ዘላለማዊ ቃል ወልድ ከአብ በኑባሬው ያነሰ እና ለአብ የሚገዛ ነውን?

“…በዚያን ጊዜ ልጁ ራሱ ደግሞ ሁሉን ላስገዛለት ይገዛል።”
1ኛ ቆሮንቶስ 15፥28
"…τότε καὶ αὐτὸς ὁ υἱὸς ὑποταγήσεται τῷ…"
1Cor 15:28

ሃይፖታጌሴታይ/ὑποταγήσεται የሚለው ቃል ሃይፖታሶ/ὑποτάσσω ከሚለው ስርወ ቃል የመጣ ሲሆን መታዘዝ፣ መተናነስ ወይም ደግሞ መገዛትን የሚያመለክት ነው። አንዳንድ ሐያስያንና የክርስቶስን አምላክነት የሚክዱ(ሙስሊሞችንም ያጠቃልላል) መናፍቃን በ1 በቆሮንጦስ ምእራፍ 15 ላይ አብ ሁሉን ነገር ለወልድ ካስገዛለት በኋላ ወልድ ራሱ ደግሞ ሁሉን ላስገዛለት ለእርሱ እንደሚገዛ የሚናገረውን ክፍል በመጎንተል ክርስቶስ ኢየሱስ አምላክ አይደለም ለማለት ይዳዳቸዋል። መገዛት ወይም መተናነስ (subordination) የሚለው ቃል በምን አግባብና አገባብ እንደሚውል ከማየታችን በፊት ስለ ነባቤ እንሰተ ቃል (subordination view) በትንሹ እንመለከታለን። በSubordinationism ዙርያ እስከ 4 መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ ብዙ ሀሳቦችንና አስተምህሮቶች ተሰንዝረውበታ። በዚህም ዙሪያ የሁለት ጎራዎችን ምድብ ነጥብ በነጥብ እንመልከት፦

አንደኛው፦ ሆሞዮስዮስ/ὁμοιούσιος

ሆሞዮስዮስ የሚለው የግሪክ ቃል
“ሆሞዮስ/ὅμοιος” “ተመሳሳይ” ወይም “ተቀራራቢ” ከሚለውና “ኡሲያ/οὐσία” “ኑባሬ” ወይም “ባህሪ” ከሚሉት ጥምር ቃላቶች የተገኘ ሲሆን ኢንግሊዘኛው ontological subordination ሲለው የአማርኛው የቁም ፍቺው ደግሞ “ኑባሬያዊ እንሰት” ወይም “በባህሪ መተናነስን” ያመላክታል። በዚህ መርሆተ ቃል በነገረ ክርስቶስ(christology) ዙሪያ ብዙ የኑፋቄ ትምህርቶች ተነስተዋል። ከእነዚህም መካከል እውቁ የኑፋቄ መምህር የአሌክሳንድሪያው ጳጳስ አርዮስ ከክርስትናውና ከቅዱሱ መጽሐፍ ያፈነገጠ አስተምህሮ በመለኮታዊ በኑባሬ ወይም በባህሪ አንጻር ያለን መተናነስን ወይም መበላለጥን (ontological subordination) አስተማረ። በአሁኑ ጊዜ ለተነሱት የኑፋቄ ትምህርቶች ለጅሖቫ ምስክሮች ለኢብዮኒዝም(Ebionism) አስተምህሮ እንደውም ለመሐመዳውያን ለእስልምና መነሳሳት ትልቅ ጠባሳ ጭሮ ያለፈ እንደሆነ ይገመታል።

ሁለተኛው፦ ሆሙስዮስ/ὁμοούσιος

ሆሙስዮስ ማለት “ኡሲያ/οὐσία” “በኑባሬ” ወይም “በባህሪ” አንድ አይነት ወይም እኩል መሆንን ያሳያል። በ325 አ.ም በኒቂያው ጉባኤ ላይ በተደረገው ጉባኤ የአርዮስን የተሳሳተ የሰቦርዲኔሽናል ፈርጅ ማለትም የወልድን ለአባቱ መገዛቱ  ontological subordination ወይም “ኑባሬያዊ እንሰት” በማውገዝ የክርስቶስ ለአባቱ መገዛቱ ግብራዊ እንሰት/functional subordination ያመላክታል በማለት ወልድ ከአብ ጋር በባህርዮቱና በኑባሬው ከአባቱ ጋር እኩል ወይም አንድ አይነት (ሆሙስዮን ቶ ፓትሪ/ὁμοούσιον τῷ Πατρί) መሆኑን ገልጸውልናል።

