ለሙስሊም ሰባኪያን ሙግት ምላሽ
የእግዚአብሔር ቅዱስ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ የተገለጠ አምላክ መሆኑንና ከእርሱም በፊት የነበሩት ነብያት እና የእምነት አባቶች ከዛም በመቀጠል በሐዲስ ኪዳን የነበሩት ሐዋርያቶች እርሱን እንደተከተሉ የክርስትና መሠረት እምነት የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምራል። በተጻራሪው ግን ቅዱሳት መጻሕፍት ተጽፈው ከተጠናቀቁ ከብዙ መቶ ዓመታት በኋላ የመጣው እስልምና ደግሞ በቀድሞ ነቢያት ተወርቶ እና ተሰብኮ የማይታወቅ አምላክ አስተዋወቀን፤ ከዛም አልፎ ተርፎ ተከታዮቹ ሙስሊም እንጂ ክርስቲያን አይደሉም ብሎ ብቻውን ቆሞ ያስተምራል። ኢስላም ናቸው እንጂ ክርስቲያን አይደሉም የሚለው ንግግር በብዙ ሙስሊሞች ዘንድ እንደ ትልቅ ርዕስ አድርገው ክርስቲያኖችን ጋርም በጥያቄ መልክ ሲቀርብ ይስተዋላል። እኛም ይህን አስተምሮታቸው ከሆነው ከቁርኣን የመነጨ እና ጥያቄያቸው በራሱ ማስረጃ የሌለው ኪስ ወለድ ሙግት ሀሳብ መሆኑን እንመለከታለን።
በመጀመሪያ ግን ክርስቲያን እና ደቀመዛሙርት ማለት ምን ማለት ነው?
ክርስቲያን(Χριστιανούς/ክሪስትያኑስ)፦ ማለትም የክርስቶስ ተከታይ ወይም በክርስቶስ ህግ እና ትምህርት የሚመራ ማለት ነው። የእርሱ አቻ ቃል የክርስቶስ ደቀመዝሙር/μαθητής ሲሆን ጥቅልል ትርጉሙ “ የክርስቶስ ተማሪ ”ወይም” የክርስቶስ ተከታይ” ማለት ነው። የሐዋርያቶች ደቀመዝሙር የነበሩት ከማን እግር ስር እንደተማሩ ለመግለፅ ይህንን ቃል ይጠቀሙትም ነበር። ለቅምሻ ታህል ደቀመዝሙር በሚለው ቃል ላይ አንድ ምሳሌ ላሳይ፦ ጶሊቃርጶስ በ70ዓ.ም ተወልዶ በ155 ዓ.ም ወይም በ160 ዓ.ም የሞተ የሐዋሪያው ዮሐንስ ደቀመዝሙር(ማቴቴስ/μαθητής) እንደነበር የቤተክርስቲያን የታሪክ መጻሕፍት ያወሱናል። በተጨማሪ ቅዱስ ዲዮናስዮስ ዘአቴንስ ደግሞ ስሙም በሐዋ17:34 ላይ የተጠቀሰ ሲሆን ይህ የቤተክርስቲያን አባት ደግሞ የሐዋርያው ጳውሎስ ደቀመዝሙር (ማቴቴስ/μαθητής) እንደነበር ይነገራል። ይህ ማለት ጶሊቃርጶስ የሐዋርያው ዩሐንስ ተከታይ ሲሆን፤ ቅዱስ ዲዮናስዮስ ዘአቴንስ የቅዱስ ጳውሎስ ደቀመዝሙር እንደሆነና የአስተማሪያቸው ማቴቴስ ተብለው መጠራታቸውም ከታሪክ ክታባት እንረዳለን። በአንዳንድ የሙስሊም ተሟጋቾች የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀመዛሙርት እንዲሆኑ እንጂ ክርስቲያን እንዲሆኑ ኢየሱስ ሐዋርያትን አላዘዘም ይላሉ። ነገር ግን የክርስቶስ ደቀመዝሙር ማለት እና ክርስቲያን ከሚለው ቃል ጋር ተመሳሳይ ነው። ስለዚህ ደቀመዛሙርቴ ካለ( ዮሐ 15:8፣ 13:35፣ ማር 14:14፣ ሉቃ 22:11፣ ማቴ 26:18…) የእርሱ ተከታይ(ክርስቲያን) መሆናቸውን ምንም ሳናቅማማ እንቀበላለን ማለት ነው።
