የኒቂያ ጉባኤ እና ጥንታዊያን አበው

ለሙስሊም ሰባክያን ሙግት ምላሽ

ሰሞኑን በሙስሊሞች ዘንድ በማህበራዊ ሚዲያ ሲሰራጩ ከነበሩ ሙግቶች መካከል አንዱ ተከታዩ አንድ ሙስሊም የጻፈው ጽሑፍ ነው። የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ የዕውቀቱ ልክ በጽሑፎቹ ውስጥ የሚታየው ከሆነ ራሱን የማስተማር ብቃት እንዳለው ሰው በመቁጠር ለመጻፍ መድፈሩ፤ አንባቢያኑም ደግሞ ይህንን ሙግት ከቁም ነገር ቆጥረው መቀበላቸው የሚያሳዝን ነው። ሙግቱም እንዲህ ሲል ይጀምራል፦

አብዱል

በአሏህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡ 112፥3 «አልወለደም አልተወለደምም»፡፡ ጥንት ላይ የነበሩ ነቢያት እንዲሁ ኢየሱስ እና ሐዋርያት አሓዳዊያን”Unitarian” የነበሩ ሲሆን ከሐዋርያት ኅልፈት በኃላ የተነሱ የቤተክርስቲያን አበው ደግሞ በሂደት “ክልዔታውያን”Binitarian” ነበሩ። ከክልዔታውያን አበው መካከል ጠርጡሊያኖስ”Tertullian” ስለ ወልድ ሲናገር እንዲህ ይለናል፦ “አብ አጠቃላይ ባሕርይ ነው፥ ነገር ግን ወልድ የአጠቃላዩ መገኘት እና ክፍል ነው” (Against Praxeas (Tertullian), Chapter 9)

መልስ

የብሉይ ኪዳንን ቅዱሳት መጽሐፍት ስንመለከት እግዚአብሔር አምላክ ነጠላ አንድ ነበረ ማለት አንችልም። ለዚህም ማሳያ መጽሐፍ ቅዱስ በዘፍጥረት 1፥26 እንዲህ ይላልና፦ “እግዚአብሔርም አለ፦ ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር፤ የባሕር ዓሦችንና የሰማይ ወፎችን፥ እንስሳትንና ምድርን ሁሉ፥ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ይግዙ።” የእግዚአብሔርን ሥሉስ አሓዳዊነት ከሚያመለክቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች መካከል አንዱ ከላይ ያነበብነው ጥቅስ ነው። እግዚአብሔር አብ ዓለማትን በልጁ መፍጠሩን (ዕብ1፥2፤ ዮሐ1፥3፤ ቆላ1፥16-17) እንዲሁም ደግሞ ፍጥረትን በማስገኘት ሒደት ውስጥ መንፈስ ቅዱስ ጉልሕ አስተዋጽኦ እንደነበረው ቅዱሳት መጻሕፍት አበክረው ይነግሩናል (ዘፍ 1፥3 ፤ ኢዮ33፥4)። በዘፍጥረት 1፥26 ላይም በብዙ ቁጥር ግስ “እንፍጠር” (נַעֲשֶׂה “ናዓሴህ”)፣ በብዙ ቁጥር ስሞች “በመልካችን” (בְּצַלְמֵ֖נוּ “ቤጻልሜኑ”) እንዲሁም “ምሳሌአችን” ( כִּדְמוּתֵנוּ ”ኪድሙቴኑ”) ማለቱ አሐዱ ሥሉስን እንደሚያመለክት በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑራን የሚስማሙበት እውነታ ነው፡፡ በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ በገጻችን የጻፍነው ጽሑፍ መመልከት ይቻላል።[1] ይህ ሙስሊም ጸሐፊ ቀጠል አድርጎ የቤተክርስቲያን አበው ሥላሴያውን አልነበሩም ብሎ በድፍረት ይናገራል። ነገር ግን ይህ ፍጹም ሐሰት እና ቅጥፈት ነው። ይባስ ብሎ ጠርጡሊያኖስንም ጨምሮ የጥንት ቤተክርስቲያን አባቶች “Binitarian” ናቸው ይለናል። በዚህ ንግግሩ ጸሐፊው የቤተክርስቲያን ታሪክ እውቀት የለውም ወይም ደግሞ ሆነ ብሎ አንባቢያኑን እየዋሸ ነው ማለት ነው። ሙስሊሙ ወገናችን ላነሳው ሀሳብ ምላሽ ከመስጠታችን በፊት በትምህርተ ሥላሴ ላይ የቤተ-ክርስቲያን አበው የነበራቸው አቋም ጥርት ያለ እንደነበር እስኪ በጥቂቱ እንመልከት፦

1) ፖሊካርፕ (Polycarp):- በ70ዓ.ም ተወልዶ በ155 ዓ.ም ወይም በ160 ዓ.ም የሞተ፣ የሐዋሪያው ዮሐንስ ደቀ መዝሙር የነበረ ሲሆን የሰምርኔስ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ የነበረ ሰው ነው። ትምህርተ ሥላሴን በተመለከተ እንዲህ ይላል፦

ሁሉን ቻይ እግዚአብሔር ሆይ…ዘላለማዊና ሰማያዊ በሆነ ሊቀ ካህናት፣ በምትወደውና ባከበርኸው ልጅህ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ለአንተና ለእርሱም እንዲሁም ለመንፈስ ቅዱስ አሁንም ሆነ ለዘላለም ክብር ይሁን[2]

2) ዮስጢኖስ ሰማዕት(Justin Martyr) ፦ በቤተክርስቲያን የእምነት ተሟጋችና አቃቤ እምነት የነበረው ይህ አባት በ100 ዓ.ም ተወልዶ በ165 ዓ.ም እንደሞተ ይገመታል። ይህ አባት በአቅብተ እምነት ጽሑፉ ላይ ትምህርተ ሥላሴን በተመለከተ እንዲህ በማለት ጽፏል፦

የዓለማት ጌታ በሆነው በእግዚአብሔር አብ፣ በመድሐኒታችንም ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲሁም በመንፈስ ቅዱስ ስም በውሃ መታጠብን ያገኛሉ።[3]

3) አግናጢዮስ ዘአንጾኪያ(Ignatius of Antioch) ፦ የአንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ የነበረና ከ98 ዓ.ም እስከ 117 ዓ.ም መካከል ሰማዕት እንደሆነ የሚነገርለት አባት ክርስትናን ከመናፍቃን በመከላከሉ ዙሪያ ብዙ የጻፈ ዐቃቤ ክርስትና ነው። ትምህርተ ሥላሴን በተመለከተ እንዲህ በማለት ጽፏል፦

