መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ/Sola scriptura/ – ክፍል 1

መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ማለት የቤተክርስቲያን ብቸኛው የማይሳሳተው ባለሥልጣን መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ነው። ይህን ስንል ግን ብዙዎች ተሳስተው የሚወስዱት ብቸኛ ባለስልጣን ነው ብለን ይመስላቸዋል። ይሄ ግን ስህተት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ የማይሳሳት ብቸኛ ባለሥልጣንና ዳኛ ማለታችን መሆኑን ይዘነጉታል።

ይሄን ልዩነት እንዴት ተቀመጠ ቢባል በቤተክርስቲያን የተለያዩ ሊሳሳቱ የሚችሉ ነገር ግን ሥልጣናት አሉ ከነዚህም ለምሳሌነት፦ ክሪዶች፣ ካታኪዝም፣ ኮንፌሽኖች፣ ጉባኤያት አንዳንዶቹ ናቸው። እነዚህም ደግሞ ሊሳሳቱ የሚችሉና በመጽሐፍ ቅዱስ መታረም ሚችሉ ናቸው።(የቤተክርስቲያን አባቶች ይሄን መስፈርት ሲጠቀሙ እንደነበር በብዙዎቹ ዘንድ የታወቀ ነው።)

ስለዚህ እኛ ክላሲካል ፕሮቴስታንት ከማንላቸውና ሶላ ስክሪፕቹራን በተሳሳተ መልኩ ተረድተው የሚተቹ ሰዎች ሁሉም አስተምህሮ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ግልጽ በግልጽ መቀመጥ አለበት የሚል አስተምህሮ ነው። ስለዚህ ሌሎች ጉባኤያት ሆኑ አበው አያስፈልጉም የሚሉ ናቸው ይሉናል። እኛ ግን የምንለው ከሐዋርያት በኋላ ያሉትን ጉባኤያት ሆነ አባቶች እንቀበላለን።[1] መቀበላችን እነሱንም ጨምሮ በቤተክርስቲያን ያሉ ባለሥልጣን አካላት ሊሳሳቱ የሚችሉ ናቸው። ስለዚህ በሚሳሳቱና በሚያስተምሩት በመጽሐፍ ቅዱስ ሥልጣን መታረም አለባቸው የሚል እንጂ። በዚህ ምክንያት ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ የሁሉም ዳኛና የሁሉም መሠረትና መዛኝ ማለት ነው።

ታሪካዊው ፕሮቴስታንት መጽሐፍ ቅዱስ ብቻን ስናነሳ ሁለት ዋና ዋና ነገሮችን ስለመፅሃፍ ቅዱስ እናነሳለን፦

1) የመጽሐፍ ቅዱስ ባህርይ

መጽሐፍ ቅዱስ እስትንፋሰ መለኮት የሆነ የጌታ ቃል ነው። ከእግዚአብሔር መሆኑ ደግሞ በባሕሪው  የተለየ ያደርገዋል(ontologically unique) ይህንንም በ 2ጴጥ 1፥21 እና በ1ጢሞ 3፥16 ተገልፆ እናገኛለን።

መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ንግግርና የእግዚአብሔር ቃል ነው። ሮሜ 3፥2 ማቴ19፥4-5 ላይ ተገልፆ እናገኛለን።
የእግዚአብሔር ቃል ስለሆነ ፈጽሞ ሊሻር እንደማይችል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐንስ 10፥35 ላይ፦

“መጽሐፉ ሊሻር አይቻልምና እነዚያን የእግዚአብሔር ቃል የመጣላቸውን አማልክት ካላቸው"

በማለት እንደማይሻር አጥብቆ ይናገራል። እግዚአብሔር ሊሳሳት አይችልም መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ የእግዚአብሔር ቃል ነው ስለዚህ መጽሃፍ ቅዱስ ሊሳሳት አይችልም። ይህንን ሐሳብ ቅዱስ አውግስጢኖስ ዘሒፖ(Augustine of Hipo) በመደገፍ መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ዝንፈተ እውነት የሌለበት እንደሆነ ይናገራል፦

I have learned to yield this respect & honour #only to the scripture, of these #alone do I most firmly believe that completely #inerrant (free from error)—-Letters, 82:3

ትውፊትም, የአምልኮ ሥርዓቶች ሆኑ ጉባኤያት ስህተት ሊገኝባቸው ይችላል። ምክንያቱም የትውፊት አስተላለፋቸውን በተመለከትን ጊዜ በሰዋዊ አተረጓጎም, በተፈጥሮዋቸው የሚሳሳቱ ስለሆኑ እና በባህል ጫና ውስጥ የታሰረ በመሆኑ ትክክለኛውን መልዕክቱ የተበላሸ ሊሆን ይችላል። በተለይም ትውፊት እና የቤተክርስቲያን ሥርዓቶች በዘመናት መሐል የተለያየ ብርዘት እና ለውጥ ሊገባባቸው የሚችሉ ናቸው። ለምሳሌ ያክል በካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የጳጳሳቱ መብት እያደገ እየተሻሻለ በመምጣት ወደ ፖፑ አይሳሳቴነት በመጨረሻም ወደ ስህተት መምጣታቸው የሚዘነጋ አይደለም። በተጨማሪም በነገረ ማሪያም ያላቸውን ዶክትሪን እጅጉን እየለጠጡ በመምጣታቸው ወደ Immaculate conception(አንዳንድ ኦርቶዶሳውያንም ይህንኑ አስተምሮ ይቀበላሉ) እንዳመሩ እንመለከታለን። የፑርጋቶሪ ጽንሰ ሐሳብ ሌላው የሚጠቀሱ ጉዳዮች ናቸው። በኦርቶዶክሱም ሆነ በካቶሊኩም የሚስተዋለው የመጽሐፍ ቅዱስ የቀኖና ችግር ስንመለከት ትውፊት በዘመናት መካከል ሊቀያየር እና ሊበከል የሚችል ጉዳይ ሁኖ እናገኘዋለን።

