“ብትወዱኝ ትእዛዜን ጠብቁ። እኔም አብን እለምናለሁ ለዘላለምም ከእናንተ ጋር እንዲኖር ሌላ አጽናኝ (ἄλλον παράκλητον) ይሰጣችኋል፤”
ዮሐንስ 14፥15-16
እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ኅልው አምላክ በራሱ የቆመ ማንነት ያለውና ከሥሉሳዊ አካላት መካከል አንዱ አካል ነው። ስለ መንፈስ ቅዱስ አካላዊ ማንነት ከማውራታችን በፊት በተወሰነ መጠን ስለ አካል ምንነት ለመመልከት እንሞክር፦
አካል የምንለው መጠሪያ በጣም ልም ከሆነ ብናኝና በጣም ረቂቅ ከሆነ ትናኝ እጅግ በጣም ረቂቅ ከሆነ አየር ጀምሮ የመጨረሻ ጥጥርነትና ጉልህነት እስካለው ውፍረት ደንዳናነትም ድረስ በዚያ በሚገኝ ዐቅምና ብቃት እንደየ መጠኑ እንደየ መልኩ ተወስኖ እንደሚታወቅ ሁሉ፤ በዓለም ግዘፍ አካል ተብሎ ይሰየማል። በሌላም አገላለጽ በሰማይ ያለው የሚዳሰስና የሚገሰስ የሚቋጠርና በአምስቱ የስሜት ህዋሳት ተደርሶበት የሚጨበት ነገር ሁሉ በዓለመ ግዘፍ አካልነት እንዳለ ያለ መሆኑ ይታወቃልና አካል በሚል ስያሜ መጠራት ገንዘቡ ነው።[1]
ነገር ግን አካል የሚለው ስያሜ በአምስቱ ህዋሳት ብቻ ለሚታወቀው ነገር ብቻ ሳይሆን ለማይታይ ለማይዳሰስ፣ ለማይገሰስ፣ ለማይቋጠር ነገር ግን በህያውነት፤ በዓለመ ነፍስ የሚኖር እኔ የሚል ነባቢ ለባዊ አለሁ ባይ ሁሉ አካል አለው ተብሎ ሊጠራ ይችላል።[2] እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ የራሱ የሆነ አካል ያለው አምላክ ነው። መንፈስ ቅዱስ አካል አለው ስንል ከሌላው የስላሴ አካላት ራሱን ችሎ ለራሱ ብቁዕ የሆነ ዕውቀት ቀዋሚነት ያለው አለሁ ባይ ቁመና መሆኑን አመላካች መገለጫ ነው። ከአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ የተለያዩ የምንፍቅና አንጃዎች በመንፈስ ቅዱስ ላይ በተለያየ መንገድ አስተምህሮና ልምምዶች ተነስተው ነበር። በመንፈስ ቅዱስ ላይ ምንፍቅናዊ ዘመቻ የከፈቱትን ቡድኖች ኔውማቶማኪያውያን የሚልን ስያሜን ተሰጥተው ነበር። ኔውማቶማኪ(Pneumatomachi) ወይም በግሪኩ (Πνευματομάχοι) የሚለው ቃል ኔውማ(πνεῦμα) ማለትም መንፈስ እና ማኬ(μάχη) ውጊያ፤ በአንድ አካል ላይ በአሉታዊ ሁኔታ መነሳትን ወይም ጠበኛ መሆንን ሲገልጽ በአጠቃላይ የመንፈስ ቅዱስ ጠበኞች፣ ተቃዋሚዎች አልያም በመንፈስ ቅዱስ ማንነትና ምንነት ላይ በአሉታዊ ጎን የተነሱ ማለት ነው።[3] ለምሳሌ ያክል መቅዶናውያን (የመቅዶኒዮስን አስተምህሮተ ምንፍቅና የሚከተሉ)፣ አርዮሳውያንና ከፊል አርዮሳውያን፣ ሰባልዮሳውያ ወዘተ ተጠቃሽ ናቸው። አንዳንዶቹ የምንፍቅና ቡድኖች የመንፈስ ቅዱስን መለኮትነት ሲክዱ አንዳዶቹ ደግሞ ከነጭራሹን መንፈስ ቅዱስ ህልውና የሌለው ማለትም በራሱ የቆመ ወይም አካል የለውም ብለው ያምናሉ ያስተምራሉ። በዚህ ጽሑፍ መንፈስ ቅዱስን አካላዊ ማንነትን ለሚክዱት ቡድኖች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምላሽን ከሰዋስው እና ከአውዳዊ ዳሰሳ አንጻር አንዳንድ ነጥቦች ለመዳሰስ እንሞክራለን፦