በጌታችንና በሐዋርያት ትምህርት እድትጸኑ፣ የምታደርጉት ነገር ሁሉ በስጋና በመንፈስ እንዲከናወንላችሁ፣ በእምነትና በፍቅር፤ በወልድ፣ በአብና በመንፈስ ቅዱስ፣ በመጀመሪያው እና በመጨረሻው፤ ከተወደደው ጳጳሳችሁ፣ በጎ ከሆነው የሽማግሌአችሁ መንፈሳዊ አክሊል፣  እናም እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ካሉ ዲያቆናት ጋር አጥኑ። በስጋችሁም በመንፈሳችሁም አንድነት እንዲኖራችሁ ክርስቶስ ኢየሱስ ለአብ በስጋው እንደተገዛለት፣ ሐዋርያት ለክርስቶስ ለአብ እና ለመንፈስ ቅዱስ እንደተገዙ፣ እናንተም ለጳጳሳችሁ እና እርስ በእርሳችሁ ተገዙ(ታዘዙ)። [4]

4) ጠርጡሊያኖስ ወይም ተርቱሊያን (Tertullian 160-215) አፍሪካዊ ዕቃቤ ክርስትና እንዲሁም የነገረ መለኮት ሊቅ ነው። የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን አባት የሆነው ጠርጡሊያኖስ በሥላሴያዊ አስተምህሮ ላይ ለሚነሱ ኑፋቄዎች መልስ በመስጠትና በክርስቲያናዊ ሥነ-መለኮት ከሚሰሩ አቃብያነ አባቶች መካከል አንዱ ነው። ለምሳሌ በመናፍቃን ሙግት ላይ ባነሳው በፕራክሲየስ (against praxeas) የሞዳሊዝም አራማጅ የሆነው የፓትሪፓሺያን(Patripassian) ሐሳብ አንስቶ እንዲህ ሲል በሙግቱ ላይ ጽፏል፡-

ሶስቱ አብ፣ ወልድና መንፈሱ ናቸው። ሶስት ናቸው። ነገር ግን በሁናቴ አይደለም በግብር እንጂ፤ በኑባሬም አይደለም በአካል እንጂ፤ በስልጣን ወይም በሐይል አይደለም በገጽታ እንጂ ሆኖም ግን እግዚአብሔር አምላክ አንድ ኑባሬ፣ ስልጣን፣ ሐይል አለው ምክንያቱም በአካል፣ በግብርና በአይነት በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ የተገለጠ አንድ አምላክ ነውና..[5]

እንግዲህ ጠርጡሊያኖስ እና ሌሎች በርካታ አበው አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ ከዘላለም ያለመሽቀዳደም እንዲሁም ያለመነጣጠል አሐዱ ሥሉስ እንደነበሩ ይነግሩናል። እንደ ሮሙ ቀለሜንጦስ(30-95)፣ ሔሬኒየስ (115-190) እና ቀጰዶቃውያን አበው (Cappadocian Fathers) ያሉ የቂሳርያው ትልቁ አባት ባስልዮስ፣ ጎርጎርዮስ ዘንዚናዙ፣ ጎርጎሪዮስ ዘኑሲስ እንዲሁም ሌሎች የቤተክርስቲያን አባቶች እንዘርዝር ብንል ትምህርተ ሥላሴን በተመለከተ በድርሳናቸው የጻፉትን እልፍ መረጃ እናገኛለን። ስለዚህ ሙስሊሙ ጸሐፊ “የቤተክርስቲያን አባቶች ስለ ሥላሴ ግንዛቤ የላቸውም ይልቅ አብና ወልድን ብቻ ጠቅሰው መንፈስ ቅዱስ ህልውና የለውም ብለዋል” በማለት “ክልዔታውያን “Binitarian” ነበሩ” በማለት በጽሑፉ ያሰፈረው ፈጽሞ ከእውነት የራቀ ነው። ይህን መሠል ሙግት ደሞ ከላይ ባስቀመጥናቸው የአባቶች ትምህርት ውድቅ ይሆናል። በመቀጠል ይህ ሙስሊም ጸሐፊ ሙግቴን ይደግፋል በማለት የአርዮሳውያንን ሙግት በመውሰድ ለመሞገት ሲጣደፍ ይስተዋላል። ሙስሊሙ ጸሐፊ ይህንን ሀሳቡን ለመደገፍ የጠቀሰው የጠርጡሊያኖስ ሥራ ከሆነው “Against Praxeas” ከተሰኘው ጽሁፍ ነው። ይህ አባት በጽሑፉም ሆነ በቃል የሥላሴን ትምህርት እውነተኝነት እየተሟገተ እና የሞዳሊዝምን (አብ፣ ወልድ እና መንፈስ አንድ ነጠላ አካል ነው ለሚሉ) ትምህርት አቀንቃኝ መናፍቃን እየሞገተ የጻፈው ጽሁፍ ነው። በዚህ ዐውደ-ጽሑፍ ጠርጡሊያኖስ የሚከራከረው በሦስት አካል ስለተገለጠው አንዱ መለኮት ነው።

በምዕራፍ 9 ሙሉ አውዱ እንዲህ ሲል ይጽፋል፦

“Bear always in mind that this is the rule of faith which I profess; by it, I testify that the Father, and the Son, and the Spirit are inseparable from each other, and so will you know in what sense this is said. Now, observe, my assertion is that the Father is one, and the Son one, and the Spirit one, and that They are distinct from Each Other. This statement is taken in a wrong sense by every uneducated as well as every perversely disposed person, as if it predicated a diversity, in such a sense as to imply a separation among the Father, and the Son, and the Spirit.”

