October 2025

የማርቆስ እና እስረኛው ታሪክ

በሰሞኑን በተነሳው በቻርሊ ከርክ ሕልፈት ምክንያት ሁለት ጽንፍ ጎራዎችን እንመለከታለን። አንዱ ጎራ በዚህ ሀሳቡ አልስማማውም ሲል ይኼኛው አይደለም እንዲያማ አይባልም በዚህ ሀሳቡ እጋራዋለሁ በማለት ሲወያዩ ስመለከት ነበር። በእርግጥ ቻርሊን በአንዳንድ ሀሳቦቹ ባልስማማም ነገር ግን በወጣቱ ዘንድ ያለውን ተጽዕኖ እና ወደ ኋላ ገሸሽ በማይለው አቋሙ ሁሌ የማደንቀው ሰው ነው። በሳልና አዕምሮውን የሚጠቀም፣ በልቡን የማያምንበት ከሆነ የማያደርግ ነበር። በኋላ በተለያዩ ገጾች የሚጻፉትንና ደጋግመው የሚመጡትን የተለያዩ ጽሑፎችና የምስል ቪዲዮዎችን ለመመልከት ሞክሬ ነበር። በእርሱም ህልፈት ምክንያት ብዙዎች ከኢ-አማንያን ወደ ክርስትና እንደመጡና ቤተክርስቲያንን ሥፍራ አጣን እስከማለት ደርሰው እንደተገኙ እንመለከታለን። ይኼንን ታሪክ ስመለከት በሞቱ ብዙዎችን መጥራቱን ሳስብ የማርቆስና የእስረኛው ታሪክ ጋር ከዚህ ቀደም ፊልጵስዩስን በማጠናበት ጊዜ ከጻፍኩት ጽሑፍ ጋር የቻርሊ ከርክ ታሪክ ተመሳሰለብኝ። የማርቆስ እና የእስረኛው ታሪክ በፊልጵስዩስ 1፥21 ላይ የተመሠረተ አፈ-ታሪክ ነው። ከታሪኩ በፊት ቃሉ እንዲህ ይነበባል፦ “ለእኔ ሕይወት ክርስቶስ፥ ሞትም ጥቅም ነውና።”  — ፊልጵስዩስ 1፥21 ማርቆስ በፊልጵስዩስ የሚኖር ወጣት ለእምነቱ ታጋይ ሰው ነበር። ማርቆስ በክርስትና ምክንያት ዘወትር በሮማውያን እና በቅርብ ወዳጆቹ መገለል ከዛም ታልፎ መከራ በገጠመው ቁጥር ኹል ጊዜ ወደ እስር ቤት ይሄዳል። በዛም እስር ቤት በእምነቱ ጽኑ የሚባለውን ጳውሎስን እንዲጎበኝ ይሄድ ነበር። የእስር ቤቱ ጨለማ ክፍል ሁልጊዜ ለማርቆስ አስጨናቂው መንገዱ ነበር፣ ነገር ግን ጳውሎስ በዚያ ውስጥ ሁልጊዜ ደስታ የተሞላበት ዓይን ነበረው። አንድ ምሽት ላይ እንደተለመደው ለጉብኝት በሚሄድበት ጊዜ ማርቆስ ስለ ጳውሎስ ከሚደርስበት መከራ መደሰት ምክንያቱ ምን እንደሆነ እንዲህ ሲል ጠየቀው፦ «ጳውሎስ፣ ነገ ሊገደሉህ ሲሆን እንዴት እንደዚህ ፊትህ ላይ ደስታ ይታያል? ሞትን አትፍራም?» ይለዋል ጳውሎስም ከትከሻው ላይ እጁን አሳረፈ እና እንዲህ አለ፦ «ማርቆስ፣ ከክርስቶስ ውጪ በዚህ ዓለም ሳለህ ጥሩ ሆነ መጥፎ የሚባል ነገር የለም። ለእኔ ሕይወት ክርስቶስ፥ ሞትም ጥቅም ነውና። ባለሁበት ዘመን ሁሉ ክርስቶስን እናገራለሁ፤ በዚህም የክርስቶስ አካል ፍጹማን ይሆኑ ዘንድ በመከራዬ ሁሉ አጽናናለሁ። በዚህስ ብሞት ግን፣ ከእርሱ ጋር እኖራለሁ። እኔ እንዴት እጎዳለሁ?» በማለት መለሰለት። ማርቆስ ተደነቀ። «እንግዲህ… በኑሮህም በሞትም ክርስቶስ ድሌ ነው የምትለኝ?» አለ። ጳውሎስም፦ «አዎን። ይህች ዓለምን እንዳልመስል በደማስቆ መንገድ ላይ ሕይወትና አገልግሎትን ሰጥቶኛል። በዛም በተቀበልኩት ሕይወት ሞት ወደ እኔ ቢመጣ አልሰጋም ምክንያቱም የምቀምሰው ጽዋ ክርስቶስን ራሱን ይሰጠኛል። ስለዚህ አንዳችም አልሰጋም።» በማለት መለሰለት። እነዚህ ቃላት በእሥረኛ ጠያቂው በማርቆስ ልብ ውስጥ በጽኑ ጠነከሩ። ከብዙ ዓመታት በኋላ፣ በፊልጵስዩስ ላይ ስደትና መከራ በክርስቲያኖች ላይ መጣ። በዛም መከራ ውስጥ ማርቆስ የጳውሎስን ቃል በልቡ አሰበ። በዚያም ሸንጎ ተይዞ ስለ እምነቱ ሞት ቅጣትን በማርቆስ ላይ ሊያደርሱበት በተሰለፉ ጊዜ፣ ቆመና እንዲህ ብሎ ቃሉን ተናገረ፦ «በህይወት መኖሬ በክርስቶስ ውስጥ አገልግሎት እና ፍሬያማ ሥራዬ ነው። ሞት ቢመጣ ደግሞ ከክርስቶስ ጋር መኖርን የሚሰጠኝ ሕያው ድልድይ ነው። ለእኔም ይህ ደግሞ የተሻለ ነው አላቸው።…» አጠገቡ የነበሩት፣ ሊገድሉት ከሚፈልጉት መካከልም አንዳንዶች የማርቆስን እምነት ምንኛ ነው? በማለት እርስ በእርሳቸው አንጎራጎሩ። ዳግመኛም ማርቆስ የመጨረሻ የክህደት ቃልህን አስፍርና ተናገር ባሉት ጊዜ « ለእኔ ሕይወት ክርስቶስ፥ ሞትም ጥቅም ነውና…» በማለት አጠናቀቀ ንግግሩን። የማርቆስም ሞት በፊልጵስዩስ ቤተክርስቲያንም በዙሪያዋ ባሉት ሁሉ ላይ ብዙዎች ጋር ደረሰ። ብዙዎች በጽናት ተመሰረቱ፣ በዛችም ከተማ ወንጌሉ ብዙዎችን እየለወጠ ሄደ። ይሄን እምነት መርሕ አድርገው የቤተክርስቲያን አባቶች ብዙዎች እንደ ሻማ ቀልጠውበታል። ለዚህም ነው ጠርጡልያንም ሲናገር The blood of the Martyrs is the seed of the Church(የሰማዕታት ደም የቤተክርስቲያን ዘር ነው) ያለው። በአጭሩ የቻርሊ ከርክ ፖለቲካ አቋም ምንድነው? የሚል ትርጉም ሳይሆን ጽሑፉ ትኩረት የሚሰጠው በእርሱ ህልፈት ምክንያት የመጣውን ሰዎች ባሰብን ቁጥር እግዚአብሔር በቃሉ ሞትም ጥቅማችን እንደሆነ የሚነግረን። በዚህ ዘመንስ እንደ እንቁ የምናያቸውን ምሑራንን ለማጥፋት ብዙዎች የሚያቅዱት። በዚህ ሁሉ ግን እግዚአብሔር ጽኑ እምነት ሰጥቷቸው የክርስቶስን ወንጌል ለማገልገል የተሰጡ ስንቶች ይሆኑ? እንጃ፤ ለእኛ ግን እግዚአብሔር በዚህ ጽኑ እምነት ይባርከንም።

የማርቆስ እና እስረኛው ታሪክ Read More »

የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክነት

ክፍል 1 “እርሱ በባሕርዩ አምላክ ሆኖ ሳለ፣ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን ሊለቀው እንደማይገባ አድርጎ አልቈጠረውም፤”  — ፊልጵስዩስ 2፥6 (አዲሱ መ.ት) አንድ አካል አምላክ ነው የሚባለው ወይም እንደ አምላክ ሊመለክ የሚገባው አምላክ ነኝ ብሎ ስለተናገረ ብቻ ወይም ብዙዎች አምላክነቱን ስላወጁለት አይደለም። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አምላክ ነኝ ብለው የተነሱ ነገሥታትን እንመለከታለን። ለምሳሌ፦ የጢሮስ ንጉስ እኔ አምላክ ነኝ ማለቱን(ሕዝቅኤል 28፥2-9) ስንመለከት ይህ ንጉሥ እኔ አምላክ ነኝ ስላወጀ ብቻ አምላክ ነው ብሎ መፈረጅ ፈጽሞ አይቻልም። በሰውም አጀብ አንድ አካል አምላክ ስለተባለም አምላክ ሊሆን አይችልም። ምክንያቱም የግሪክ ጣዖታት እንዲሁ ተብለው ምንነታዊ ለውጥ ስላላሳዩን። ክርስቶስ ኢየሱስ አምላክ ለመሆኑ የአምላክነት ግብሩን፤ ባህሪዎቱንና ሐልዎቱን በተለያየ መንገድ መጽሐፍ ቅዱስ ሲናገር፤ ኑባሬውን ሲተርክና ሲገልጽልን እንመለከተዋለን። ከእነዚህም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ውስጥ አንደኛው የፊልጵስዩስ መልእክት ም2 ቁ6-7 ነው፦ ⁶ እርሱ በባሕርዩ አምላክ ሆኖ ሳለ፣ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን ሊለቀው እንደማይገባ አድርጎ አልቈጠረውም፤ ⁷ ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ፣ በሰውም አምሳል ተገኝቶ፣ ራሱን ባዶ አደረገ” ፊልጵስዩስ 2 (አዲሱ መ.ት) ὃς ἐν μορφῇ θεοῦ ὑπάρχων οὐχ ἁρπαγμὸν ἡγήσατο τὸ εἶναι ἴσα θεῷ, Προς Φιλιππησιους 2:6 በጽርዑ ሞርፌ/μορφῇ የሚለው ቃል ኑባሬያዊ መገኘትን፣ ሁናቴን ወይም ባህሪዎተ መልክን የሚገልጽ ቃል ሲሆን ክርስቶስ ኢየሱስ (ወልድ) እም ቅድመ አለም በኑባሬው በባህሪዎተ መልኩ ራሱ አምላክ ሆኖ የሚኖር አካል እንደሆነ ይገልጻል። በተጨማሪም በባለቤትነት ሙያ (Nominative case) የመጣው ሁፓርኾን/ὑπάρχων የሚለው ቃል በአሁን ጊዜ አመልካች ግስ(Present participle tense) መምጣቱ ወልድ ከዘላለም ጀምሮ ከአብ ጋር አብሮ ህያው አብሮ እኩል አብሮ ዘላለማዊ እንደሆነ በሚገልጽ መልኩ እንደመጣ የክፍሉን ሰዋሰው ይነግረናል። ይህም ደግሞ ለወልድ ኑባሬ ጅማሮ አለው ፍጡር እንጂ ፈጣሪ አይደለም ለሚሉት አርዮሳውያን እና ኢብዮናውያን (Ebionite/Ἐβιωναῖοι) በተለምዶው አዶፕሽኒስቶች የሚባሉት የምን*ፍቅና የአስተምህሮቶችን መሰረታቸውን የሚንድ ክፍል ነው። ሙግታችንን ጠበቅ ለማድረግ ያክል ከተመለከትን ደግሞ ወልድ አምላካዊ ባህሪ ከጥንተ ዘላለም ጀምሮ በዚሁ መልክ ሲኖር የነበረው አምላክ ወደ ፈጠራት ጠባበ አለም የሰውን ወይም የባሪያን ባህሪ(መልክ) ይዞ መምጣቱ “ከእግዚአብሔር አብ ጋር መተካከልን ሊለቀው እንደማይገባ አድርጎ አልቈጠረውም” በማለት ብርሃነ አለም ቅዱስ ጳውሎስ ፍንትው አድርጎ የወልድን መለኮታዊ ባህሪዎት ከእግዚአብሔር አብ ጋር እኩል እንደሆነ ያሳየናል። ከአምላክ ጋር እኩል መሆን ወይም በጽርዑ ቶ ኢናይ ኢሳ ቴኦ/τὸ εἶναι ἴσα θεῷ የሚለው ሐረግ እግዚአብሔር ወልድ ከእግዚአብሔር አብ ጋር በባህሪው እኩል ወይም አንድ አይነት ሆሙስዮስ/ὁμοούσιος እንደሆነ በግልጽ ሁኔታ ሲነግረን የአርዮሳውያንን መርሆተ ቃል የሆነውን ተመሳሳይ ወይም ተቀራራቢ ባህሪዎት ሆሞዮስዮስ/ὁμοιούσιος የሚለውን ምንፍቅና አፈር ከመሬት የሚደባልቅ ክፍል እንደሆነ እንመለከታለን። በቁጥር ሰባትን አንድ በአንድ ስንመለከተው “የባሪያን መልክ ይዞ” የሚለው ሐረግ በፊት የተገለጠበት ቅድመ ኑባሬያዊ ባህሪዎት እንደነበረው ቁልጭ አድርጎ ያሳየናል፤ እርሱም በቁጥር 6 ላይ እንዳየነው የወልድ አምላካዊ መልክ (ባህሪ) ከጥንተ ዘላለም ጀምሮ ገንዘቡ የሆነ ምንነት ነው። “በሰውም ምሳሌ ሆኖ” የሚለው አገላለጽ ደሞ ወደ ምድር በመጣ ጊዜ ፈጣሪ በፍጡራን ምሳሌ ሆኖ ሰዋዊ ባህሪዎትን እንደተላበሰ ያሳየናል። ቀጥሎም “ራሱን ባዶ አደረገ” የሚለው ደሞ አንድ ነገር ባዶ ሆነ የሚባለው ያ ነገር መጀመሪያውኑ የሆነ ነገር ሲኖረው ነው። ክርስቶስ ኢየሱስ ደግሞ ራሱን ባዶ አደረገ ሲባል አምላካዊ ሙሉነት የነበረው አካል ወደ ፈጠረው፣ ወዳዘጋጀው፣ ሰዋዊ ባህሪዎት ዝቅ ብሎ በመምጣቱ ነው። ስለዚህ ክርስቶስ ኢየሱስ ሰው ሁኖ ከመምጣቱ በፊት በአምላካዊ ሙሉነት የሚኖር አምጻኤ ኩሉ አምላክ እንደሆነ እንመለከታለን። በመጨረሻም የክርስቶስን አምላክነት የማያምኑ እንዲህ ሲሉ፦”…ክርስቶስ ኢየሱስ (ወልድ) በእግዚአብሔር ወይም በአምላክ መልክ መኖሩ አዳም በእግዚአብሔር መአልክና ምሳሌ በተፈጠረበት ሒሳብና ቀመር ነው…” ይሞግታሉ። ነገር ግን የሁለቱን ክፍሎች የጽርዑን የቃላት አገባብ እና አውዳዊ ምልከታ ባደረግን ጊዜ ፈጽመው የየቅል ሐሳብ እንደሆነ እንረዳለን፦ እግዚአብሔርም አለ፦ ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር/καὶ εἶπεν ὁ θεός Ποιήσωμεν ἄνθρωπον κατ᾽ εἰκόνα ἡμετέραν καὶ καθ᾽ ὁμοίωσιν…>>  — ዘፍጥረት 1፥26 በዘፍጥረት 1፥26 መልክ ብሎ የገባው የግሪኩ ቃል ኤይኮና/εἰκόνα ሲሆን ምሳሌ የሚለው ደሞ ሆሞዮሲን/ὁμοίωσιν በሚለው የቃላት አገባብ እንደተሰደረ እንመለከታለን። ኤይኮና/εἰκόνα የሚለው ቃል ኤይኮን/εἰκών ማለትም ምስለ መልክን መመሳሰል ወይም መቀራረብ(በውጫዊ ማንነት መገለጫ) የሚል ትርጉም አለው። እግዚአብሔር አምላክ ሰውን በእኛ መልክ(ኤይኮና ሄሜቴራን/εἰκόνα ἡμετέραν) እንፍጠር ሲል በጽድቅና ቅድስና(ኤር 4:24)፤ እንዲሁም በመገንዘብ ችሎታንና እውቀትን(ቆላ 3:10) የመሳሰሉትን የምስስሎሽ መገለጫዎች በሚገልጽ አገባብና አግባብ መምጣቱ ቅብል ነው። ነገር ግን የሰው ልጅ በእግዚአብሔር መልክና አምሳል መፈጠሩ በእርግጥ የሚካፈለው ባህሪ እንዳለው ሁሉ የማይካፈለው ባህሪ አለ። በዛው በፊልጵስዩስ መልእክት 1:7 እና 2ኛ ጴጥሮስ 1፥4 ላይ የእግዚአብሔር የባህሪው ተካፋዮች እንደሆንን ይናገራል፦ “ስለ ክፉ ምኞት በዓለም ካለው ጥፋት አምልጣችሁ ከመለኮት ባሕርይ ተካፋዮች(κοινωνοὶ φύσεως) በተስፋ ቃል እንድትሆኑ፥ በእነዚያ ክብርና በጎነት የተከበረና እጅግ ታላቅ የሆነ ተስፋን ሰጠን።”2ኛ ጴጥሮስ 1፥4 ተካፋይ ወይም በግሪኩ ኮይኖኖስ/κοινωνός የሚለው ቃል የሰው ልጅ ከእግዚአብሔር ፈጽሞ የማይካፈለው ወይም የቀረበት ነገር እንዳለ አመላካች ነው። ይህንን ሐሳብ በሌላ ክፍል በስፋት እንመለከተዋለን። ነገር ግን ክርስቶስ ኢየሱስ ከእግዚአብሔር አብ ጋር የማይጋራው ሆነ የማይካፈለው ባህሪ የለም። ከላይ በፊልጵስዩስ መልእክት 2:6 ከአብ ጋር በመለኮተ ባህሪዎት እኩል ወይም አንድ እንደሆነ ተመልክተናል። ስለዚህ አምላክ ክርስቶስ ኢየሱስ በአምሳለ ሰውነት መገለጡ (እንደ ሰው መብላት መጠጣቱ፤ መተኛት መነሳቱ፤ መወለድ ማደጉ ወዘተ) መለኮታዊ ክብር እንደሌለው የሚያሳየን ተግባር አይደለም። እርሱ ወደዚች ወደ ፈጠራት አለምና ሰውነት ከመገለጡ በፊት አምላካዊ ምንነት፤ ክብርና መለኮታዊ ኑባሬ ከጥንተ ዘላለም ጀምሮ ገንዘቡ ያደረገ ኃያል አምላክ ነው።

የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክነት Read More »

Scroll to Top