Blog & Articles

የጥንቱን ሃይማኖት!

የዚህን ታላቅ ፕሮቴስታንት ሐዳሲ ንግግር ያስተዋለ የትኛውም በፕሮቴስታንት ጥላ ውስጥ ያለ ሰው በቀጣይ ሚያስተውለው ወንጌላዊያን አብያተክርስቲያናት የገቡበትን ችግር ታሪካዊነቱ ቀርቶ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆነ የአምልኮ ስርአት ችግር ነው።[ይህ ችግር በተለያዩ ቦታዎች የሚደረጉ ቅጥ ያጣ ፈንጠዝያን ጨምሮ የሚያካትት ነው።] ይህን ችግር ግን በታሪካዊው ወይም በክላሲካል ፕሮቴስታንት መነጽር ስናየው የቀድሞው መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ባለው በቤተክርስቲያናዊ አስተምህሮ የበለጠገ አምልኮ እንዲሁም ለእነዚህ ቅጥ ላጡ አካላት እጅግ የታመነ የእምነት አቋም እንዳለው ቢታወቅም ልንክድ ማንችለው እውነት ግን ወንጌላዊያን አብያተክርስቲያናት ውስጥ ሚታየው ስረአት አልባ የአምልኮ ስርአት አግባብ ያልሆነ ብቻ ሳይሆን እጅግ ስህተት የሆነ ልምምድ መሆኑን ነው።(መታረምና መታየት ያለበት መሆኑን ይህ ጽሑፍ አጥብቆ ይናገራል) እንዲያው የዚህን ጉዳይ ጉድለት ትኩረት ሰጥተን ብንመለከተው ችግር ሆኖ ምናገኘው የእውነት ጉድለት ሳይሆን፥ ለድህረ ዘመናዊነት እጅግ የተጋለጥን መሆናችን፣ ቃሉን ሳይረዱት “ሃይማኖት አያድንም” የሚሉና የአስተምህሮን አስፈላጊነት የጣሉ ሰባኪያንና መምህራንን በተሃድሶው ክርስቲያን ማህበረሰብ ዘንድ ምስባክ ላይ ማቅረባችን፤ ይህንንም ተከትሎ አጥንትን ከመጋጥ ይልቅ ወተት መጋትን የሚወድ፣ በእምነቱ በቆየበት ልክ እውቀትንና ብስለትን ያጣ ምእመን ማፍራታችን ለዚህም የልጆች ፈንጠዝያ ሥርአተ አምልኮ መፍያና ማሟያ እንዲሆኑ ጆሮአችንን ለማከክ የፈቀዱን ሰዎች መሪዎችና እረኞች እንዲሁም መጋቢያን ዝም ማለታቸው ነው።(አጥብቀው የሚቃወሙና አጥብቀው የሚገስጹ እንዳሉ መዘንጋት የለብንም) መፍትሔ፦ መፍትሔው ሐዳሲያኑ የቆሙበትንና እኛም የተነሳንበትን እውነት አለመጣል ነው። ምክንያቱም ጌታን ለምን እንደተከተልነው እናውቅ ዘንድ ይገባናልና። ስለዚህ እውነትን በሙላት ልንካፈል እንጂ እምነትን አስታከን ለወደቀው አዳማዊ ማንነታችን ነፃነትን በመስጠት አለማዊነትን ልንለማመድ አይደለም። መሰረታችና አስተምህሮአችን የሆነው“የእግዚአብሔር ቃል ብቻ” “የእምነት መግለጫችንም” ብቻ ሳይሆኑ ምስባኮቻችንን፣ ልምምዶቻችንንና አምልኮአችንን የቆምንበት እውነት ሊገልጹ ይገባል። የዚህ ችግር ጉዳት “ውሃ ሲወስድ እያሳሳቀ ነው” እንዲሉ አበው እንደ ምእራባዊያን ሳይታወቀን ቀስ እያልን ለዘብተኞች እንዳንሆን። ወንድምና እህት ክርስቲያኖች ሁላችን ለምን እንደተጠራን ካወቅን እንግዲህ እንንቃ። ከራሳችን፣ ከቤተክርስቲያን ጣዕመ ዜማ ካለው አምልኮ፣ ከቅዱሳን ስብስብ(ማህበር) አስበልጠን የተሸከምነውን አለማዊነትንና ለአለማዊነት ያዘመመን ለዘብተኛ ክርስትናን ፈፅመን እናስወግድ፥ ማን እንደሆንን እናውቃለንና። ➠ የተሐድሶአችን ጥሪ ወደቀደመው እምነት እንመለስ እንደሆነ ሁሉ፥[2] ➠ እንደ ቀድሞው የአምልኮአችንን ማእከል፥ ቅዱሳት ምስጢራትንና የእግዚአብሔርን ቃል መሠረታችን እናድርግ። ➠ ሥላሴያዊ የሆኑ መዝሙሮችና ስብከቶች ስርአትና ልምምድ ይሁኑልን፥ ➠ እንደ እምነታችን እንዘምር፣ እንስበክ፣ እናስተምር። ይህ ሁሉ ሲሆን በመንፈስ ቅዱስ ሃይል፥ በልጁም በክርስቶስ ኢየሱስ በኩል ለእግዚአብሔር አብ ክብር ይሆን ዘንድ። ቅዱስ ባስሊዮስ ዘቄሳርያ በእንተ መንፈስ ቅዱስ መጽሐፉ ላይ፦ “…ቤተ ክርስቲያን የጠበቀችው ሐይማኖት በሐዋርያት የተላለፈውን ነው፣ የተቀበልነው እንዳናጠፋ ከአባቶች እምነት ጋር ጸንተን እንኑር !..” በማለት የተሐድሶ አበው እንዳስቀመጡት ባስልዮስ ያስቅምጠዋል። ታዲያ ቤተክርስቲያን ከዚህች ወጥመድ ታመልጥ ዘንድ የተሐድሶውን ወቅት በማየት መነጽራችንን ወደ ቀደመው አምልኮዎቻን እንመለስ ስንል ይህን ጽሑፍ እንቋጫለን። በአሚነ ሥላሴ ያጽናን። አሜን! ማጣቀሻ [1] The first book of discipline, Volume 3 page 34 [2] ተሐድሶ ማለት አዲስ ክርስትና መመሥረትና መቀጠል አይደለም። ይልቅ ወደ ቀደመው ውብ ክርስትና ቃሉ ብቻ የበላይ ወደ ሆነባት ክርስትና እንመለስ እንጂ።