“እኔ የምመሰክረው የእምነት መርህ ይህ መሆኑን ልብ በሉ። በዚህም አብ፣  ወልድና መንፈስም የማይነጣጠሉ እንደ ሆኑ እመሰክራለሁ። ነገር ግን በምን መንገድ ይህ እንደሚባል አስተውሉ።  እንግዲህ የኔ ሙግት “አብ አንድ እንደ ሆነ፣ ወልድም አንድ እንደሆነ፣ መንፈስም አንድ እንደ ሆነ፤ ነገር ግን እርስ በርሳቸውም ልዩ (distinct) እንደ ሆኑ ነው። ይሄም አገላለጽ ባልተማረ ሁሉ እንዲሁም ጠማማ አስተሳሰብ ባላቸው ሰዎች ሁሉ በተሳሳተ መንገድ ይወሰዳል። በአካላቱ[በአብ፣ በወልድ እና በመንፈስ] መካከል መለያየትን እንዳለብ በሚያመለክት መልኩ ብሎም በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ መካከል  መነጣጠል እንዳለ በማሳየት አጣምመው ይተረጉማሉ።[6]

ሙስሊሙ ጸሐፊም ከላይ ጠቅሶ የጻፈው በዚህ ምዕራፍ ውስጥ የተጠቀሰ ሲሆን። ከአውዱ ውጭ ገንጥሎ በማውጣት ለአንባቢያኑ ጽፎላቸዋል። የጠርጡሊያኖስ ጽሁፍ እንዲህ ይነበባል፦

“Thus the Father is distinct from the Son, being greater than the Son, in as much as He who begets is one, and He who is begotten is another; He, too, who sends is one, and He who is sent is another; and He, again, who makes is one, and He through whom the thing is made is another……..Lord Himself employs this expression of the person of the Paraclete, so as to signify not a division or severance, but a disposition, of mutual relations in the Godhead.”

የወለደው ሌላ፤ የተወለደም ሌላ ነው፤ የላከው ሌላ፣ የተላከውም ሌላ፣ ደግሞም  የሚሠራው ሌላ፣ ነገር ሁሉ የተፈጠረበት ሌላ እንደሚሆን እንዲሁ አብ ከወልድ ልዩ ነውና ከወልድ የሚበልጥ ነው።  ጌታ ራሱ ስለ ጰራቅሊጦስ አካል ሲገልፅ ይህንን አገላለጽ ተጠቅሟል። ይህም መለያየትን ወይም መነጠልን ሳይሆን በመለኮት ህላዌ ውስጥ ያለውን የእርስ በእርስ ግንኙነት ለማመልከት ነው።[7]

እንግዲህ ጠርጡሊያኖስ ወልድን “የተፈጠረ” ብሎ ላለመጥራት በጽሑፉ ላይ ጥንቃቄ እንደሚያደርግ ልብ ማለቱ አስፈላጊ ነው። “አብ ከወልድ የተለየ አካል” የሚለውን አነጋገር ጠርጡሊያኖስ ደጋግሞ ሲጠቀም ontological subordination (ኑባሬያዊ እንሰት ወይም ማነስ) በሚገልጽ መልኩ ሳይሆን “በመለኮት ውስጥ ያለውን የእርስ በርስ ግንኙነትና የአካል ሦስትነት” በሚያሳይ መልኩ ነው። በቀላል አነጋገር የጠርጡሊያኖስ ሐሳብ ሥላሴ በአካል ሦስት ሆነው መስተጋብራዊ ግንኑነት እንዳላቸው ማሳየት ነው። ይህም ለአብ የአባትነትን ግብር ክርስቶስን ከመላኩ ጋር በማያያዝ ነው። ይህም ክርስቶስ ለአብ በግብራዊ እንሰት(functional subordination) ነው። ለዚህም ነው ጠርጡሊያኖስ በጽሑፉ ላይ አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ ሦስት አካላት መሆናቸውን አጽንኦት በመስጠት የጋራ ግብራቸውንም በመለየት ጽፎ የሞዳሊዝም አቀንቃኝ ለሆነው ምላሹን የሚያስቀምጠው። ይህንን ሥላሴዊ ትምህርት ስለሚያምን ነው ጠርጡሊያን፦ “እኔ የምመሰክረው የእምነት መርህ ይህ መሆኑን ልብ በሉ። በዚህም አብ፣  ወልድና መንፈስም የማይነጣጠሉ እንደ ሆኑ እመሰክራለሁ።” በማለት የተናገረው። በዚህም ጠርጡሊያን ነጠላዊ እምነት ያለው አባት አለመሆኑን በዚህ እናውቃለን። የጠርጡሊያኖስ ጽሑፍ ሐሳብ ይህ ሆኖ ሳለ ግን ይህ ሙስሊም ጸሐፊ ከድህረገጾች የተቃረሙ ጽሑፎችን በማስነበብ ጠርጡሊያኖስ ሥላሴያዊ አይደለም ብሎ ለመሞገት ይዳዳዋል። አብዱል እንዲህ ሲል ይቀጥላል፦

አብዱል

አንድ ሰው ሰውነቱ ከራሱ ጋር ኖሮ ኖሮ ልክ ሲወልድ አባት እንደሚባለው አንድ አምላክ አምላክነቱ ከራሱ ጋር ኖሮ ኖሮ ልክ ሲወልድ አብ ተባለ የሚል ትምህርት ያስተማረው ጠርጡሊያኖስ ዘካርቴጅ ነው፦ ምክንያቱም አምላክ እንዲሁ አብ ነው፥ እንዲሁ ደግሞ እርሱ ፈራጅ ነው። ሁልጊዜም አምላክ በሆነው መሠረት ላይ ብቻ እርሱ ግን ሁልጊዜ አብ እና ፈራጅ አልነበረም፥ ከወልድ በፊት አብ ሊሆን አይችልም፤ እንዲሁ ከኃጢአት በፊት ፈራጅ  ሊሆን አይችልም። ነገር ግን በእርሱ ዘንድ ኃጢአት ባልነበረበት እና እንዲሁ ወልድ ባልነበረበት ወቅት ጊዜ ነበር፥ የመጀመሪያው ጌታ ፈራጅ ሆኖ እና የኃለኛ አብ ሆኖ መመሥረት ነበር። በዚህ መንገድ እርሱ ጌታ ሊሆን ከነበረባቸው ነገሮች በፊት ጌታ አልነበረም፥ ነገር ግን እርሱ ግን ወደፊት በሆነ ጊዜ ብቻ ጌታ ሊሆን ነበር። ልክ እንደዚሁ እርሱ በወልድ አብ እንደ ሆነ በኃጢአትም ፈራጅ ሆነ። Against Hermogenes(Tertullian) chapter 3

