ቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለባቸው ናቸው፤ ለማስተማር፣ ለመገሠጽ፣ ለማቅናት በጽድቅም መንገድ ለመምከር ይጠቅማሉ።
2ኛ ጢሞ 3፥16 (አዲሱ መ.ት)
መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ለክርስትና እምነተ መርሕ መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ የማይሳሳትና ሊሳሳት የማይችል ባለሥልጣን እንዳለው የሚገልጽ ክርስቲያናዊ መርሕ ነው። ይሄንን ሐሳብ ብርሐነ አለም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለመንፈሳዊ ልጁ ለጢሞቴዎስ በጻፈለት መልዕክት ላይ ቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ እስትንፋሰ እግዚአብሔር (ቴዎኔዩስቶስ/θεόπνευστος) መሆናቸውን ሲነግረው እንመለከታለን። በዚህም መሠረት ቅዱሳት መጻሕፍት እስትንፋሰ እግዚአብሔር አፊዎተ እግዚእ ማለትም በቀጥታ መለኮታዊ ግልጠት መሆናቸውን እና ከዚህም የተነሳ እውነተኛ እና ሕጸጽ አልቦ ናቸው ብለን እናምናለን። የቤተ ክርስቲያን አበው ይህንኑ ሐሳብ ሲደግፉ ይስተዋላል። የአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን አባት ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ(John Chrysostom) ክፍሉን በድርሳኑ ላይ ሲያብራራ ቅዱሳት መጻሕፍት አፊዎተ እግዚእ መሆናቸውን እና ለአማኞች ትክክለኛ የቅድስና እና የህይወት መንገድ መሮች መሆናቸውን ይናገራል።[1] ቅዱስ ሔሬኔዎስ ዘሊዮን በመድፍነ መናፍቃን መጽሐፉ ላይ ቅዱሳን መጻሕፍት እስትንፋሰ እግዚአብሔር እና የበላይ ባለስልጣን መሆናቸውን በመግለፅ እውነተኛው የክርስትና አስተምህሮ መሠረት የሆኑ እና ሐሰተኛውን አስተምህሮ የምንከላከልባቸውም (የምንመክትባቸው) ጭምር እንደሆኑ ይገልጻል (Against Heresies)። ቅዱሳት መጻሕፍት የእግዚአብሔር እስትንፋስ በመሆናቸው ስለ እውነት ፤ ክርስትያናዊ የሕይወት መርህ እና ድነት አስፈላጊ የሆኑትን ሥነመለኮታዊ አስተምህሮ ሁሉ በውስጡ ያካተቱ በመሆናቸው ለዚህም አስተምህሮ ብቁ ባህሪዎት እንዳላቸው እንመለከታለን። ቅዱስ አትናቴዎስ (Athanasius of Alexandria) በክታቡ እንዲህ ሲል ይናገራል፦
The Holy Scriptures, given by inspiration of God, are of themselves sufficient toward the discovery of truth.[2]
ነገር ግን የእግዚአብሔር ቃል ለክርስቲያን ሥነመለኮት ብቁ ነው ስንል በራሱ ትውፊትን የሚያገልል ወይም የሚቃወም ተደርጎ በፍጹም መታሰብ የለበትም። ይሄ አስተምህሮ ግን ማለትም የመፅሐፍ ቅዱስን በቂነት(Material Sufficiency) ልጅ የጥንት ማህበረሰብ ስምምነት(ኮንሴንሰስ ፓትረም) ያለው እምነት መሆኑ ፕሮቴስታንት በዚህ ላይ ጽኑ መሠረት እንዳለው እናውቃለን። ይሄ አስተምህሮ ግን ለትውፊት, ለአምልኮ ሥርዓት ሆኑ ለጉባኤያት አስተምህሮ እና እውነተኝነት ትክክለኛው መመዘኛ መጽሐፍ ቅዱስ መሆኑን የሚናገርም ነው።
በተጨማሪም ሁሉም ከፍተኛ ባለሥልጣን ለሚለው ለመጽሐፍ ቅዱስ መገዛት እና ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ህብረት መፍጠር እንዳለባቸው የሚያመላክትም ጭምር ነው። ምክንያቱም ትውፊት, የአምልኮተ ሥርዓት ሆኑ, ጉባኤዎች የማይሳሳቱ ስላልሆኑ ማለትም ሊሳሳቱ የሚችሉ በመሆናቸው ምክንያት መመዘን ያለባቸው አይሳሳቴና የእግዚአብሔር እስትንፋስ በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ነው። ይህንን ሐሳብ ቅዱስ አውግስጢኖስ ዘሒፖ(Augustine of Hipo) በመደገፍ መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ዝንፈተ እውነት የሌለበት እንደሆነ ይናገራል፦
I have learned to yield this respect & honor only to the scripture, of these alone do I most firmly believe that completely inerrant (free from error) [3]
ትውፊትም, የአምልኮ ሥርዓቶች ሆኑ ጉባኤያት ስህተት ሊገኝባቸው ይችላል። ምክንያቱም የትውፊት አስተላለፋቸውን በተመለከትን ጊዜ በሰዋዊ አተረጓጎም, በተፈጥሮዋቸው የሚሳሳቱ ስለሆኑ እና በባህል ተጽዕኖ የታሰረ በመሆኑ ትክክለኛው መልዕክቱ ተበላሽቶ(ተቀይሮ) ሊሆን ይችላል። በተለይም ትውፊት እና የሃይማኖት ሥርዓታዊ ድርጊቶች በዘመናት መሐል የተለያየ ብርዘት እና ለውጥ ሊገባባቸው የሚችሉ ናቸው። ለምሳሌ ያክል በካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የጳጳሳቱ መብት እያደገ እየተሻሻለ በመምጣት ወደ የፖፑ አለመሳሳት(papal Infallibility) በመጨረሻም ወደ ስህተት መምጣታቸው የሚዘነጋ አይደለም። በተጨማሪም በነገረ ማሪያም ያላቸውን ዶክትሪን እጅጉን እየለጠጡ በመምጣታቸው ወደ Immaculate conception(አንዳንድ ኦርቶዶሳውያንም ይህንኑ አስተምሮ ይቀበላሉ) እንዳመሩ እንመለከታለን። የፑርጋቶሪ ምልከታ ሌላው የሚጠቀሱ ጉዳዮች ናቸው። በኦርቶዶክሱም ሆነ በካቶሊኩም የሚስተዋለው የመጽሐፍ ቅዱስ የቀኖና ችግር ስንመለከት ትውፊት በዘመናት መካከል ሊቀያየር እና ሊበከል የሚችል ጉዳይ ሁኖ እናገኘዋለን። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በማቴዎስ ወንጌል 15:3 ላይ በመለኮታዊ ግልጠት ላይ ያልተመሠረተውን ያልሆነውን የአይሁዳውያንን ትውፊት ሲመረመር እንመለከታለን። የመጽሐፍ ቅዱስ ብቻ እነዚህ ሁሉ ትውፊት እና ስርዓተ አምልኮ በሕጸጽ አልቦው እና በአይለወጤው በእስትንፋሰ እግዚአብሔር ቃል መሠረት ተመዝነው መጥራት ያለባቸው ጉዳዮች መሆናቸውን የሚገልጽ ክርስቲያናዊ መርህ ነው። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ትክክለኛው ሚዛን እና የሁሉ የበላይ ሊሳሳት የማይችል ባለስልጣን የሆነ ያለው ነው።
ማጣቀሻ
1] Homilies on 2 Timothy
2] Against the Heathen, 1:3
3] Letters, 82:3