የዮሐንስ ወንጌል አጭር ሐተታ

መግቢያ

➥የዮሐንስ ወንጌል በዘመናት መሐል በቤተክርስቲያን ተወዳጅነቱን ጠብቆ የቆየ መጽሃፍ ሲሆን በሌሎች ለዘብተኛ ምሁራን ደግሞ “አራተኛው ወንጌል” በመባል ይጠራል። ከጥንታዊት ቤተክርስቲያን አባቶች መካከል አንዱ የሆነው ቀለሜንጦስ ዘእስክንድሪያ ደግሞ መንፈሳዊ ወንጌል በማለት አቆላምጦታል [1]፤ ይህንን ያለበትም ምክኒያት ዮሃንስ ወንጌሉን የጻፈው በመንፈስ ቅዱስ አነሳሽነት ነው ብሎ ስላመነ እንደነበር የአውሳብዮስ ዘቂሳርያ ዘገባ ያሳያል። ወንጌሉ ምንም ያህል አከራካሪ ጉዳዮች ቢኖሩበት፤ ከዘመናውያኑ ሥነ መለኮት ምሁራን አንዱ የሆነው ኮሊን ክሩዝ ደግሞ “ኁልቆ መሳፍርት ለሌላቸው የክርስትና ትውልዶች መነሳሳት የፈጠረና በስርዓት ላጠኑት ሁሉ ታላላቅ ሽልማቶችን ያስታቀፈ” [2] በማለት መስክሮለታል።

የጸሃፊው ማንነት

➥የወንጌሉን ትክክለኛ ጸሃፊ በተመለከተ የተለያዩ አመለካከቶች ቢኖሩም በሐዋርያው ዮሃንስ ስለመጻፉ የሚቀርቡ ሃሳቦች ከሌሎች ይልቅ ተጨባጭነት አላቸው። በቅድሚያ የመጽሃፉን ውስጣዊ ማስረጃዎች (internal evidences) እንመልከት። ጸሃፊው የአረማይክ ቋንቋ ችሎታ ያለው አይሁዳዊ ስለመሆኑ ለሚጠቅሳቸው አንዳንድ የእብራይስጥና አራማይክ ቃላት ትርጉም ማስቀመጡ ምስክር ነው፤ የአይሁድን ወግና ስርአት ጠንቅቆ የሚያውቅ ሰው መሆኑን የገዛ ጽሁፉ ያሳያል (ዮሃ 4፡ 9፣ 20)፤ ስለ መጀመሪያው ክፍለ ዘመን የእስራኤል መልክአ ምድራዊ አቀማመጥ በትክክል እንደሚያውቅም ከወንጌሉ ላይ መረዳት ይቻላል (ዮሃ 1፡44፣ 2፡1፣ 4፡5፣ 4፡21፣ 9፡7፣ 11፡18፣ 18፡1)፤ እንደዚሁም የአይን ምስክርና የኢየሱስ የቅርብና ተወዳጅ ሰው እንደነበርም ይናገራል (ዮሃ 1፡14፣ 19፡35) [3]።ከኢየሱስ የቅርብ ደቀ መዛሙርት መሃል ያዕቆብ ብዙም ሳይቆይ ስለሞተ፤ እንዲሁም ጴጥሮስ ቶማስና ፊሊጶስ በሶስተኛ መደብ እየተጠሩ ስለተዘገቡ የጸሃፊው ማንነት ዮሃንስ የመሆኑ እውነታ የበለጠ ተአማኒነት አግኝቶአል። ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጪ ያሉ ማስረጃዎችን (External Evidences) በአጭሩ ስንዳስስ ደግሞ የጥንት የቤተክርስቲያን አባቶችን ምስክርነት እናገኛለን።ከላይ እንደተመለከትነው አውሳብዮስ ዘቂሳርያ በዘገበው መሠረት የእስክንድርያው ቀለሜንጦስ ይህንን ወንጌል መንፈሳዊ ወንጌል ብሎ ጠርቶታል። ቀለሜንጦስ ወንጌሉን በዚህ ስም የጠራውም ዮሐንስ ወንጌሉን የጻፈው በደቀ መዛሙርት ተገፋፍቶና በመንፈስ ቅዱስ ተነሳስቶ እንደሆነ በማመኑ እንደነበረ አውሳብዮስ ጨምሮ ዘግቧል [4]። በመሆኑም ቀለሜንጦስ አራተኛው ወንጌል የተጻፈው በሐዋርያው ዮሐንስ እንደሆነ ያምን ነበር። 200 ዓ.ም አካባቢ እንደጻፈ የሚገመተው ኢራኒየስ ወንጌሉን የጻፈው የተወደደው ደቀ መዝሙር ዮሐንስ መሆኑንና የጻፈውም በኤፌሶን ሳለ እንደነበረ ተናግሯል [5]። በተጨማሪም የተወሰኑትን የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ዝርዝር ይዞ የተገኘውና ከ 180-200 ዓ.ም ድረስ እንደተጻፈ የሚገመተው የሙራቶሪያን ጽሁፍ አራተኛውን ወንጌል በዮሐንስ እንደተጻፈ ይመሰክራል። ዮሐንስ ወንጌሉን እንዴት ጻፈው? ለሚለው ጥያቄ ይህ ጽሁፍ ተአማኒ ዝርዝር ባይኖረውም ወንጌሉ በተጻፈባቸው አመታት ውስጥ ጸሃፊው ዮሐንስ መሆኑ ይታመንበት እንደነበር ያሳያል [6]። በመሆኑም ከውስጣዊ ማስረጃዎች ጸሃፊው ፍልስጤም ምድር ውስጥ የሚኖር አይሁዳዊ መሆኑን፣ የኢየሱስ የአይን ምስክር መሆኑን፣ከአስራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት አንዱ መሆኑንና ከጽሁፉ ዝርዝሮች በመነሳት ጸሃፊው ዮሐንስ እንደሆነ መገመት እንደሚቻል ስንረዳ ከውጫዊ ማስረጃዎች ደግሞ ወንጌሉ ለተጻፈበት ዘመን የሚቀርቡ አባቶችና ተጨማሪ ጽሁፎች የዮሐንስን ጸሐፊነት እንደሚደግፉ መገንዘብ ይቻላል። የዮሐንስ ወንጌል በራሱ በዮሐንስ መጻፉን የሚጠራጠሩ ምሁራን ቢኖሩም ከላይ ባነሳናቸው ማስረጃዎች መሠረት ጸሃፊው ሐዋርያው ዮሐንስ መሆኑን ተቃውሞ በብቃት የሚቆምና ተለዋጭ ጸሃፊ በርግጠኝነት የሚያቀርብ መከራከሪያ ግን ሊገኝ አልቻለም።

