ኢድ አል አድሃ(عيد الأضحى) ኢድ(عيد) ማለት በአል፣ ድግስ ወይም ለመታሰቢያነት የሚከበር ነገር ማለት ሲሆን አድሃ (أضحى) ወይም ቁርበን (قربان) ወይም ደግሞ የእብራይስጡ አቻ ቃል ቆርባን(קׇרְבָּן) ማለት “መስዋዕት/መባ” ማለት ነው። ኢድ አል አድሃ ሁለተኛው የሙስሊም ወገኖቻችን ክብረ በአል ነው። በዚህም ክብረ በአል ሙስሊም ወገኖቻችን ለመስዋዕትነት የሚሆነውን የበግ፣ የግመል፣ የፍየል ወየም የጠቦትን…ወዘተ የመሳሰሉትን የእንስሳትን ደምን ያፈሳሉ። የበአሉ እርሾ ወይም ጅማሮ በቁርአን ውስጥ የኢብራሂም(ዐሰ) ልጁን ለአምላኩ ለመሰዋት የታዘዘበትን ቀን ለማሰብ ሲባል የሚከበር በአል ነው። በቁርአን ላይ አላህ በሱረቱ አልሷፍፋት (የተሰላፊዎቹ ምዕራፍ) ላይ ስለ ተሰላፊዎች እምነት በሚናገርበት ክፍል በቁጥር 83 ላይ ከአማኞች መካከል የሆነው ኢብራሂም (ዐሰ) አንደኛው እንደሆነ ይናገራል። በዛው ክፍል በቁጥር 100 ላይ ደግሞ ኢብራሂም (ዐሰ) አንድን ጸሎትን ሲጸልይ እንመለከታለን፦
As-Saffat 37:100
ጌታዬ ሆይ! ከመልካሞቹ የሆነን (ልጅ) ስጠኝ፡፡(رَبِّ هَبْ لِى مِنَ ٱلصَّلِحِينَ)
የኢብራሂምም አምላክም ታጋሽ በሆነ ወጣት ልጅም ባሪያውን አበሰረው። ኢብራሂም (ዐሰ) ከባዱ ፈተና የሚጀምረው በቁጥር 102 ላይ ነው። አምላኩ የሰጠው ልጅ ለስራ በደረሰ ጊዜ ኢብራሂም (ዐሰ) በራዕይ አንድ ልጁን እንደሚያርድ ሁኖ ያልማል። እርሱም ለልጁ ስለ ራዕዩ ምን እንደሚያስብ በጠየቀው ጊዜ “የታዘዝከውን ሥራ” ብሎ ሲፈቅድለት እንመለከታለን።
አሁን ዋናው ጉዳይና ጥያቄ ያ ለኢብራሂም (ዐሰ) የተበሰረው የመስዋዕቱ ልጅ ማነው? የሚለው ንግርት ነው!
የዘመናችን የሙስሊም ኡስታዞች ሽንጣቸውን ገትረው በመከራከር በቁርአኑ ላይ የመስዋዕቱ ልጅ ኢስማኢል ለማስመሰል የቁርአኑን አያህ የማይቀባቡት ነገር የለም። ከሁሉም በላይ ደግሞ አጃኢብ የሚያስብለው ጥርት እና ጥንፍፍ ብሎ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተነገረለትን የቃል ኪዳን ልጅ ይስሐቅን በእስማኤል ተክተውና አንሻፈው የመስዋዕቱ ልጅ እስማኤል እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል ማለታቸው ነው። “..የያዙት ነገር..” እንደሚሉት አበው በእኛ ዘንድ የሙስሊም ኡስታዞች መካከል ይሄንን ዜማ መስማቱ የተለመደ ነው። ሲጀመር ኡስታዞቹ የማይሆን የማይሆን የሙግት ነጥቦቻቸውን እየሰካኩ ለሙስሊሙ ተደራሲያን እየፈተፈቱ ሲያጎርሷቸው እኛንም (የክርስቲያኑን ማህበረሰብ) ለማታለል መጣጣራቸው ሳስብ ይገርመኛል። ለማንኛውም የኡስታዞቻቸውን ድርሳነ ባልቴት ወይም የአሮጊቶች ተረት የሆነውን የሙግት ሐሳባትን በሁለት ጎራዎች ከፍለን ስለ መስዋዕቱ ልጅ ማንነት እንመለከታለን፦
የቁርአናዊ ሙግት
