባቢው መልዕክቴ በዚህ ወቅት ላይ የጥሞና ጊዜ ያጣህ እና ረፍት የሌለህ ሆይ “እርሱ ሰላም የሚሰጥ እረፍት ነውና በልብህ ታስገባው ዘንድ አሳሰብኩህ”። አሜን።[፩][፪][፫] መልካም የጥሞና ጊዜ ይሁንላችሁ…..! [፩] ከሚባለው በላይ ከደረሰበት መከራ አንጻር ይገርማል ጥቂት ሆና ትታየን ዘንድ አንባቢው ያስተውል። [፪] ይደንቃል ስንል ከእውነት የሆነ መደነቅ እንዲሆን ሰሚው ከንግግል ባለፈ ከልብ በኾነ ፍቅር ትል እንደሆን አሳሰብኩህ። [፫] ምንጭ፦ አጭር ማስታወሻ በወንድም David Yeshua, ያልታተመ በጽሑፍ ላይ ካለ መጣጥፍ የተወሰደ።

ይገርማል…ይደንቃል….! Read More »

ሆሣዕና <አሁን አድን….!>

ደጉ ጌታ መጣ ተገለጠ ሰዎችም ተቀበሉት። ከተቀበሉት መካከል ሰው ብቻ ሳይሆን ከምድር ፍጥረታት መካከል ያለች አንዲት ውርጭላ ከአህያይቱም ጋር ነበረች። አህያይቱም ተነሳች ክብሯን አየች፣ ንጉስም ተቀመጠባት፤ አምላክ ሥጋን ለብሶ መጣ ወደ ምድር አቤቱ ዛሬ አድን ሆ…ሆ ብለን ሆሣዕና[፩] እንድል። የቀደመው ተተንብዮ የነበረው ትንቢቱ ተፈፀመ ሆ…! እያልን ከተገኘው የዘንባባ ዝንጣፊ ከእግሩ ሥር እያቀረብን። ንጉሡም ተራመደ[፪] አለፈ የትንቢቶቹ ምጻሜ ሊቃረብ ሆነ…! ይኼን ለመረዳት ጥሞና መውሰዱ ሳያሻን አይቀርም ከበፊቱ ይልቅ ሆሣዕና እንድልን።   መልካም የጥሞና ቀን እና ምሽት…! [፩] ሆሣዕና|Hosanna፦ ዋሴ ና፣ አዳኜ ና፣ ጠባቂዬ ድረስ ማለት ነው። ‘ዋስ’ እና ‘ና’ ከሚሉ ቃላት የተመሠረተ ቃል ነው።[…አድነን፡ እባክኽ አድነን…መድኅኒትነት፤ መሆን ወይም መባል።] [፪] ጌታ ወደ ኢየሩሳሌም በገባ ጊዜ ህጻናት ካዜሙት ቃል፥ ሆሣዕና ፥ “…ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ በጌታ ስም የሚመጣ የተባከ ነው፤ ሆሣዕና በአርያም እያሉ ይጮኹ ነበር።” (ማቴ 21፡9)

ሆሣዕና <አሁን አድን….!> Read More »

“ጣዕመ ዜማ የሌለው እንቢተኛ ልብ…!”

