ሑባል(هبل)

እስልምና እና የአረቡ ጣዖታት

ክፍል 1

እንደሚታወቀው እስልምና ሲነሳ በአእምሯችን ፈጥኖ የሚሳለው የገሚሱ ጨረቃ እና ኮከብ አርማ ነው። በትላልቅ መስጂዶች አናት ላይ በሚናራዎች[¹] እንዲሁም እስላማዊ በሆኑ ኪነ ህንጻዎች ላይ የሚስተዋል ምልክት ነው። በሰባተኛው መቶ ክ/ዘ መጀመሪያዎቹ አካባቢ የእስላማዊ አገሮች መገበያያ የጨረቃ እና ኮከብ ምስል ያለው ሳንቲሞችን እንደሚጠቀሙ አርኪዎሎጂስቶች ያትታሉ።[²] በ11ኛው መቶ ክ/ዘ ግብጻውያን እና ሶርያውያን ይህንን ምልክት ለጌጣጌጣቸው ማስዋቢያነትም ይጠቀሙት ነበር።[³] በተጨማሪም አንዳንድ አገራት ማለትም እንደ አልጀሪያ፣ አዘርባጃን፣ ኮሞሮስ፣ ማሌዥያ፣ ሞሪታንያ፣ ፓኪስታን፣ ቱኒዚያ፣ ቱርክ፣ የቱርክ ሪፐብሊኳ ሰሜኒቷ ቆጵሮስ፣ ኡዝቤክስታ የምዕራብ ሰሐራ …ወዘተ  እስላማዊ አገራት ይህንኑ አርማ እንደ ሀገራዊ መለያ ሰንደቅ ማድረጋቸው ይታወቃል።[⁴]

እስልምና ከጨረቃ እና ኮከብ ምልክት ጋር ምን ግንኙነት አለው?

ይህንን ግንኙነት ለመረዳት ዲነል ኢስላም ከመጀመሩ በፊት ጥቂት አመታት እልፍ ብለን ስንመለከት በመካ ይመለኩ ከነበሩ ጣዖታት መካከል አንዱ ሑባል(هبل)  የጨረቃ እና የከዋክብት አምላክ እንደነበር የታሪክ መዛግብት ያትታሉ።[⁵] ሑባል(هبل) የአሏህ ቤት ተብሎ በሚጠራው በካዕባ ውስጥ ትልቅ ስፍራ የነበረው እና ለነገደ አረቡ ጣዖት አምላኪያን ሐያል አምላክ እና ታላቁ ጣዖታቸውም ነበር።[⁶] የሑባል ሌላኛው ስሙ “ሏህ” በመባል ይታወቅ ነበር። እንደ ሮበርት ሞሪ ያሉ ስኮላሮች ጥናት መሠረት ከአርኪዎሎጂስቱ ተመራማሪ ሁጎ ዊንክለር ጥናት በመነሳት “አሏህ” የሚለው ስም ለቅድመ እስላማዊ የአረብ ማህበረሰብ አፈታሪክ ውስጥ ለጨረቃ አምላካቸው ስያሜ እንደዋለ ይነግረናል።[⁷] ጁሊየስ ዌልሃውሰንም ጨምሮ የእስልምና ሐይማኖት ከማንሰራራቱ በፊት የአሏህ ቤት ተብሎ የሚጠራው ካዕባ በጣዖቱ ሑባል ሐውልቶች ቁሳቁሶችና ስዕላት ተሞልቶ እንደነበርና ሑባል የአሏህ የመጀመሪያ ስሙም እንደነበር ይናገራል።[⁸] ነገር ግን በእስልምናውም ላሉ ሊቃውንቶች ሆነ ለለዘብተኛ የታሪክ አጥኝዎች ጥያቄ የሆነው ክስተት አሏህ ስለዚህ ታላቅ የአረቦች ጣዖት በሐዲሱ ላይ አንድ ሱፍያን ኢብን ሀርብ የተባለ የቁረይሽ የጦር መሪ ከባድር ጦርነት በኋላ ድልን እንዲሰጣቸው እንደተጣራና ሑባልን እንዳመሰገነ[⁹] ከመጥቀሱ ባለፈ በቁርአኑ ውስጥ በስሙ ተጠቅሶ አለመነሳቱ ነው። እንደ እነ አል ላት አል ኡዛ እና እንደ እነ አል መናት ያሉ ጣዖቶች በቁርአኑ ውስጥ ተጠቅሰው ሳሉ ጣዖቱ ሑባል አለመጠቀሱ አጠያያቂ ጉዳይ ነው። እንደ አንዳዶች አባባል ቁርአን በካዕባ ስለነበሩ ሶስት መቶ ስልሳ ጣዖቶች እያንዳንዱን ስም እየጠቀሰ ግድ መናገር የለበትም ይላሉ። ነገር ግን ቁርአን በቁረይሾች ነገድ እንደ ሑባል በገነነ መልኩ የማይመለኩትን በስም ጠቅሶ ከገለጠ ስለ ሑባል አለማውራቱ አግራሞትን የሚያጭር ጉዳይ ሁኖ እናገኘዋለን። ይህ የሆነበት እንደምክንያት የሚነሳው የእስልምናው ሐይማኖት ቆርቋሪ እና መስራች የሆነው መሐመድ ከጣዖቱ ሑባል ጋር የተቆራኘ ታሪክ ስላለው ነው። ነብይ ተብዬው ከመወለዱ በፊት አያቱ አብዱል ሙጠሊብ የጣዖቱ ሑባል አምላኪ እንደነበር የእስልምና ታሪክ መዛግብት ይናገራሉ።[¹⁰] አብዱል ሙጠሊብ ከልጆቹ መኻል እጣው የወደቀበትን ልጅ በአሁኑ ጊዜ ቅዱስ ስፍራ ተብሎ በሚጠራው በካዕባ ለጣዖት ሑባል መስዋዕት አድርጎ ለማቅረብ በደጋን እጣ በልጆቹ ላይ ይጥላል። የደጋኑም ጫፍ የመሐመድ አባት በሆነው በአብደላህ ላይ ያመልክታል። የመሐመድም አያት ልጁን ለመሰዋት ማረጃ እንዳነሳና ነገር ግን ቁረይሾች፣ ከመኸዙም ጎሳ የሆነው አጎቱ እና ወንድሙ ልጁን እንዳይሰዋ አሳምነው አብዱል ሙጠሊብ በመሐመድ አባት አብደሏህ ምትክ የሚሆን የግመል መስዋዕት ለሑባል እንዳቀረበ እንመለከታለን።[¹¹] እንደውም እንደ ጠበሪ ዘገባ አብዱል ሙጠሊብ መሐመድ ጨቅላ እንደነበር ወደ ጣዖቱ ሑባል ፊት ያመጣው እንደነበር ይተርካል።[¹²] ይህ ሁሉ የታሪክ ማስረጃዎች የሚያሳዩን የቁርአኑ ደራሲ መሐመድ ከሑባል ጣዖት ጋር ገና ከመወለዱ ጀምሮ ህጻንም እያለ ጥብቅ ቁርኝት እንደነበረው ያሳያል።

ምንም እንኳን መሐመድ በካዕባ የሚገኙትን የሑባልን ጣዖት እና መገልገያዎችን ለማጥፋት ቢሞክርም የሑባል ጣዖት የአምልኮ ስርአቶችን ለምሳሌ በካዕባ ዙሪያ ጠዋፍ ማድረግን(የቅድመ አረባውያን የጣዖት አምላኪዎች ልምምድ ነበር ለጣዖት ሑባልም ይህንኑ የአምልኮ ስርአት አምላኪዎቹ ይከውኑ ነበር) የጣዖቱ ስም ከአምላኩ ስም ጋር ማመሳሰሉ(ቀደምት እስልምና የጣዖት አምላኪያውያን አምላካቸውን ላህ ወይም ሑባል በማለት ይጠሩት እንደነበር እና የእስልምናው አምላክ ስም ከጣዖታውያኑ ጋር ጥልቅ ቁርኝት ነበረው) በተጨማሪም የአሁኑ የሙስሊም  ማህበረሰብ የሚጠቀምበት የእምነት መለያ አርማቸው ያደረጉት በጥንቱ የአረብ ጣዖት አምላኪያን ዘንድ ለሑባል የተሰጠ የጣዖታቸው መለያ መሆኑ ይህ ሁሉ የሚያሳየን እስልም የቅድመ አያቶቹን የአረብ ጣዖታውያንን የሐይማኖት ስርአት፣ ስያሜ የማምለኪያ ቦታ(ካዕባ) እና የመለያ ምልክቱን መኮረጁ ወልደ ጣዖታውያን የእምነት መሠረት መሆኑን በግልጽ ሁኔታ መረዳት የምንችለው የሐይማኖት ቡድን እንደሆነ ነው። መጽሐፍ ቅዱሳችን ግን፦

“እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝና ለእናንተ ጣዖት አታድርጉ፥ የተቀረጸም ምስል ወይም ሐውልት አታቁሙ፤ ትሰግዱለትም ዘንድ በምድራችሁ ላይ የተቀረጸ ድንጋይ አታኑሩ።”
  — ዘሌዋውያን 26፥1

በማለት እንዳናመልክና እውነተኛውን ጌታ እንድንከተል ያደርገናል። እግዚአብሔር በዚህ መንገድ ይመራቸው ዘንድ ፀለይን አሜን።

ማጣቀሻዎች

[¹] International Federation of Red Cross & Crescent Societies

[²] S. Album & T. Goodwin – Syllogue Of Islamic Coins In The Ashmolean – The Pre-Reform Coinage Of The Early Islamic Period – 2002, Volume I, Ashmolean Museum: Oxford (UK), pp. 6-7

[³] “Pendant (Egypt) (30.95.37)”. In Heilbrunn Timeline of Art History. New York: The Metropolitan Museum of Art, 2000–. (October 2006)

[⁴] Islamic flags – Flags Of The World, October 18, 2008

[⁵] Karen Armstrong (2000,2002). Islam: A Short History. pp. 11

[⁶] ዝኒ ከማሁ

[⁷] Morey, Robert(1994)The Moon-god Allah in Archeology of the Middle East. Newport, Research & Education Foundation.

[⁸] Wellhausen, Julius. Reste Arabischen Heidenthum, pp. 75/ Hawting, Gerald R.(1999). The Idea of idolatry & the emergece of Islam: from polemic to History. pp. 112

[⁹] Winckler, Hugo(1901) Arabisch, Semitisch, Orientalisch: Kulturgeschichlich-Mythologische Untersuchung.Berlin:W. Peiser pp. 83

[¹⁰] Ibn Hisham 1/151-155; Rahmat-ul-lil’ alammeen 2/89, 90

[¹¹] ዝኒ ከማሁ

[¹²] Mohammed ibn Jarir al-Tabari, The History of the Prophet & Kings,1:157

ለሌሎች ያጋሩ

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top