ከአዲስ አበባ ወጣ ብላ በምትገኝ በአንዲት ገጠራማ አካባቢ የሚኖሩ አነስተኛ ማህበረሰብ ነበሩ። አብዛኛዎቹ የአውራጃው ነዋሪዎች ጣዖት አምላኪያን የነበሩና ስለ እግዚአብሔር መኖር የማያቁ የሆኑ እንደዋዛ የሚታለፉም አይደሉም። በዛ መካከል እውነትን የሚያቁ ጥቂት ክርስቲያኖች ግን አልጠፉም ነበር፡፡ ያው ጭስ ባለበት ጥቂትም ቢሆን እሳት አይጠፋም እንደሚባለው ተረቱ አንዳንድ ቦታዎች ላይ ሰፍረው ነበር።(ከዛ በፊት ሚሶናውያን በስፍራው ተልከው ወንጌልን ያደረሱ የነበሩ ይመስላል።) በጥልቀት በማህበረሰቡ ጫና ምክንያት ግን ወንጌልን ባለማድረሳቸው ብርቱ ክርስቲያን እንቁጠር ብንል እንደ ቦዘና ሽሮ ጥቂት ሥጋ ጣል ጣል ይመስል በትግል ነው የምናገኘው፡፡ (ያው ቦዘና ስለምወድ ምሳሌ ተጠቀምኳት፤ የምትወዱ ሰዎች ካላችሁ ከአፍቃሬ ነኝ ለማለት ነው)።
በአንድ ወቅት እኒያ ወንጌልን የሰሙት ሰዎች ላልሰሙ ሰዎች ለማድረስ ለሁለት ተከፍለው ለጣዖት አምላኪውና አንዱ ወገን ደሞ አምላክ የለም(እግዚአብሔርን ለማያቀው) ተበታትነው በአንድነት ማሰራጨት ጀመሩ። በማህበረሰቡ መካከል በብዙ ታወቁ፣ ክርስትና ከዛች መንደር አልፎ ቀያቸውን ሙሉ አጥለቀለቀው፡፡ የዚህ ሁሉ ብርታትና የአንድነታቸው ምክንያት ለቤተክርስቲያን ቀናኢ ሀሳብ አለን ማለታቸውና አንዱ በአንዱ ስራ ጣልቃ ሳይገባ፣ ሳይንቅ፣ የሚሰራውን አገልግሎት ሳያሰናክልና ክፉ ሳያስብ አንድነትን ስለመረጠ ነበር። የሆነው ሁሉ ግን በአንዲት ክፉ ቀን ይሄ አንድነት ብዙ ርቀው እንዳይሄዱና ተሰናክለው እንዲወድቁ አደረጋቸው፡፡ የሰላሟ መንደርም ሁከት ተጀመረ። ለዚህ ሁሉ ጉስቁልና መንስኤ ክፋት ማሰባቸው ነበር። በተጨማሪም ሐዋርያው ጴጥሮስ በክታቡ እንዲህ ያለውን መዘንጋታቸው ነበር፦
“እግዚአብሔርንም በመምሰል የወንድማማችን መዋደድ፥ በወንድማማችም መዋደድ ፍቅርን ጨምሩ።'' 2ኛ ጴጥሮስ 1፥7
እግዚአብሔርን ምሰሉ በተባሉበት ቦታ ይልቅ የራስን ፍላጎትን በሰዉ ዘንድ መሳላቸው፣ ከአሻጥር ይልቅ መዋደድን ሳሉ በተባሉበት ቦታ ላይ የእኔ ወንጌል በላጭ የእግዚአብሔሩ ሀሳብም በእኔ ተገልጧልና ፍቅር እኔ ጋር ነው፤ የእርሱ ወንጌል እንዲህ…በማለት ለማህበረሰቡ አልባሌ ስብከት ማሰማት ጀመሩ። ይሄ ነበር የውድቀታቸው ምክንያቱ፡፡
ታሪኩ በዚህ አላበቃም ቢያበቃማ ጥሩ ነበር፤ እነዚያ ወንጌል የሰሙ ያመልኩበትም የነበረችው ቤት በዚህ ሽኩቻ ወደቀች፣ የመንደሪቷ ቤተክርስቲያን ፖለቲካ ስለያዛት ተናደች፣ የአንዱን ግለሰብ ትችት ለገሃዱ ዓለም መናገር የሚያመጣውን ጦስ ስላልተገነዘቡ ጣዖት አምላኪያኑ ወደ እጣናቸውና ደም ማፍሰስ፤ አምላክ የለሾቹ ወደ ቁዘማቸው ገቡ፡፡ ይሄን ሁሉ ታሪክ ያነበብክ አንባቢዬ የነገሩ መጎሳቆል ለምን የሆነ ይመስልሃል? እንዲያ እንዲህ ብለህ ልታብራራ ከቻልክ ጥያቄው ላንተ በዝርዝር ከታች ላስቀምጥልህ፦
➞ የክርስቲያኖቹ እንዲያ መሆን መንስኤው ምንስ ይሆን?
➞ በዚህስ ዘመን ምን እየሰማህ ይሆን?
➞ በዚህ ታሪክ ላይ ቀይራለሁ ብለህ ምታስበው ነገር ይኖር ይሆን?
ኦኦኦ….ጥያቄማ አላብዛ ይቅር፤ ይሄ አጭር ማስታወሻዬ ጽሑፍ ለካ ብዙ ጥያቄ ያግዳል..! ጽሑፏም ጣፍጣ ለአንባቢያን በአጭሩ አትቀርብ ይሆን በሚል አሳጥሬዋለሁ፡፡ አድማጬና አንባቢዬ ሆይ..! ስትመልሳቸው ሐዋሪያው ጨምሩ ማለት ምን ማለት ይሆን? የምትለዋን ነገር ባትረሳት ጥሩ ነው፡፡ ጨረስኩ እያልኩ ቀጠልኩ አይደል ጨርሻለሁ።[2]
1] ሰሞናዊውን የክርስቲያን ማህበረሰብ ሁኔታ ስንመለከት ይሄ ታሪክ ለመጻፍ ተነሳሁ። ከእግዚአብሔር አገልጋይ ሆነው ግን በእግዚአብሔር ዓለም ውስጥ የሌለን ማንነት ለማሳየት፣ ለማጉላት መሞከራቸውን ሳይ እግዜሩ ይፋረድ አልኩና ይሄን አጭር ታሪክ በአጭር ማስታወሻዬ አካተትኩላችሁ።
2] በመጨረሻም ይሄን የጽሑፍ ልጥፍ ለማለት የፈለገውና የተነገረው ሳይገባህ ቅርጫፉን ይዘህ በደፈናው የምትቆጣ፣ ምዕመኑን ጨፍላቂና እብሪተኛ መጋቢ ሆይ….! ቤተክርስቲያን ላይ መንግስት ለመሆን የምታስቡም ጭምር ካላችሁ…! ይቺ አጭር ፖስት ለእናተ ትቀርብልኝ ዘንድ አሳሰብኩ።
እግዚአብሔር በዚህ ዘመን ከምንሰማው ነገር ሁሉ ይጠብቀን። አሜን።