መናፍቃን እና እንቢተኛ ልብ አንድ ናቸው። ሁለቱም ስተው ሳሉ ጭብጨባ ይሻሉ፤ መናፍቅ ሁሌ የሳተ ስለሆነ ከቅዱሳት መጽሐፍት መውጣቱ በቀላሉ ያሳብቅበታል። እንቢተኞቹ ግን ተበጥረው ከመናፍቃኑ መለየቱ የሰሚው ድርሻ ነው። በዚህች አጭር ጽሑፍ ግን የምታደምጥ እና የምትሰማ አንባቢ ሆይ ዕቡይ[፩] ልብ ያላቸውን ሰዎች በዚህ ለያቸው፦ “የቅዱሳት መጻሕፍት ትርጓሜ ቃናው ጠፍቶባቸው፤ አቃቢነ ክርስትና ዕቡይ ሰው ልሁን ልደመጥ ማለታቸው መሠረታዊ መለያቸው ነው። በመጨረሻም አንባቢ ሆይ..! ያው ዕቡይ ዕቡየ ልብ ነው። ዕቡየ መንፈስም።[፪] እኒህን ዕቡያን ከመናፍቃኑ ለመቆንጠር ቢያዳግትም…. ሥነ-ምግባራቸውን በሚያስተምሩት አስተምህሮ ከቅዱሳት መጽሓፍት እና ከቤተክርስቲያን ትምህርት አፈንግጦ ወጥ መሆናቸውን በጩኸቱ፣ በሥነ-ምግባሩ እና በሚያደርገው ክዋኔ ለክተህ ታውቅ እንደሆነ እወቅ።[፫] [፩] በቁሙ ትቢተኛ፣ ኵሩ፣ ልቡ ያበጠ፣ የተነፋ፡፡ ምንጭ፤ መጽሐፈ ሰዋሰው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ (ኪዳነ ወልድ ክፍሌ) [፪] ኦ ዘያነብብ!! በእለ ምግባሮሙ ወበስብከቶሙ እም ቅዳሳት መጻሕፍት ወ ትምህርተ ቤተክርስቲያን አእምር ከመ ለሊሆሙ ውጉዛን ውእቶሙ! [፫] Tertullian,De praescriptione haereticorum (On the prescription of heretics), Chap. 43፡ You can judge the quality of their faith from the way they behave. Discipline is an index to doctrine. [፬] Erasmus, Paraphrase On Matthew, Chap. 7፡ “If you observe their lives and character more attentively, you will find them to be self-pleasing, everywhere serving their own advantage, arrogant, vindictive, envious, disparaging, thirsting for glory, often both devoted to their bellies and acting completely in their own interests, rather than in the interest of the flock or of the gospel.”

“ጣዕመ ዜማ የሌለው እንቢተኛ ልብ…!” Read More »

የጥንቱን ሃይማኖት!

