“የእንበረም(አምራም/עַמְרָם) ሚስት ስም ዮካብድ(ዮኬቬድ/יוֹכֶבֶד) ነበረ። እርስዋ በግብፅ ከሌዊ የተወለደች የሌዊ ልጅ ነበረች፤ ለእንበረምም አሮንንና(አኻሮን/אַהֲרוֹן) ሙሴን(ሞሼኽ/מֹשֶׁה) እኅታቸውንም ማርያምን(ሚርያም/מִרְיָם) ወለደችለት።”— ዘኍልቁ 26፥59
በመጽሐፍ ቅዱሳችን መሰረት የአሮን (አኻሮን/אַהֲרוֹן)፣ የሙሴና(ሞሼኽ/מֹשֶׁה) የነብይቷ ማርያም(ሚርያም/מִרְיָם) አባታቸው እንበረም(አምራም/עַמְרָם) ነው።
እንበረም በእብራይስጡ አምራም/עַמְרָם በ ፊደል ሜም “ם” ሲያበቃ በአረበኛው መጽሐፍ ቅዱስ ላይ አምራም(عمرام) በፊደል ሚም(م) የሚጨርስ ቃል ነው፦
أبْناءُ عَمْرامَ هُمْ هارُونُ وَمُوسَى وَمَرْيَمُ
የእንበረምም ልጆች አሮን፥ ሙሴ፥ ማርያም።”— 1 ዜና 6፥3
በቁርአኑ ላይ ደግሞ ኢምራን(عمران) በፊደል ኑን(ن) በሚያበቃ ስም ተጠቅሶ እናገኘዋለን[¹]።
ذكر نسب موسى بن عمران
(የአት-አጠበሪ ታሪክ ቅጽ3)
ቀዓት(ቀኻት/קְהָת) ልጅ የሆነው እንበረም(1 ዜና 6፥2) የመጀመሪያ ልጁ ነብይቷ ማርያም ስትሆን ሙሴ እና ወንድሙ አሮን የተወለዱት 1400-1500 ዓ.ዓ እንደሆነ ይታሰባል[²]። ከዚህ ሁሉ ዘመናት በኋላ በዘመነ አዲስ ኪዳን ጊዜ የጌታችንና የመድኃኒታችን እናት የሆነችው ቅድስት ድንግል ማርያም ኢየሱስን እንደወለደች ቅዱሱ መጽሐፋችን ይነግረናል። መጽሐፍ ቅዱስ የቅድስት ድንግል ማርያምን አባትና እናት ባይጠቅስልንም ብዙ ድርሳናትና ታሪካዊ መጽሐፍት ኢዮአቄም(Joachim) እና አና(Anne) እንደሆኑ ይነግሩናል[³]።
ባጭሩ የሙሴ እህት ነብይቷ ማርያም ጺን ምድረ በዳ እንደሞተች በኦሪት ዘኍልቁ ም.20 ቁ.1 ላይ እንመለከታለን። ቅድስት ድንግል ማርያም ከሙሴ እህት ማርያም ጋር በማንነት ሆነ በነበሩበት ጊዜ ይለያያሉ። እንደዚህ ያክል የመጽሐፍ ቅዱሱን በንጽጽራዊ ትንተና ከተመለከትን ወደ ቁርአኑ እንለፍና የመሐመድን በታሪክ ላይ የፈጸመውን ወንጀል እንመልከት፦
መሐመድ በቁርአኑ ላይ የኢሳ እናት ማርያምን እና የነብዩ ሙሴ እና የአሮን እህት ማርያምን እንደ አንድ ሴት አድርጎ ማስተማሩ ነው!!!