በመጀመሪያ ኢስማኢል ነብይ መሆኑ ለመስዋዕትነት የተዘጋጀው ልጅ እርሱ ነው የሚያስብለን አንድምታ የለም። ምክንያቱም እንዲሁ ኢስሐቅም ነብይ መሆኑን ቁርአናቸው ይነግረናል(Al-‘Ankabut 29:27)።[1] ስለዚህ ስለ ኢስማኢል ነብይነት መጥቀስና ማጠቃቀስ ጉንጭ ማልፋት ካልሆነ በስተቀር ለሙግቱ እንብዛም ውጤት የለውም። ለማንኛውም ኡስታዞቹ ያነሷቸውን ዋና ዋና ነጥቦችን እንመለከታቸዋለን።
ቀጠሮ አክባሪው
የዘመናችን የሙስሊም አቃብያነ እምነት ነን የሚሉት በሱረቱ መርየም 54 ላይ የተጠቀሰውን ክፍል ከሱረቱ አልሷፍፋት 102 ጋር በማጣመር የተሳሳተ ምስስሎሽን (wrong analogy) በመፍጠር ለመስዋዕትነት የቀረበው ኢስማኢል መሆኑን ለማሳየት ሞክረዋል። ነገር ግን በክፍሉ ላይ አውዳዊ ምልከታ ስናደርግ ሙግታቸው የሚያስኬድ ሁኖ አናገኘውም፦
Maryam 19:54
በመጽሐፉ ኢስማዒልንም አውሳ፡፡ እርሱ ቀጠሮን አክባሪ ነበረና፡፡ መልክተኛ ነቢይም ነበር፡፡(وَٱذْكُرْ فِى ٱلْكِتَٰبِ إِسْمَٰعِيلَۚ إِنَّهُۥ كَانَ صَادِقَ ٱلْوَعْدِ وَكَانَ رَسُولًا نَّبِيًّا )
በዚህ ክፍል ላይ አላህ የኢብራሂምን ልጅ ኢስማኢልን ሲያመሰግነው እንመለከታለን። ኢስማኢል የአረቦች ሁሉ አባት ነበር። በተጨማሪም እርሱ ለቃለ ማሐላው እውነተኛና ታማኝ እንደነበር የሙስሊም ሊቃውንት ይናገራሉ።[2] የክፍሉን አውደ ሕታቴ ለመረዳት ቁጥር 55ን መመልከቱ አስፈላጊ ነው፦
Maryam 19:55
ቤተሰቦቹንም በሶላትና በዘካ ያዝ ነበር፡፡ እጌታውም ዘንድ ተወዳጅ ነበር፡፡(وَكَانَ يَأْمُرُ أَهْلَهُۥ بِٱلصَّلَوٰةِ وَٱلزَّكَوٰةِ وَكَانَ عِندَ رَبِّهِۦ مَرْضِيًّا )
ኢስማኢል በጌታው ዘንድ ተወዳጅ የሆነበትና ከላይ ደግሞ አላህ ኢስማኢልን እንዲያስቡ ለምእመናን ሲናገር በኢስማኢል የግብር ጉዳይ ረገድ መሆኑ ግልጽ ነው። ኢስማኢል ለአላህ ለሆኑ ስራዎች ላይ ታማኝና አክባሪ ነብይ መሆኑን ከክፍሉ አውድ መረዳት እንችላለን። እንደውም የእንግሊዘኛው ትርጉም ቁጥር 54ን የሚገልጸው “he was true to his promise” ለቃለ መሐላው እውነተኛ ወይም ታማኝ እንደሆነ በሚያሳይ መልኩ ነው።
And mention in the Book, Ishmael. Indeed, he was true to his promise, and he was a messenger and a prophet./English - Sahih International (Maryam 19:54)/
በተጨማሪም ኢብን ጁረይጅ ስለ ኢስማኢል ሲናገሩ፦
"He did not make any promise to his Lord, except that he fulfilled it./የሚፈጽመውን ካልሆነ በቀር ኢስማኢል ምንም አይነት ቃለ መሐላ ለጌታው አይገባም "Ibn Jurayj
ስለዚህ ኢስማኢል ለቃለ መሐላው እውነተኛ፣ ታማኝና አክባሪ መሆኑን የሱረቱ መርየም ቁጥር 54 አውዳዊ አንድምታው ፍንትው አድርጎ ያሳያል። ቀጠሮ ከሚለው ፍታቴ ይልቅ ቃለ መሐላ ወይም ቃልኪዳን(promise) እንደሆነ የክፍሉ ዙሪያ ገባ ይነግረናል። “ቀጠሮውን አክባሪ” የሚለው ኃይለቃል በተጨማሪም የማያስኬደው በመጀመሪያ አላህ በሱረቱ አልሷፍፋት 102 ላይ ራዕይን ያሳየው ለኢብራሂም (ዐሰ) እንጂ ለልጆቹ ለኢስሐቅ ወይም ለኢስማኢል ፈጽሞ አይደለም።
