ትምህርተ ሥላሴ እና የቤተክርስቲያን ታሪክ

የመጽሐፍ ዳሰሳ [1]

በመጀመሪያ ይህን ክፍል ለማጥናት ምሥጢረ ስላሴ ምን ማለት ነው!?

የትምህርተ ሥላሴ ቀዳማይ አመንጪ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። አንዳንድ ሥላሴን ስሩን ሳይዙት አውቀን ጨርሰናል በማለት ሲናገሩ አስተውያለሁ በዕውነቱ ያሳዝናል ለዚህም ነው በተለይ በአባቶች መምህራን የምሥጢረ ሥላሴ   በስፋቱና በትልቅነቱ ሲነገርም እንዲህ ይባላል፦

“..ምሥጢረ ሥላሴን ጠልቆ ለማወቅ መሞከር ባሕረ ውቅያኖስን በዕንቁላል  እየቀዱ ለመጨረስ እየጨለፉም ለመጨለጥ እንደ ማሰብ ነው ይላሉ…” እውነት ነው፤ ለሰው ከተሰጡ ስራዎች ምሥጥረ ሥላሴን ከመመርመር የሰፋና እና የከበደ የለም።

➝ ሆኖም ስለ ሥላሴ በትክክል ማሰብ ለክርስቲያናዊ ኑሮ ዋንኛ ነገር መሆኑን አንባቢ ልብ ይበል። አይሁድ፣ ክርስቲያኖችና ሙስሊሞች አንድን አምላክ ሲያመልኩ፥ የሥላሴን ትምህርት በአንድ አምላክ ከሚያምኑ ሌሎች ሁሉ ክርስቲያኖች ይለዩዋቸዋል። ስለዚህ ክርስቲያን ለራሱ ብቻ ሳይሆን የራሱን እምነት ለሌሎች ለመግለጥም የሥላሴን ትምህርት ማወቅ ይገባዋል።

➝ሥላሴ የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ
አይገኝም። በግእዝ ቋንቋ ቃሉ ሦስትነት ማለት ነውና በትምህርተ መለኮት ጥቅም ላይ ሲውል..በአንዱ እግዚአብሔር ሦስት አካላት እንዳሉ ያሳስባል። በ2ኛው መቶ ዓመት የአንጾኪያ ጳጳስ የነበረው ቴዎፍሎስ በግሪክ ቋንቋ ትሪአስ እና ጠርጡሊያን በላቲን ቋንቋ ትርንታስ በእንግሊዘኛው ደግሞ TRINITY የሚለው ሲሆን፣ ቃሉ “Tri” ወይም “ሦስት” እና “Unity” ወይም “ኅብረት/አንድነት” ከሚሉት ሁለት የላቲን ቃላቶች የመጣና አንድ ቃል ሆኖ በተገናኝ የሚነበብ (“tri” + “unity” ) ነው።

ሥላሴ የሚለው ቃልና ትምህርቱ እንደ መነጥር ሆነው በመፅሐፍ ቅዱስ ያለውን ትምህርት ጉልሕ ሆኖ እንዲታየን ያደርጋሉ እንጂ በእግዚአብሔር ቃል ላይ አዲስን ትምህርት አይጨምሩም። ትምህርተ ሥላሴ ለክርስቲያን ረቂቅ ፍልስፍናም አይደለም። ወደፊት እግዚአብሔር ቢፈቅድ ሥላሴን በደንብ እንመረምራለን። ወደ ዋናው ርዕሳችን ወደ ሚያንደረድር ሀሳብ ስንመለስ፦

ትምህርተ ሥላሴ እንደ አርዮስ ያሉ የመናፍቃን ጥቃት በቤተክርስቲያን ላይ ሲያደርሱ የመጠበቁ ሂደት ውስጥ ትልቅ ድርሻ ከነበራቸው አትናቴዎስ(Athanasius) አንዱ ቢሆንም ርእሰ ጉዳዩን በዳበረ መልኩ የተነተኑት ቀጰዶቃውያን አበው ናቸው። በመጀመሪያ ከዛ በፊት ቀጰዶቃውያን አበው እነማን ናቸው የሚለውን በጥቂቱ እንመልከት…

