በሰሞኑን በተነሳው በቻርሊ ከርክ ሕልፈት ምክንያት ሁለት ጽንፍ ጎራዎችን እንመለከታለን። አንዱ ጎራ በዚህ ሀሳቡ አልስማማውም ሲል ይኼኛው አይደለም እንዲያማ አይባልም በዚህ ሀሳቡ እጋራዋለሁ በማለት ሲወያዩ ስመለከት ነበር። በእርግጥ ቻርሊን በአንዳንድ ሀሳቦቹ ባልስማማም ነገር ግን በወጣቱ ዘንድ ያለውን ተጽዕኖ እና ወደ ኋላ ገሸሽ በማይለው አቋሙ ሁሌ የማደንቀው ሰው ነው። በሳልና አዕምሮውን የሚጠቀም፣ በልቡን የማያምንበት ከሆነ የማያደርግ ነበር። በኋላ በተለያዩ ገጾች የሚጻፉትንና ደጋግመው የሚመጡትን የተለያዩ ጽሑፎችና የምስል ቪዲዮዎችን ለመመልከት ሞክሬ ነበር። በእርሱም ህልፈት ምክንያት ብዙዎች ከኢ-አማንያን ወደ ክርስትና እንደመጡና ቤተክርስቲያንን ሥፍራ አጣን እስከማለት ደርሰው እንደተገኙ እንመለከታለን። ይኼንን ታሪክ ስመለከት በሞቱ ብዙዎችን መጥራቱን ሳስብ የማርቆስና የእስረኛው ታሪክ ጋር ከዚህ ቀደም ፊልጵስዩስን በማጠናበት ጊዜ ከጻፍኩት ጽሑፍ ጋር የቻርሊ ከርክ ታሪክ ተመሳሰለብኝ። የማርቆስ እና የእስረኛው ታሪክ በፊልጵስዩስ 1፥21 ላይ የተመሠረተ አፈ-ታሪክ ነው። ከታሪኩ በፊት ቃሉ እንዲህ ይነበባል፦
“ለእኔ ሕይወት ክርስቶስ፥ ሞትም ጥቅም ነውና።”
— ፊልጵስዩስ 1፥21
ማርቆስ በፊልጵስዩስ የሚኖር ወጣት ለእምነቱ ታጋይ ሰው ነበር። ማርቆስ በክርስትና ምክንያት ዘወትር በሮማውያን እና በቅርብ ወዳጆቹ መገለል ከዛም ታልፎ መከራ በገጠመው ቁጥር ኹል ጊዜ ወደ እስር ቤት ይሄዳል። በዛም እስር ቤት በእምነቱ ጽኑ የሚባለውን ጳውሎስን እንዲጎበኝ ይሄድ ነበር። የእስር ቤቱ ጨለማ ክፍል ሁልጊዜ ለማርቆስ አስጨናቂው መንገዱ ነበር፣ ነገር ግን ጳውሎስ በዚያ ውስጥ ሁልጊዜ ደስታ የተሞላበት ዓይን ነበረው። አንድ ምሽት ላይ እንደተለመደው ለጉብኝት በሚሄድበት ጊዜ ማርቆስ ስለ ጳውሎስ ከሚደርስበት መከራ መደሰት ምክንያቱ ምን እንደሆነ እንዲህ ሲል ጠየቀው፦
«ጳውሎስ፣ ነገ ሊገደሉህ ሲሆን እንዴት እንደዚህ ፊትህ ላይ ደስታ ይታያል? ሞትን አትፍራም?» ይለዋል ጳውሎስም ከትከሻው ላይ እጁን አሳረፈ እና እንዲህ አለ፦
«ማርቆስ፣ ከክርስቶስ ውጪ በዚህ ዓለም ሳለህ ጥሩ ሆነ መጥፎ የሚባል ነገር የለም። ለእኔ ሕይወት ክርስቶስ፥ ሞትም ጥቅም ነውና። ባለሁበት ዘመን ሁሉ ክርስቶስን እናገራለሁ፤ በዚህም የክርስቶስ አካል ፍጹማን ይሆኑ ዘንድ በመከራዬ ሁሉ አጽናናለሁ። በዚህስ ብሞት ግን፣ ከእርሱ ጋር እኖራለሁ። እኔ እንዴት እጎዳለሁ?» በማለት መለሰለት። ማርቆስ ተደነቀ። «እንግዲህ… በኑሮህም በሞትም ክርስቶስ ድሌ ነው የምትለኝ?» አለ።