فَلَمَّا بَلَغَ مَعَهُ ٱلسَّعْىَ قَالَ يَٰبُنَىَّ إِنِّىٓ أَرَىٰ فِى ٱلْمَنَامِ أَنِّىٓ أَذْبَحُكَ فَٱنظُرْ مَاذَا تَرَىٰۚ قَالَ يَٰأَبَتِ ٱفْعَلْ مَا تُؤْمَرُۖ سَتَجِدُنِىٓ إِن شَآءَ ٱللَّهُ مِنَ ٱلصَّبِرِينَ
ከእርሱ ጋርም ለሥራ በደረሰ ጊዜ «ልጄ ሆይ! እኔ በሕልሜ እኔ የማርድህ ሆኜ አያለሁ፡፡ ተመልከትም፤ ምን ታያለህ?» አለው፡፡ «አባቴ ሆይ! የታዘዝከውን ሥራ፡፡ አላህ ቢሻ ከታጋሾቹ ሆኜ ታገኘኛለህ» አለ፡፡
በተጨማሪም አላህ የመስዋዕቱን ቀጠሮ የሰጠው ለአባቱ ለኢብራሒም(ዐሰ) እንጂ ለልጁ አልነበረም። ምክንያቱም የራዕዩና የትእዛዙ አክባሪ አባቱ እንጂ ልጁ አይደለም። በተጨማሪም በቀጠሮው ቀን ለመሰዋት ልጁን የወሰደው አባትየው እንጂ ልጁ አይደለም። ስለዚህ ለመስዋዕትነት የተቀጠረው ኢስማኢል የቀጠሮው አክባሪ ነበር የሚለው አንድምታ ኪስ ወለድ እንጂ አውዳዊ አለመሆኑን ለመረዳት አያዳግትም።
የኢብራሒም ጸሎት
ሌላው የሙግት ነጥብ ብለው የሚያቀርቡት ደግሞ “ኢስማኢል/إِسْمَٰعِيْل” ማለት “አምላክ ይሰማል” ማለት ስለሆነ ኢብራሒም ደግሞ በቁጥር 100 ላይ ወደ አላህ በጸለየው መሰረት ልጅን ሰጠው የሚል ነበር። ነገር ግን ከአውዱ ተነስተን ስንመለከት አላህ ለኢብራሒም በጸሎቱ መሰረት የተሰጠው ልጅ ኢስሐቅ እንጂ ኢስማኢል እንዳልሆነ እንረዳለን። ሲጀመር ኢስሐቅ(إسحاق) ወይም በእብራይስጥ ይሽሐቅ(יִשְׂחָק) ደስታ፣ ሳቅ ወይም ብስራት ማለት ነው። በቁጥር 100 ላይ ነብዩ ኢብራሂም(ዐሰ) ጌታዬ ሆይ! ከመልካሞቹ የሆነን (ልጅ) ስጠኝ(رَبِّ هَبْ لِى مِنَ ٱلصَّلِحِينَ) ብሎ ከጸለየ በኋላ፤ በቁጥር 101 ላይ ጌታውም ታጋሽ በሆነ ወጣት ልጅም አበሰርነው (فَبَشَّرْنَٰهُ بِغُلَٰمٍ حَلِيمٍ) ብሎ ሲናገር እንመለከታለን። አስተውሉ! የጌታው መልስ ላይ “አበሰርነው” የሚለውን ቃል ከኢስሐቅ ጋር እንጂ ከኢስማኢል የስም ትርጉም ጋር ፈጽሞ የሚገናኝ አይደለም። እንደውም ስለ ልጁ ማንነት በዛው ሱራ በቁጥር 112 ላይ ግልጽ አድርጎ የብስራቱ ልጅ ኢስሐቅ እንደሆነ ይነግረናል በኢስሐቅም አበሰርነው፡፡ ከመልካሞቹ የሆነ ነቢይ ሲሆን(وَبَشَّرْنَٰهُ بِإِسْحَٰقَ نَبِيًّا مِّنَ ٱلصَّلِحِينَ)
በተጨማሪ በሱረቱ ሁድ 11፡69-71 ያለውን ክፍል ስንመለከት በቁጥር 101 ላይ ታጋሽ በሆነ ወጣት ልጅም አበሰርነው የሚለው ንግግር ለኢስሐቅ መሆኑን ግልጽ የሚያደርግ ክፍል ነው።
11:69 – መልክተኞቻችንም ኢብራሂምን በ(ልጅ) ብስራት በእርግጥ መጡት፡፡ ሰላም አሉት፡፡ ሰላም አላቸው፡፡ ጥቂትም ሳይቆይ ወዲያውኑ የተጠበሰን የወይፈን ስጋ አመጣ፡፡