መንፈስ ቅዱስ በራሱ ኃይል አይደለም ኃይልን ለባህሪው ገንዘብ ያደረገ አምላክ እንጂ
መንፈስ ቅዱስ የራሱ የሆነ ማንነት የለውም “እርሱ የእግዚአብሔር ሐይል ብቻ ነው” ለሚሉ መናፍቃን መጽሐፍ ቅዱሳችን መልስ አለው፦
“ወንጌላችን በኃይልና በመንፈስ ቅዱስ በብዙ መረዳትም እንጂ በቃል ብቻ ወደ እናንተ አልመጣምና፤ በእናንተ ዘንድ ስለ እናንተ እንዴት እንደ ነበርን ታውቃላችሁ።”
— 1ኛ ተሰሎንቄ 1፥5
የተሰሎንቄን መልዕክት ጸሐፊ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ኃይልን(δυνάμει) እና መንፈስ ቅዱስን(πνεύματι ἁγίῳ) በማለያየት “እና(ካይ/καὶ)” በሚለው መስተጻምር ቃላቶቹን ሲሰነጥቃቸው እንመለከታለን። ይህም ማለት መንፈስ ቅዱስ ከኃይል የተለየ ማንነት እንደሆነ ያስረዳል። መንፈስ ቅዱስ በራሱ ኃይል ሳይሆን ኃይልን ባህሪው ያደረገ አምላክ ነው(ሉቃ 4፥14፣ ሐዋ 1፥18፣ ሮሜ 15፥13, 18-19)።
በሐዋርያት ስራ ላይ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመንፈስ ቅዱስን መምጣት ሲናገር መንፈስ ቅዱስን እና ሐይልን ለያይቶ በመናገር እንጂ መንፈስ ቅዱስ ራሱ ሐይል ነው ወይም ሐይል በወረደባችሁ ጊዜ ፈጽሞ አላለም። እንዲያውም መንፈስ ቅዱስ በእነርሱ ላይ በወረደ ጊዜ ሐይልን እንደሚቀበሉ ያስረዳል። ይህም ማለት ሐይል ከመንፈስ ቅዱስ የሚወጣ ባህሪዎት ነው፦
“ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ፥ በኢየሩሳሌምም በይሁዳም ሁሉ በሰማርያም እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ አለ።”
— ሐዋርያት 1፥8
በሁለተኛ፦ መንፈስ ቅዱስ ከአብ እና ከወልድ የተለየ የራሱ የሆነ ማንነት ያለው አካል ነው
“ብትወዱኝ ትእዛዜን ጠብቁ። እኔም አብን እለምናለሁ ለዘላለምም ከእናንተ ጋር እንዲኖር ሌላ አጽናኝ (ἄλλον παράκλητον) ይሰጣችኋል፤”
— ዮሐንስ 14፥15-16
“ሔቴሮስ/ἕτερος” የሚለው የጽርዕ(ግሪክ) ቃል የተለየ፣ ሌላ ወይም አንድ አይነት ያልሆነ የሚል ትርጉም ሲኖረው አብዛኛውን ጊዜ በአይነትም ሆነ በአካል የተለየን ነገር የሚያመለክት ነው።[4] “አሎስ/ἄλλος” የሚለው የጽርዕ (ግሪክ) ቃል ደግሞ በአይነታቸው ተመሳሳይ የሆኑ ነገሮችን ነገር ግን በአካል ወይም በቁጥር የተለያዩ መሆናቸውን የሚገልጽ ቃል ነው።[4]
ለምሳሌ፦
“በክርስቶስ ጸጋ እናንተን ከጠራችሁ ከእርሱ ወደ ልዩ ወንጌል( #ἕτερον εὐαγγέλιον) እንዲህ ፈጥናችሁ እንዴት እንዳለፋችሁ እደነቃለሁ፤” — ገላትያ 1፥6
ሔቴሮን ኢዋንጌሊዮን(ἕτερον εὐαγγέλιον) የሚለው ሐረግ በአይነቱም ሆነ በይዘቱ ለገላትያ ሰዎች ከተሰበከላቸው ከቀድሞው ከእውነተኛው እና ከቀጥተኛው ወንጌል ፍጹም ሌላ (ሔቴሮስ/ἕτερος) ወይም የተለየ መሆኑን የሚገልጽ ነው።
