ጽሑፍ፦ Samuel Green
ትርጉም፦ David Yeshua
ይህ መጣጥፍ፣ በሊቁ አርጌንስ ድርሳን ውስጥ ስለ አዲስ ኪዳን የሰፈረውን ንግግር መሠረት በማድረግ የሚያብራራ እና በሙስሊሞች መካከል ለሚደረገው ውይይት እንዴት በጥቅም ላይ መዋል እንዳለበት የሚተነትን ነው።
ከሙስሊም ወገኖች ጋር በሚደረጉ ውይይቶች መካከል የአዲስ ኪዳን ቅጂ ተዓማኒነት በተደጋጋሚ የሚነሳ ጉዳይ ሲሆን፣ አንዳንድ ሙስሊሞች የአዲስ ኪዳን ጽሑፍ ተዓማኒ አለመሆኑን ለማስረዳት የአርጌንስን ጽሑፍ በማስረጃነት ያቀርባሉ። በዚህም ጽሑፍ የእስክንድሪያው አርጌንስን(ከ184 – 253 ዓ.ም) የኖረ የቤተክርስቲያን ሊቅ ሲሆን እውን ስለ አዲስ ኪዳን ጥንታዊያን ቅጂች የተዛባ ምልከታን ያምናልን? የሚለውን በመተንተን የማስቀምጥ ይሆናል። የሊቁ ጽሑፍ እንዲህ ይነበባል፦
“The differences among the manuscripts [of the Gospels] have become great, either through the negligence of the copyists or through the perverse audacity of others; they either neglect to check over what they have transcribed, or, in the process of checking, they lengthen or shorten, as they please.”1
“በእደ ክታባት ገልባጮች ቸልተኝነት አልያም በሌሎች እኩይ አላማ የተነሳ በወንጌላት እደ ክታባት ቅጂዎች መካከል ያለውን ልዩነት እጅግ የጎላ መሆን ችሏል። የገለበጡትን ጊዜ ሰጥተው ለመርመር ቸል ይላሉ አልያም ደግሞ በሚመረምሩበት ወቅት እንደ ልባቸው ፈቃድ ያስረዝሙታል ወይም ያሳጥሩታል።”
ከዚህ ከአርጌንስ ጽሑፍ በመነሳት ሙስሊም ወገኖች የአዲስ ኪዳን እደክታብ በሦስተኛው ክፍለ ዘመን ላይ ከባድ ችግሮች እንደነበሩበት እና በዚህም ምክንያት ዛሬ ላይ በእጃችን የሚገኙ ምንባባት ተዓማኒ እንዳልሆነ ይደመድማሉ፤ ጨመርም አድርገው ቁርዓን እንዲህ ዓይነት የጽሑፍ ግድፈቶች እንደሌሉበት ይደመድማሉ። አንድ ክርስቲያን ይህን የአርጌንስን አባባል እንዴት ሊረዳው ይገባል? ለዚህስ ሙግትና መልስ ለሚሻ ጥያቄ ምን ብሎ መመለስ አለበት? የሚለውን እኔ በሦስት የመልስ ነጥቦችን አስቀምጣለሁ።
ነጥብ አንድ፦ ሊቁ አርጌንስ የአዲስ ኪዳንን ጽሑፍ ተዓማኒነትን በፍጹም አይክድም። ይልቅ በድርሳናቶቹ ሁሉ የአዲስ ኪዳን ምንባባትን በማጣመር የሚቀጥል ሲሆን፣ እንደ እስትንፋሰ እግዚአብሔር ቃሉን ይተማመንባቸዋል። ይህ ማለት፣ አርጌንስ አንዳንድ ሙስሊሞች ወደ ደረሱበት ዓይነት ድምዳሜ መሠረት በፍጹም አልደረሰም ማለት ነው።