የብዙ ዘመናት ልዩነት ያላቸው በሁለት ታሪኮች መካከል ያለ መመሳሰልን ማለትም፦
➙ የሙሳ ወንድም ሃሩን እና የኢሳ እናት ወንድም ሃሩን
➙የሙሳ አባት ኢምራን እና የኢሳ እናት አባት ኢምራን
➙ ራሷ ባለ ታሪኳ የኢሳ እናት መርየመ እና የሙሳ እህት መርየም
ያለውን መመሳሰል ስንመለከት በይበልጥ ታሪኩን እንድንመረምር አድርጎናል። በዚህም ጉዳይ በርከት ያሉ ዳዒዎችና ለእስልምናና ለመሐመድ ዘብ(ጥበቃ) እቆማለሁ የሚሉት ዳዕዋጋንዲስቶች የሙግት ነጥብ ይሆኑናል ብለው የሚሰነዝሯቸውን ነጥቦች እንመልከት፦
የስም መመሳሰል፦
በዚህ የሙግት ነጥባቸው ላይ የኢሳ እናት የሆነችው የመረየም ወንድም ሃሩንና የሙሳ ወንድም ሃሩን ሁለት የተለያየ ማንነትና በተለያየ ጊዜ የነበሩ ሰዎች ናቸው ይላሉ። ይሄን የሙግት ነጥባቸውን ይደግፍልናል ብለው የሚጠቅሱት ሐዲስ አል-ሙጊራህ ኢብኑ ሹዕባ የሚባል ሰው ወደ ነጅራን በሄደ ጊዜ በዛ አካባቢ ያሉ ክርስቲያኖች በሱረቱል መርየምን (19:28) ላይ የተጠቀሰውን «…የሃሩን እኅት ሆይ!…» የሚልን ጽሑፍ እንዳነበቡና ሙሳ ደግሞ ከዒሣ ብዙ ጊዜ በፊት እንደነበር በነገሩት ጊዜ ጥያቄውን ይዞ ለመሀመድ አቀረበላቸው። መሀመድም በመልሳቸው “የድሮ ሰዎች ከራሳቸው በፊት ከነበሩት የነቢያቶች ስሞች ከነቢያቱ ህልፈት በኋላ ይጠቀሙ ነበር” ብሎ ነገረው(ኢማም ሙስሊም መጽሐፍ 38 ሐዲስ 13)።
አስተውሉ፦ በሐዲሱ መሠረት የመጽሐፉ ባለቤቶች የሚባሉት ክርስቲያኖች ስለ ኢየሱስ እናት የማርያም ወንድም ስለሆነው አሮን የሚባል ወንድም እንዳላት በጭራሽ የማያውቁ እንደሆኑና አል-ሙጊራህ ኢብኑ ሹዕባ የሚባለው ሙስሊም ሙእሚን ግራ ተጋብቶ ጉዳዩ ጥያቄ እንደፈጠረበት እንመለከታለን። በተጨማሪም የምእመናን እናት የሆነችው አዒሻ (ኡም አል-ሙእሚኒን/أمّ المؤمنين) እንኳን እንደማታውቅ ከከዓብ (ረዐ) ጋር ባደረገችው ንግግር እንረዳለን[⁴]
“…’የሃሩን(የአሮን) እህት!’ (የሱራ 19 28) የሙሴን ወንድም አሮንን አያመለክትም። ዓኢሻ(ረዐ) ለከዓብ(ረዐ) “ #ዋሽተሃል” በማለት መለሰችለት።….”