የተጻፈበት ዘመንና ስፍራ

➥ልክ እንደ ጸሃፊው ማንነት ሁሉ በዘመናችን ምሁራን ዘንድ ወንጌሉ መቼ እንደተጻፈ የማያባራ ክርክር ይደረጋል። አንዳንዶች የተጻፈው በ2ኛው ክፍለ ዘመን መካከለኛ አመታት፤ ማለትም 150 ዓ.ም አካባቢ እንደሆነ በማንሳት ይከራከራሉ። ይሁን እንጂ የሥነ ቁፋሮ (Archaeology) ጥናቶች የሚያሳዩት የዮሐንስ ወንጌል የተጻፈው በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን መገባደጃ ላይ መሆኑን ነው። የዮሐንስ ወንጌል የመጀመሪያው እደ-ክታብ Papyrus 52 የሚባል ሲሆን የምዕራፍ 18ን የተወሰኑ ክፍሎች የያዘና በ130 ዓ.ም አካባቢ እንደተጻፈ የሚገመት ቁራጭ ብራና ነው። ቀጥሎም ከምዕራፍ 1-14 ድረስ ያለውን አብዛኛውን ክፍልና የቀሩትን ምዕራፎች በከፊል የያዘው Papyrus 66፤ እንዲሁም ከምእራፍ 1-11 እና ከ12-15 ድረስ የያዘው Papyrus 75 ከጥንታዊ እደ ክታባት ይመደባሉ። እነዚህ እደ ክታባት ከሁለተኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ይመዘዛሉ [7]። እንግዲህ እስካሁን የሚታወቀው የመጀመሪያው የወንጌሉ ቅጂ (P 52) የተጻፈው እንደተገመተው በ 130 አካባቢ ከነበረ የመጀመሪያው ጽሁፍ የተጻፈው በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን መሆኑ ግድ ነው። ወንጌሉ የት ተጻፈ? ለሚለው ጥያቄ ደግሞ በቀለሜንጦስ ዘእስክንድርያንና በኢራንየስ ትውፊቶች ላይ መደገፍ ግድ ይለናል። ቀለሜንጦስ እንደጻፈው ዮሐንስ ከፍጥሞ ደሴቱ ስደት ወደ ኤፌሶን የተመለሰው ንጉሡ ዶሚሽያን ከሞተ በኋላ (ከ 81-96) ሲሆን ኢራኒየስ ደግሞ ሐዋርያው እስከ ትራጃን ንግስና ዘመን ድረስ (ከ98-117) እዚያው ኤፌሶን እንደነበረ ይናገራል [8]። ይህም ወንጌሉን በዚያ ጊዜ (በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን መጨረሻ) በኤፌሶን ሳለ ጽፎታል የሚል ግምትን አሳድሯል። ስለዚህም የዮሐንስ ወንጌል ከ80-90 ዓ.ም ሐዋርያው ዮሐንስ በኤፌሶን ሳለ የጻፈው ወንጌል መሆኑ በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት አለው።