ስለ ክርስትና እና ደቀመዝሙር ይህን ያህል ካየን ነብያቱ ክርስቲያን ነበሩ ወይ? ክርስቲያን ከነበሩስ ምንድነው ማስረጃቹ? የሚለውን በመመለስ እንዝለቅ።
የክርስቶስ ምስክርነት
በማቴዎስ ወንጌል 5፡3-13 ላይ በተለምዶ ይህ ክፍል የተራራው ስብከት በመባል የሚታወቅ ሲሆን ሙሉ ዐውደ ምልከታ እያነበባቹ ስትወርዱ ቁጥር 11-12 ላይ አንድ አስደናቂ ንግግር እንመለከታለን እንዲህ ይላል፦
“ሲነቅፉአችሁና ሲያሳድዱአችሁ በእኔም ምክንያት ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲናገሩባችሁ ብፁዓን ናችሁ።”
ማቴዎስ 5፥11
እዚህ ክፍል ላይ ኢየሱስ እርሱን በመከተላቸው ስለሚደርስባቸው ነቀፌታ፣ ስደትና ችግር ሁሉ መፍራት እንደሌለባቸው፤ ጨምሮም ብፁዓን እንደሆኑ ይነግራቸዋል። ስደቱም በክርስቶስ ያለ መሆኑን በቁጥር 11 ላይ በእኔ ምክንያት የሚል ንግግር ያስቀምጣል። በዚህም አላበቃም ይቀጥልና በቁጥር 12 ላይ እንዲህ ይለናል፦
“ዋጋችሁ በሰማያት ታላቅ ነውና ደስ ይበላችሁ፥ ሐሴትም አድርጉ፤ ከእናንተ በፊት የነበሩትን ነቢያትን እንዲሁ አሳድደዋቸዋልና።”
ማቴዎስ 5፥12
ክርስቶስን የሚከተሉ ሰዎች ዋጋቸው ታላቅ እንደሆነ! እርሱንም መከተል የዚህ ስደት እና እንግልት ከንቱ እንዳልሆነ፤ ይልቁንም “ከእናተ በፊት የነበሩትን ነብያቶች እንዲሁ አሳድዷቸዋልና በማለት በረከቱን ይነግራቸዋል። ምክንያቱም በክፍሉ ዐውድ ሲብራራ እነርሱ ተነቅፈዋል፣ ያላቸው ነገር አጥተዋል፣ ስለ እርሱ ሲሉ መረባቸውን ጥለው ተከትለውታል መሠደዱ እና ማጣቱ “በእኔ ምክንያት ነው ይላቸዋል” ነገር ግን እኔን መከተላችሁ ከንቱ አይደለም፤ ብሎ ይቀጥልና፦ ከእናተ በፊት የነበሩትን ነብያት እንዲሁ አሳድዷቸዋልና በማለት ከቀድሞ ነብያት ጋር አገናኝቶት የቀድሞዎቹም መሠደዳቸው በእርሱ መሆኑን ይነግራቸዋል።
በተጨማሪም በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 23፥34-37 ላይ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የኦሪት ህግ መምህራንን እና ፈሪሳውያንን ሲነቅፍ እንዲህ ብሎ ሲናገር እንመለከታለን፦
ማቴዎስ 23
³⁴ ስለዚህ፥ እነሆ፥ ነቢያትንና ጥበበኞችን ጻፎችንም ወደ እናንተ እልካለሁ፤ ከእነርሱም ትገድላላችሁ ትሰቅሉማላችሁ፥ ከእነርሱም በምኵራባችሁ ትገርፋላችሁ ከከተማም ወደ ከተማ ታሳድዳላችሁ፤
³⁵ ከጻድቁ ከአቤል ደም ጀምሮ በቤተ መቅደስና በመሠዊያው መካከል እስከ ገደላችሁት እስከ በራክዩ ልጅ እስከ ዘካርያስ ደም ድረስ በምድር ላይ የፈሰሰው የጻድቅ ደም ሁሉ ይደርስባችሁ ዘንድ።
³⁶ እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ሁሉ በዚህ ትውልድ ላይ ይደርሳል።
