የነገረ ምክንያትነት ህግ(Law of Causality) – ክፍል 1

“ሰነፍ በልቡ፦ አምላክ የለም ይላል”
  — መዝሙር 14፥1

የነገረ ምክንያትነት ህግ(Law of Causality) የፍልስፍና እና የሳይንሱ መሠረታዊ መርህ ሲሆን ማንኛውም ውጤት የራሱ የሆነ መንስኤያዊ እርሾ እንዳለው የሚያትት መርህ ነው። ምክንያትነት አመላካችነቱ የሆነ ነገር እንዲከሰት የሚያደርገውን ውጤት አዘል መንስኤን የሚያሳይ ነባቤ ቃል ነው። ክርስቲያናዊው የነገረ መለኮት እና የፍልስፍናው ሊቅ ዊሊያም ሌን ክሬግ ወደ ህላዌ የመጣ አካል ሁሉ ለመገኘቱ ምክንያት የሚሆን ከሳች ሐይል እንዳለ ይናገራል። በተጨማሪም ማንኛውም ነገር ከምንም እንደማይገኝ ይናገራል[1]፦

“ከምንም ምንም ነገር ሊከሰት አይችልም አልያም አንድ ነገር ከምንም ተነስቶ ህልው ሊሆን አይችልም”
  — ክሬግ —

አንድ ነገር ከምንም ተነስቶ ሊከሰት ካልቻለ ለህልውናው መንስኤ የሆነ አንድ ምክንያት እንዳለ አመላካች ነው።[2] ነገር ግን ይህ አይነቱ ነባቤ ቃል የማይዋጥላቸው በፍልስፍናው አለም ያሉ ሳይንቲስቶች መኖራቸው የማይካድ ሐቅ ነው። ለምሳሌ ቴዎረቲካል ፊዚሽያኑ አሌክስ ቪሌንኪን ሁሉ አቀፉ ሕዋ በቅጽበታዊ(ድንገታዊ) ክሳቴው ከወናዊ ኳንተም (quantum vacuum) የመነጨ መሆኑ እና ይህም ደግሞ ሕዋ ከምንም ነገር ሊመጣ እንደሚችል የሚያሳይ ነው በማለት ይናገራል።[3] ይህንን ሐሳብ በመደገፍ ዴቪድ አልበርት ወናዊ ኳንተም (quantum vacuum) ነገሮች ከምንም መፈጠር እንደሚችሉ ያሳያል የሚል እምነት አለው።[4] በሌላ በኩል ደግሞ በሐይማኖታዊው ፍልስፍና የሚታወቀው ሪቻርድ ስዊንበርን አንድ ነገር ድንገት ያለ ምንም ምክንያት ህልውና አገኘ የሚለው ሙግት ሕጸጻዊ እና ኢ ምክንዮአዊ ሙግት ነው ሲል የእነ ዴቪድ አልበርት እና የአሌክስ ቪሌንኪንን እሳቤ ክፉኛ ይቃወማል።[5] በተለይ እውቁ እና በሳይንሱ አለም በክኑሳዊያን ተመራማሪዎች ትልቅ ተቀባይነት ያገኘው የታላቁ ፍንዳታ ቴዎሪ(Big Bang Theory) ሕዋ ኅሉቃዊ ጅማሮ(finite beginning) ያለው መሆኑን የሚያሳየውን መርህ ስንመለከት ይበልጡን አለም ካለመኖር ወደመኖር ያመጣት ከሳች ሐይል እንዳለ አመላካች ቴዎሪ ሁኖ እናገኘዋለን። ስለዚህ ሕዋ ያልነበረበት ካለ ለመገኘቱ ውጤት ከሳች አንድ ሐይል መኖሩን አንጡራዊ ቅድመ ሁኔታ ሁኖ እናገኘዋለን። ዊሊያም ሌን ክሬግ ይህ አይነቱ ከሳች አካል በአራት ወሳኝ ባህሪያተ ነጥቦች ይገልጹታል፥[6]

1) ጊዜአልቦ ማንነት(Timeless):- በታላቁ ፍንዳታ ቴዎሪ(Big Bang Theory) ጊዜ የሚባለው መስፈሪያ በራሱ ህላዌ ያገኘ በመሆኑ ጊዜን አስገኚው አካል ከጊዜ ውጭ ወይም ዘላለማዊ የሆነ ምንነት ነው

2) ኢ-ቁሳዊነት(Immaterial):- ቁሳዊ አካላት የተፈጠሩበት ምክንያት ስለሆነ ምክንያታዊው አካል ኢ-ቁሳዊነትን ባህሪዎት ገንዘቡ ያደረገ ነው