ተመልከቱ! አብ ያለ አባትነት ከፍጥረት በፊት ወልድን እስከሚወልድበት ጊዜ ብቻውን በአምላክነት ነበር የሚለው እሳቤ የጠርጡሊያኖስ እሳቤ ነው፦ ከፍጥረት በፊት እስከ ወልድ ውልደት ነበረ፥ ከሁሉ ነገር በፊት አምላክ ብቻውን ነበረ።Against Praxeas (Tertullian) Chapter 5

መልስ

በድጋሚ ሙስሊሙ ጸሐፊ “የጠርጡሊያኖስ ሐሳብ” ብሎ በጽሑፉ ላይ ያስቀመጠው ሁለተኛው ጥቅስ “ወልድ የማይኖርበት ጊዜ ነበር። ከሁሉም ነገር በፊት እግዚአብሔር ብቻውን ነበር” የሚለው ነው። ይህን ከላይ ሙስሊሙ ያስቀመጠውን ሙግት በምንመረምርበት ጊዜ  ከሁለት የተለያዩ የጠርጡሊያኖስ ጽሑፎች የተወጣጡ እና በተለያዩ አውዶች የተነገሩ ሀሳቦችን ያለ አግባብ በማጣመር የተቀመጠ ሀሳብ እንደሆነ እንረዳለን።  ጠርጡሊያኖስ “ወልድ ያልነበረበት ጊዜ ነበር” ብሎ ቃል በቃል ባይናገርም “Against Hermogenes” በተሰኘው ስራው ላይ “ቁስ ከእግዚአብሔር ጋር አብሮ የሚኖር፣ ዘላለማዊ እና ያልተፈጠረ ነው” የሚለውን መምህር ለመቃወም በሰራው ሥራ እንደዚያ የሚመስል ንግግር ነገር ተናግሯል። ጠርጠሉያኖስ በምዕራፍ 3 ላይ ሄርሞጌኔስ “እግዚአብሔር ዘላለማዊ ጌታ እንዲሆን እርሱ ጌታ የሚሆንበት ነገር ከዘላለም መኖር አለበት። ስለዚህ ቢያንስ በእግዚአብሔር ዘንድ ዘላለማዊ የሆነ አንድ ነገር መኖር አለበት። ይህ ነገር ቁስ ነው።” የሚለውን አስተምህሮ ይሞግታል። ጠርጡሊያኖስ ግን አብዛኞቹ የእግዚአብሔር የማዕረግ ስሞች ከፍጥረት በኋላ ካለው ሁኔታ ጋር የተያያዙ እንጂ ከዚያ በፊት አይደሉም በማለት ይህን የሄርሞጌኔስ ሀሳብ አጥብቆ ይቃወማል።  ሐሳቡንም እንዲህ በማለት ያቀርባል፦

“For from the moment when those things began to exist, over which the power of a Lord was to act, God, by the accession of that power, both became Lord and received the name thereof. Because God is in like manner a Father, and He is also a Judge; but He has not always been Father and Judge, merely on the ground of His having always been God. For He could not have been the Father previous to the Son, nor a Judge previous to sin. There was, however, a time when neither sin existed with Him, nor the Son; the former of which was to constitute the Lord a Judge, and the latter a Father.”

የጌታ ኃይል የተገለጠባቸው ነገሮች ሕላዌ ካገኙበት ጊዜ ጀምሮ እግዚአብሔር፣ በእነዚያ ነገሮች ላይ ኃይሉን ለመጠቀም እድል በማግኘቱ፣ በእነርሱ ላይ ጌታ ሆነና በዚያም ማዕረግ ታወቀ። ምክንያቱም እግዚአብሔር በዚያ መንገድ አባት ነው፤ ልክ እንደዚያው ደግሞ ፈራጅ ነው፤ ነገር ግን ሁሌም አምላክ ሆኖ በተገለጠበት ሁኔታ አባትና ፈራጅ አልነበረም። ከወልድ በፊት አባት ወይም ከኃጢአት በፊት ፈራጅ ሊሆን አይችልም ነበርና። ይሁን እንጂ ከእርሱ ጋር ኃጢአትም ሆነ ወልድ ባልነበሩበት ዘመን፤ የፊተኛው ጌታን ፈራጅ፣ የኋለኛው ደግሞ አባት ያደርገው ነበር።[8]

እርግጥ የጠርጡሊያኖስ ኪታብ ከላይ የተቀመጠው ሐሳብ ይህ ብቻ ቢሆን ኖሮ፣ የሥላሴ ሁለተኛ አካል የሆነው ወልድ በአንድ ወቅት ወደ ሕልውና እንደመጣ በእርግጠኝነት ያመነ ነበር ብለን በሚል ልንወስድ እንችል ነበር። ነገሩ ግን የተገላቢጦሽ ሆኖ የጠርጡሊያኖስ ሐሳብም ሆነ ነጥብ ወልድ ጅማሮ አለው የሚል አይደለም። ልክ እንደ ቀደመው ጥቅስ፣ ጠርጡሊያኖስ የሚናገረው በሥላሴ ውስጥ ስላሉት አካላት ግንኙነት ነው። የጠርጡሊያኖስን ጽሑፍ ስናነብ “አባት” እና “ልጅ” የሚሉትን የማዕረግ ስሞች ይመለከታቸው የነበረው የአምላክ እሳቤው “economy” ብሎ ከሚጠራውና በዛሬው ጊዜም የሃይማኖት ምሑራን ዘንድም “the economic Trinity” ብለው ከሚጠሩት አንጻር ነው። Economic Trinity አብ ወልድና መንፈስ ቅዱስ እርስ በእሳቸውና ከተቀረው አለም ጋር ያለቸውን ግንኙነት የሚመለከት ትምህርት ነው። ቃሉ ከግሪኩ Oikonomos ከሚለው ቃል የመጣ ሲሆን መስተጋብራዊ ግንኙነትን ያሳያል። እያንዳንዱ የሥላሴ አካል የራሱ ግብር ያለው ሲሆን ከተቀረው አለም ጋርም በግብር የተለያየ ግንኙነት አለው። አባት ልጁን ወደ ምድር ልኮታል፣ ልጁም በመታዘዝ የአባቱን ፈቃድ ለመፈጸም ተልኳል። አብና ወልድ ደሞ መንፈስ ቅዱስን ልከዋል። ነገር ግን ወልድ አብን አልላከም አብም አልተላከም፣ አብ አንድያ ልጅ ተብሎም አልተጠራም። መንፈስ ቅዱስም አብንና ወልድን አልላከም። ደግሞም አስቀድመው የወሰኑንና የመረጡንም ወልድና መንፈስ ቅዱስ አይደሉም። ይህንን የሚያሳየን Economic trinity ይባላል።

እግዚአብሔር ብቻውን ነበር?