“ስምዖን ጴጥሮስም ሌላውም ደቀ መዝሙር(አሎስ ማቴቴስ/ἄλλος μαθητής) ኢየሱስን ተከተሉ። ያም ደቀ መዝሙር በሊቀ ካህናቱ ዘንድ የታወቀ ነበረ፥ ወደ ሊቀ ካህናቱም ግቢ ከኢየሱስ ጋር ገባ፤”— ዮሐንስ 18፥15
በግሪኩ “አሎስ/ἄλλος” የሚለው ቃል ከስምዖን ጴጥሮስ የተለየ ማንነት እንዳለ ወይም በማንነታዊ መገለጫ ፈጽመው የተለያዩ አካላቶች እንደሆኑ የሚያሳይ ቃል ነው። ይህም ማለት ደግሞ ሁለት በአገልግሎታቸው፣ በምንነታዊ ባህሪዎታቸው(ሰው በመሆናቸው) እና የመጠሪያ ማዕረጋቸው አንድ አይነት የሆኑ ነገር ግን በአካል ሆነ በማንነታቸው ደግሞ የተለያዩ ሁለት ሰዎች መሆናቸውን ይገልጻል።
የሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስን የጽሑፎቹን የሰዋሰው አወቃቀርና የቃላት አጠቃቀም በተመለከትን ጊዜ ምን ያክል ለቋንቋ ህግጋት ጥንቃቄዎችን እንደሚያደርግ እናስተውላለን። በዮሐ 14፥15-16 ላይ ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ ከእኛ ጋር ለዘላለም የሚኖረው አጽናኙ በአካል ከአብ እና ከወልድ የተለየ፤ በባህሪዎቱ እና በምንነቱ ደግሞ ከአብ እና ከወልድ ጋር ተስተካክሎተ ኑባሬ ያለው አካል መሆኑን ለመግለጽ “አሎስ/ἄλλος” የሚለው የጽርዕ (ግሪክ) ቃል እንደተጠቀመ እንመለከታለን። በተጨማሪም ቁጥር 17ን ስንመለከት፦
“ እርሱም(αὐτὸ) ዓለም የማያየውና የማያውቀው ስለ ሆነ ሊቀበለው የማይቻለው የእውነት መንፈስ ነው፤ ነገር ግን ከእናንተ ዘንድ ስለሚኖር በውሥጣችሁም ስለሚሆን እናንተ ታውቃላችሁ።”
— ዮሐንስ 14፥17
በዚህ ክፍል ላይ የእውነት መንፈስ(τὸ πνεῦμα τῆς ἀληθείας/ቶ ኒውማ ቴስ አሌቴያስ) የተባለው አካል እርሱ(αὐτὸ) ሊባል የሚችል ማንነታዊ ቅዋሜ ያለው አካል እንደሆነ በግልጽ ሁኔታ ያስረዳል።[5] በተጨማሪም “..ከእናንተ ዘንድ ስለሚኖር/ὅτι παρ’ ὑμῖν μένει…” በሚለው ሐረግ ውስጥ “ስለሚኖር” ማለትም በግሪኩ ሜኔይ/μένει በሚለው ግሳዊ ቃል በተባእታይ ጾታ የመጣ እርሱ/He የሚል ውስጠ ተውላጠ ስም እንዳለ እንመለከታለን። በተለያዩ የዮሐንስ ወንጌል ክፍሎች ላይ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መንፈስ ቅዱስን እርሱ እያለ በተባዕታይ ጾታ ሲጠራው እንመለከታለን። ይሄ ደግሞ የመንፈስ ቅዱስን አካላዊ ማንነት የሚያስረዳ ነው። መንፈስ ቅዱስ በኑባሬያዊ ማንነቱ በግዑዝ ጾታ አለመጥራቱ የራሱ የሆነ ማንነት እንዳለው አስረጂ እና አመላካች ነጥብ ነው።[6] ቀጥሎ በዮሐንስ ወንጌል ላይ መንፈስ ቅዱስ እርሱ እየተባለ በተባዕታይ ጾታ የተጠራባቸውን ክፍሎች እንመልከት፦
በዮሐንስ 14፥26 እና 15፥26 ላይ መንፈስ ቅዱስ በሶስተኛ መደብ ሰብአዊ ተውላጠ ስም ኤኬይኖስ/ἐκεῖνος “እርሱ” ተብሎ ተጠርቷል። በተጨማሪም አጽናኝ በግሪኩ ፓራክሌቶስ/παράκλητος የሚለው ስም በባለቤት ሙያ በተባዕታይ ጾታ የመጣ ስም ነው፦
“አብ በስሜ የሚልከው ግን መንፈስ ቅዱስ የሆነው አጽናኝ (ፓራክሌቶስ/παράκλητος) እርሱ (ኤኬይኖስ/ἐκεῖνος) ሁሉን ያስተምራችኋል እኔም የነገርኋችሁን ሁሉ ያሳስባችኋል።”