ቀጰዶቃውያን አበው(Cappadocian Fathers) የሚባሉት ውስጥ፦

  1. የቂሳርያው ትልቁ አባት ባልዮስ( Basil The Great)
  2. ጎርጎርዮስ ዘእንዚናዙ(Gregory of Nazianzus)
  3. ጎርጎሪዮስ ዘኑሲስ (Gregory Nyssa) ናቸው። ከላይ እንዳልኳቹህ እንደ እግረ መንገድ ዳሰሳ አደረግን እንጂ ወደፊት በስፋት እንመለከተዋለን።

ትምህርተ ሥላሴ በቤተክርስቲያን ታሪክ ቅድመ ጉባኤ ኒቂያ አበው ግንዛቤአቸው ምን ነበር?

ከላይ እንዳየነው ሥላሴ የሚለው ቃል በአዲስ ኪዳን ባይገኝም ትምህርተ ሥላሴ የነገረ መለኮት ዐብይ ርዕስ መሆኑን አይተናል። የአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች ምን ያህል ትምህርተ ሥላሴን እንደተረዱት ባናውቅም ግን፥ እግዚአብሔር ሦስት አካላት እንዳሉ አምነው የመለኮትን አንድነትንና የአካል ሦስትነትን ለትምህርታቸው መሠረት አደረጓቸው። የትምሕርተ ሥላሴ ቀዳሚ አመንጪ መጽሐፍ ቅዱስ ቢሆንም፣ በሐዋሪያት እግር ስር የተማሩ ቀደምት የሆኑ የቤተክርስቲያን አበው ምን አሉ የሚለውን ጉዳይ መቃኘት፣ የተዛባ የታሪክ መረጃ ያላቸው ሰዎችን ለማቅናት ጠቃሚነት ስላለው ይህ ጽሑፍ ዳሰሳዊ ጥናት ስለሆነ የሁሉንም አበው እማኝነትና ትምህርት በክፍል አንድ በስፋት ማቅረብ ስለማይቻል በተወሰነው እንመለከታለን።

1) ጶሊቃርጶስ (Polycarp) :- በ70ዓ.ም ተወልዶ በ155 ዓ.ም ወይም በ160 ዓ.ም የሞተ፣ የሐዋሪያው ዮሐንስ ደቀ መዝሙር የነበረ እንዲሁም የሰምርኔስ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳሳት የነበረ ሰው ነው።..ይህ ሰው ትምህርተ ሥላሴን በተመለከተ እንዲህ ብሏል፦

“ሁሉን ቻይ እግዚአብሔር ሆይ…ዘላለማዊና ሰማያዊ በሆነ ሊቀ ካህናት በምትወደውና ባከበርኸው ልጅህ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ለአንተና ለእርሱም እንዲሁም ለመንፈስ ቅዱስ አሁንም ሆነ ለዘላለም ክብር ይሁን”[2]

2) ዮስጦስ ሰማዕት (Justin Martyr) ፦ የቤተክርስቲያን አቃቤ እምነት የነበረና የሰማዕትነትን ክብር የተቀናጀው ይህ አባት አባት በ100 ዓ.ም ተወልዶ በ165 ዓ.ም እንደ ሞተ ይገመታል። ይህ አባት ትምህርተ ሥላሴን በተመለከተ እንዲህ ብሏል፦

“የዓለማት ጌታ በሆነው በእግዚአብሔር በስመ አብ፣ በመድሐኒታችንም ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲሁም በመንፈስ ቅዱስ በውሃ መታጠብን ያገኛሉ”[3]

3)አግናጢዮስ ዘአንጾኪያ (Ignatius of Antioch) ፦ የአንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳሳት የነበረና በ98 ዓ.ም ወይም በ117 ዓ.ም እንደሞተ የሚገመት ክርስትናን ከመናፍቃን በመከላከሉ ዙሪያ ብዙ የጻፈ ዐቃቤ ክርስትና ነው። እንዲህም አለ፦