የዚህን ታላቅ ፕሮቴስታንት ሐዳሲ ንግግር ያስተዋለ የትኛውም በፕሮቴስታንት ጥላ ውስጥ ያለ ሰው በቀጣይ ሚያስተውለው ወንጌላዊያን አብያተክርስቲያናት የገቡበትን ችግር ታሪካዊነቱ ቀርቶ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆነ የአምልኮ ስርአት ችግር ነው።[ይህ ችግር በተለያዩ ቦታዎች የሚደረጉ ቅጥ ያጣ ፈንጠዝያን ጨምሮ የሚያካትት ነው።] ይህን ችግር ግን በታሪካዊው ወይም በክላሲካል ፕሮቴስታንት መነጽር ስናየው የቀድሞው መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ባለው በቤተክርስቲያናዊ አስተምህሮ የበለጠገ አምልኮ እንዲሁም ለእነዚህ ቅጥ ላጡ አካላት እጅግ የታመነ የእምነት አቋም እንዳለው ቢታወቅም ልንክድ ማንችለው እውነት ግን ወንጌላዊያን አብያተክርስቲያናት ውስጥ ሚታየው ስረአት አልባ የአምልኮ ስርአት አግባብ ያልሆነ ብቻ ሳይሆን እጅግ ስህተት የሆነ ልምምድ መሆኑን ነው።(መታረምና መታየት ያለበት መሆኑን ይህ ጽሑፍ አጥብቆ ይናገራል) እንዲያው የዚህን ጉዳይ ጉድለት ትኩረት ሰጥተን ብንመለከተው ችግር ሆኖ ምናገኘው የእውነት ጉድለት ሳይሆን፥ ለድህረ ዘመናዊነት እጅግ የተጋለጥን መሆናችን፣ ቃሉን ሳይረዱት “ሃይማኖት አያድንም” የሚሉና የአስተምህሮን አስፈላጊነት የጣሉ ሰባኪያንና መምህራንን በተሃድሶው ክርስቲያን ማህበረሰብ ዘንድ ምስባክ ላይ ማቅረባችን፤ ይህንንም ተከትሎ አጥንትን ከመጋጥ ይልቅ ወተት መጋትን የሚወድ፣ በእምነቱ በቆየበት ልክ እውቀትንና ብስለትን ያጣ ምእመን ማፍራታችን ለዚህም የልጆች ፈንጠዝያ ሥርአተ አምልኮ መፍያና ማሟያ እንዲሆኑ ጆሮአችንን ለማከክ የፈቀዱን ሰዎች መሪዎችና እረኞች እንዲሁም መጋቢያን ዝም ማለታቸው ነው።(አጥብቀው የሚቃወሙና አጥብቀው የሚገስጹ እንዳሉ መዘንጋት የለብንም) መፍትሔ፦ መፍትሔው ሐዳሲያኑ የቆሙበትንና እኛም የተነሳንበትን እውነት አለመጣል ነው። ምክንያቱም ጌታን ለምን እንደተከተልነው እናውቅ ዘንድ ይገባናልና። ስለዚህ እውነትን በሙላት ልንካፈል እንጂ እምነትን አስታከን ለወደቀው አዳማዊ ማንነታችን ነፃነትን በመስጠት አለማዊነትን ልንለማመድ አይደለም። መሰረታችና አስተምህሮአችን የሆነው“የእግዚአብሔር ቃል ብቻ” “የእምነት መግለጫችንም” ብቻ ሳይሆኑ ምስባኮቻችንን፣ ልምምዶቻችንንና አምልኮአችንን የቆምንበት እውነት ሊገልጹ ይገባል። የዚህ ችግር ጉዳት “ውሃ ሲወስድ እያሳሳቀ ነው” እንዲሉ አበው እንደ ምእራባዊያን ሳይታወቀን ቀስ እያልን ለዘብተኞች እንዳንሆን። ወንድምና እህት ክርስቲያኖች ሁላችን ለምን እንደተጠራን ካወቅን እንግዲህ እንንቃ። ከራሳችን፣ ከቤተክርስቲያን ጣዕመ ዜማ ካለው አምልኮ፣ ከቅዱሳን ስብስብ(ማህበር) አስበልጠን የተሸከምነውን አለማዊነትንና ለአለማዊነት ያዘመመን ለዘብተኛ ክርስትናን ፈፅመን እናስወግድ፥ ማን እንደሆንን እናውቃለንና። ➠ የተሐድሶአችን ጥሪ ወደቀደመው እምነት እንመለስ እንደሆነ ሁሉ፥[2] ➠ እንደ ቀድሞው የአምልኮአችንን ማእከል፥ ቅዱሳት ምስጢራትንና የእግዚአብሔርን ቃል መሠረታችን እናድርግ። ➠ ሥላሴያዊ የሆኑ መዝሙሮችና ስብከቶች ስርአትና ልምምድ ይሁኑልን፥ ➠ እንደ እምነታችን እንዘምር፣ እንስበክ፣ እናስተምር። ይህ ሁሉ ሲሆን በመንፈስ ቅዱስ ሃይል፥ በልጁም በክርስቶስ ኢየሱስ በኩል ለእግዚአብሔር አብ ክብር ይሆን ዘንድ። ቅዱስ ባስሊዮስ ዘቄሳርያ በእንተ መንፈስ ቅዱስ መጽሐፉ ላይ፦ “…ቤተ ክርስቲያን የጠበቀችው ሐይማኖት በሐዋርያት የተላለፈውን ነው፣ የተቀበልነው እንዳናጠፋ ከአባቶች እምነት ጋር ጸንተን እንኑር !..” በማለት የተሐድሶ አበው እንዳስቀመጡት ባስልዮስ ያስቅምጠዋል። ታዲያ ቤተክርስቲያን ከዚህች ወጥመድ ታመልጥ ዘንድ የተሐድሶውን ወቅት በማየት መነጽራችንን ወደ ቀደመው አምልኮዎቻን እንመለስ ስንል ይህን ጽሑፍ እንቋጫለን። በአሚነ ሥላሴ ያጽናን። አሜን! ማጣቀሻ [1] The first book of discipline, Volume 3 page 34 [2] ተሐድሶ ማለት አዲስ ክርስትና መመሥረትና መቀጠል አይደለም። ይልቅ ወደ ቀደመው ውብ ክርስትና ቃሉ ብቻ የበላይ ወደ ሆነባት ክርስትና እንመለስ እንጂ።

የጥንቱን ሃይማኖት! Read More »

Scroll to Top