ሰላም። በመጀመሪያ ከእኛ ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብ ዝግጁና ፍቃደኛ በመሆናችሁ እግዚአብሔርን እናመሰግናለን። ምናልባት ይህን በእጃችሁ ያለውን መጽሐፍ አዲስ እና እንግዳ ሆኖባችሁ ይሆናል። ዛሬ በዚህ ጽሑፍም በእጃችሁ የሚገኘው መጽሐፍ ቅዱስ የሚለው መጽሐፍ ምንድነው የሚለውን በአጭሩ የምንተዋወቅ ይሆናል። ክርስቲያኖች 66ቁጥሮች ርዝማኔ ያላቸው መጻሕፍ አላቸው። እነዚህም መጻሕፍትበሁለት ክፍል ይቀመጣሉ። እነርሱም ብሉይ ኪዳን እና አዲስ ኪዳን በማለት ይከፈላሉ። ብሉይ ኪዳን 39 አዲስ ኪዳን ደግሞ 27 መጻሕፍትን ይዘዋል። መጽሐፍ ቅዱስ የሚለው ቃል የእንግሊዝኛው አቻ ትርጉም “ባይብል” የሚለው “ቢብሊያ” ከሚለው የጽርእ(የግሪክ) ቃል የመጣ ሲሆን “መጻሕፍት” ማለት ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በአንድ ግለሰብ እንዲሁም በጥቂት ዓመታት ውስጥ የተጻፈ መጽሐፍ ሳይሆን፣ በብዙ መቶ ዘመናት ውስጥ በተለያዩ ቋንቋዎች ከ40 በላይ ጸሐፊያን ያሉትና በ1500 ዓመታት ውስጥ የተጻፉ የተለያዩ መጻሕፍት ስብስብ ነው፡፡ በእርሱም ውስጥ እግዚአብሔር በቀጥታ ከህዝቡ ጋር ይነጋገራል፣ በሌላ ጊዜ ደግሞ በቅዱሳን ሰዎች ሐሳብና ቃል አማካኝነት ሲናገር፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ በዘመን መጨረሻ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ተግልጦ ተናግሮናል። በመጽሐፍ ቅዱስ ምሑራን የጊዜ አመዳደብ መሰረት የመጀመርያው ክፍል ከክርስቶስ ልደት በፊት በ1400 ዓ.ዓ. አካባቢ እንደሆነና የመጨረሻው ደግሞ ከክርስቶስ ልደት በኋላ በ90 ዓ.ም. አካባቢ እንደተጻፈ ይታመናል። መጽሐፍ ቅዱስን ስናነብ ማወቅ ካሉብን ልዩ ሁኔታዎች መካከል መጽሐፍ ቅዱስ እንደ ቁርአን እና ሌሎች አይነት መገለጥ እንዳልሆነ ነው። ይህን ለመረዳት ጳውሎስ ለመንፈሳዊ ልጁ ለጢሞቴዎስ በላከው 2ኛ ጢሞቴዎስ 3፥16-17 እንዲህ ሲል ይናገራል፦
“የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ፥ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል።”
በዚህ ክፍል ላይ ጳውሎስ የእግዚአብሔርን ቃል፣θεόπνευστος “ቴኦፕኔውስቶስ” መሆኑን ሲናገር የቃሉ ፍቺ θεό “ቴኦ” ማለት “እግዚአብሔር” እና πνευστος “ፕኔውስቶስ” ማለትም “መንፈስ” ከሚሉ ሁለት የጽርእ ቃል የተገኘ ነው፤ በአንድ ላይ ሲነበቡም “እስትንፋሰ እግዚአብሔር” የሚል ነው። ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስ ሁሉ በእግዚአብሔር መንፈስ እስትንፋስ የተጻፈ ነው፤ የሰዎችን ልብ ሁሉ የሚቀይር እንዲሁም በእምነት የሚያነብ የእርሱን ድምፅ ይሰማል። በግልጽ ልብና አእምሮ ካነበብነው፣ እግዚአብሔር እኛ በማናቀው መንገድ ሲናገረን እንገኛለን። ስለዚህ ይህ የያዛችሁት መጽሐፍ ሌሎች ጋር እንዳለ አይነት መጽሐፍ እንዳልሆነ በእነዚህ መንገዶች ትረዳላችሁ።
የመጻሕፍቱ ዝርዝር
| # | መደቦች | የመጽሐፍቱ ብዛት | መጻሕፍቱ |
