ሰላም እንደምን ቆያችሁን በባለፈው ልጥፍ ማለትም በመጽሐፍ ዳሰሳችን የትምህርተ ሥላሴ ቀዳማይ አመንጪ ጉባኤ ኒቂያ አለመሆኑን በአጭሩም ቢሆንም አይተናል። ይህ አይነት አስተሳሰብ ላላቸው(ቅድመ ኒቂያ ጉባኤ ያሉት የቤተ ክርስቲያን አበው ሥላሴን የሚገልጽ ነገር ፈጽሞ አላስተማሩም) ለሚሉት ትችት ታሪክን ካለማንበብ የመነጨ እንደሆነ እናስተውላለን። ይህንን ማሳያ ከሌሎች አበው አንጻር በማቅረብ እንዘልቃለን። የቤተ ክርስቲያን አበው ስለ ሥላሴ የነበራቸውን መረዳት እዚህ ጋር አምጥቶ መጻፍ እጅጉን ብዙ ነው። ከእነዚህም መካከል ጥቂቱን እናጋራችሁ፦
1)Clement of the Rome(30-95)
ቅዱስ ቀለሜንጦስ የሐዋርያውን ቅዱስ ጳውሎስን ኤፌሶን ላሉት ምእመናን በጻፈው መልእክት ላይ በምዕራፍ 4 ከቁጥር 4 እስከ 6 ባለው ሐሳብ ተሞርክዞ የስላሴን አንድነትና ሶስትነት ሲገልጽ እንመለከተዋለን፦
“….አንድ አምላክ፤ አንድ ክርስቶስ፣ በእኛ ላይ የፈሰሰው አንድስ የጸጋው መንፈስ ያለን አይደለንምን? [1]
ኤፌሶን 4፥4-6
"…⁴ በመጠራታችሁ በአንድ ተስፋ እንደ ተጠራችሁ አንድ አካልና አንድ መንፈስ አለ፤ ⁵ አንድ ጌታ አንድ ሃይማኖት አንዲት ጥምቀት፤ ⁶ ከሁሉ በላይ የሚሆን በሁሉም የሚሠራ በሁሉም የሚኖር አንድ አምላክ የሁሉም አባት አለ።(------ኤፌሶን 4፥4-6)
2)Hippolytus of Rome(3rd ce. earlier)፦
በ3ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ የሮሙ ሂፖሊተስ ኖተስ(Noetus) ለተባለ የሰምርኔስ ክርስቲያን(Christian from Smyrna) ሂፖሊተስ ምንፍቅና ነው ብሎ ያመነበትን የፓትሪፓሻውያንን አመለካከት ሲያራምድ ለነበረው መናፍቅ ምላሽ በኖተስ ላይ የጻፈው ጽሑፍ ስለ አስተምህሮተ ስላሴ እንዲህ ብሎ ሲሞግት እንመለከታለን፦
“…እንግዲህ የአብን መስተጋብራዊ ግንኙነትን፤ ፈቃዱንና አብም ከዚህ መንገድ ውጭ ሊመለክ እንደማይፈልግ አውቆ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀመዛሙርቱ ይሄንን ትእዛዝ ሰጣቸው፦’እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው…'(— ማቴዎስ 28፥19-20) ከእነዚህም አንዱን ያጎደለ ሰው እግዚአብሔርን ፍጹም በሆነ መንገድ እንዳላከበረ ጭምር አሳይቶናል። ምክንያቱም እግዚአብሔር የሚከብረው በስላሴ በኩል ነው። አብ ፈቅዷልና ወልድ አደረገ መንፈስ ቅዱስም ተገለጠ ይቺም የአብ ቃል ናትና…”[2]
3) ጠርጡሊያኖስ ወይም ተርቱሊያኖስ (Tertullian 160-215) ፦
የጥንቷ የቤተ ክርስቲያን አባት የሆነው ጠርጡሊያኖስ በስላሴያዊ አስተምህሮት ላይ ለሚነሱ ኑፋቄዎች መልስ በመስጠትና ቤተክርስቲያን እምነት ላይ ከሚሰሩ አቃብያነ አባቶች መካከል አንዱ ነው። ለምሳሌ በመናፍቃን ሙግት ላይ ባነሳው በፕራክሲየስ (against praxeas) ለሞዳሊስት አራማጅ የሆነው የፓትሪፓሺያን(Patripassian) ሐሳብ አንስቶ እንዲህ ሲል በሙግቱ ላይ ጽፏል፡-