“ከሁሉም ነገር በፊት እግዚአብሔር ብቻውን ነበር” የሚለው ሐረግ እንደገና የመጣው ከጠርጡሊያኖስ “Against Praxaes” ነው። በምዕራፍ 5 ላይ ሙሉ አውዱ እንዲህ ሲል ተጽፏል

“I am led to other arguments derived from God’s own dispensation, in which He existed before the creation of the world, up to the generation of the Son. For before all things God was alone—being in Himself and for Himself universe, and space, and all things. Moreover, He was alone, because there was nothing external to Him but Himself. Yet not even then was He alone; for He had with Him that which He possessed in Himself, that is to say, His own Reason. For God is rational, and Reason was first in Him, and so all things were from Himself. This Reason is His own Thought (or Consciousness) which the Greeks call λόγος, by which term we also designate Word or Discourse.”

አለም ከመፍጠሩ በፊት ወደ ነበረበት ከእግዚአብሔር ዘመን ጀምሮ እስከ ወልድ ትውልድ ድረስ ወደሚነሱት ሌሎች መከራከሪያ ነጥቦች አመራለሁ። ከሁሉም በፊት እግዚአብሔር ብቻውን ነበርና፤ እርሱም በራሱ ሕላዌ ይኖር ነበር። አጽናፈ ዓለሙን፣ ኅዋንና ሁሉንም ነገር ለራሱ ፈጥሯል። በተጨማሪም እርሱ ብቻውን ነበር፤ ምክንያቱም ከእርሱ በቀር ምንም ውጫዊ ነገር አልነበረም። ነገር ግን በዚያን ጊዜም ቢሆን እርሱ ብቻውን አልነበረም፣  ምክንያቱም እርሱ በራሱ ውስጥ ያሉት ከእርሱ ጋር ነበሩ። ለማብራራት ያህል የእርሱ አመክንዮን ማለቴ ነው። እግዚአብሔር ምክንያታዊ ነውና፣ አመክንዮ በመጀመሪያው በእርሱ ውስጥ ነበር። ሁሉም ነገር ደግሞ ከእርሱ ነበር። ግሪኮች ሎጎስ (λόγος) ብለው የሚጠሩት ይህ በእርሱ ህልውና ውስጥ ያለው አመክንዮ፤ በዚህ ምክንያት ቃል ወይም ምክንዮ ብለንም እንጠራዋለን።[9]

እንግዲህ ከዚህ ጽሑፍ የምንረዳው ነገር ጠርጡሊያኖስ ሙግቱን ከትንሽ ወደ ትልቅ በማድረግ ይዘልቃል። የእኛ ፍጽምና የጎደለው ሰብዓዊ አስተሳሰብ እና ንግግራችን እንኳን የእግዚአብሔር ቃል ተፈጥሮውን እንዴት ለዘላለም እንደሚጋራ የሚያሳይ ምስል ይሰጠናል። እንዲህ ሲል በመቀጠል ጽፏል፦

“Thus, in a certain sense, the word is a second person within you, through which in thinking you utter speech, and through which also, (by reciprocity of process,) in uttering speech you generate thought. The word is itself a different thing from yourself. Now how much more fully is all this transacted in God, whose image and likeness even you are regarded as being, in as much as He has reason within Himself even while He is silent, and involved in that Reason His Word! I may therefore without rashness first lay this down (as a fixed principle) that even then before the creation of the Universe God was not alone.”

ስለዚህ፣ በተወሰነ መልኩ፣ ይህ ቃል በውስጣችሁ ሁለተኛ አካል ነው። በእሱ አማካኝነት ያሰባችሁትን ንግግር ትናገራላችሁ። ደግሞም  በንግግር ሀሳብን ታመነጫላችሁ። ቃሉ ራሱ ከእናንተ የተለየ ነገር ነው። እንደ ማንነቱ በመልኩና በምሳሌው የተቆጥራችሁ እናንተ ጋር ያለው ይህ ባህርይ በእግዚአብሔር ዘንድ ምንኛ አብልጦ በሙላት የሚሰራ ነው፣ እርሱ ዝም ቢል እንኳን በራሱ ውስጥ በሙላት አመክንዮ አለው። በዚያም አመክንዮው ውስጥ ቃሉ ይካተታል። ስለዚህ ያለ ችኮላ አስቀድሜ እኔ ይህን (እንደ ቋሚ መርህ) አስቀምጣለሁ፦ ያኔ አጽናፈ ዓለም ከመፈጠሩ በፊት እንኳን እግዚአብሔር ብቻውን አልነበረም።[10]

እንግዲህ ይሄ ሙስሊም ሰባኪ የጠርጡሊያኖስን ሐሳብ በተሻንፈፈ ትርጉም ሄዶ የማይለውን ለማለት ሞክሯል። ነገር ግን ይህ አባት “ይሁን እንጂ ከእርሱ ጋር ኃጢአትም ሆነ ወልድ ባልነበሩበት ዘመን፤ የፊተኛው ጌታን ፈራጅ፣ የኋለኛው ደግሞ አባት ያደርገው ነበር” (There was, however, a time when neither sin existed with Him, nor the Son; the former of which was to constitute the Lord a Judge, and the latter a Father.) የሚለውን ሀሳብ የተጠቀመው በስሁት አወቃቀር ተተርጉሞ ለሐሰት የእስልምና ትምህርት እንዲውል ፈፅሞ አይደለም። አርዮሳውያን በተለምዶ “የይሖዋ ምስክሮች” የምንላቸው አካላት ይህንን ሃሳብ ቆንጽለው ወልድ የሌለበት በጊዜ (There was a time when son existed with Him) ነበር ይላሉ። ነገር ግን ይሄ አባት ሊል የፈለገው ወልድ በሌለበት ጊዜ እግዚአብሔር አምላክን አባት ያደርገው ነበር፣ ነገር ግን ከልጅ ወይም ከወልድ በፊት እግዚአብሔር አምላክን አባት ተብሎ ሊጠራ አይችልም (He could not have been the Father previous to the Son) ነው እያለ ያለው። ሐሳቡን አጠናክሮት ሲያቀርብ አብ አባት ያልተባለበት ጊዜ ከሌለ ወልድ ልጅ ያልተባለበት (ለዓይን ጥቅሻ ያህል እንኳ ያልነበረበት) ዘመን የለም የሚል ትርጓሜ የሚያስቀምጥ ነው። ይሄንንም ሀሳቡን ደሞ ሁሉም አበው ይቀበሉታል።

