የህፃናት ጥምቀት | Infant Baptism

ክፍል ፩

ብዙ ሰዎች የህፃናት ጥምቀትን አስተምህሮ ለመቀበል የሚከብዳቸውና በተደጋጋሚም የሚጠይቁት ነገር ቢኖር እንዴት ህፃናት ማመን ይችላሉ? የሚለው ነው። በእርግጥ በጠቅላላ ይህንን አስተምህሮ የማያምኑ ሁሉ ቀዳሚ ምክንያታቸው “ህፃናት ማመን አይችሉም” የሚል ነው።

መቼም ሁላችንም እንደምንስማማው ሰው ለመዳን የእግዚአብሔርን ቃል ሰምቶ ማመን አለበት። መጽሐፍ ቅዱስ ሰው ለመዳን ማመን እንዳለበት መሐከለኛ አስተምህሮው አድርጎ የሚያስቀምጠው ነገር ነው። ነገር ግን አንድ የምናውቀው ነገር ህፃናት ወንጌልን ብንሰብክላቸው ሰምተው ከዛም አሰላስለው የተነገራቸውን ተረድተውት ፤ በተገለጠም መልኩ እምነታቸውን አያሳዩም ወይም አይናገሩም። ስለዚህም ብዙዎች ከዚህ ተነስተው ህፃናት ሊያምኑ አይችሉም ብለው በማመን እነሱን ማጥመቅ ይከለክላሉ።

በአጭሩ የዚህ አይነቱ አስተሳሰብ ስህተት የሚጀምረው ራሳቸው ጥያቄ አድርገው ከሚያቀርቡት ከእምነት ምንነት ነው። እምነትን በትክክል በመረዳት ብቻ ይህን አረዳድ ማስካከል ይቻላል።

እንግዲህ እምነት ማለት ሰዎች ከእግዚአብሔር በነፃ የቀረበላቸውን የተጨረሰና የተጠናቀቀ ድህነት የሚቀበሉበት እጅ ነው።(ይህንን በሌላ ጽሑፍ የእምነት ብቻ አስተምህሮና የቅዱሳት ሚሥጢራት አስተምህሮ ንፅፅር በስፋት አብራርቼ አስቀምጣለሁ።) በታሪካዊው ፕሮቴስታንቱ አስተምህሮ መሠረት እውነተኛ አዳኝ እምነት በሶስት መሠረታዊ ነገሮች ላይ የሚመሠረት ወይም የሚተረጎም ነው። እነርሱም እውቀት ፣ ፍቅር እና መደገፍ (Trust) ናቸው። አንድ ሰው ለማመን የሚታመንበት ነገር ሊቀርብለት እርሱንም በሆነ መልኩ ሊያውቅ፣ ሊረዳ ወይም ሊያስተውል ይገባል። በመቀጠልም ይህ አዳኝ እምነት በፍቅር የሚሰራ ነው። ማለትም ከፍቅር ባህሪ ጋር የተጋመደና የፍቅር ድርጊቶችንም የሚያፈልቅ ነው። ሶስተኛውና ትልቅ ዋጋ ያለው ደግሞ(Definitional Aspect) ደግሞ መደገፍ(Trust) ነው። ይህም ማለት እምነት በአማኙ ደካማነት ፣ አለመቻልና ባዶነት ላይ ተመስርቶ የሚታመነው አካል ባለው ጥንካሬ፣ ችሎታ፣ አቅምና ብርታት ላይ ራስን መጣልና መደገፍ ነው። ከዚህ የመደገፍ(Trust) ትርጉሙ አንፃር እምነት ሙሉ ለሙሉ ተቀባይ ነው እንጂ ሰጪ አይደለም ማለት ነው። እምነት የሚያድነውም በዚህ በተቀባይ ባህሪው ብቻ ነው። ይህንን እውነተኛ እምነት/Fides Directa/ ብለን እንጠራዋለን።

እምነትን በዚህ መልኩ ከተረጎምነው ሌላው መረዳት ያለብን አንድ ልዩነት/Distiniction/ አለ። እርሱም Councious Faith እና Uncouncious Faith ናቸው። እንተርጉማቸው።

Conscious Faith/አስተውሎታዊ እምነት/፦ ይህም አማኙ በውል ተረድቶትና አውቆት የሚይዘው እምነት ነው። ይህም አንድ ሰው ስለ እምነቱ ያለውን ጥልቅ የሆነ አመክንዮአዊ ምልከታና ምክንያታዊ ግንዛቤን ያካትታል።

Unconscious Faith/ደመ-ነፍሳዊ እምነት/፦ ይህም በአንድ ሰው ውስጥ ያለ ነገር ግን ገና በንቃት ወይም በዕውቀት ያልተገለጠ የእምነት ዓይነት ነው። ይህም ስለ እምነት ያለን አመክንዮአዊ ትንታኔ ወይም ምክንያታዊ መረዳትን አይዝም።

እነዚህን ሁለት ልዩ ባህርያት/Distinictions/ ህፃናቱ ጋር ሳንሄድ ከትላልቅ ሰዎች በመነሳት መረዳት እንችላለን። ለመጀመሪያው የእምነት አይነት ምንም የራቀ ማስረጃም አያስፈልግም። ለምሳሌ ይህን ጽሑፍ የምታነቡት አንባቢያን ለአፍታ ወደራሳችሁ ዞር ብላችሁ ስለእምነታችሁ ካስተዋላችሁ ካደረጋችሁ እርሱ በቂ ማስረጃ ይሆናችኋል። ሁለተኛውን የእምነት አይነት ግን አቅርበንም፣ አርቀንም በተለያዩ መንገዶች ልንመለከተው እንችላለን። ከቅርቡ ለመነሳት ያህል ለምሳሌ በቀን ውሏችን ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ትኩረታችንን በሚወስዱ ስራና የተለያዩ ድርጊቶች በተወጠርንበት ሰአት አስተንትኖታዊ እምነት/ Councious Faith/ አይኖረንም። በዚህ ውስጥ የትኛውም ከራሳችን ውጪ ሙሉ ትኩረታችንን የሚወስዱ ድርጊቶች ሙሉ ለሙሉ ሊካተቱ ይችላሉ። ይህ የዕለት ተዕለት ኑሮዋችን ውስጥ የሚከናወን ከመሆኑ አንፃር ቀላሉና ቅርቡ ምሳሌ ይሆናል። ምናልባት ሰፋ አድርገን ከሩቁ ካየነው ደግሞ እውነተኛ እምነት የነበራቸውና የዳኑ ነገር ግን በአደጋ ምክንያት ራሳቸውን የሳቱ ወይም ሲብስ ኮማ ውስጥ የገቡ ሰዎችን መጥቀስ እንችላለን። በእርግጥ እዛም ሳይደርስ ሁላችንንም የሚያካትት ሙሉ ለሙሉ የፍቃድም/Will/ ሆነ የነቃ የአእምሯዊ ህላዌን/Intellect Conciousness/ የምናጣበት እጅግ ቅርብ የሆነውን የሌሊት እንቅልፍ በምሳሌነት ማንሳት እንችላለን። በእነዚህ ሁሉ ውስጥ ግን ምንም እንኳ አስተንትኖታዊ እምነት/ Councious Faith/ ባይኖረንም ግን እምነታችንም አይጠፋም።

በአጭሩ እነዚህ ከላይ ያሉት ሁሉ ሰው የፍቃዱም ሆነ የመረዳቱ ችሎታዎች ሙሉ ለሙሉ ተግባራቸውን በንቃት በማይሰሩበት በዛ ሁኔታ ውስጥ ቢሆንም ግን እውነተኛ እምነት መኖርና መቀጠል መቻሉን የሚያስረግጡ ናቸው።

