አስተምህሮተ ሥላሴ አሕዳዊ ወይስ መድብላዊ?

“እስራኤል ሆይ፥ ስማ፤ አምላካችን እግዚአብሔር  አንድ_እግዚአብሔር ነው፤”
  — ዘዳግም 6፥4

ሞኖቴይዝም(monotheism) የሚለው ግሪክ(ጽርዕ) ቃል ከሁለት ቃላት የተዋቀረ ሲሆን ሞኖስ(μόνος) ማለት አንድ ወይም ብቸኛ ማለት ሲሆን ቴዎስ(θεός) ማለት ደግሞ አምላክ ማለት ነው። በአጠቃላይ በስነመለኮት አንጻር አሐዳዊ አስተምህሮት የሚያንጸባርቅ አመለካከት ሞኖቴይዝም (monotheism) ይባላል። ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ የመድብለ አማልክት አራማጆች ፖሊቴይዝም(Polytheism) ይባላሉ። ፖሉ(πολύ) ወይም ፖሊ ማለት ብዙ ማለት ነው። ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በፖሊቴይዝም ረገድ የሚታወቁ አገራት መካከል ሮማውያንና ግሪካውያን ግምባር ቀደም ነበሩ። ግሪካውያን ለብዙ ነገር አምላክ አላቸው። ለፍቅር፣ ለሰላም፣ ለቀን፣ ለጦር፣ ለወቅቶች፣ ለእድል….ወዘተ ለእያንዳዱ ተግባር አማልክት ነበሯቸው። ከሁሉም በላይ ደግሞ በጣም የሚገርመው የሚያመልኩት ነገር ከመብዛቱ የተነሳ ለማይታወቅ አምላክ በግሪኩ አግኖስቶ ቴዎ(Ἀγνώστῳ θεῷ) ብለው መስዋዕትን ያቀርባሉ[ሐዋ 17:23]። በሐዋርያት ስራ ም.17 ቁ.16-34 ላይ ያለውን ክፍል ስንመለከት ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የግሪክ መዲና በሆነችው በአቴና ሲዘዋወር ያገኘው ነገር ከተማውን የሞሉት የሚታወቁና የማይታወቁ የአማልክት መሰዊያዎችን ነበር። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በቁጥር 24 ላይ አንድ ወሳኝ ንግግርን በአርዮስፋጎስ አደባባይ ላይ ቆሞ ስለ ክርስትና አስተምህሮ ሰበከ።

“ዓለሙንና በእርሱ ያለውን ሁሉ የፈጠረ አምላክ እርሱ የሰማይና የምድር ጌታ ነውና እጅ በሠራው መቅደስ አይኖርም፤”
  — ሐዋርያት 17፥24
"ὁ θεὸς ὁ ποιήσας τὸν κόσμον καὶ πάντα τὰ ἐν αὐτῷ, οὗτος οὐρανοῦ καὶ γῆς ὑπάρχων κύριος οὐκ ἐν χειροποιήτοις ναοῖς κατοικεῖ." (Πραξεις Αποστολων 17:24)

በክፍሉ ላይ እርሱ ወይም ሆውቶስ/οὗτος የሚለው በባለቤትነት ሙያ(Nominative case) የመጣው ነጠላ መደብ ተውላጠ ስም እየገለጸ ያለው አምላክ(ቴዎስ/θεὸς) እና ጌታ(ኩርዮስ/κύριος) የሚለውን ስም ነው። ይሄ ደግሞ በክርስትና አስተምህሮት ውስጥ ነጠላ ምንነት ያለው አሐዳዊ አምላክ ወይም ጌታ እንዳለ ያሳያል። እግዚአብሔር አምላክ በምንነት ደረጃ(በስልጣን፣ አገዛዝ፣ በባህሪይ፣ በመፍጠር) አንድ ወይም ነጠላ አምላክ እንደሆነ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በአርዮስፋጎስ አደባባይ ለአቴና ሰዎች አጥብቆ ሲናገር እናስተውላለን። ይሄ ንግግር ደግሞ አስተምህሮተ ክርስትና(ሥላሴያውያን) አሕዳዊ የመለኮት አስተምህሮ(Monotheism) እንዳላቸው የሚያረጋግጥ ነው። በሚገርም ሁኔታ ደግሞ በንጽጽር መልኩ የአቴና ሰዎች መድብላዊ አማልክት (Polytheism) አምላኪዎች እንደሆኑ በቁጥር  23 ላይ ገልጾልን እንመለከታለን፦