| 1 | የሙሴ ሕግ (ፔንታቱክ) | 5 | ዘፍጥረት – ዘዳግም |
| 2 | የታሪክ መጻሕፍት | 12 | እያሱ – አስቴር |
| 3 | ቅኔ/ግጥም | 5 | እዮብ – መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን |
| 4 | አበይት ነብያት | 5 | ኢሳይያስ – ዳንኤል |
| 5 | ደቂቅ ነብያት | 12 | ሆሴዕ – ሚልኪያ |
| ➡ አጠቃላይ ብሉይ ኪዳን | 39 | ||
| 6 | ወንጌላት | 4 | ማቴዎስ – ዮሐንስ |
| 7 | የታሪክ መጽሐፍ | 1 | ሐዋርያት ሥራ |
| 8 | የጳውሎስ መልእክታት | 13 | ሮሜ – ፊልሞና |
| 9 | አጠቃላይ መልእክታት | 8 | ዕብራውያን – ይሁዳ |
| 10 | ራዕይ(አቡቀለምሲስ) | 1 | ራዕይ |
| ➡ አጠቃላይ አዲስ ኪዳን | 27 | ||
| ➡ ጠቅላላ ድምር | 66 | ||
መጽሐፍ ቅዱስ በአጭሩ
የመጽሐፉ ዋና ዋና መልእክቶች፦ በኦሪት ዘፍጥረት ምዕራፍ 1 ላይ ዓለምን የፈጠረ እግዚአብሔር እንደሆነ ገልጾ በማሳየት ይጀምራል። በዚህም እግዚአብሔርም ፍጥረታትን በስድስት ቀን እንደፈጠረ በሰባተኛው ቀን እንዳጠናቀቀ እንመለከታለን። በዚህም ውስጥ “ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር” በማለት ሰው የሚለውን ከፍጥረቱ ሁሉ መካከል ልዩ አድርጎ እንደሰራው፣ ስማቸውንም አዳም እና ሔዋን እንደነበሩ እንመለከታልን። በዚህም የፍጥረት መጽሐፍ ላይ የምንረዳው የዓለማትና የእኛ ሠሪ አንዱ እግዚአብሔር ብቻ እንደሆነ አስተዋውቆ ይጀምራል። ነገር ግን ብዙም ሳይቆይ በቅድስና የተመሰገነውን አምላክ አዳምና ሔዋን ኃጢአት ሰርተው እንዳሳዘኑት በዚህም ከእግዚአብሔርም ጋር የነበራቸው ግንኙነት ሲያጡ እንመለከታለን። ከዚያም እግዚአብሔርም በሙሴ በማስነሳት(ዘፀአት 7) በእርሱ በኩል አሥርቱን ትእዛዛት(በዘፀአት 20) እንዴት እንደሰጣቸው እንመለከታለን። በታሪክ መጻሕፍት ውስጥ የኪዳኑ ሕዝብ ኪዳን ከሌላቸው ጣኦት አምላኪያን ጋር የነበራቸውን ውጣ ውረድና የእግዚአብሔርን ፍቅሩ ጽድቁን ባደረጉት የቁጣው ፀሐይ ደግሞ ባልፈለጉት ላይ እንደወጣች በሰፊው ተከትቦ እናገኛለን። በእያንዳንዱ ታሪኮችን ውስጥ የምንገነዘበው ነገር እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ያለው የታመነ ፍቅሩ ነው፤ እርሱም በደንዳናው ሕዝበ እስራኤል ላይ ምን ያህል ታጋሽ የሆነ ፍቅር እንዳለው በስፊው ተቀምጦልናል። ለምሳሌ፦ እንደ ኖኅ፣ አብርሃም፣ ሙሴ፣ ኢዮብ፣ ዳዊት እና ሌሎች ያሉ የተወሰኑ ሰዎችን በልዩ መንገድ ጠርቶ ይህ ኃያል አምላክ በየዘመናቱ ፍቅሩን ሲገልጥ እናገኘዋለን።
እነዚያ የመረጣቸው የኪዳኑ ሕዝብ በኋላም ከአመጻቸው የተነሳ ለእግዚአብሔር ሕግ መታዘዝ እንዳቃታቸው ስለዚህም እግዚአብሔር በመጨረሻው ዘመን የሰው ልጆች ያፈረሱትን የድሮውን ኪዳን ለመፈጸም እና አዲስን ኪዳን ከህዝቡ ጋር ለማቆም አንድያ ልጁን የላከው። ይህ አዲሱ ኪዳን ግን በደካማ የሰው ልጆች ሥራና ታዛዥነት ላይ የተመሰረተ ሳይሆን፣ በሰማያዊው አዳኝ፣ በዘላለማዊው ቃል በሆነው በመሲሕ ላይ ነው። ይህ መሲሕ በብሉይ ኪዳን ዘመን ጌታችን ኢየሱስ ከድንግል ከመወለዱ ከ700 ዓመት በፊት በነብዩ ኢሳይያስ ላይ ተነግሮለታል። አሁን የትንቢቱ ፍጻሜው ቀረበና እርሱ ራሱ በትልቁ የሮም ግዛት እጅጉን ደሳሳና አናሳ በሆነች ቤት የተወለደ ሆኖ መጣ።(ዮሐንስ 1፥14) አዎን ከላይ እንዳልነው እግዚአብሔር ኃያልና የከበረ ነው፣ ነገር ግን እርሱን እንድናውቀው ግን የባሪያን መልክ ያዘ።(ፊልጵስዩስ 2)