³⁷ ኢየሩሳሌም ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ነቢያትን የምትገድል ወደ እርስዋ የተላኩትንም የምትወግር፥ ዶሮ ጫጩቶችዋን ከክንፎችዋ በታች እንደምትሰበስብ ልጆችሽን እሰበስብ ዘንድ ስንት ጊዜ ወደድሁ! አልወደዳችሁምም።
ትኩረት ሰጥታቹ ተመልከቱ፤ ቅዱሱም ማቴዎስ የክርስቶስን ንግግር አጽንዖት ሰጥቶ ነው እየጻፈልን ያለው። የጌታችን የኢየሱስ ንግግርም ዝም ብሎ ሀይለ ቃል አይደለም ይልቁን የርዕሳችን ዋና ማገር እንጂ። እንዲህ ነው ነገሩ፦
ጌታችን እሱን ባለመቀበላቸው የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች በራሳቸው ላይ ሊደርስባቸው ያለውን መከራ ተናግሯል ነገር ግን ከዛ መከራ ያርፉ ዘንድ ዶሮ በክንፎቿ ስር እንደ ምትሰበስብ ሲጠራቸው እንመለከታለን። በዛው ክፍል ላይ፦ “እኔ ወደ እናንተ ነቢያትን እልካለሁ” ስለዚህ ያለ ጥርጥር እዚህ ነብያትንን፣ ሐዋርያትን እና ሌሎች የእሱን ተከታዮች መሆኑን እየገለፀ ነው። ይህ ማለት ምን ማለት ነው? በድጋሚ ወደ ማቴዎስ ተመልሳቹ ጌታችን የተናገረውን እና ያለውን አስተውሉ፦
“ከአቤል…እስከ ዘካሪያስ” ስለ አቤል ሞት ተጽፎ የሚገኘው በዘፍ 4፥8 ላይ ሲሆን፣ ስለ ዮዳሄ ልጅ ስለ ዘካሪያስ ሞት ደግሞ በ2ዜና 24፥20-22 ተጽፏል። ጌታችን ኢየሱስ በዚህ ላይ ምን እያለ ነው ከተባለ በአይሁድ የቅዱሳት መጻሕፍት ቅደም ተከተል መሠረት፣ መጽሐፈ ዜና መዋዕል የብሉይ የመጨረሻ መጽሐፍ ነው። “ከአቤል እስከ ዘካሪያስ” የሚለው አባባል እኛ “ከዘፍጥረት እስከ ራዕይ” ከምንለው ጋር ተመሳሳይ ነው። ታዲያ ጌታችን ይህን ሀይለ ቃል መጠቀሙ የብሉይ አጠቃላይ ሰማዕታን የሆኑ መልዕክተኞች እርሱ እንደላካቸው ማስገንዘቡን እንመለከታለን። አስተውሉ እኔ ልኬ ነበር ገደላችሁ እያላቸው ነው። የትኛው ነብይ እንዲህ ሊናገር ይችላል? ለዚህም ነው ከጌታችን ንግግር ተነስተን ኢየሱስ ያህዌ ነው፣ የቀድሞም ነብያት እርሱን ሲከተሉ ነበር የምንለው።
የእነዚህ ክፍል ማብራሪያ ከሌሎች ቅዱሳት መጽሐፍት ጋር በማመሳከር ከእነርሱ(ከሐዋርያቶቹ) በፊት የነበሩት ነቢያትና የእምነት አባቶች ጨምሮ ክርስቶስን እንደተከተሉ ስለ እርሱም ሲሉ መከራን እንደተቀበሉ እናም እንደተነቀፉ ከዚህ በመቀጠል በቅድመ ተከተል እንመለከታለን።
የሌሎች ሰዎች ምስክርነት
ቅዱሳት መጻሕፍት ከዚህ ርዕስ አንፃር ምን ያስተምራሉ? የሚለውን ለመመለስ በዕብራውያን መልዕክት ምዕራፍ 11:1-40 ያለውን መመልከት ለዚህ ጥያቄ ጥሩ ምላሽ የምናገኝ ይሆናል። በዚህ የታሪክ ምዕራፍ ስለ እምነት አባቶች ከሚያወሳ ክፍል ከሆነው ዕብራውያን ምዕራፍ 11:25-26 የሙሴ ያሳለፈው የህይወት ውጣውረድ እንዲህ እንዲህ በማለት ያስቀምጣል፦
“ከግብፅም ብዙ ገንዘብ ይልቅ ስለ ክርስቶስ መነቀፍ እጅግ የሚበልጥ ባለ ጠግነት እንዲሆን አስቦአልና ለጊዜው በኃጢአት ከሚገኝ ደስታ ይልቅ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር መከራ መቀበልን መረጠ፤ ብድራቱን ትኵር ብሎ ተመልክቶአልና።”