(ተፍሲር ኢብን ከሲር 19:28)
በእነዚህ ሁሉ ሰዎች ማለትም ለአንዳንድ ሙስሊሞች እንግዳ የሆነና በመሐመድ ዘመን የነበሩት የተማሩ ዐረብ ክርስቲያኖች(የመጽሐፉ ባለቤቶች) የማየታወቅን ታሪክ መሐመድ ከየት አምጥቶ ነው አሮን(ሃሩን) የሚባል የማርያም(መርየም ) ወንድም አለ ያለን? በተጨማሪም የኢሳ እናት የሆነችው የመረየም ወንድም ሃሩንና የሙሳ ወንድም ሃሩን የተለያዩ ሰዎች ናቸው ካሉን አንድ ወሳኝና አነጋጋሪ ጥያቄ መጠየቃችን አይቀሬ ነው በታሪክ ስለማይታወቀው ሰውዬ(የኢሳ እናት የመረየም ወንድም ሃሩን ተብዬው) እንደዚህ ያክል አስፈላጊና የኢሳ እናት መረየም በእርሱ እስከምትጠራ ስላስደረገው ሰው እንዴት ቁርአን ችላ ብሎ አለፈው እናም ስለሱ የሚናገሩ የታሪክ መዛግብት እንዴት ልናጣ ቻልን? ወይም ደግሞ የሙሴ (ሙሳ) ወንድም የሆነውን አሮንን(ሃሩን) የኢሳ እናት ለሆነችው ማርያም(መርየም) ወንድም መስሎት እንደነበር ይሄም ደግሞ የመሐመድ አላዋቂነት ማለትም በታሪክ ላይ የሰራው ወንጀል መሆኑን ማወቅ ይጠበቅብናል።
ኢኽዋህ(إِخْوَة)
የሙሳ ወንድም እና የመርየም ወንድም አንድ ማንነት ናቸው ስንል አማኞች ወንድም እና እህት ናቸው በሚል ቀመርና ስሌት ነው ይሉናል። ይሄም የሙግት ነጥባቸው መፍለክለኪያ(ማምለጫ) ያጣ ሰው ለማምለጫ ከሚፈጥረው ቀዳዳ ተለይቶ አልታየኝ። በሃገሬው አባባል “…ከቀዳዳ ይሻላል ጨምዳዳ…” እንደሚባለው ነጥቦቻቸው የመሐመድን ስህተት መደበቅ ሳይችልላቸው ሲቀር ከአንዱ ወደ አንዱ በይሻላል መንፈስ ይራወጣሉ። ለማንኛውም በአማኞች መካከል ኢኽዋህ(إِخْوَة) ማለትም ወንድማማችነትና እህትማማችነት ቢኖርም አሁንም የሱረቱል መርየም(19:28) ከጥያቄ አያመልጥም።
ቁርአኑ ስለ ሙሳ ከወንድሙ ሃሩን ይልቅ በስፋት ነግሮን ሳለ ሙሳ ሳይጠቀስ ሃሩን የተጠቀሰበት አግባብ ግልጽ አይደለም።
ደግሞስ መርየም አባቷ ኢምራን እያለ በሙሳ ወንድም በሃሩን ስም መጠራቷ ምንን ያመለክታል? ደግሞም በሌላ ክፍል በሱራ 33 እና 66:12 ላይ “የኢምራን ሴት ልጅ” በመባሏ ወደ ሱራ 19:28 ስንመጣ ከሩቅ ዘመን ባለ ሰው ስም መጠራቷ ጉዳዩን የበለጠ ብዥታንና እና ችግርን አስከትሏል። ለዚህ ሁሉ ጥያቄ መልስ የሚሆነው የመሐመድን ስህተት መቀበል ነው።
በተጨማሪም መሐመድን ለዚህ ትልቅ ስህተት ያበቃው አንዳንድ ምንጫቸው በቅጡ ከማይታወቁ በክርስትናው ላይና በአይሁዳውያን መጽሐፍት ላይ ከሚጨመሩ አፈታሪኮች የሰማውን በራሱ አገላለጽ ስለሚዘግብ ነው። ሱረቱ መርየም የተወሰኑ ክፍሎች የአፖክሪፋን ታሪኮች እንደ የያዕቆብ ፕሮቶቫንጄሊየም (Protoevangelium of James) እና የሐሰተኛው-ማቴዎስ ወንጌል(gospel of Pseudo-Matthew) ካሉ አፈ ታሪኮች የአዋልድ ታሪኮች ተመሳሳይነት ያለው ታሪክ እናገኝበታለን። ለምሳሌ የቴምር ዛፉ ስር የተፈጠረው ታሪክ[⁵] ስለ መርየም ወላጆች ታሪክ[⁶] ለአብነት ተጠቃሽ ናቸው። በተጨማሪም በአረባዊቷ ምድር በፍልስጤም ውስጥ በቅድስት ድንግል ማርያም የተሰየመ የባይዛንታይን ቤተክርስቲያን አለ።
