“በእግዚአብሔር ሃይማኖት ውስጥ የሰው አእምሮ የፈለሰፈው አምልኮ፣ ማክበር ወይም አገልግሎት ሁሉ ያለ እግዚአብሔር ግልጽ ትዕዛዝ ከሆነ ጣዖት አምልኮ ነው።”[1]
የዚህን ታላቅ ፕሮቴስታንት ሐዳሲ ንግግር ያስተዋለ የትኛውም በፕሮቴስታንት ጥላ ውስጥ ያለ ሰው በቀጣይ ሚያስተውለው ወንጌላዊያን አብያተክርስቲያናት የገቡበትን ችግር ታሪካዊነቱ ቀርቶ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆነ የአምልኮ ስርአት ችግር ነው።[ይህ ችግር በተለያዩ ቦታዎች የሚደረጉ ቅጥ ያጣ ፈንጠዝያን ጨምሮ የሚያካትት ነው።]
ይህን ችግር ግን በታሪካዊው ወይም በክላሲካል ፕሮቴስታንት መነጽር ስናየው የቀድሞው መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ባለው በቤተክርስቲያናዊ አስተምህሮ የበለጠገ አምልኮ እንዲሁም ለእነዚህ ቅጥ ላጡ አካላት እጅግ የታመነ የእምነት አቋም እንዳለው ቢታወቅም ልንክድ ማንችለው እውነት ግን ወንጌላዊያን አብያተክርስቲያናት ውስጥ ሚታየው ስረአት አልባ የአምልኮ ስርአት አግባብ ያልሆነ ብቻ ሳይሆን እጅግ ስህተት የሆነ ልምምድ መሆኑን ነው።(መታረምና መታየት ያለበት መሆኑን ይህ ጽሑፍ አጥብቆ ይናገራል)
እንዲያው የዚህን ጉዳይ ጉድለት ትኩረት ሰጥተን ብንመለከተው ችግር ሆኖ ምናገኘው የእውነት ጉድለት ሳይሆን፥ ለድህረ ዘመናዊነት እጅግ የተጋለጥን መሆናችን፣ ቃሉን ሳይረዱት “ሃይማኖት አያድንም” የሚሉና የአስተምህሮን አስፈላጊነት የጣሉ ሰባኪያንና መምህራንን በተሃድሶው ክርስቲያን ማህበረሰብ ዘንድ ምስባክ ላይ ማቅረባችን፤ ይህንንም ተከትሎ አጥንትን ከመጋጥ ይልቅ ወተት መጋትን የሚወድ፣ በእምነቱ በቆየበት ልክ እውቀትንና ብስለትን ያጣ ምእመን ማፍራታችን ለዚህም የልጆች ፈንጠዝያ ሥርአተ አምልኮ መፍያና ማሟያ እንዲሆኑ ጆሮአችንን ለማከክ የፈቀዱን ሰዎች መሪዎችና እረኞች እንዲሁም መጋቢያን ዝም ማለታቸው ነው።(አጥብቀው የሚቃወሙና አጥብቀው የሚገስጹ እንዳሉ መዘንጋት የለብንም)
መፍትሔ፦
መፍትሔው ሐዳሲያኑ የቆሙበትንና እኛም የተነሳንበትን እውነት አለመጣል ነው። ምክንያቱም ጌታን ለምን እንደተከተልነው እናውቅ ዘንድ ይገባናልና። ስለዚህ እውነትን በሙላት ልንካፈል እንጂ እምነትን አስታከን ለወደቀው አዳማዊ ማንነታችን ነፃነትን በመስጠት አለማዊነትን ልንለማመድ አይደለም።
መሰረታችና አስተምህሮአችን የሆነው
“የእግዚአብሔር ቃል ብቻ” “የእምነት መግለጫችንም” ብቻ ሳይሆኑ ምስባኮቻችንን፣ ልምምዶቻችንንና አምልኮአችንን የቆምንበት እውነት ሊገልጹ ይገባል። የዚህ ችግር ጉዳት “ውሃ ሲወስድ እያሳሳቀ ነው” እንዲሉ አበው እንደ ምእራባዊያን ሳይታወቀን ቀስ እያልን ለዘብተኞች እንዳንሆን።
ወንድምና እህት ክርስቲያኖች ሁላችን ለምን እንደተጠራን ካወቅን እንግዲህ እንንቃ። ከራሳችን፣ ከቤተክርስቲያን ጣዕመ ዜማ ካለው አምልኮ፣ ከቅዱሳን ስብስብ(ማህበር) አስበልጠን የተሸከምነውን አለማዊነትንና ለአለማዊነት ያዘመመን ለዘብተኛ ክርስትናን ፈፅመን እናስወግድ፥ ማን እንደሆንን እናውቃለንና።
➠ የተሐድሶአችን ጥሪ ወደቀደመው እምነት እንመለስ እንደሆነ ሁሉ፥[2]
➠ እንደ ቀድሞው የአምልኮአችንን ማእከል፥ ቅዱሳት ምስጢራትንና የእግዚአብሔርን ቃል መሠረታችን እናድርግ።
➠ ሥላሴያዊ የሆኑ መዝሙሮችና ስብከቶች ስርአትና ልምምድ ይሁኑልን፥
➠ እንደ እምነታችን እንዘምር፣ እንስበክ፣ እናስተምር።
ይህ ሁሉ ሲሆን በመንፈስ ቅዱስ ሃይል፥ በልጁም በክርስቶስ ኢየሱስ በኩል ለእግዚአብሔር አብ ክብር ይሆን ዘንድ። ቅዱስ ባስሊዮስ ዘቄሳርያ በእንተ መንፈስ ቅዱስ መጽሐፉ ላይ፦
"…ቤተ ክርስቲያን የጠበቀችው ሐይማኖት በሐዋርያት የተላለፈውን ነው፣ የተቀበልነው እንዳናጠፋ ከአባቶች እምነት ጋር ጸንተን እንኑር !.."
በማለት የተሐድሶ አበው እንዳስቀመጡት ባስልዮስ ያስቅምጠዋል። ታዲያ ቤተክርስቲያን ከዚህች ወጥመድ ታመልጥ ዘንድ የተሐድሶውን ወቅት በማየት መነጽራችንን ወደ ቀደመው አምልኮዎቻን እንመለስ ስንል ይህን ጽሑፍ እንቋጫለን።
በአሚነ ሥላሴ ያጽናን። አሜን!
ማጣቀሻ
[1] The first book of discipline, Volume 3 page 34
[2] ተሐድሶ ማለት አዲስ ክርስትና መመሥረትና መቀጠል አይደለም። ይልቅ ወደ ቀደመው ውብ ክርስትና ቃሉ ብቻ የበላይ ወደ ሆነባት ክርስትና እንመለስ እንጂ።