የጥንቱን ሃይማኖት! Read More »

መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ እና ሕጸጽ አልቦ

ቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለባቸው ናቸው፤ ለማስተማር፣ ለመገሠጽ፣ ለማቅናት በጽድቅም መንገድ ለመምከር ይጠቅማሉ።2ኛ ጢሞ 3፥16 (አዲሱ መ.ት) መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ለክርስትና እምነተ መርሕ መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ የማይሳሳትና ሊሳሳት የማይችል ባለሥልጣን እንዳለው የሚገልጽ ክርስቲያናዊ መርሕ ነው። ይሄንን ሐሳብ ብርሐነ አለም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለመንፈሳዊ ልጁ ለጢሞቴዎስ በጻፈለት መልዕክት ላይ ቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ እስትንፋሰ እግዚአብሔር (ቴዎኔዩስቶስ/θεόπνευστος) መሆናቸውን ሲነግረው እንመለከታለን። በዚህም መሠረት ቅዱሳት መጻሕፍት እስትንፋሰ እግዚአብሔር አፊዎተ እግዚእ ማለትም በቀጥታ መለኮታዊ ግልጠት መሆናቸውን እና ከዚህም የተነሳ እውነተኛ እና ሕጸጽ አልቦ ናቸው ብለን እናምናለን። የቤተ ክርስቲያን አበው ይህንኑ ሐሳብ ሲደግፉ ይስተዋላል። የአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን አባት ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ(John Chrysostom) ክፍሉን በድርሳኑ ላይ ሲያብራራ ቅዱሳት መጻሕፍት አፊዎተ እግዚእ መሆናቸውን እና ለአማኞች ትክክለኛ የቅድስና እና የህይወት መንገድ መሮች መሆናቸውን ይናገራል።[1] ቅዱስ ሔሬኔዎስ ዘሊዮን በመድፍነ መናፍቃን መጽሐፉ ላይ ቅዱሳን መጻሕፍት እስትንፋሰ እግዚአብሔር እና የበላይ ባለስልጣን መሆናቸውን በመግለፅ እውነተኛው የክርስትና አስተምህሮ መሠረት የሆኑ  እና ሐሰተኛውን አስተምህሮ የምንከላከልባቸውም (የምንመክትባቸው) ጭምር እንደሆኑ ይገልጻል (Against Heresies)።  ቅዱሳት መጻሕፍት የእግዚአብሔር እስትንፋስ በመሆናቸው ስለ እውነት ፤ ክርስትያናዊ የሕይወት መርህ እና ድነት አስፈላጊ የሆኑትን ሥነመለኮታዊ አስተምህሮ ሁሉ በውስጡ ያካተቱ በመሆናቸው ለዚህም አስተምህሮ ብቁ ባህሪዎት እንዳላቸው እንመለከታለን። ቅዱስ አትናቴዎስ (Athanasius of Alexandria) በክታቡ እንዲህ ሲል ይናገራል፦ The Holy Scriptures, given by inspiration of God, are of themselves sufficient toward the discovery of truth.[2] ነገር ግን የእግዚአብሔር ቃል ለክርስቲያን ሥነመለኮት ብቁ ነው ስንል በራሱ ትውፊትን የሚያገልል ወይም የሚቃወም ተደርጎ በፍጹም መታሰብ የለበትም። ይሄ አስተምህሮ ግን ማለትም የመፅሐፍ ቅዱስን በቂነት(Material Sufficiency) ልጅ የጥንት ማህበረሰብ ስምምነት(ኮንሴንሰስ ፓትረም) ያለው እምነት መሆኑ ፕሮቴስታንት በዚህ ላይ ጽኑ መሠረት እንዳለው እናውቃለን። ይሄ አስተምህሮ ግን ለትውፊት, ለአምልኮ ሥርዓት ሆኑ ለጉባኤያት አስተምህሮ እና እውነተኝነት ትክክለኛው