የዮሐንስ ወንጌል ዋና ዋና ይዘቶች

➥በመጀመሪያው ምእራፉ ስለዋና ገጸ ባህርዩ ማንነት በዝርዝር ይናገራል። ይህም ገጸ ባህርይ በመጀመሪያ ከእግዚአብሔር ጋር
የነበረው በፍጥረት ስራ ላይ ተሳታፊ የነበረውና በኋላም ሰው ሆኖ የመጣው ኢየሱስ መሆኑን ይናገራል።

➥እስከ ምእራፍ 12 ድረስ ሰፋ ባሉ ንግግሮችና በተአምራት የተገለጠውንና በልጁ ለሚያምኑ ሁሉ የዘለአለም ህይወት የሚሰጥ
አባቱን የተረከውን ኢየሱስን በተዋበ የመክፈቻ ንግግር መልክ እናገኛለን።

➥ከምእራፍ 13 – 20 ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ለቀጣይ ዘመናት ሲያዘጋጅ፣ ሲመክራቸውና ሲጸልይላቸው፣ እንዲሁም ስቃዩን፣ ስቅለቱንና ሞቱን እንዲሁም ትንሳኤውን ያስቃኘናል።

➥ምእራፍ 21 ተጨማሪ የትንሳኤውን ምስክርነቶች፣ ለጴጥሮስ የተሰጠውን ተልአኮ ከሞቱ ትንበያ ጋር፣ እንዲሁም የተወደደውን ደቀ መዝሙር ምስክርነት ያስቃኘናል [9]።

የዮሃንስ ወንጌል ልዩ ባህርያት

➥በሶስቱ ተመሳሳይ ወንጌላት ዘገባ የኢየሱስ አገልግሎት ትኩረት ያደረገው በገሊላ ሲሆን የዮሃንስ ወንጌል ግን በብዛት የኢየሱስን የይሁዳና የኢየሩሳሌም አገልግሎት ያስቃኘናል።