11:70 – እጆቻቸውም ወደ እርሱ የማይደርሱ መኾነቸውን ባየ ጊዜ ሸሻቸው፡፡ ከነሱም ፍርሃት ተሰማው፡፡ «አትፍራ እኛ ወደ ሉጥ ሕዝቦች ተልከናልና» አሉት፡፡
11:71 – ሚስቱም የቆመች ስትኾን (አትፍራ አሉት) ሳቀችም፡፡ በኢስሐቅም አበሰርናት፡፡ ከኢስሐቅም በኋላ (በልጁ) በያዕቁብ (አበሰርናት)፡፡
ከኢስሐቅ ሌላ አካል
በዚህኛው የሙግት ሐሳብ ላይ ደግሞ
በቁጥር 112 በኢስሐቅም አበሰርነው፡፡ ከመልካሞቹ የሆነ ነቢይ ሲሆን በሚለው ክፍል ላይ በኢስሐቅም ስለሚል “-ም” የምትለው ጥገኛ ምእላድ ከኢስሐቅ ተጨማሪ ሌላ አካል እንዳለ ያመለክታል የሚል ሙግት ነው። ነገር ግን ይሄ ሐሳብ ፈጽሞ የሚያስኬድ አይደለም። አብዱሉ በክፍሉ ላይ ሁለት ልጅ የተባሉ አካላት እንዳሉ ይናገራል። የመጀመሪያው ታጋሽ በሆነ ወጣት ልጅም ሲሆን ሁለተኛው በኢሥሐቅ ብሎ ከፋፍሎ እንመለከታለን። እንደዛ ከሆነ የሙግቱ ሃሳብ አጠያያቂ ይሆናል። ምክንያቱም በእርሱ ሎጂክ ከሄድን በቁጥር 101 ላይ አላህ ለኢብራሒም ታጋሽ በሆነ ወጣት ልጅም አበሰርነው (فَبَشَّرْنَٰهُ بِغُلَٰمٍ حَلِيمٍ ) በሚለው አንቀጽ ላይ ወጣት ልጅም በሚለው ኃይለ ቃል ይሰመርበት “-ም” የምትለው ምእላድ አሁንም በእነርሱ ሎጂክ ኢስማኢል ነው ብለው ከሚያምኑት አካል ሌላ ከእርሱ በፊት የተጠቀሰ አካል አለ እያሉን እንደሆነ አንባቢ ልብ ይበለው። ያ አካል መቼም ኢስሐቅ ነው እንዳይሉ በእነርሱ አባባል ገና በቁጥር 112 ላይ ዘግይቶ የተጠቀሰ መሆኑ ግልጽ ነው። በቁጥር 112 ላይ በኢስሐቅም ሲል ከእርሱ በፊት የተጠቀሰው አካልን (ወጣት ልጅ) የሚያመለክት ከሆነ በቁጥር 101 ላይ ወጣት ልጅም ሲለን ማንን ይገልጻል እያሉን እንደሆነ ጥያቄውን ለአብዱሎቹ ትተነዋል። ነገር ግን “-ም” የምትለው ጥገኛ ምእላድ ከተጨማሪ አካል ከመግለፅ ባሻገር አንድን ነገር ትኩረት(emphasis) ለመስጠት እንደምትገባ መረዳት ይኖርብናል።
በመጨረሻም የሙስሊም አቃብያነ እምነት ተሟጋቾች ለመስዋዕትነት የቀረበው ኢስማኢል መሆኑን እንኳን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለማረጋገጥ ይቅርና በራሳቸው መጽሐፍ በቁርአኑ ላይ ማረጋገጥ ፈጽመው አይችሉም። ጥንታዊያን ሙስሊም ሊቃውንት ለመስዋዕት በቀረበው ልጅ ማንነት ዙርያ ስምምነት የላቸውም፡፡[3] እውቅ ጥንታዊ የሙስሊም ሊቃውንቶች ለምሳሌ ኢብን ቁጠይበኽ እና አል ጠበሪ የመሳሰሉ የሙስሊም ሊቃውንቶች ሱራ 37፡100-107 በሚያብራሩበት አንድምታ ላይ የመስዋዕቱ ልጅ ይስሐቅ መሆኑን ጽፏል።[4] ሌሎች የቁርአን እውቅ ሙፈሲሮችም እንደ ኢብን አባስ[5] እና እንደ ሁለቱ ጃለሎችም[6] ያሉ የሙስሊም ሊቃውንቶች ለመስዋዕት በቀረበው ልጅ ማንነት ዙርያ ግልጽ የሆነ እና ተመሳሳይ አቋም የላቸውም። አንዳድ ሐዲሳትም ጭምር ለመስዋዕትነት የቀረበው ልጅ ኢስሐቅ እንደሆነ ይናገራሉ፦