መጽሐፍ ቅዱስ በባህሪው  ልዩ መሆኑ ስልጣኑ ደግሞ ከሌሎቹ የተለየ እንዲሆን ያደርጋል። ይህንን በቀጣዩ ነጥብ ላይ እንመለከተዋለን።

2) ሁለተኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ሚና ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል ስለሆነ  በቤተክርስቲያን ካሉ ከሁሉም ባለስልጣናት በላይ ስልጣን አለው። በማር 7፥ 9-13 ና በማቴ 23፥2-3 ኢየሱስ ከአይሁድ ትውፊት በላይ ቅዱሳን መጽሐፍት ስልጣን እንዳላቸው ይናገራል። እንዲያው ለምን ቅዱሳት መጻሕፍት ከትውፊቶቻችን መብለጣቸው በመፅሃፍት ውስጥ በግልፅ አልተነገረንም ሚል ጥያቄ ቢነሳ መልሱ ሚሆነው ሁሉም ነገር ቃል በቃል ሊጻፍ አይገባውም ነው። ይልቁኑ ጳውሎስ ለገላቲያ ቤተክርስቲያን በጻፈው መልእክት ከተነገረን ወንጌል ሚለይ የትኛውም አይደለም ምድራዊ ሰማያዊ አካል እንኳን ቢሆን የተረገመ ይሁን ይላል። ይህም መጽሐፍ ቅዱስ በሁሉም ላይ ባለሥልጣን ሚሆነው እግዚአብሔር በሁሉም ላይ ባለሥልጣን ስለሆነ መሆኑን ያስረዳናል። ስለዚህ በጳውሎስ ስብከት መሰረት የትኛውም ስብከት በመጽሐፍ ቅዱስ ተመዝኖ ነው ተቀባይነት ሊኖረው ሚገባው።

ቤተክርስቲያን ልትሳሳት ማትችል ነችን?

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በ1ቆሮ 11፥2 ና በ2ጢሞ 2፥15 ላይ ሐዋሪያት በቃላቸው እንዳሰተማሩ ተፅፏል። ይህን ትውፊት ከሌላው ትውፊት ልዩ ሚያደርገው ሐዋሪያት በህይወት በነበሩበት ዘመን የተነገረ መሆኑ ነው። ምንም እንኳ ሐዋሪያት በቃላቸው ያስተማሩት ሊሳሳት ማይችል ትምህርትም ቢሆንም ነገር ግን በተነገረው ትውፊት infallibility እና ያ ትውፊት በተላለፈበት መንገድ መካከል ልዩነት አለ። ትውፊቱ የተላለፈበት መንገድ infallible አይደለምና።

አዲስ ኪዳን መጻሕፍት ውስጥ ስለቤተክርስቲያን ሥልጣን ስራ ባህሪ በግልፅና በጥልቀት ተጽፎ ብናገኝም ቤተክርስቲያን ልትሳሳት ማትችል መሆኗን ሚናገር ክፍል አንድም የለም። ይሄም ብቻ ሳይሆን የቤተክርስቲያንን infallibility አገናኝተን ልንተረጉምበት የምንችለው አንዳች የሐዋሪያት ጽሑፍ የለንም። ይልቁኑ እነዚህ ትምህርቶች በቤተክርስቲያን ታሪክ አርፍደው የመጡ ናቸው።(ቤተክርስቲያን በዘመናት ተሳስታለች ማለት ግን በፍጹም ጠፍታ ነበር ማለታችን አይደለም። በዚህ ርዕስ ላይ ወደፊት የምንላችሁ ነገር ይኖራል) ስለዚህ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጪ ድህረ ሐዋሪያዊ የሆነ ሊሳሳት የማይችል ምንም አይነት ሥልጣን ያለው አካል የለም።

ስናጠቃልል Sola scriptura/መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ/ ፍፁም እምነታችንን ሊሳሳት በሚችል ምድራዊ አካል ሳይሆን ሊሳሳት በማይችለው ፍፁም በሆነው በእግዚአብሄር ላይ እንድናደርግ ሚያመለክት ትምህርት ነው።

ማጣቀሻ

1] 39 Articles of Religion, v 8

ለተጨማሪ ንባብ

1] Gavin Ortlund, What it means to be Protestant.

2] Keith A. Mathison, The shape of Sola Scriptura

ለሌሎች ያጋሩ

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top