ነጥብ ሁለት፦ ችግሩ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ለማወቅ አርጌንስ ስለጠቀሳቸው የምንባባት ልዩነቶች (textual variants) አንዳንድ ምሳሌዎችን ማየት ያስፈልገናል። እነዚህ ምሳሌዎች ከሌሉ፣ በቀላሉ የተጋነነ ወይም ተገቢ ያልሆነ የተሳሳተ ግንዛቤ በሊቁ ላይ ሊፈጠርብን ይችላል። እንደ መልካም አጋጣሚ ሆኖ፣ እነዚህ ምሳሌዎች በቀላሉ ይገኛሉ፤ ምክንያቱም አርጌንስ ራሱ በድርሳኑ ውስጥ ጠቅሷቸዋል። ብሩስ ሜትዝገር (Bruce Metzger) የአርጌንስ ጽሑፎች በጥልቀት በመመርመር እነዚህን የጽሑፍ ልዩነቶች ሰብስቧቸዋል። የምርምሩም ውጤት ‘Explicit References in the Works of Origen to Variant Readings in New Testament Manuscripts’2 በተሰኘው ጽሑፍ ላይ ታትሟል። በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ሜትዝገር አርጌንስ የጠቀሳቸውን 22 የጽሑፍ ልዩነቶች አቅርቦ ይወያይባቸዋል። ስለሆነም፣ አርጌንስ በትክክል ስለ ምን እየጻፈ እንደነበረ ማወቅ እንችላለን። አርጌንስ የጠቀሳቸው የ22ቱ ልዩነቶች ማጠቃለያ የሚከተለው ነው፦
- ማቴዎስ 4፥17፦ አብዛኞቹ የአዲስ ኪዳን ምንባባት “መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ” ይላሉ። ጥቂቶቹ ደግሞ “መንግሥተ ሰማያት ቀርባለች” የሚል ብቻ አላቸው።
- ማቴዎስ 8፥28-32 (ማርቆስ 5፥1-17፣ ሉቃስ 8፥26)፦ አንዳንዶቹ የእጅ ጽሑፎች “ወደ ጌርጋሴኖን አገር” ይላሉ። ሌሎች ደግሞ “ወደ ጌዴሬኖን አገር” ይላሉ።
- ማቴዎስ 16፥20፦ አንዳንዶቹ የእጅ ጽሑፎች “ያን ጊዜም ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ አስጠነቀቃቸው” ይላሉ። ሌሎች ደግሞ “ያን ጊዜም ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ አዘዛቸው” ይላሉ።
- ማቴዎስ 18፥1፦ አንዳንዶቹ የእጅ ጽሑፎች “በዚያች ሰዓት ደቀ መዛሙርት ወደ ኢየሱስ ቀረቡ” ይላሉ። ሌሎች ደግሞ “በዚያ ቀን ደቀ መዛሙርት ወደ ኢየሱስ ቀረቡ” ይላሉ።
- ማቴዎስ 21፥5፦ አብዛኞቹ የእጅ ጽሑፎች “በአህያና በጭነት እንስሳ ግልገል በውርጫይቱ ላይ” ይላሉ። አንዳንዶቹ ደግሞ “በአህያና በጭነት እንስሳ ውርጫ ላይ” ይላሉ።
- ማቴዎስ 24፥19፦ አንዳንዶቹ የእጅ ጽሑፎች “ለርጉዞችና ለሚያጠቡ” ይላሉ። ሌሎች ደግሞ “ለርጉዞችና ወደፊት ለሚያጠቡ” ይላሉ።
- ማቴዎስ 27፥16-17፦ አብዛኞቹ የእጅ ጽሑፎች “በርባን” ይላሉ። ጥቂቶቹ ደግሞ “ኢየሱስ በርባን” ይላሉ።
- ማርቆስ 2፥14፦ አብዛኞቹ የእጅ ጽሑፎች “የእልፍዮስን ልጅ ሌዊን በመቅረጫ ቦታ ተቀምጦ አየው” ይላሉ። አንዳንዶቹ ደግሞ “የእልፍዮስን ልጅ ያዕቆብን በመቅረጫ ቦታ ተቀምጦ አየው” ይላሉ።