አብዱል

በሁለቱ ውዝግብ የመጀመሪያው ዓለም ዓቀፍ ሲኖዶስ በኒቂያ ተካሄደ፥ “ሲኖዶስ” σύνοδος ማለት “ጉባኤ” “ስብሰባ”council” ማለት ነው። ኒቂያ፣ ቆስጠንጢኒያ፣ ኤፌሶን እና ኬልቄዶን በጥንት ጊዜ ቱርክ ውስጥ የሚገኙ ከተሞች ናቸው። በ325 ድኅረ ልደት በንጉሥ ቆስጠንጢኖስ ሊቀ መንበርነት የኒቂያ ጉባኤ ላይ 318 ኤጲጵ ቆጶሳት ከመላው ዓለም ተሰብስበው “ሆሙኡሲዮስ” እና “ሆሞኡሲዮስ” የሚባሉ ክርክሮችን ለመታደም መጡ፥ “ሆሙኡሲዮስ” ὅμοιοιούσιος የአርዮስ አቋም ሲሆን “ሆሞኡሲዮስ” ὁμόιοιούσιος ደግሞ የአትናቴዎስ አቋም ነው። “ኡሲያ” οὐσία የሚለው ቃል “ኤይሚ” εἰμί ማለትም “ነኝ” ከሚል አያያዥ ግሥ የተገኘ ሲሆን “ህላዌ” “ሃልዎት” “ኑባሬ” የሚል ትርጉም አለው፥ “ሆሙስ” ὅμοιος ማለት “የተለያየ” ማለት ሲሆን “ሆሞስ” ὁμός ማለት ደግሞ “ተመሳሳይ” ማለት ነው።

፨አርዮስ፦ “ወልድ ፍጡር ነው፥ አንዱ አምላክ አብ እና ኢየሱስ “ሆሙኡሲዮስ” ὅμοιοιούσιος ማለትም “የተለያየ ህላዌ” እንጂ ተመሳሳይ አይደለም” በማለት ኢየሱስ “ሆሙኡሲዮን ቶ ፓትሪ” ὅμοούσιον τῷ Πατρί ማለት “ከአብ ጋር የተለያየ ህላዌ ነው” የሚል አቋም ነበረው።

፨አትናቴዎስ፦ “ወልድ ፍጡር አይደለም፥ አንዱ አምላክ አብ እና ኢየሱስ “ሆሞኡሲዮስ” ὁμόιοιούσιος ማለትም “ተመሳሳይ ህላዌ” እንጂ የተለያየ አይደለም” በማለት ኢየሱስ “ሆሞኡሲዮን ቶ ፓትሪ” ὁμόούσιον τῷ Πατρί ማለት “ከአብ ጋር ተመሳሳይ ህላዌ ነው” የሚል አቋም ነበረው።

መልስ

በመጀመሪያ ደረጃ ይሄ ሙስሊም ጸሐፊ ግሪክ እንደማይችል ከዚህ ቀደም ጽሑፎቻችን አስነብበን ነበር። ስህተት የማይሰለቸው አብዱል በጽሑፉ ላይ አርዮስ እና አትናቴዎስ የሚለያዩበትን ሁለት የግሪክ ፊደላት ኢዮታ እና ኦሚክሮን(ι,ο) ባለማወቁ ምክንያት ለአትናቴዎስም ለአርዮስም ὁμόιοιούσιος የሚለውን ተጠቅሟል ብሏል። ይሄ ደግሞ ፍጹም ስህተትና ይሄን ሙግት ያነሳው ተሟጋች አካል ምስራቅ ከምዕራብ እንደሚርቅ ከእውቀት የራቀ መሆኑን ያሳብቅበታል። ነገሩን ለአንባቢያን ግልጽ ለማድረግ ሆሙስዮን (ὁμοούσιον) የሚለው የግሪክ ቃል ሆሙስዮስ (ὁμοούσιος) ከሚለው ስርወ ቃል የመጣ ሲሆን፤ ሆሙስዮስ ማለት ሆሞ(ὁμο…)  አንድ ወይም እኩል ማለት ሲሆን “ኡስያ (οὐσία)” ደግሞ “ባህሪ(essence)” “ምንነት” ማለት ነው። በአጠቃላይ ሆሙስዮስ (ὁμοούσιος) የሚለው ቃል በባህሪ፣ በምንነትና በኑባሬ አንድ ወይም እኩል የሆነ ማለት ነው። ስለዚህ ሐዋርያዊ አበው በውሳኔያቸው ላይ የገለጹልን መግለጫ ወልድ ከአብ ጋር በባህሪ፣ በምንነትና በኑባሬ እኩል ወይም አንድ አይነት እንደሆነ ነው። አርዮስ በዚህ ሰዓት ምን ይል ይሆን? የሚለውን ስንጠይቅ እርሱና ተከታዮቹም በኒቂያው ጉባኤ በሌላ ጎን ሆነው ሆሙስዮስ (ὁμοούσιος) የሚለው ቃል በመቃወም “ወልድ ከአብ ጋር ተመሳሳይ ወይም ተቀራራቢ ማንነት በግሪኩ ሆሞዮስዮስ (ὁμοιούσιος) ነው” ብለው ከመጽሐፍ ቅዱሱና ከጉባኤው አፈነገጡ። የአርዮስ ወገን ሆሞዮስዮስ የሚለው የግሪክ ቃል “ሆሞዮስ (ὅμοιος)” “ተመሳሳይ” ወይም “ተቀራራቢ” ከሚለውና “ኡሲያ (οὐσία)” “ኑባሬ” ወይም “ባህሪ” ከሚሉት ጥምር ቃላቶች በማገናኘት ወልድ ከአብ ጋር በባህሪ፣ በምንነትና በኑባሬ ተመሳሳይ ወይም ተቀራራቢ ነው የሚል አቋም በማምጣት ቅዱሳት መጽሐፍትን ተቃርነው እንደ ቆሙ እንመለከታለን። መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ ከአብ ጋር እኵል ነው(ፊል2፥6) የባሕርይው ትክክለኛ ነጸብራቅ(ዕብ 1፥3) ነው ከማለቱ አንጻር (ሆሙስዮስ) ማለትም ከአብ ጋር እኵል ሥልጣን አለው የሚለው ቃል ይህንን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት የሚገልጽ ትምህርት ነውና የእነ አትናቴዎስ የእምነት መግለጫ ይህንን እውነት ያማከለ ነው። በዚህ አላበቃም ሙስሊሙ ጸሐፊ ይቀጥላል፦