መመዘኛ መጽሐፍ ቅዱስ መሆኑን የሚናገርም ነው። በተጨማሪም ሁሉም ከፍተኛ ባለሥልጣን ለሚለው ለመጽሐፍ ቅዱስ መገዛት እና ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ህብረት መፍጠር እንዳለባቸው የሚያመላክትም ጭምር ነው። ምክንያቱም ትውፊት, የአምልኮተ ሥርዓት ሆኑ, ጉባኤዎች የማይሳሳቱ ስላልሆኑ ማለትም ሊሳሳቱ የሚችሉ በመሆናቸው ምክንያት መመዘን ያለባቸው አይሳሳቴና የእግዚአብሔር እስትንፋስ በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ነው። ይህንን ሐሳብ ቅዱስ አውግስጢኖስ ዘሒፖ(Augustine of Hipo) በመደገፍ መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ዝንፈተ እውነት የሌለበት እንደሆነ ይናገራል፦ I have learned to yield this respect & honor only to the scripture, of these alone do I most firmly believe that completely inerrant (free from error) [3] ትውፊትም, የአምልኮ ሥርዓቶች ሆኑ ጉባኤያት ስህተት ሊገኝባቸው ይችላል። ምክንያቱም የትውፊት አስተላለፋቸውን በተመለከትን ጊዜ በሰዋዊ አተረጓጎም, በተፈጥሮዋቸው የሚሳሳቱ ስለሆኑ እና በባህል ተጽዕኖ የታሰረ በመሆኑ ትክክለኛው መልዕክቱ ተበላሽቶ(ተቀይሮ) ሊሆን ይችላል። በተለይም ትውፊት እና የሃይማኖት ሥርዓታዊ ድርጊቶች በዘመናት መሐል የተለያየ ብርዘት እና ለውጥ ሊገባባቸው የሚችሉ ናቸው። ለምሳሌ ያክል በካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የጳጳሳቱ መብት እያደገ እየተሻሻለ በመምጣት ወደ የፖፑ አለመሳሳት(papal Infallibility) በመጨረሻም ወደ ስህተት መምጣታቸው የሚዘነጋ አይደለም። በተጨማሪም በነገረ ማሪያም ያላቸውን ዶክትሪን እጅጉን እየለጠጡ በመምጣታቸው ወደ Immaculate conception(አንዳንድ ኦርቶዶሳውያንም ይህንኑ አስተምሮ ይቀበላሉ) እንዳመሩ እንመለከታለን። የፑርጋቶሪ ምልከታ ሌላው የሚጠቀሱ ጉዳዮች ናቸው። በኦርቶዶክሱም ሆነ በካቶሊኩም የሚስተዋለው የመጽሐፍ ቅዱስ የቀኖና ችግር ስንመለከት ትውፊት በዘመናት መካከል ሊቀያየር እና ሊበከል የሚችል ጉዳይ ሁኖ እናገኘዋለን። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በማቴዎስ ወንጌል 15:3 ላይ በመለኮታዊ ግልጠት ላይ ያልተመሠረተውን ያልሆነውን የአይሁዳውያንን ትውፊት ሲመረመር እንመለከታለን። የመጽሐፍ ቅዱስ ብቻ እነዚህ ሁሉ ትውፊት እና ስርዓተ አምልኮ በሕጸጽ አልቦው እና በአይለወጤው በእስትንፋሰ እግዚአብሔር ቃል መሠረት ተመዝነው መጥራት ያለባቸው ጉዳዮች መሆናቸውን የሚገልጽ ክርስቲያናዊ መርህ ነው። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ትክክለኛው ሚዛን እና የሁሉ የበላይ ሊሳሳት የማይችል ባለስልጣን የሆነ ያለው ነው። ማጣቀሻ 1] Homilies on 2 Timothy 2] Against the Heathen, 1:3 3] Letters, 82:3

መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ እና ሕጸጽ አልቦ Read More »

Scroll to Top