ጳውሎስም፦ «አዎን። ይህች ዓለምን እንዳልመስል በደማስቆ መንገድ ላይ ሕይወትና አገልግሎትን ሰጥቶኛል። በዛም በተቀበልኩት ሕይወት ሞት ወደ እኔ ቢመጣ አልሰጋም ምክንያቱም የምቀምሰው ጽዋ ክርስቶስን ራሱን ይሰጠኛል። ስለዚህ አንዳችም አልሰጋም።» በማለት መለሰለት። እነዚህ ቃላት በእሥረኛ ጠያቂው በማርቆስ ልብ ውስጥ በጽኑ ጠነከሩ። ከብዙ ዓመታት በኋላ፣ በፊልጵስዩስ ላይ ስደትና መከራ በክርስቲያኖች ላይ መጣ። በዛም መከራ ውስጥ ማርቆስ የጳውሎስን ቃል በልቡ አሰበ። በዚያም ሸንጎ ተይዞ ስለ እምነቱ ሞት ቅጣትን በማርቆስ ላይ ሊያደርሱበት በተሰለፉ ጊዜ፣ ቆመና እንዲህ ብሎ ቃሉን ተናገረ፦ «በህይወት መኖሬ በክርስቶስ ውስጥ አገልግሎት እና ፍሬያማ ሥራዬ ነው። ሞት ቢመጣ ደግሞ ከክርስቶስ ጋር መኖርን የሚሰጠኝ ሕያው ድልድይ ነው። ለእኔም ይህ ደግሞ የተሻለ ነው አላቸው።…» አጠገቡ የነበሩት፣ ሊገድሉት ከሚፈልጉት መካከልም አንዳንዶች የማርቆስን እምነት ምንኛ ነው? በማለት እርስ በእርሳቸው አንጎራጎሩ።
ዳግመኛም ማርቆስ የመጨረሻ የክህደት ቃልህን አስፍርና ተናገር ባሉት ጊዜ « ለእኔ ሕይወት ክርስቶስ፥ ሞትም ጥቅም ነውና…» በማለት አጠናቀቀ ንግግሩን። የማርቆስም ሞት በፊልጵስዩስ ቤተክርስቲያንም በዙሪያዋ ባሉት ሁሉ ላይ ብዙዎች ጋር ደረሰ። ብዙዎች በጽናት ተመሰረቱ፣ በዛችም ከተማ ወንጌሉ ብዙዎችን እየለወጠ ሄደ። ይሄን እምነት መርሕ አድርገው የቤተክርስቲያን አባቶች ብዙዎች እንደ ሻማ ቀልጠውበታል። ለዚህም ነው ጠርጡልያንም ሲናገር The blood of the Martyrs is the seed of the Church(የሰማዕታት ደም የቤተክርስቲያን ዘር ነው) ያለው። በአጭሩ የቻርሊ ከርክ ፖለቲካ አቋም ምንድነው? የሚል ትርጉም ሳይሆን ጽሑፉ ትኩረት የሚሰጠው በእርሱ ህልፈት ምክንያት የመጣውን ሰዎች ባሰብን ቁጥር እግዚአብሔር በቃሉ ሞትም ጥቅማችን እንደሆነ የሚነግረን። በዚህ ዘመንስ እንደ እንቁ የምናያቸውን ምሑራንን ለማጥፋት ብዙዎች የሚያቅዱት። በዚህ ሁሉ ግን እግዚአብሔር ጽኑ እምነት ሰጥቷቸው የክርስቶስን ወንጌል ለማገልገል የተሰጡ ስንቶች ይሆኑ? እንጃ፤ ለእኛ ግን እግዚአብሔር በዚህ ጽኑ እምነት ይባርከንም።