ወደ መጀመሪያው ጥያቄ ስንመለስ ቀድመን መረዳት ያለብን ነገር “ህፃናት ማመን አይችሉም!” የሚሉ ወንድሞች በዚህ አገላለፃቸው በጭራሽ ህፃናት የማመን አቅምና ችሎታ የላቸውም(Capacity to Believe) እያሉን አይደለም። ምክንያቱም እነዚህ ክሂሎች ግዴታዊ ባህሪያት በማንኛውም ሰው ውስጥ የሚቀመጡ ሰው ሰው ለመሆኑ በባህሪያዊ ግዴታ የሚይዛቸው(Intrinsic Property) ናቸውና። ስለዚህ በብቸኝነት ለእውነተኛ እምነት እና ግዴታዊ ውሳኝ ቅድመ ሁኔታ አድርገው የሚያስገቡት ከላይ የተቀመጠውን አስተውሎታዊ እምነትን(Conscious Faith) ነው። እርሱም በቀጣይነት ያለንበትን ሁኔታ በመመርመር እና ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ማስጨበጥ ነው።

ነገር ግን ከላይ ከተቀመጡት ሁለቱ ልየነቶች የምንረዳው ለእውነተኛ እምነት (Fides Directa) አስተውሎታዊ እምነትን(Conscious Faith) በጭራሽ ውሳኝ ቅድመ-ሁኔታ(necessary condition) ሊሆን እንደማይችል ነው። ይህ ካልሆነ ግን በUnconscious Faith/ደመ-ነፍሳዊ እምነት/ ስር በተዘረዘሩት ምሳሌዎች ውስጥ ያሉ አማኝ ሰዎችን በጠቅላላ ወደ ኢ-አማኒነት እየገለበጥን ልናስቀምጣቸው እንገደዳለን። ምክንያቱም ይህን አመለካከት እንደ ቅድመ-ሁኔታ ካደረግው ከእርሱ የወጣውን እምነትም ሙሉ ለሙሉ ስለሚጠፋ።

ከዚህ ቀጥሎ መጨመር የሚያስፈልገን ነጥብ በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት ያለውን አንድ መፅሀፍ ቅዱሳዊ እውነት ነው። እርሱም እምነት ራሱ የእግዚአብሄር ስጦታ መሆኑ ነው። መፅሐፍ ቅዱስ መንፈስቅዱስ በሚሰጠው የቃሉ ብርሀን እና እርሱም ይዞት በሚመጣው ፀጋ እምነትን በነፍሳችን ውስጥ እንደሚፈጥር መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምረናል። እዚህ ላይ መሳሳት የሌለብን ይህ ማለት እግዜር ነው የሚያምንልን ማለት አይደለም። አማኞቹ እኛ ነን። ነገር ግን የምናምንበትን ልብ እንዲያምን የሚቀርፀውም ሆነ የምናምንበትን ያንን የእምነት ይዘት(content) የሚያቀርብልን መንፈስቅዱስ ነው ማለት ነው። መንፈስ ቅዱስ ይህንን ስራ እንዳይሰራ በብቸኝነት የሚከለክለው ነገር ደግሞ ተቃውሞና እምቢታ(Will full Rejection) ብቻ ነው። ህፃናት ግን መንግስተ ሰማይ የተወከለባቸው ፤ እኛንም እንኳን መንግስቱን ለመምሰል ወደ ኋላ ተመልሰን እነርሱን እንድንመስላቸው የተነገረላቸው ናቸው። መቼም ምሰሉ የተባልነው ቁመታቸውን አይደለም። ይህም ራሳቸውን አዋርደው የተሰጣቸውን ሁሉ ያለተቃውሞ የሚቀበሉ መሆናቸውን እርሱም እምነታቸውን(Fides Directa) እንጂ! ስለዚህ መንፈስቅዱስ ልክ በእኛ ውስጥ እምነትን እንደሚሰራ በእነርሱም ውስጥ ሊሰራ የማይችልበት ምንም ምክንያት የለም ማለት ነው። የእግዚአብሔር ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ።

ለሌሎች ያጋሩ

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top