በማቴዎስ 28:19 በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም የሚለው ሐረግ የአካል ሦስትነትን አያሳይም የሚሉ መናፍቃን ሙግት የሚንድ ሆኖ የሚቀጥ ነው። ምክንያቱም ከስም ባሻገር የአካላዊ ሶስትነትን ያሳያል። በአንደኛው መቶ ክፍለ ዘመን ውስጥ እንደተጻፈ የሚታመነው ዲዳኬ (ትምህርተ ሐዋርያት) ጽሑፍ ላይ ስለ ጥምቀት ስርአት በማቴዎስ ወንጌል ላይ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተላለፈውን ትእዛዝና ሐዋርያት በዛ ዘመን እንዴት እንደሚያጠምቁ ሲያብራራ እንመለከታለን፦
"…ስለ ጥምቀትም ረገድ እንዲህ አጥምቁ፤ ይህን ሁሉ በመጀመሪያ ከተናገርክ በኋላ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም በሕያው ውኃ አጠምቁ ("…βαπτίσατε εἰς τὸ ὄνομα τοῦ πατρὸς καὶ τοῦ υἱοῦ καὶ τοῦ ἁγίου πνεύματος…")…….በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም ራስ ላይ ሦስት ጊዜ ውኃ አፍስሱ…" [ትምህርተ ሐዋርያት ስለ ጥምቀት ህግጋት][1]
አንዳንድ ጸረ ስላሴያውያን የማቴዎስ ወንጌል 28:19 የስላሴን አስተምህሮ አያሳይም በማለት ክፉኛ ሲሞግቱ እንመለከታለን። ነገር ግን ይሄ አካሄዳቸው የበኩረ ጽሑፋቱን ቋንቋ ያማከለ ሙግት ፈጽሞ አይደለም። ይሄም የሚያሳየው የሰዋሰው ሙግት ላይ ምን ያህል ደካማ መሆናቸውን ነው። ይባሱን ብሎ ጽሑፉ በጥንታውያን ክታባት ላይ አይገኙም የሚሉም መጥተዋል። ለዛሬ እኛ በማቴዎስ ወንጌል 28:19 ያለው ጽሑፍ ላይ እናተኩር። ጥንታዊ ሰነድ የሆነው ዲዳኬ (ትምህርተ ሐዋርያት) የጥምቀት ስርዓትን በተመለከተ የአብ የወልድና የመንፈስ ቅዱስ ስም ከመጠቀሱም ባሻገር አካላዊ ልዩነቶች (Personal Distinction) እንዳላቸው በግልጽ ያሳያል። ይህም ማለት አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ እያንዳንዱ አካል እኔነት እንዳለው የሚያሳይ ክፍል ነው። የክፍሉን የሰዋሰው መዋቅር ከመመልከታችን በፊት አንድ ወሳኝ ህግ እንመልከት፦
በ1735-1813 ይኖር የነበረው የግሪክ ቋንቋ ሊቅ እንዲሁም ባለ ብዙ ዘርፈ ሙያ ባለቤት የሆነው ግራንቪል ሻርፕ ስለ ውስን መስተኣምር አገባብ እና የአረፍተ ነገሩን አተረጓጎም ሒደት ላይ ባስቀመጠው ስድስት ህጎች መካከል በስድስተኛው ነጥብ ላይ እንዲህ የሚል መርህ እናገኛለን፦
“ሁለት ወይም ከዛ በላይ ተመሳሳይ ሙያ(case) ያላቸው ስሞች(የማዕረግ )፤ በ ‘እና/ካይ (καὶ)’ ተያይዘው፤ በስሞቹ መጀመሪያ ላይ ውስን መስተኣምር ካለ አረፍተ ነገሩ ስለ ተለያየ አካል(person) የሚናገር ነው”[2]
"πορευθέντες οὖν μαθητεύσατε πάντα τὰ ἔθνη, βαπτίζοντες αὐτοὺς εἰς τὸ ὄνομα τοῦ πατρὸς καὶ τοῦ υἱοῦ καὶ τοῦ ἁγίου πνεύματος"[Κατα Μαθθαιον 28:19]
- በአብ (ቶው ፓትሮስ/τοῦ πατρὸς)
- በወልድ (ቶው ሁዮው/τοῦ υἱοῦ)
- በመንፈስ ቅዱስ (ቶው አጊዮው ኒውማቶስ/τοῦ ἁγίου πνεύματος)
በዚህ ህግ መሰረት የማቴዎስ ወንጌል 28፥19 ያለው ክፍል ይሄንኑ ህግ አሟልቶ እንመለከታለን። አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ የሚሉት የማዕረግ ስሞች ተመሳሳይ ሙያ ያላቸው ነጠላ ስሞች(የቃል ክፍሉ Noun, የሙያ መደቡ Genitive case, የብዜት ቁጥሩ Singular) ስለሆኑ አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ የተለያዩ ማንነቶች እንደሆኑና ያልተጨፈለቁ አካላቶች መጠቀሳቸው በግልጽ ህጉ ይደግፍልናል። ይህ ደግሞ ስም ብቻ መጠቀሱን አይተን በቀላሉ እንድናልፍ የሰዋሰው ውቅረ ህጉ አይፈቅድልንም። በዚህም መስፈርት ከሄድን ከማቴዎስ ወንጌል በተጨማሪ በ2ኛ ቆሮንቶስ ም.13 ቁ.14 የሰዋሰው አወቃቀሩ ተመሳሳይ ነው የህጉን መስፈርት ያሟላል። ጸጋ ሰላም ይብዛላችሁ!
ዋቢ ምንጮች
[¹] Didache-ΔΙΔΑΧΗ ΤΩΝ ΔΩΔΕΚΑ ΑΠΟΣΤΟΛΩΝ 6:1
[²] W. D. McBrayer, ed., Granville Sharp’s Remarks on the Uses of the Definitive Article in the Greek New Testament (Atlanta: The Original Word, 1995), p.25. Once More, Matthew 28:19 and the Trinity, Robert M. Bowman, Jr