ተመሳሳዮቹ ወንጌላት የኢየሱስን ምሳሌያዊ ንግግሮች፣ የእግዚአብሔርን መንግስት የተመለከቱ ስብከቶቹን፣ እንዲሁም በተለያዩ ርእሰ ጉዳዮች ላይ ያደረጋቸውን ንግግሮች (ለምሳሌ ስለ ምጽዋት፣ ስለጋብቻና ፍቺ፣ ስለግብር ስለጭንቀት፣ ስለሃብት፣ ወዘተ…) ሲያስነብቡን የዮሃንስ ወንጌል ግን “እኔ… ነኝ” በሚሉ ሃረጋት በሚጀምሩ ኢየሱስ ስለራሱ በተናገራቸው ንግግሮች ይታወቃል። የዮሃንስ ወንጌሉ የኢየሱስ ንግግር ከሶስቱ ተመሳሳይ ወንጌላት በተለየ ከላይና ከታች፣ ብርሃንና ጨለማ… ወዘተ በሚል ሁለት ነገሮችን በተነጻጻሪነት በሚመለከት አጻጻፉ ይታወቃል። በዮሃንስ ወንጌል በተዘገበው የኢየሱስ አገልግሎት የሚገኙት ክስተቶች በሌሎቹ ወንጌላት ውስጥ አይገኙም። ማለትም የወይኑ ተአምር (2: 1-11)፣ ከኒቆዲሞስ ጋር ያደረገው ጭውውት (3:1-13)፣ የሳምራዊቷ ሴት ታሪክ (4:1-42)፣ የቤተዛታው ኩሬ ፈውስ (5:1-18)፣ የሰሊሆም መጠመቂያው ፈውስ (ምእራፍ 9)፣ የአላዛር ከሞት መነሳት (ምእራፍ 11)፣ ኢየሱስ የደቀ መዛሙርቱን እግር ማጠቡ (13: 1-11)፣ እንዲሁም ኢየሱስና ጲላጦስ ያደረጉት ዘለግ ያለ ንግግር (18:28-19:22) የሚገኙት በዮሃንስ ወንጌል ብቻ ነው [10]

የዮሐንስ ወንጌል ስነ መለኮት

➥የዮሐንስ ወንጌል በውስጡ ብርሃንና ጨለማ፣ ሞትና ህይወት የሚሉ ሐሳቦች በተነጻጻሪነት ተደጋግመው ተነስተዋል፤ ይህም የኖስቲክ እሳቤን የያዘ ወንጌል እንደሆነ እንዲታሰብ ምክንያት ሆኗል። ነገር ግን የኖስቲክ መምህራን ስጋን ሁሉ እንደ እርኩስ ነገር ስለሚቆጥሩ አምላክ በስጋ እንደመጣ የሚናገረው የዮሐንስ ወንጌል ከእነርሱ አስተምህሮ በተቃራኒ እንደሚቆም ለመረዳት አይከብድም[11]። ይህ ወንጌል ልዩ የሆነ ነገረ ክርስቶስን ይዟል፤ ይህንንም ኢየሱስ አባቱን ለመተረክ ከሰማይ የመጣ፤ ተግባሩንም ተወጥቶ ወደመጣበት የተመለሰ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ በአግባቡ በማሳየት ገልጦታል። (ዮሐ 1:18፣ 3:13፣ 6፡33፣ 38)። በስጋ የተገለጠ አምላክ የሚልን ነገረ ክርስቶስ በዋናነት የምናገኘውም እዚሁ ወንጌል ውስጥ ነው። መንፈስ ቅዱስ በታሪካዊው ክርስቶስ (Historical Jesus) የተገለጠውን እውነት ወደ አማኞች በማምጣት ተግባሩ ተገልጧል። የዩሐንስ ወንጌል በቃልና በስራ ለእግዚአብሔር የመታዘዝን ስነ ምግባር በኢየሱስ በኩል ያስተምራል። ዋናውን የኢየሱስን ትእዛዝ ፍቅርንና ትህትናን በአማኞች መሃል ያስተዋውቃል (ዮሐ 13:14)። ይህንንም ኢየሱስ ራሱ በተግባር በማድረግ አስተምሯል (ዮሐ 15:12-14) [12]