- ሉቃስ 1፥46፦ አብዛኞቹ የእጅ ጽሑፎች “ማርያምም እንዲህ አለች፦ ‘ነፍሴ ጌታን ታከብረዋለች’” ይላሉ። አንዳንዶቹ ደግሞ “ኤልሳቤጥም እንዲህ አለች፦ ‘ነፍሴ ጌታን ታከብረዋለች’” ይላሉ።
- ሉቃስ 9፥48፦ አብዛኞቹ የእጅ ጽሑፎች “ከሁላችሁ የሚያንስ እርሱ ታላቅ ነውና” ይላሉ። አንዳንዶቹ ደግሞ “ከሁላችሁ የሚያንስ እርሱ ታላቅ ይሆናልና” ይላሉ።
- ሉቃስ 14፥19፦ አብዛኞቹ የእጅ ጽሑፎች አብዝሀኞቹ እደክታባት፤ ልፈትናቸውም እሄዳለሁ፤ ይቅር እንድትለኝም እለምንሃለሁ ሲሉ የተቀሩት እደክታባት ደግሞ ልፈትናቸውም እሄዳለሁ፤ በዚህም ምክንያት ይቅር እንድትለኝ እለምንሃለው ይላሉ።
- ሉቃስ 23፥45፦ አብዛኞቹ የእጅ ጽሑፎች “ፀሐይም ጨለመ” ይላሉ። አንዳንዶቹ ደግሞ “ፀሐይ ብርሃኑን አጣ (ከሸፈ)” ይላሉ።
- ዮሐንስ 1፥3-4፦ አብዛኞቹ የእጅ ጽሑፎች “ሕይወት በእርሱ ነበረች” ይላሉ። አንዳንዶቹ ደግሞ “ሕይወት በእርሱ ናት” ይላሉ።
- ዮሐንስ 1፥28፦ አርጌንስ እጅ ላይ የነበሩት የእጅ ጽሑፎች በሙሉ “ይህ ነገር በዮርዳኖስ ማዶ በቢታንያ ሆነ” የሚሉ ነበሩ። አርጌንስ ግን ትክክለኛው ቦታ “ቤተ ራባ” መሆን አለበት ብሎ ያምን ነበር።
- ዮሐንስ 3፥34፦ አብዛኞቹ የእጅ ጽሑፎች “እግዚአብሔር መንፈሱን ሰፍሮ አይሰጥምና” ይላሉ። አንዳንዶቹ ደግሞ “እግዚአብሔር መንፈሱን በከፊል አይሰጥምና” ይላሉ።
- ሮሜ 3፥5፦ አብዛኞቹ የእጅ ጽሑፎች “እንደ ሰው ልማድ እላለለሁ” ይላሉ። አንዳንዶቹ ደግሞ “እንደ ሰዎች ልማድ እናገራለሁ” ይላሉ።
- ሮሜ 5፥14፦ አብዛኞቹ የእጅ ጽሑፎች “ኃጢአታቸው እንደ አዳም መተላለፍ ላልሆነው” ይላሉ። ጥቂቶቹ ደግሞ “ኃጢአታቸው እንደ አዳም መተላለፍ ለሆነው” ይላሉ።
- ሮሜ 7፥6፦ አብዛኞቹ የእጅ ጽሑፎች “አሁን ግን ከሕግ ተፈትተናል” ይላሉ። አንዳንዶቹ ደግሞ “አሁን ግን ከሞት ሕግ ተፈትተናል” ይላሉ።
- ሮሜ 14፥23 እና 16፥25-27፦ በአንዳንድ የእጅ ጽሑፎች ላይ ከምዕራፍ 16፥25-27 ያለው የምስጋና ጸሎት (doxology) በሮሜ መልእክት ማብቂያ ላይ ይገኛል። በሌሎች የእጅ ጽሑፎች ላይ ደግሞ ይህ ምስጋና ከምዕራፍ 14፥23 ቀጥሎ ተቀምጧል። ጽሑፉ በማንኛውም ሁኔታ ግን አንድ ዓይነት ነው።
- ቆላስይስ 2፥15፦ አብዛኞቹ የእጅ ጽሑፎች “በእርሱ ድል ነሳቸው” ይላሉ። አንዳንዶቹ ደግሞ “በመስቀሉ ድል ነሳቸው” ይላሉ።
- 2 ጢሞቴዎስ 4፥6፦ አብዛኞቹ የእጅ ጽሑፎች “የምሄድበትም ጊዜ ደርሶኣል” ይላሉ። አንዳንዶቹ ደግሞ “የሕይወቴ ጊዜ ደርሷል” ይላሉ።
- ዕብራውያን 2፥9፦ አንዳንዶቹ የእጅ ጽሑፎች “ያለ እግዚአብሔር ረዳትነት ስለ ሰው ሁሉ ሞትን ይቀምስ ዘንድ” ይላሉ። ሌሎች ደግሞ “በእግዚአብሔር ጸጋ ስለ ሰው ሁሉ ሞትን ይቀምስ ዘንድ” ይላሉ።
መደምደሚያ ሐሳብ