“ሙሐመድ ኢብን አል-ሙንተሸር እንዳስተላለፈው አላህ ከጠላቶቹ ቢታደገው ራሱን ለመሰዋት ስዕለት የተሳለ አንድ ሰው ነበረ፡፡ ኢብን አባስን ለምክር በጠየቀው ጊዜ መስሩቅን እንዲያማክረው ነገረው፡፡ እርሱን ባማከረ ጊዜ እንዲህ የሚል ምላሽ ሰጠው፡- ‹‹ራስህን አትሰዋ ምክንያቱም አማኝ ከሆንክ አማኝ ነፍስ ትገድላለህና ከሃዲ ከሆንክ ደግሞ ወደ ገሃነም ትፈጥናለህና፤ ነገር ግን በግ በመግዛት ለድኾች ስትል መስዋዕት አድርግ ምክንያቱም ይስሐቅ ካንተ የተሻለ ሆኖ ሳለ በበግ ተዋጅቷልና፡፡›› ጉዳዩን ለኢብን አባስ ባወጋው ጊዜ ‹‹እኔም ልነግርህ የፈለኩት ውሳኔ ይኸው ነበር›› በማለት መለሰለት፡፡”——(ሚሽካት አል-መሳቢህ)[7]
ለተጨማሪ ማብራሪያ እና ማጣቀሻ ከእውነት ለሁሉ ድረገጽ ላይ( http://www.ewnetlehulu.org/am/our-answers/hasentaju/ch5_2/) ይመልከቱ።
ስለዚህ የሙስሊም አቃብያነ እምነት ነን ባይ ኡስታዞች በባዶው ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ዘለው ከሚገቡ ይልቅ መጀመሪያ ከቁርአናቸው በመነሳት ሙግታቸውን በማረቅ፣ በማረምና ወጥነት በማስያዝ ቢጀምሩ የተሻለ ይመስለኛል። በክፍል ሁለት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሙግት ብለውያነሷቸውን አስቂኝ የሙግት ነጥቦች ምልከታና ትችቶችን ከእርምታዊ ማብራሪያዎች ጋር የምንቃኝ ይሆናል። ለማንኛውም ለመላው የሙስሊም ተከታዮች የ1443ኛው ኢድ አል አድሓ በዓልን ከቀድሞው የሞኝነትና ሐሰተኛ አስተምህሮ ተላቅቃችሁ እውነትን ከመጽሐፍ ቅዱስ እንድትማሩ እንጋብዛችኋለን። ጸጋ ሰላም ከእናተ ጋር ይሁን!
ማጣቀሻዎችና ማስፈንጠሪያ
[¹] Lives of the Prophets, L. Azzam, Isaac and Jacob^ Storie
[²] Tafsir ibn Kathir 19:54
[³] Gibb and Kramers. A Shorter Encyclopaedia of Islam; p. 175
[⁴] Al-Tabari. The History of al-Tabari, Vol. II, Prophets and Patriarchs, trans. William M. Brenner [State University of New York Press, Albany 1987], p. 89)
[⁵] anwîr al-Miqbâs min Tafsîr Ibn ‘Abbâs; Online Edition: https://altafsir.com/Tafasir.asp?tMadhNo=0&tTafsirNo=73&tSoraNo=37&tAyahNo=102&tDisplay=yes&UserProfile=0
[⁶] Tafsir al-Jalalayn; Online Edition: https://altafsir.com/Tafasir.asp?tMadhNo=0&tTafsirNo=74&tSoraNo=37&tAyahNo=107&tDisplay=yes&UserProfile=0
[⁷] Mishkat Al-Masabih English Translation With Explanatory Notes by Dr. James Robson, Volume I [Sh. Muhammad Ahsraf Publishers, Booksellers & Exporters, Lahore-Pakistan, Reprint 1990], p. 733