አብዱል

ጉባኤው የማታ ማታ ኢየሱስ “ቴዎን ኤክ ቴዉ” Θεὸν ἐκ Θεοῦ ማለትም “ከአምላክ የተገኘ አምላክ ነው” በማለት አጸደቀ፥ “አምላክ አምላክን አህሎ እና መስሎ፣ ከባሕርይ ባሕርይ ወስዶ፣ ከአካል አካል ወስዶ ተወለደ” በማለት “ሆ ቴዎስ ሆ ሁዎስ” Ο Θεός ο γιος ማለትም “እግዚአብሔር ወልድ”God the Son” የሚል የአቋም መግለጫ ተሰጠ።  ከዚህ ጉባኤ ተነስተን ጥያቄ እናጭራለን፦

፨በኒቂያ ጉባኤ ድንጋጌ ላይ አምላክ አምላክን ከወለደ ሁለት አምላክ አይሆንም?

፨አምላክ አምላክን አስገኘ የሚለው ትምህርት ሕሊናስ ይቀበለዋልን?

፨ማስገኘት መንስኤ መገኘት ውጤት ከሆነ መቀዳደም ስላለ ጅማሮ እና መነሾ ያለው አምላክ ምን ዓይነት አምላክ ነው?

ይህ የነገረ ክርስቶስ”Christology” ውዝግብ ጠመዝማዛ መንገዱ የጀመረው ከዚህ ጉባኤ ጀምሮ ነው። አንብሮስ ዘሚለን “አብ የወልድ ኑባሬ ምንጭ እና ሥር ነው”ይለናል፦ “አብ የወልድ ኑባሬ ምንጭ እና ሥር ነው” Exposition of the Christian Faith (Ambrose) > Book IV(4) Chapter 10 Number 133

አብ አስገኚ ወልድ ግኝት ከሆነ በመስኤ እና በውጤት በመካከላቸው መቀዳደም አለ፥ ዛሬ ላይ ዐበይት ክርስቲያኖች፦ “ወልድ ከአብ ባሕርይ ባሕርይን ወስዶ፣ ከአካሉ አካልን ወስዶ እና አብን አህሎና መስሎ ከእርሱ ወጣ፣ ተወለደ፣ ተገኘ” በማለት አሏህን ወላዲ መሢሑን ተወላዲ በማድረግ ለአሏህ ቁራጭን አደረጉለት፦ 43፥15 ከባሮቹም ለእርሱ ቁራጭን ልጅ አደረጉለት፡፡ ሰው በእርግጥ ግልጽ ከሓዲ ነው፡፡ وَجَعَلُوا لَهُ مِنْ عِبَادِهِ جُزْءًا ۚ إِنَّ الْإِنسَانَ لَكَفُورٌ مُّبِينٌ

ከአንዱ አምላህ ባሕርይ ባሕርይን ወስዶ፣ ከአካሉ አካልን ወስዶ፣ እርሱን  አህሎና መስሎ ከእርሱ ወጣ፣ ተወለደ፣ ተገኘ ማለት የአምላክን አንድነት ክፉኛ የሚያናጋ ትምህርት ነው።

መልስ

ይህ ከስህተቶቹ የማይማር አብዱል የግሪኩን አነባብ በድጋሚ ተሳስቷል። “ο γιος”  ሆ ሁዎስ ተብሎ አይነበብም። እዚህ ጋር ለተነሳው ሙግት ከዚህ ቀደም ኢየሱስ የተደረገና የተገኘ አምላክ ነውን? በሚለው ልጥፋችን መልሰነው ነበር። በአጭሩ ለመመለስ ያህል በጉባኤው ውሳኔ ላይ የተገኘ እና የተፈጠረ ለሚለውን አጠር አድርገን እናሳይ፦

“ከብርሃን የተገኘ ብርሃን ከእውነተኛ አምላክ የተገኘ አምላክ በተፈጠረ ሳይሆን በተወለደ፥ ከአብ ጋር በመለኮት አንድ በሆነ (ὁμοούσιον τῷ Πατρί/ ሆሙስዮን ቶ ፓትሪ)” በሚለው አውደ ሐሳብ ላይ “በተገኘ” የሚለው ቃል ላይ አንደኛ ወልድ ፍጡር መሆኑን አያሳይም። ሁለተኛ ደግሞ ወልድ በሀልወቱ በሆነ ጊዜ የመጣ መሆኑን አያሳየንም። እነዚህን ሁለት ሐሳቦች ከማብራራቴ በፊት ግሪኩን ቃል በቃል እንመልከተው፦

“…τὸν ἐκ τοῦ Πατρὸς γεννηθέντα πρὸ πάντων τῶν αἰώνων, Φῶς ἐκ Φωτός, Θεὸν ἀληθινὸν ἐκ Θεοῦ ἀληθινοῦ, γεννηθέντα οὐ ποιηθέντα, ὁμοούσιον τῷ Πατρί…”