በሊቁ አርጌንስ ክታብ ውስጥ በጉልህ 22 የምንባብ ልዩነቶች ሰፍረዋል። ከእነዚህ ውስጥ በ20ቹ ላይ የታየው የእጅ ጽሑፎች ምንባባት ልዩነት በአጠቃላይ ከአንድ ቃል ጋር የተያያዙ ሲሆን፤ እርሱም ተመሳሳይ ትርጉም ያለው ሌላ ተመሳሳይ ቃል(synonym)፣ የተለየ የሰዋስው አወቃቀር፣ የተለየ ስም፣ የጎደለ ወይም የተጨመረ ቃል ተገኝቶ ሊሆን ይችላል። ጽሑፉ አንድ ዓይነት ሆኖ ሳለ፣ አርጌንስ አሁንም ጥያቄ የነበረበት ሁለት ምሳሌዎች ግን ነበሩበት። ይህም የሆነበት ምክንያት ሊቁ አርጌንስ ምሑርና ባለ ብዙ ቋንቋዎች ባለቤት እንደመሆኑ መጠን፣ የላቀ የጽሑፍ ጥራትና ወጥነትን ይፈልግ እንደነበረና ያንን ዓረፍተ ነገር የጻፈውም ለዚሁ እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም። በዚህም ሊቁ ከሰጣቸው ምሳሌዎች ውስጥ መረዳት የምንችለው፣ በአዲስ ኪዳን ጽሑፍ ላይ ምንም ዓይነት ጠንካራ የሚባል ችግር እንደሌለ ነው። ብዙውን ጊዜ ከአንድ ቃል ጋር የተያያዙ ጥቂት የጽሑፍ ልዩነቶች ያሉ ሲሆን፣ እነዚህንም ‘የምንባቤያዊ ሕየሳ’ (textual criticism) መስፈርትን በመጠቀም ለይቶ ማስተካከል ይቻላል። ስለሆነም፣ አርጌንስ አዲስ ኪዳንን በተመለከተ ችግሮች እንዳሉበት ያስቀምጣል ማለት እጅጉን ማጋነን ነው። የቀረበውም ማስረጃ ይህንንም በፍጹም አያሳይም።
ሦስተኛውና የመጨረሻው ነጥቤ፦ የእስልምና ምሑራን ቁርዓንን በሚተረጉሙበት(በሚያብራሩበት) ጊዜ፣ ልክ እንደ ሊቁ አርጌንስ ሁሉ እነርሱም በቁርዓን ጽሑፍ ውስጥ ስላሉት የቅጂ ልዩነቶች(variants) ይወያያሉ።
ለዚህም ሦስት ምሳሌዎች ላንሳ፦
አል-ጠበሪ እና ቁርዓን 2:2133፦
በዑስማን የተደነገገው(የተመደበው) መደበኛ የቁርዓን ጽሑፍ ‘የሰው ልጆች ሁሉ አንድ ማኅበረሰብ ነበሩ፤ ከዚያም አላህ ነቢያትን አስነሳ’ ይላል። ሆኖም በአብደላህ ኢብን መስዑድ የቁርዓን ቅጂ ላይ ‘የሰው ልጆች ሁሉ አንድ ማኅበረሰብ ነበሩ፤ ከዚያም ተለያዩ(ተጣሉ)፤ አላህም ነቢያትን አስነሳ’ የሚል ነበር።
ሳሂህ አል-ቡኻሪ እና ቁርዓን 92:3 4፦
በዑስማን የተደነገገው መደበኛ የቁርዓን ጽሑፍ ‘ወንድና ሴትን በፈጠረው እምላለሁ’ ይላል። ሆኖም በአብደላህ ኢብን መስዑድ የቁርዓን ቅጂ ላይ ‘በወንዱና በሴቷ እምላለሁ’ የሚል ነበር።
አብደላህ ዩሱፍ አሊ እና ቁርዓን 33:6 5፦
በዑስማን የተደነገገው መደበኛ የቁርዓን ጽሑፍ ‘ነቢዩ ለምእመናን ከነፍሶቻቸው ይልቅ ቅርብ ነው፤ ሚስቶቹም እናቶቻቸው ናቸው’ ይላል። ሆኖም በኡበይ ኢብን ካዕብ የቁርዓን ቅጂ ላይ ‘ነቢዩ ለምእመናን ከነፍሶቻቸው ይልቅ ቅርብ ነው፤ እርሱም ለእነርሱ አባት ነው፤ ሚስቶቹም እናቶቻቸው ናቸው’ የሚል ነበር።