“ የምታመልኩትን እየተመለከትሁ ሳልፍ፦ ለማይታወቅ አምላክ የሚል ጽሕፈት ያለበትን መሠዊያ ደግሞ አግኝቼአለሁና፦ እንግዲህ ይህን ሳታውቁ የምታመልኩትን እኔ እነግራችኋለሁ።”
  — ሐዋርያት 17፥23
"διερχόμενος γὰρ καὶ ἀναθεωρῶν τὰ σεβάσματα ὑμῶν εὗρον καὶ βωμὸν ἐν ᾧ ἐπεγέγραπτο· Ἀγνώστῳ θεῷ. ὃ οὖν ἀγνοοῦντες εὐσεβεῖτε, τοῦτο ἐγὼ καταγγέλλω ὑμῖν."
(Πραξεις Αποστολων 17:23)

የምታመልኩትን ከሚለው አማርኛ ይልቅ የበኩረ ቋንቋው(ግሪኩን) ይበልጡን መመልከቱ ጠቃሚ ነው። ምክንያቱም ” የምታመልኩትን” ብሎ የገባው
ታ ሴባስማታ ሁሞን(τὰ σεβάσματα ὑμῶν) የሚል የግሪኩ ሐረግ ነው። ሴባስማታ (σεβάσματα) የሚለውን የግሪክ ቃል ነጥለን ስንመለከተው የመጣው በቀጥተኛ ተሳቢ ሙያ(Accusative case) በብዙ ቁጥር አመልካች መደብ(plural form) በግዑዝ ጾታ(Neuter Gender) የገባ ሲሆን በቀጥታ ሲተረጎም የሚመለኩ ነገሮች የሚል ትርጓሜን ይሰጣል። ይህ ማለት ደግሞ ከላይ ለማየት እንደሞከርነው መድብለ አማልክት አምላኪዎች(Polytheists) እንደሚባሉ ተመልክተናል። ስለዚህ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በአቴና የሚገኙት ጣኦት አምላኪ ሰዎች መድብለ አማልክት አምላኪዎች (Polytheists) እንደሆነ እግረ መንገዱን ሲናገራቸው እንመለከታለን።

በመጨረሻም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በክርስትናና በግሪካውያን መካከል ያለውን የነገረ መለኮት ልዩነት በግልጽ ሁኔታ አሳይቷል። ደግሞ እኛ ክርስቲያኖች የክርስትናችን አስተምህሮ በሥላሴ እምነተ አምድ ላይ የተመሰረተ ነው። በታሪክም ውስጥ ነብያት በብሉይ ሐዋርያት በአዲስ ኪዳን አስተምረው አልፈዋል። ቤተ ክርስቲያንም ይህን እውነት ተቀብላና አምና ስታስተምረውና ስትጠብቀው ቆይታለች። ሥላሴ የሚለው ቃል በራሱ የእግዚአብሔር የመለኮታዊ መገለጫ ስያሜ ነው። ሥላሴ የግእዝ ቃል ሲሆን ሠለስት ሦስት፤ ሠለሰ ሦስት ሆነ ማለት ሲሆን “ሥላሴ” ማለት ደግሞ ሦስትነት በአንድነት ማለት ነው።ይህም ማለት አንድ ሲሆን ሶስትነትም እንዳለው የሚያመለክት ነው። ይህም ደግሞ እግዚአብሔር በስም፣ በአካልና በግብር በሶስትነት የተገለጠ አምላክ ሲሆን በመለኮታዊ ስልጣን፣ በአገዛዝ፣ በባህሪ፣ በመፍጠርና በፍቃድ አንድ የሆነ አምላክ ነው። ስለዚህ አስተምህሮተ ሥላሴ ፈጽሞ ሥሉስ አማልክትን (Tritheism) የሚያሳይ አይደለም። በሥሉስ አማልክት (Tritheism) የሚያምኑት ሞርሞኖች (የመጨረሻው ዘመን ቅዱሳን) የጆሴፍ ስሚዝ ተከታዮች እንጂ ሥላሴያውያን አይደሉም። ስለ ሞርሞኖች በሰፊው በሌላ ጊዜ እንመለሳለን። ብዙ ለዘብተኛም ሆኑ አጥባቄያነ የነገረ መለኮት ሊቃውንት አስተምህሮተ ሥላሴን የአሕዳዊ የመለኮት አስተምህሮ እንደሆነ በጥናታቸው አረጋግጠውት እንመለከታለን።

ለተጨማሪ ምንጮች፦

William F. Albright, From the Stone Age to Christianity; H. Richard Niebuhr; Monotheistic Religion resources; Kirsch, God Against the Gods; Woodhead, An Introduction to Christianity; The Columbia Electronic Encyclopedia Monotheism; The New Dictionary of Cultural Literacy, monotheism

ለሌሎች ያጋሩ

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top