“በእምነትና በፍቅር፤ በወልድ፣ በአብና በመንፈስ ቅዱስ፤ በመጀመሪያው እና በመጨረሻው፤ ከሚያስደንቅ ጳጳስችሁ ጋር እናም እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ካሉ ዲያቆናት ጋር በሚገባ በጠበቀ መንፈሳዊ አክሊል የምታደርጉትን ሁሉ በስጋና በመንፈስ እንዲከናወን በጌታችንና በሐዋርያት ትምህረት እድትጸኑ አጥኑ። ክርስቶስ ኢየሱስ ለአብ በስጋው እንደተገዛለት እናም ሐዋርያት ለክርስቶስ፣ ለአብና ለመንፈስ ቅዱስ እደሚታዘዙ እናንተም ለጳጳሳችሁ እና እርስ በእርሳችሁ ተገዙ(ታዘዙ) በዚያን ጊዜ በስጋችሁም በመንፈሳችሁም አንድነት ይኖራችኋል።”[4]

4) ጠርጡሊያኖስ ወይም ተርቱሊያኖስ (Tertullian 160-215) ፦ አፍሪካዊ ዕቃቤ ክርስትና እንዲሁም የነገረ መለኮት ሊቅ ነው። ክርስትናን ከመናፍቃንና ከሌሎች ሐያስያን ለመከላከል ብዙ ጽፎአል፦

“አብና ወልድ ሁለት ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ደግሞ ሦስት መሆናቸውን እንገልጻለን። የቁጥሩንም ቅድመ ተከተል ከድነት አንጻር ነው….ይህም አንድነትና ሦስትነትን መሠረት አድርጎ ሦስቱንም ማዕከል ያደረገ ነው፤ እነርሱም አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ። [አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ] ሦስት ናቸው….ነገር ግን በባሕርይ ሳይሆን በገጽ፣ በኀይል ሳይሆን ነገር ግን በዐይነት። በባሕርይና (Substance) በኀይል አንድ ናቸው፤ ምክንያቱም አንድ አምላክ ብቻ ስላለና ይህም ባሕርይ፣ ገጽና ዐይነት በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ዙሪያ ያለ በመሆኑ”[5]

5) አርጌንስ (Origen 185-254) ፦ የእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን የነገረ መለኮት ምሁር ነው። አርጌንስ ክርስትናን በተመለከተ ብዙ የጻፈ ነው፦

“የእግዚአብሔር ቃል ወይም የእግዚአብሔር ጥበብ ጅማሬ አለው የሚል ማንኛውም ሰው፣ ቢያንስ እግዚአብሔርን መናቁ እንደሆነ ልብ ሊለው ይገባል…ምክንያቱም እግዚአብሔር ባለፉት ዓመታት ሆነ ዘመናት ከዚህ ውጪ ሊገመት በሚችልበት ጊዜ ሁሉ፣ እግዚአብሔር የጥበብ ባለቤት ነውና ይህ እውነት ለእግዚአብሔር አብ እንደሆነው ሁሉ ለወልድም ነው”[6]

“እውነታው ይህ ከሆነ [መንፈስ ቅዱስ አሁን እንደ ሆነው ሁሉ ዘላለማዊ ካልሆነ፣ በዘመናት ውስጥ ዕውቀትን ገብይቶ መንፈስ ቅዱስን መሆን ከቻለ] መንፈስ ቅዱስ ለዘላለም ዓለም መንፈስ ቅዱስ መሆን ካልቻለ፣ እንደማይለወጠው አብና እንደ ልጁ ሁሉ መንፈስ ቅዱስ የሥላሴ አንዱ አካል ነው ማለት አይቻልም”[7]

“የመለኮት ምንጭ ብቻ ሁሉን ነገር በቃሉና በምክንዩው የሚይዝ ከሆነ፣ በሥላሴ አካላት ውስጥ መበላለጥ ወይም መተናነስ የለም”[8]