ወንጌሉ የተጻፈበት አላማ

➥ለዚህ ጥያቄ እንደ መልስ የሚቀርበው የመጀመሪያው መላ ምት ዮሐንስ ወንጌሉን የጻፈው ለሶስቱ ወንጌላት ተጨማሪ ድጋፍ ይሆን ዘንድ ነው ይላል። በዚህ መላ ምት መሠረት ሐዋርያው ከእርሱ በፊት የተጻፉትን ሶስቱን ወንጌላት በተመለከተ ጊዜ ይዘታቸው አላረካውም፤ ስለዚህም ወንጌሉን በዚህ መልኩ ጻፈው። ነገር ግን ወንጌሉ በሶስቱ ወንጌላት ላይ ጥገኝነት ባለማሳየቱ ይህ መላ ምት ብዙውን ጊዜ ውድቅ ይደረጋል። ሌሎች ደግሞ ስጋ ሁሉ ርኩስ ነው የሚለውን የኖስቲካውያን ትምህርት ለመዋጋት እንደተጻፈ ይናገራሉ። ነገር ግን የኖስቲክ ትምህርት የሁለተኛው ክ/ዘ ትምህርት እንደመሆኑ በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን የተጻፈውን ወንጌል እንደ ውጊያ መሳሪያነት እንዳንመለከተው ይገዳደራል። ሌላው ታሳቢ አላማ ደግሞ ዮሐንስ ወንጌሉን የጻፈው የማያምኑ አይሁዳውያንን ለመዋጋት ነው ይላል። እንደ ማስረጃም “አይሁድ” የሚለው ቃል ከሌሎች ጸሃፊያን ይልቅ በዮሐንስ ጥቅም ላይ መዋሉን ያቀርባሉ። ነገር ግን ይህ የወንጌሉ አንድ ትኩረት እንጂ ዋና አላማ አይደለም በማለት ውድቅ የሚያደርጉት ምሁራን ይበዛሉ [13]። የወንጌሉ አላማ በዚህ ደረጃ የሚያመራምር ሆኖ ቢገኝም ጸሃፊው ግን ለአንባቢያኑ ሊናገር የፈለገውን ነገር በግልጽ አስቀምጧል። ኢየሱስ እርሱ በአባቱ ተልኮ ከሰማይ የመጣ፤ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን ማስረዳት የዮሐንስ ወንጌል ዋናው አላማ ነው (ዮሐ 20:30-31)።

ለዛሬዎቹ አማኞች የዮሐንስ ወንጌል የሚሰጠን ጥቅም 

➥ልክ ቀድሞ ለመጀመሪያዎቹ ተደራሲያን ጠቅሞ እንደነበረው ለኛ ለዛሬዎቹ አንባቢዎችም የኢየሱስ ክርስቶስን የእግዚአብሔር ልጅነት በማስረዳት ነገረ ክርስቶሳችንን እንድንቃኝ ያስችለናል። እንደዚሁም ከእግዚአብሔር ጋር ትክክለኛ ግንኙነት መመስረት የሚቻልበትን የመታዘዝ ልብ ዛሬም ከኢየሱስ አገልግሎት እየተማርን እንድንተገብረው ያግዘናል። በተጨማሪም አማኞች እርስ በርሳቸው የመዋደዳቸውንና በአንድነት የመኖራቸውን ጥቅም ሲያስተምረን መንፈስ ቅዱስ በእኛ ህይወት ውስጥ የሚሰራውን ታላቅ ስራም በየእለቱ ያስገነዝበናል።

ዋቢ መጻሕፍት

[1] Eusebius of Caesarea, Ecclesiastical History Book 6, Chap. 14, Verse 7
[2] Kolin J. Kruse; TNTC Vol. 4, John: an introduction and commentary; 2003; page 20
[3] የአዲስ ኪዳን ቅኝት፤ ሜሪል ሲ. ቴኒ (የአማርኛው ትርጉም)፣ የኢትዮጵያ ቃለ ህይወት ቤተክርስቲያን፤ 1998 ዓ.ም
[4] THE GOSPEL ACCORDING TO JOHN (REVISED); Leon Morris: 1971: page 53
[5] JOHN THE NIV APPLICATION COMMENTARY; GARY M. BURGE, 1973: Page 28
[6] Exposition of the Gospel according to John; William Hendriksen; Baker book house: 1953: page 29
[7] The Gospel according to John- The pillar New Testament commentary; D.A Carson; Page 31
[8] Kolin J. Kruse; TNTC Vol. 4, John: an introduction and commentary; 2003; page 36
[9] Kolin J. Kruse; TNTC Vol. 4, John: an introduction and commentary; 2003; page 20
[10] [John: a commentary; Marianne Meye Thompson: The New Testament library: 2015; page 2-3]
[11] The Gospel of John: a commentary; Rudolf Bultmann: 1971: page page 8
[12] D. Moody Smith; John – Abingdon New Testament Commentaries; 1999 page 46
[13] THE GOSPEL ACCORDING TO JOHN (REVISED); Leon Morris: 1971: page 49

ለሌሎች ያጋሩ

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top