— ዕብራውያን 11፥25-26
በደንብ አስተውሉ የዚህን ክፍል ጥቅስ ከማቴዎስ ወንጌል 5:11-12 ጋር ስናነፃፅረው ጥልቅ መልዕክት ይነግረናል። ከላይ በተራራው ስብከት ላይ እርሱን በመከተል ስለሚደርስ መከራ ከነገራቸው በኋላ በዚህም ሳያበቃ እነርሱ ብቻ ሳይሆኑ በእርሱ ምክንያት መከራው የበዛባቸው የቀድሞም ነቢያቶችም ጭምር በመከራ ውስጥ ማለፋቸውንና የቀኝ እጃቸውን አሻራ አሳርፈው እንዳለፉ ይነግረናል። ታዲያ ከቀድሞ ነብያት ውስጥ ታላቁ ነቢይ የነበረው ሙሴ <<ከግብፅ ጮማ እና ብዙ ገንዘብ ይልቅ ስለ ክርስቶስ መከራን መቀበል>> እንደመረጠ የዕብራውያን መጽሐፍ ይነግረናል። ስለዚህ ክርስቲያን በሚለው የቃሉ ትርጓሜ መሠረት በመነሳት ከቀድሞ ነብያት ውስጥ ሙሴ ክርስቲያን ማለትም የክርስቶስ ደቀመዝሙር (μαθητής/ማቴቴስ) እንደነበረ እንመለከታለን ማለት ነው። ታዲያ ታላቁ የብሉይ ኪዳን ነቢይ ሙሴ እንዴት ሆኖ ነው ክርስቶስን ተከትሎ ሙስሊም የሚሆነው? ሙስሊም ማለትስ ክርስቶስን መከተል ነውን? መልሱን ለአንባቢ ልተወው። የዕብራውያን መልዕክት ጸሐፊ በዚህ አላበቃም ተጨማሪ ጥልቅ ጠቢብ ሚስጥር እንዲህ በማለት ለተደራሲያኑ ይገልፅላቸዋል፦
“እነዚህም ሁሉ በእምነታቸው ተመስክሮላቸው ሳሉ የተሰጠውን የተስፋ ቃል አላገኙም፥ ያለ እኛ ፍጹማን እንዳይሆኑ እግዚአብሔር ስለ እኛ አንዳች የሚበልጥ ነገርን አስቀድሞ አይቶ ነበርና።”
ዕብራውያን 11፥39-40
እነዚህ ሁሉ የተባሉት በቁጥር 38 ላይ በጠቅላላ ለመተረክ ጊዜ ያጥረኛል ያላቸውን መሆኑን በክፍሉ ዐውደ ምንባቤ ላይ መረዳት ይቻላል። ከላይ ባለው ጥቅስ በመጨረሻ ቁጥር ስር እንዲህ የሚል ሃይለ-ቃል እናገኛለን፦ “ያለ እኛ ፍፁማን እንዳይሆኑ” ይህ ክፍል በተዘዋዋሪ ምን እያለን እንደሆነ በቀላሉ ስንመልከት፦
<<የቀድሞ አባቶችና ነብያቶች በሙሉ እኛ የተከተልነው ክርስቶስን ስለተከተሉ ማለትም የቀድሞቹ የተስፋ ቃል እምነት እኛ ደግም የተስፋ ቃል ፍፃሜ ስንሆን ፍፁማን ሆነዋል፤ ምክንያቱም ከእነርሱ የተቀበልነው የእምነት ሚስጥር ማስፈፀሚያ ነንና፤ በተስፋ ቃል ዘመን ተሳለምው የነበሩት ተገልጦ በእኛ ላይ ተፈፀመ። የቀድመው ዘመን የተስፋ ቃል ታጋዮች ናቸው፣ እኛ ደግሞ የተስፋ ቃል ፍፃሜ ታጋይ ነንና። ከጊዜ በኋላ የበቀለ ክርስትና የለንም እኛም አይደለንም። ምክንያቱም የቀድመው ነብያትና የእምነት አባቶች ያለ እኛ ፍፁማን አይሆኑምና>> ይህን ነው የዕብራውያን መጽሐፍ ተራኪ ከምዕራፉ ዐውድ ሊገልፅ የፈለገው።
ታዲያ እነዚህ የእምነት አባቶች ያመኑትን እና የተከተሉት እኛ ክርስቲያኖች ያመነውን እና የተከተልነውን ክርስቶስን ነውን? የሚል ጥያቄ ከወገኖቻችን ቢቀርብልን በኩራት አዎ! እንላለን። ለዚህም ማጣቀሻ ይሆን ዘንድ ይህንን ክፍል እንመልከት፦