“…ሶስቱ አብ፣ ወልድና መንፈሱ ናቸው። ሶስት ናቸው ነገር ግን በሁናቴ አይደለም በግብር እንጂ፤ በኑባሬም አይደለም በአካል እንጂ፤ በስልጣን ወይም በሐይል አይደለም በአይነት እንጂ ሆኖም ግን እግዚአብሔር አምላክ አንድ ኑባሬ፣ ስልጣን፣ ሐይል አለው ምክንያቱም በአካል፣ በግብርና በአይነት በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ የተገለጠ አንድ አምላክ ነውና…”[3]
4)አርጌንስ (Origen 185-254) ፦
አርጌንስ የተባለው አባት ከጠርጡሊያኖስ ትምህርት በመነሳት ከእርሱ ጋር በተመሳሰለ ሁኔታ ስለ አስተምህሮተ ስላሴን ሲደግፍ እንመለከታለን። ነገር ግን አርጌንስ በስላሴ አካላት መካከል እንደ ጠርጡልያኖስ በደረጃ (ወይም በsubordination) ረገድ ልዩነት መኖሩን እንደሚያምን ከጽሑፋቱ እንመለከታለን። ሆኖም ግን ኦሪገን የጻፈው የመጀመሪያው መርህ (De Principiis or Peri Archon) እጅግ ጥንታዊ የሆነ የስነ መለኮት ትምህርት ግኝት እንደሆነ ሊቃውንት ያትታሉ። በጽሑፉም ላይ በስላሴ ማመን እንዴት አስፈላጊ እንደሆነ አትቶልን እናገኛለን፦
“…ስላሴ ዘላለማዊ ነው……….በእርግጥ ከስላሴ ውጭ ያሉ ነገሮች ሁሉ በጊዜና በእድሜ ሊለኩ ይችላሉ። ደግሞም ማንም ሰው ለመዳን ወይም “እንደገና ከእግዚአብሔር ለመወለድ” አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ እንደሚያስፈልገውና ከሥላሴ እምነት ውጪ ደህነትን የማያገኝበትን እንዲሁም ያለ መንፈስ ቅዱስ የአብ ወይም የወልድ ተካፋይ መሆንን የማይችልበትን ምክንያት ለምን እንደሆነ መጠየቁ ተገቢ ይመስለኛል። በእነዚህ ነጥቦች ላይ በመወያየት ለመንፈስ ቅዱስ፣ ለአብ እና ለወልድ ልዩ የሆነውን ተግባር(አስተምህሮ) መግለጽ እንደሚያስፈልግ አያጠራጥርም።”[4]
5)Gregory Thaumaturgus-Wonder worker/ጎርጎርዮስ ገባሬ ተአምራት ወመንክራት/(205–270)፦
“ሁሉም(አካላቶች) አንድ ምንነት፤ አንድ ባህሪዎት እና አንድ ፈቃድ አላቸው። ይህ ደግሞ “ቅድስት ስላሴ” ተብሎ ይጠራል። እንዲሁም እግዚአብሔር በንዑሳን ስሞች፣ በአንድ ምንነት ሶስት አካላት እና በአንድ አይነት ዘር (አካላቶቹ በባህሪ ደረጃ) የተገለጠ አምላክ ነው።”[5]
ይሄን ካየን ከሁሉ በፊት የሌለ በኒቂያ ነው የሥላሴ ትምህርት የተጀመረው የሚልን ነገር በፍፁም እንደሙግት አንድም ሰው በክርስቲያኖች ላይ ሊያቀርብ በፍፁም አይችልም ማለት ነው። ሌሎች ተጨማሪ የቤተክርስቲያን አበው ላይ የሚነሳውን ተቃውሞ በባለፈው ልጥፋችን ጠርጡሊያኖስ በመቀጠል እንደምናስቀምጥ ነግረናችሁ ነበር። የሌሎቹንም አባቶች በክፍል በክፍል አደራጅተን የምናቀርብ ይሆናል። ጸጋ ሰላም ከሁላችን ጋር ይሁን
ማጣቀሻ
1] /1Clement 46:6/
2] /—Against Noetus Ch. 14./
3] /Against Paraxeas 2/
4] /De Principiis, book 1, chapter 3
The Trinity according to Origen/
5] Gregory Thaumaturgus, On the Trinity. ANF, VI:48