ይህ ቤተክርስቲያን ከእስልምና ወግ ጋር ጥልቅ እና የተወሳሰበ ግንኙነት አለው እንዳለው ታሪክ ይነግረናል። በመሐመድ ዘመን አካባቢ ይህች ቤተክርስቲያን የክርስትና አምልኮ ማዕከል ነበረች። በቅዳሴ ወቅት ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭ ከሚነበበው ከካቶሊክ እና ከኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በተቃራኒ በዚህ ጊዜ ለንባብ ከአፖክሪፋ እና ከሌሎች ቀኖናዊ ያልሆኑ መጽሐፍት መነበቡ የተለመደ ነው። በተጨማሪም የተለያዩ የክብረ በዓላት የምታከብር ቤተ ክርስቲያን ነበረች። ለምሳሌ ላይ በነሐሴ ወር አጋማሽ ላይ ቀን 14 ከነብዩ ኤርምያስ ሕይወትም ከአዋልድ መጽሐፍት ይነበብ ነበር። በምንባቡ ላይ መሐመድ በሱረቱል በመርየም ላይ እንዳሰፈረው አይነት ማለትም ሃሩን(አሮን) የማርያም (መርየም) ወንድም በማለት የተጠቀሰን ጽሑፍ እናገኛለን[⁷]፦
“ነቢዩ [ኤርምያስም] እንዲህ አለ – መምጣቱ ለእርስዎ እና ለሌሎች ልጆች በዓለም ምልክት መጨረሻ ይሆናል ።
57 እንዲሁም የተደበቀውን ታቦት ከዓለት ላይ የሚያወጣ የለም ከማርያም ወንድም አሮን በስተቀር ።
(The Lection of Jeremiah)
በተመሳሳይ ሁኔታ ቁርአኑ ስለ ማርያም (መርየም) ሲናገር ሃሩን(አሮን) የማርያም (መርየም) ወንድም እንደሆነ ዘግቦልን አግኝተናል፦
19፥28 « የሃሩን እኅት ሆይ! አባትሽ መጥፎ ሰው አልነበረም፡፡ እናትሽም አመንዝራ አልነበረችም» አሏት፡፡ يَا أُخْتَ هَارُونَ مَا كَانَ أَبُوكِ امْرَأَ سَوْءٍ وَمَا كَانَتْ أُمُّكِ بَغِيًّا
በመጨረሻም ለመሐመድ ዘብ እንቆማለን ባዮቹ አብዱሎች ታሪክን በመደበቅ የመሐመድን ስህተቶችና አላዋቂነቱን ለመደበቅ መፍጨርጨራቸው የሚያዋጣ አይደለም። መሐመድ ከታሪክ አንጻር ሲሳሳት ይሄ የመጀመሪያው እንዳልሆነ ከታሪክ መዛግብት ዘንድ ብዙ መረጃዎችን ስንበረብር የሚጋለጥ ሐቅ ነው። እስከምንገናኝ በክርስቶስ ፍቅር ቸር ሰንብቱ!
ማጣቀሻዎች እና ማስፈንጠሪያዎች
[¹] https://al-maktaba.org/book/9783/383
[²] የተለያዩ የታሪክ ተመራማሪዎች እና ጸሐፊዎች ስለ ሙሴ የውልደት ዘመን ላይ የተለያየ አስተያየቶችን ሰንዝረዋል። በአማካይ ከወሰድነው ሙሴ እና ወንድሙ አሮን የተወለዱት 1400-1500 ዓ.ዓ ገደማ እንደሆነ አብዛኞቹ ምሁራን ይስማሙበታል(Seder Olam Rabbah,
Jerome’s Chronicon (4th century) gives 1592 for the birth of Moses,The 17th-century Ussher chronologycalculates 1571 BC (Annals of the World, 1658 paragraph 164)
[³] The gospel of the birth of Mary, 1:1-2, Gambero, Luigi (1999). Mary and the Fathers of the Church: The Blessed Virgin Mary in Patristic Thought. Ignatius Press.ISBN 978-0-89870-686-4.
[⁴] https://quran.al-islam.com/Page.aspx?pageid=221&BookID=11&Page=1
[⁵] The Gospel of Pseudo-Matthew Chapter 20
[⁶] Protoevangelium of James Gospel
[⁷] Guillaume Dye, “The Qur’ān and its Hypertextuality in Light of Redaction Criticism,” The Fourth Nangeroni Meeting Early Islam: The Sectarian Milieu of Late Antiquity? (Early Islamic Studies Seminar, Milan) (15-19 June 2015)