ሔሬኔዎስ(Irenaeus)፦ በ115 ዓ.ም ተወልዶ 190 ዓ.ም ሞተ፣ በልጅነቱ የሐዋርያው ዩሐንስ ደቀ መዝሙር ከነበረው ከጶሊቃርጶስ እግር ሥር የተማረ እንዲሁም የልዮን ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳሳት የነበረ ሰው ነው፦

“ቤተ ክርስቲያን በዓለም ሁሉ እንዲሁም እስከ ዓለም ዳርቻ ድረስ ብትበተንም፣ ቤተ ክርስቲያን ከሐዋርያትና ከእነርሱ ደቀ መዛሙርት የተቀበለችውን የሚከተለውን መሠረተ እምነት ነው፦…..ሁሉን ቻይ የሆነ እና ሰማይንና ምድርን እንዲሁም ባሕርን በእነዚህም ውስጥ የሚኖሩትን ሁሉ የፈጠረ አንድ እግዚአብሔር፤ በእግዚአብሔር ልጅ በአንዱ በኢየሱስ ክርስቶስ፣ ለድነታችን ሲል ትስብእት የሆነ፣ በመንፈስ ቅዱስ፣ የእግዚአብሔርን ዘመን በነብያቱ ያበሠረ እንዲሁም የተወዳጁ ጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ምጽአት፣ ከድንግል መወለድ፣ ሕማም፣ ከሙታን መነሣት፣ በአካለ ሥጋ ወደ ሰማይ ማረግ፣ “ሁሉን አንድ አድርጎ ለመሰብሰብ በአብ ክብር ከሰማይ መገለጥ፣ የሰው ልጆችን ሁሉ በአዲስ አካል ከሙታን ማስነሳት፣ ይኸውም ክርስቶስ ኢየሱስ ጌታችንና አምላካችን እንዲሁም አዳኛችንና ንጉሣችን መሆኑን፣ በማይታየው አብ ፈቃድ “በሰማይና በምድር ከምድርም በታች” ያለ ጉልበት ሁሉ እንዲበረከክለት፣ ምላስም ሁሉ ኀጢአት ብሎ እንደ ተሰዋ እንዲመሰክርለት ነው…”[9]

ከጉባኤ ኒቂያ በፊት እንዲህ አይነት እምነት ያላቸው ከሆነ፣ የአስተምሮው ቀዳማይ አመንጪ ጉባኤ ኒቂያ ነው የሚባል ነገር ፈፅሞ የለም። ከሁሉ በፊት የሌለ በኒቂያ ነው የሥላሴ ትምህርት የተጀመረው ቢባል እንኳን ክርስቲያኑ ማህበረሰብ ከቀድሞው አስተምሮው ጋር የማይጣጣም ነው በሚል ተቃውሞ ለምን አላቀረበም? ለምንስ አላወገዘም? ኖሮስ ካለ ለምን በታሪክ ተዘግቦ አልተገኘም!?

እነዚህን ከዚህ መጽሐፍ ዳሰሳ ካየን በተጨማሪ ጥናት ደግሞ በክፍል ሁለት ተመሳሳይ ሙግት አንስተን በጠርጡልያኖስ ላይ የሚነሱትን ሙግቶች የምንዳስስ ይሆናል።

ማጣቀሻ

1] ትምህርተ ሥላሴ መሠረታውያን በዶ/ር ተስፋዬ ሮበሌ

2] Martyrdom of Polycarp, 14. ANF, I:42.

3] Justin, First Apology, LXI. ANF, I:183.

4] Epistle to the Magnesians, Chapter 13

5] Tertullian, Against Praxeas, 2. PL 2.156–57.፣ በቅንፍ ያለውን አይጨምርም።

6] De Princ. 1.2.; PG 11.132).

7] Alexander Roberts and James Donaldson, eds., The Ante-Nicene Fathers, Grand Rapids: Eerdmans, 1975 rpt., Vol. 4, p. 253, de Principiis, 1.111.4)

8] Roberts and Donaldson, Ante-Nicene Fathers, Vol. 4, p. 255, de Principii., I. iii. 7

9] Irenaeus, Against Heresies X.1

ለሌሎች ያጋሩ

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top