በመጨረሻም ወልድ ለአባቱ መገዛቱ፤ መታዘዙ እና ያባቱን ፈቃድ ማገልገሉ በአባትና በልጅ መካከል ያለውን የማንነትና በባህሪም ሆነ በኑባሬ መተናነስን ሆነ መበላለጥን ፈጽሞ አያመለክትም። ቅዱስ ባስልዮስ በክታቡ፦

“…አብ ከወልድ ከመንፈስ ቅዱስ ተለይቶ አንዲት ሰዓት እንደ ዓይን ጥቅሻ ያህል ስንኳ አልነበረም ሁል ጊዜ ከነርሱ ጋር የነበረ የሚኖር ነው እንጂ።…”[1]

በማለት በሥላሴ መካከል አንዳች ብልጫ ወይ መተናነስ እንደሌለ ይሄ አባት ያስቀምጠዋል። የቆሮንቶስን መጽሐፍ ለመረዳት ከቅዱሳት መጽሐፍት ምሳሌ እንጠቀም። በሉቃስ ወንጌል ምእራፍ 2 በቁጥር 51 ላይ ጌታችን ክርስቶስ ኢየሱስ በናዝሬት ከተማ ለቤተሰቡ ይታዘዛቸው እንደ ነበር ቅዱስ ቃሉ ይነግረናል። በዚህ ክፍል ላይ ይታዘዝላቸዋል የሚለው የግሪክ ቃል ከ1ኛ ቆሮንቶስ 15፥28 ወልድ ለአባቱ እንደሚገዛ በሚናገረው ክፍል ጋር ተመሳሳይ ቃልን ነው የተጠቀመው፦ (ሃይፖታሶ/ὑποτάσσω)

“ከእነርሱም ጋር ወርዶ ወደ ናዝሬት መጣ፥ ይታዘዝላቸውም (ὑποτασσόμενος) ነበር። እናቱም ይህን ነገር ሁሉ በልብዋ ትጠብቀው ነበር።” ሉቃስ 2፥51

ከዚህም የምንረዳው ክርስቶስ ኢየሱስ ለቤተሰቡ ሲታዘዝ ከእነርሱ በማንነት፤ በባህሪዎትና በኑባሬ ተናንሶ ወይም ዝቅ ማለቱን ሳይሆን በልጅና በወላጅ መካከል ያለውን መታዘዝ ወይም የመከባበር መስተጋብር በሚያሳይ ረገድ መሆኑ እውቅና ቅቡል ነው። በሌላ በኩል ደግሞ በኤፌሶን ምእራፍ 5 በቁጥር 21-22 ሐዋርያው ጳውሎስ “…ለባሎቻችሁ ተገዙ(ሃይፖታሶ/ὑποτάσσω)…”  ብሎ ሲል ሴቶች ከወንዶች እንደሚያንሱ እየገለፀ እንዳልሆነ ለገላትያ የጻፈውን መልእክት በምእራፍ 3 በቁጥር 28 ላይ ባለው በቀላሉ እንረዳለን፦

“አይሁዳዊ ወይም የግሪክ ሰው የለም፥ ባሪያ ወይም ጨዋ ሰው የለም፥ ወንድም ሴትም የለም፤ ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናችሁና።”
— ገላትያ 3፥28

በሴትና በወንድ መካከል ያለው መተናነስ ኑባሬያዊ(ontological) ሳይሆን ግብራዊ መተናነስን(functional subordination) ነው የሚያመለክተው። ስለዚህ በቆሮንቶስ 15፥28 ጥቅስ መሠረት ወልድ ከአብ ያንሳል ማለት በፍፁም አይቻልም ማለት ነው። ጸጋ ሰላም ይብዛላችሁ።

ዋቢ ምንጭ

1] ሐይማኖት አበው ምዕራፍ ፴፫ ክፍል ፭

ለሌሎች ያጋሩ

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top