በታሪክ ሂደት ውስጥ በሙስሊሞች ዘንድ ለእነዚህ የጽሑፍ ልዩነቶች የተሰጡት ምላሾች የተለያዩ ነበሩ። በእስልምና የመጀመሪያዎቹ አሥርተ ዓመታት ውስጥ እነዚህ ልዩነቶች እንደ ችግር ይታዩ የነበረ ሲሆን፣ ሦስተኛው ከሊፋ ዑስማን አንድ ወጥ የሆነ መደበኛ የቁርዓን ቅጂ እንዲዘጋጅና ሌሎች የተለያዩ የእጅ ጽሑፎች በሙሉ እንዲቃጠሉ(እንዲጠፉ) አዟል።6 ሌሎች ሙስሊሞች ደግሞ እነዚህ የጽሑፍ ልዩነቶች ትክክለኛና ተዓማኒ (authentic) እስከሆኑ ድረስ የቁርዓኑ አካል አድርገው ይመለከቷቸዋል። ይህ ማለት ልዩነቶቹ መመዘንና መፈተሽ አለባቸው ማለት ነው። ይሁን እንጂ አብዛኞቹ ሙስሊሞች ስለነዚህ የጽሑፍ ልዩነቶች ግንዛቤ የላቸውም። ‘The Encyclopedia of the Quranic Readings with an Introduction to Readings and Famous Readers’ የተሰኘው ኢንሳይክሎፔዲያ የ10,243 የጽሑፍ ልዩነቶችን ዝርዝር መረጃ ይዟል።7
ማጠቃለያ
ሊቁ አርጌንስ ስለ አዲስ ኪዳን ምንባባት ልዩነት የተናገረውን ንግግር አንዳንድ ጊዜ በሙስሊሞች ዘንድ አዲስ ኪዳን ከባድ ችግሮች እንዳሉበት ለማሳየት ጥቅም ላይ ይውላል። ነገር ግን ከላይ እንዳየነው ሊቁ በፍጹም ወደዚህ ድምዳሜ አልደረሰም፤ ከሰጣቸውም ምሳሌዎች መረዳት የሚቻለው አብዛኛውን ጊዜ ከአንድ ቃል ጋር የተያያዙ ጥቂት የጽሑፍ ልዩነቶች ብቻ መኖራቸውን ነው። እነዚህንም የምንባቤያዊ ሕየሳ(textual criticism) መሥፈርቶችን በመጠቀም ለይቶ ማስቀመጥ ይቻላል። በተጨማሪም ቁርዓን ራሱ የጽሑፍ ልዩነቶች ያሉበት መሆኑንና ሙስሊሞች ቀደም ሲልም የያዙት፣ አሁንም ድረስ እየያዙት ያለ ጉዳይ መሆኑን አይተናል። ስለሆነም ሙስሊሞች አርጌንስ አዲስ ኪዳንን ተዓማኒነት የጎደለው አድርጎ ያስብ ነበር የሚል የተሳሳተ ግንዛቤ ለመፍጠር መሞከር የለባቸውም፤ እንዲሁም ቁርዓን ከጽሑፍ ልዩነቶች የጸዳ ነው የሚል ስሜት ለመስጠትም መጣር የለባቸውም።
[ማሳሰቢያ፦ ይህ የትርጉም ጽሑፍ በጸሐፊው ሙሉ ፍቃደኝነት የተተረጎመ መሆኑን እንገልጻለን።]
ማጣቀሻዎች
- Origen, Commentary on Matthew xv. 14. Cited from Bruce M. Metzger & Bart D. Ehrman, The Text of the New Testament, Oxford University Press, Oxford, U.K. 4th edition, 2005, p. 200. ↩︎
- Bruce M. Metzger, “Explicit References in the Works of Origen to Variant Readings in New Testament Manuscripts”, in Biblical and Patristic Studies, edited by J.Neville Birdsall and Robert W.Thomson, Herder, New York, 1963, pp. 78-95. ↩︎
- Al-Tabari, The History of Al-Tabari, New York: SUNY, vol. I, p. 353. For other examples see vol. II, pp. 68, 108, 109, vol. III, p. 174. ↩︎