የክርስቶስን ሕይወትና አገልግሎት ስናነብ ሳለ በአእምሯችን ሥሑት ትርጓሜ እንዳይፈጠር ሥነመለኮታችንን የተቃኘ መሆን አለበት። በዚህም የሚያግዟችሁን ጥሩ መጋቢያን መፈለግ ጥሩ ነው። አንዳንድ መናፍቃን አምላክ አይደለም ይልቅ ሰው ብቻ ነበር በማለት ሊያስቱ ይሞክሩ ይሆናል። በዚህም ትምህርት ንፋስ ተውስደን “ኢየሱስ ሰው ብቻ ነበር” ካልን፣ ሙሉ በሙሉ እንስታለን። “ሰው አይደለም አምላክ ብቻ ነበር” ካልንም ሰውነቱን ክደናልና ከሃዲያን እንባላለን። የነገረ ክርስቶስ ጥናት ስፊ ውቂያኖስ ነው። ይህንንም ሐሳብ መምህራን ሲገልጡ “…ጥናቱም ልክ ቀጭን ምላጭ ላይ እንደመራመድ ማለት ነው። በግራ ብንወድቅ አውጣኬ አለ። በቀኝ የወደቅን የሆንን ከሆነ ድግሞ ንስጥሮስ አለ…” በማለት ያስቀምጣሉ። ታዲያ ነገረ ክርስቶሳችን ጥናቱ ያልተቃኘ ከሆነ መርማሪው እንዳይወድቅ ይፍራ። ጥሩ አንባቢ ክርስቲያን ግን በቀጭኗ ምላጭ ላይ በቀስታ ይራመዳል።
ስለዚህ በዚህን መጽሐፍ ቅዱስን ጥናት ወቅት አውዱን ያልሳተ ትርጓሜ መጠቀም፣ ተዓማኒ የሚባሉ ማብራሪያውችን ማገላበጥ፣ ታሪካዊ፣ ስዋሰዋዊ እና ቁማዊን ትርጉም ምን እንደሆነ ከሥሩ ማጥናት እጅጉን ያስፈልጋል።
ማጠቃለያ
በመጨረሻም አንድ ሰው ለምን ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር መተዋወቁ ለሕይወቱ ምን ይጠቅመዋል? ያለ እንደሆነ
አንደኛ፦ ኢየሱስ አምላኩና ጌታው እንደሆነ እንደሞተ እና በሦስተኛው ቀን ከሙታን እንደተነሳ ያምናል።
ሁለተኛ፦ ክርስቶስ በከፈለው የቤዛነት ሥራ በኩል ብቻ የዘላለም ሕይወት አለህ ስለሚለው ነው።
ሦስተኛ ፦ ሰው በሕግ ሥራ ፈጽሞ ሊጸድቅ ስለማይችል፣ በዚህም የተከፈለለትን የእዳ ክፍያ በክርስቶስ አምኖ ተስፋውንም በአለቱ ላይ ስለሚተክል ነው።(ሐዋ 4፥12)
ስለዚህ አሁን ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ያልተዋወቃችሁ ወገኖች ይህንን ታላቅ መጽሐፍ አግኝታችሁ ታነቡት ዘንድ እናበረታታችኋለን። በቃሉ ውስጥ የተገለጠውን እግዚአብሔርን ፊት ለፊት የምናይበት ሕያው መስታወት ቅዱስ ቃሉ ብቻ በመሆኑ በውጤቱ ክርስቶስ ኢየሱስን በማመን የሚገኘውን የዘላለምን ሕይወት እንደምታገኙ ባለ ሙሉ ተስፋዎች ነን፡፡



Good, appreciate it 😊
Glad to hear that, appreciate you too!
Bible matinat efeligalehu abreyachihu
ትንሽ ለመመለስ ብንዘገይም ምናልባት በደንብ ከእኛ ጋር ለመገናኘት የቴሌግራም አድራሻችንን ተጠቀሚ። ሰሞኑን እንለቃለን የምናጠናበትን ጊዜ እዛው ታገኚዋለሽ። ከዌብሳይቱ ነበር የመጣሁት ብለሽ በዚህ፦ https://t.me/Yeshua_Apologetics_Ministry ጻፊልን።
ስለ አስተያየሽ እናመሰግናለን።