በዚህ አንቀጽ ላይ “Φῶς ፎስ (ብርሃን) ἐκ Φωτός, Θεὸν ἀληθινὸν ቴዎን አሌቲኖን (እውነተኛ አምላክ) ሲል፤ “ፎስ ኤክ ፎቶስ” በቀጥታ ስንተረጉመው “ከብርሃን ብርሃን” የሚል ፍቺ አለው። ይህም የሚገልጸው አብ ብርሃን እንደሆነ ሁሉ (1ዮሐ. 1:15፣ መዝ. 27:1) ወልድም ብርሃን ነው (ዮሐ. 8:12፣ 2ጢሞ. 6:13-16) ማለታቸው መሆኑን እናያለን። ቀጥለን ደሞ “Θεὸν ἀληθινὸν ἐκ Θεοῦ ἀληθινοῦ የሚለው አንቀጽ ደግሞ በቀጥታ ሲተረጎም “ከእውነተኛ አምላክ እውነተኛ አምላክ” ማለት ሲሆን፤ አብ እውነተኛ አምላክ እንደሆነ ሁሉ (ኤር.10፡10፣ ዮሐ. 17:3) ወልድም ደግሞ እውነተኛ አምላክ መሆኑን (1ዮሐ. 5:20፣ ራዕይ 6:10፣ 3:7) የሚያትት አንቀጸ ሐረግ ነው። ይህም በመሆኑ ለትርጉም እንዲመች “የተገኘ” የሚለው ቃል ገባ እንጂ ኢየሱስ ተፈጠረ ማለት አይደለም። ህጉም እንደዛ እንድንተረጉም አይፈቅድም። ከዚህ ቀጥሎ ደግሞ በስሁት መረዳት የሚወሰዱት ሁለት ሀሳቦች “የተወለደ” እና “የተፈጠረ” የሚሉ ቃላት ናቸው። በኒቂያው ጉባኤ ላይ አንድ ወሳኝ ነጥብ በትልቁ ተስሎ እናገኛለን። “በተፈጠረ ሳይሆን በተወለደ (γεννηθέντα οὐ ποιηθέντα)” በሚለው በዚህ አንቀጽ ላይ እንደ ቅድሙ ሁለት ወሳኝ ነጥቦችን ሰፋ አድርገን እንመልከት፦ በተፈጠረ “ፖዬቴንታ” (ποιηθέντα) የሚለውን እና “በተወለደ” ጌኔቴንታ (γεννηθέντα) የሚለው ወልድ ከአብ ተወለደ እንጂ አልተፈጠረም እያለ ነው። ፖዬቴንታ (ποιηθέντα) የሚለው የግሪክ ቃል መፈጠር ከሚለው ይልቅ መሰራት ወደ ሚለው ትርጉም ይቀርባል። ይሄ ማለት “ከእውነተኛ አምላክ በተገኘ እውነተኛ አምላክ” የሚለው አንቀጽ ውስጥ አምላክ አምላክን ሰራ(ፈጠረ) የሚል ስሑት ሐሳብ እና ትርጓሜ እንደ ሙስሊሙ ወዳጄ እንዳይመጣ ወልድ “የተሰራ” ፖዬቴንታ (ποιηθέντα) ሳይሆን “የተወለደ” ጌኔቴንታ (γεννηθέντα) መሆኑን በዛው አንቀጽ ላይ ተቀምጦና ተገልጾልን እንመለከታለን። ጌኔቴንታ (γεννηθέντα) የሚለው የግሪክ ቃል ጌናኦ (γεννάω) ወይም ጌኖስ (γένος) የሚለውን ይገልጻል። ጌናኦ (γεννάω) የሚለው ቃል ደግሞ መወለድን፣ ከአብራክ መውጣትንና ከአንድ አካል መገኘትን የሚያመላክት ትርጓሜ ሲኖረው ጌኖስ (γένος) የሚለው ቃል አብዝሃኛውን ጊዜ አይነትን፣ መደብንና ባህሪን የሚገልጽ ቃል ነው። ለምሳሌ እግዚአብሔር አምላክ በዘፍጥረት መጽሐፍ ላይ የምድር አራዊትን በሚፈጥርበት ጊዜ እንደ የባሕሪያቸው (ወገን፣ ዓይነት፣ ምድብ) አድርጎ ሲፈጥራቸው እንመለከታለን። “እግዚአብሔር የምድር አራዊትን እንደ ወገኑ “ጌኖስ” (γένος) አደረገ። እንስሳውንም እንደ ወገኑ “ጌኖስ” (γένος) ፤ የመሬት ተንቀሳቃሾችንም እንደ ወገኑ “ጌኖስ” (γένος) አደረገ እግዚአብሔር ያመልካም እንደሆነ አየ።” —ዘፍ 1፥25

ስለዚህ የአርዮስ መሳት እኛ ወልድ ከአብ ተወለደ ስንል በግሪኩ “ጌኖስ” (γένος) ማለታችን እንደሆነ አለማወቁ ነው። ይህ ማለት ወልድ ከአብ ጋር አንድ መደብና ባህርይ አለው ማለት እንጂ በጊዜ ውስጥ መኖር ጀመረ ማለት አይደለም። ስለዚህ ሙስሊም ወገኖቻችን እንዳነሱት ጥያቄ መሠረት ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጡር ሳይሆን ፈጣሪ ነው። ለዛም ነው አበው፦

እርሱ እግዚአብሔር ነውና ተገዥ ሆኖ ኖሮ ወደ እግዚአብሔርነት ክብር የደረሰ አይደለም። ከአብ ጋር በአንድ ትክክልነት ሳለ የተገዥ ባሕርይን ነሣ እንጂ መለኮት ሰው ሆኖ ኖሮ ኋላ ክብር ያገኘ አይደለም።[11]

የቃሉን መረዳት በሙላት ይግለጥልን አሜን።

ማጣቀሻዎች

1] www.ewnetlehulu.net/am/genesis-1-26/

2] Martyrdom of Polycarp, 14. ANF, I:42.

3] Justin, First Apology, LXI. ANF, I:183.

4] Epistle to the Magnesians, Chapter 13

5]  /Against Paraxeas 2/

6] The Ante-Nicene Fathers – Vol. 3 – Fourth Printing (Hendrickson Publishing, 2004) 603

7] The Ante-Nicene Fathers – Vol. 3 – Fourth Printing (Hendrickson Publishing, 2004) 604

8] The Ante-Nicene Fathers – Vol. 3 – Fourth Printing (Hendrickson Publishing, 2004) 478

9] The Ante-Nicene Fathers – Vol. 3 – Fourth Printing (Hendrickson Publishing, 2004) 600

10] The Ante-Nicene Fathers – Vol. 3 – Fourth Printing (Hendrickson Publishing, 2004) 601

11] ሃይማኖተ አበው ዘቄርሎስ ምዕ 72 ቍ 9

12] De Principiis, book 1, chapter 3 The Trinity according to Origen

13] Gregory Thaumaturgus, On the Trinity. ANF, VI:48

14] De Princ. 1.2.; PG 11.132

15] Alexander Roberts and James Donaldson, eds., The Ante-Nicene Fathers, Grand Rapids: Eerdmans, 1975 rpt., Vol. 4, p. 253, de Principiis, 1.111.4

16] Roberts and Donaldson, Ante-Nicene Fathers, Vol. 4, p. 255, de Principii., I. iii. 7

17] Irenaeus, Against Heresies X.1

18] https://carm.org/jehovahs-witnesses/tertullian-and-the-watchtower

ለሌሎች ያጋሩ

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top