— ዮሐንስ 14፥26
“ዳሩ ግን እኔ ከአብ ዘንድ የምልክላችሁ አጽናኝ (ፓራክሌቶስ/παράκλητος) እርሱም ከአብ የሚወጣ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ፥ እርሱ (ኤኬይኖስ/ἐκεῖνος) ስለ እኔ ይመሰክራል፤”
— ዮሐንስ 15፥26
በተጨማሪም በዮሐንስ ወንጌል በምዕራፍ 16 ቁጥር 7 ላይ የሚላከው አካል “እርሱን” አውቶን/αὐτὸν በማለት በሶስተኛ መደብ ሰብአዊ አገናዛቢ ተውላጠ ስም ተባዕታይ ጾታ ሲጠራው እንመለከታለን፦
⁷ እኔ ግን እውነት እነግራችኋለሁ፤ እኔ እንድሄድ ይሻላችኋል። እኔ ባልሄድ አጽናኙ ወደ እናንተ አይመጣምና፤ እኔ ብሄድ ግን እርሱን (አውቶን/αὐτὸν) እልክላችኋለሁ።
…
¹³ ግን እርሱ ἐκεῖνος የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል(ሆዴጌሴይ/ὁδηγήσει)፤ የሚሰማውን (አኩሴይ/ἀκούσει) ሁሉ ይናገራል (ላሌሴይ/λαλήσει) እንጂ ከራሱ (ሄአውቱ/ἑαυτοῦ) አይነግርምና፤ የሚመጣውንም ይነግራችኋል (አናንጌሌይ/ἀναγγελεῖ)።
¹⁴ እርሱ (ኤኬይኖስ/ἐκεῖνος) ያከብረኛል፥ ለእኔ ካለኝ ወስዶλήμψεται ይነግራችኋልና።
— ዮሐንስ 16፥7፣13፣14
በቁጥር 13 እና 14 ላይ ያሉት ግሶች ስንመለከት(ይመራችኋል፣ የሚሰማውን፣ ይናገራል፣ ይነግራችኋል …ወዘተ) “እርሱ” የሚል ተባዕታይ ውስጠ ተውላጠ ስም አለ። ይህ ሁሉ የሚያሳዩት ወይም አመላካች የሆኑት የመንፈስ ቅዱስን አካላዌ ህያውነት ወይም ኅልወትን እንደሆነ እንረዳለን። ስለዚህ መንፈስ ቅዱስ ግዑዝ አካል እኔ የሚል ቅዋሜ ማንነት የሌለው እና ኢሰዋዊ አካል ማለትም እንደ ኃይል(ራሱ ኃይል የሆነ) ፈጽሞ አለመሆኑን ግልጽ እና ጥርት ባለ መልኩ በቅዱሱ መጽሐፍ ላይ ሰፍሮልን እንመለከታለን።
ማጣቀሻዎች
[¹] መሠረት ስብሐት ለአብ፣ ስላሴ በተዋህዶ1988 ዓ.ም ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት፣ ገጽ 165 እና 170
[²] ዝኒ ከማሁ
[³] የክርስትና ትምህርቶች እና የእምነት መግለጫዎች(Catechism, Creeds & confessions) ገጽ 12, Catholic Encyclopedia. New York: Robert Appleton Company.
[⁴] GRAMMAR OF THE NEW TESTAMENT IN LIGHT OF HISTORICAL RESEARCH, By A.T Robertson, The University Press Cambridge U.S.A p. 746-747,
[⁵] [⁶] ምንም እንኳን “እርሱ(αὐτὸ)” የሚለው ተውላጠ ስም በግዑዝ ጾታ ቢመጣም መንፈስ ቅዱስ ወይም በግሪኩ ኔውማ(πνεῦμα) የሚለው ቃል በተፈጥሮው ጾታው ተባዕታይ ሲሆን ነገር ግን በሰዋስው አገባቡ ጾታው ግዑዝ ጾታን ይጠቀማል። ይህ ማለት ግን መንፈስ ቅዱስ ግዑዝ ነው ማለት አያስችልም፤ የሰዋስው ጾታ ሁልጊዜ የነገሩን ምንነት ስለማይገልጽ። ከላይ እንዳየነው መንፈስ ቅዱስ በምንነቱ ምሉዕ እና ኅልው አካል ያለው ስለሆነ እርሱ ተብሎ በተባዕታይ ጾታ ተጠርቷል።