“እንግዲህ እነዚህን የሚያህሉ ምስክሮች እንደ ደመና በዙሪያችን ካሉልን፥ እኛ ደግሞ ሸክምን ሁሉ ቶሎም የሚከበንን ኃጢአት አስወግደን፥ የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን ተመልክተን፥ በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ፤ እርሱ ነውርን ንቆ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአልና።”
— ዕብራውያን 12፥1-2
ከላይ እነዚህን ሁሉ የሚያህሉ ምስክሮች እንደ ደመና የተባሉት በምዕራፍ 11፥1-40 ስላሉት የእምነት አባቶችና ነብያቶችን ነው። የእነርሱንም የህይወት ገድል አንፀባርቆ እና አጉልቶ ካሳየ በኋላ ወደ ሐዲስ ኪዳን በመምጣት በክፍሉ ላይ እንዲህ ይላል “እኛም ደግሞ” ብሎ በዘመኑ የነበሩትን የክርስቶስ ተከታዮችን በሙሉ በመጠቅለል ከእነርሱ ጋር በማገናኘት ክርስቶስ ዋና እንዳደረጉ ያስነብበናል። በሌላ አነጋገር፦
“እነዚህን የመሰሉንን ምስክሮችን እንደ ደመና የከበቡን የእምነት አባቶች እኛ የምንከተለውን ኢየሱስን ስለተከተሉ፣ ደግሞም ክርስትናን በህይወታቸው ተመስክሮላቸውና አጠናቅቀው ጨርሰው እነርሱ በምድር ስለከበሩ እኛም ገድሉን እንጋደል ዘንድ ታዘናል” እያለን ነው።
ስለዚህ እንደ ሙስሊም ወገኖቻች የሙግት ነጥብ መሰረት ስንሄድ፦ ክርስትናችን የሆነ ሰዓት የበቀለና በሰዎች የተመሠረተ ነው ብለው በሚነዙት ወሬና ተራ ከቁብ በማይቆጠር ንግግር ክርስትናን ለማጠልሸት ተነስተው እንደሚሉት ሳይሆን፤ የቀድሞ ነብያቶች ተጋድሎአቸውን እስከ መጨረሻ ፈፅመው በምድር ላይ ያከበሩት፣ እነርሱ ፍፁማን ይሆኑ ዘንድ የእነሱንም ዱላ ተቀብለው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያት ለእኛ እስከመጨረሻ የደም ጠብታ ድረስ በምድር ወድቀው በሰማይ ከብረው የአስተላለፉልንና ጥልቅ ፍቅር የታየበት የነበረ የሚያድግ የሚያፈራ ህያው ሐይማኖት በታሪክ ክርስትና ብቻ መሆኑ እጅጉን የሚያስገርም ነው። ለዚህም ነው ታላቁ የቤተክርስቲያን አባት ቅዱስ ጠርጠሉስ(Tertullian) “የሰማዕታት ደም የቤተክርስቲያን ዘር ነው” እንዲል ያደረገው።
እስቲ እኛም እንደ ዕብራውያን መልዕክት ጸሓፊ አይነት እነሱንም፣ የአዲስ ኪዳንና ከዛ በኋላ የተነሱ ቅዱሳን የእምነት አባቶችን ጨምረን ይህንን ጽሑፍ ከሚያነብ አንባቢ ጋር ከታች ያለውን ቃል አብረን እንላለን፦
“ክርስትናችን የነበረ ያለ የሚኖር የሆነና፣ እንደ ብሉያት እና ሐዲሳት የጌታም ደቀመዛሙርት፣ ከዛም በኋላ የተነሱት ቅዱሳን የእምነት አባቶችም በዘመናቸው ክርስቶስን አክብረው አለፉ። እኛም በልባችን ያለው ዕምነት እንደ ደመና የሚያህሉ ምስክሮች ያሉት ስለሆነ ከእነርሱ የተቀበልነውን የእምነት ዱላ ለማስተላለፍ ሸክምን ሁሉ አስወግደን የእምነታችንን ራስና ፈፃሚውን ክርስቶስን ተመልክተን የህይወታችንን ሩጫ በትዕግስት እንሩጥ አሜን።”