- Sahih al-Bukhari: 4944; vol. 6, bk. 60, no. 468 ↩︎
- Abdullah Yusuf Ali, The Holy Qur’an: Text, Translation, and Commentary, 4th ed., Brentwood, Md., U.S.A.: Amana Corp., 1989, footnote 3674 ↩︎
- “አነስ ኢብኑ ማሊክ እንደተረከው :- የሻም እና የኢራቅ ህዝቦች አርሜንያ እና አዛርበጃንን ለመውረር ጦርነት አውጀው በነበረበት ሰአት ሑዙይፋ ቢን አል-የመኒ ወደ ኡስማን መጣ። ሑዘይፋ በህዝቡ(በሻም እና በኢራቅ) ሁኔታ ተጨንቆ ነበር እርሱም ህዝቡ የተለያየ የቁርአን አቀራር ይቀሩ ነበር። ሑዘይፋ:- ለኡስማን እንደዚህ አለው፦”ኦ የሙስሊሞች አለቃ(አሚረል ሙእሚኒን) ይህ ህዝብ (ኡማ) እንደ ቀደምት አይሁድ እና ክርቲያኖች እንደሆነባቸው በኛም በቁዱሱ መጽሐፍ(ቁርአን) ላይ ልዩነት ከመፈጠሩ በፊት አድን” ኡስማንም ሃፍሷን አንቺ ጋ ያሉትን ቅጂ ጽሑፎች ላኪልን ቁርኣንን ፍጹም አድርገን በአንድ ቅጂ ጥራዝ ሰርተን ስንጨርስ ዋና ቅጂ ጽሑፎቹን እንመልስልሻለን አላት። ሃፍሷም ለኡስማን ላከችለት። ከዛ ኡስማን ዘይድ ኢብኑ ሣቢትን፣ አብደላህ ኢብኑ ዙቤርን፣ ሰኣድ ኢብኑ አስን እና አብዱረህማን ቢን ሐሪስ ቢን ሂሻምን በጥንቃቄ እንዲገለብጡ አዘዛቸው። ኡስማንም ለሶስት የቁረይሽ ሰዎች እንዲህ አላቸው፦ ” ከዘይድ ኢብኑ ሳቢት ጋር በማናቸውም ነጥብ በጻፈው ቁርኣን ባትስማሙ፣ እናንተ እንደገና በቁረይሾች ቋንቋ አጠቃቀም መሰረት ጻፉት አላቸው ምክንያቱም ቁርአን በነሱ ቋንቋ ስርአት ስለሆነበር የወረደው ” እነሱም እንዳላቸው አደረጉ: ብዙ ቅጂዎችን ጽፈው ከጨረሱ በሗላ ዋናውን ቅጂ ለሃፍሷ መለሰላት። ኡስማንም ለእያንዳንዱ የኢስላም ግዛት አዲስ ከተገለበጠው አንዳንድ ቅጂ ልኮ ከዚህ ውጪ ማንኛውም የተከፋፈለም የቁርአን ቅጂም ይሁን ሙሉ የተጠረዘ ቁርአን ሁሉም እንዲቃጠሉ አዘዘ::(Sahih al-Bukhari: 4987; vol. 6, bk. 61, no. 510) ↩︎
- Mu’jam al-qiraa’aat al-Quraaneeyah, ma’a maqaddimah fee qiraa’aat wa ashhar al-qurraa (The Encyclopedia of the Quranic Readings with an Introduction to Readings and Famous Readers), prepared by Ahmad Omar and AbdElal Makram, Alam Al Kotob, Cairo, Egypt, third edition, vols. 1-6, 1997, vol. 5, p. 521. ↩︎
የጽሑፍ ምንጭ፦ https://www.answering-islam.org/authors/green/origen.html