3) ልዕለ ሀይል ያለው(Powerful being):- ይህን ለቁጥር የማይመችን ፍጥረታዊው አለም ከዚህ አካል የተፈጠሩ እንደሆኑም መጠን ምክንያት እና ውጤት ከሳቹ አካል ወደር አልባ ሐይል ያለው መሆን አለበት

4) እኔ ባይ ቅዋሜ ማንነት ያለው(Personal):- የህዋ አስገኝ አካል እኔነት ያለው አካል መሆኑ መላው ፍጥረተ አለሙን ወደ መኖር ማምጣቱ ንቃተ ፈቃድ፣ እውቀት እና ስሜት ያለው አካል መሆኑን አመላካች ነው

ይህን ያለንበትን ሕዋ ስናስብ ዝም ብሎ ድንገት የተከሰተ ሳይሆን ለመከሰቱ የሆነ አካል ከጀርባ እንዳለ የተፈጥሮውን አለም ባህሪዎት ስንመለከት የምንረዳው ጉዳይ ነው። ይህ ከሳች ሐይል ደግሞ ምንም ነገር(Nothing) ሊሆን ፈጽሞ አይችልም። የክኑሳዊው ሙግት ይሄንኑ የሚያስረዳ ነው፦

  1. አዋጅ ፩፦ ወደ መኖር የመጣ(የጀመረ) ማንኛውም ነገር ለመገኘቱ(ለህላዌው) ከሳች መንስኤ አለ
  2. አዋጅ ፪፦ ሕዋ ወደ ህልውና የመጣ ነው(መኖር የጀመረ ነው)

ስለዚህ፦ ሕዋ ከሳች ምክንያተ መንስኤ አለው

ይህ የምንመለከተው አጽናፈ አለም በሆነ ጊዜ ህልው የሆነ እና ለመገኘቱ ጅማሮ ያለው ክስተት ነው። በሕዋ ውስጥ ያለ ማንኛውም ቁሳዊ አካል፣ ህያው ፍጥረት ሆነ ማንኛውም በዚህ ክበብ ውስጥ ያለ ክስተት ሁሉ ለመገኘቱ አስገኚ ምክንያት አለው። ለምሳሌ ዛፎችን ስንመለከት ለዛፎች መገኘት የዘሮች መተከል ወይም መዘራት እንደ ዋነኛ ከሳች ግብአት ነው። ይሄም ሐሳብ በፍልስፍናውም ምክንዮ ሆነ በሳይንሱ አለም ተቀባይነት አለው። ሌላው ሕዋ እራሱ ኅልቁ አላፊ ጊዜ ሊኖረው አይችልም። ምክንያቱም በእውናዊው አለም ፍጹም ኅልቁአዊ ኑባሬ (actual infinity) የሚባል ነገር እንደሌለ የሳይንሱ እና የፍልስፍናው አለም ያምናል። ክስተቶች ሁሉ ኅልቁ መሳፍርት ቢኖራቸው አጽናፈ አለሙ አሁን ያለበት ሁኔታ ላይ መድረስ እንደማይችል ይናገራሉ። በዚህ ምክንያት ሕዋ ወይም አጽናፈ አለም በሆነ ጊዜ የተከሰተ በመሆኑ ለክስተቱ ደግም ምክንያት የሌለው መንስኤያተ ምክንያት (uncaused cause) እንደሚኖረው አረጋጋጭ እውነታ ነው።

እግዚአብሔር አምላክ ክስተቶች እና ለነገሮች ሁሉ ከሳች ምክንያት የሌለው መንስኤያተ ምክንያት (uncaused cause) ነው ስንል ከላይ እንደተመለከትነው ዘላለማዊ የሆነ፣ ቁሳዊ ያልሆነ፣ የማስገኘት ልዕለ ሐይልን የተጎናጸፈ እና እኔ ባይ ማንነታዊ ቅዋሜ ያለው አካል መሆኑን የሚገልጽ ነው። ሊቁ የኒሳው ጎርጎርዮስ ስለ እግዚአብሔር ዘላለማዊነት ሲናገር፦

“የእግዚአብሔር መለኮታዊ ባህሪዎት ያልተፈጠረ እና ዘላለማዊ የሆነ፤ ምንጊዜም የነበረ፣ ያለና የሚኖር ጅማሬ እና ፍጻሜ የሌለው፤ በጊዜ እና በቦታ ያልተወሰነ፣ የማይለዋወጥ ሁልጊዜም ያው የሆነ አምላክ ነው። ስለዚህ እግዚአብሔር አምላክ የሌለበት ጊዜና ሁኔታ አለ ሊያስብለን የሚያስችል ምክንያት ፈጽሞ አይኖርም”
Against Eunomius 1:12

ሊቁ አምላክ ዘላለማዊ እና ለጅማሮው መንስኤ የሌለው በጊዜ የማይወሰን መሆኑን ይናገራል። ቅዱሱም መጽሐፍ እንደሚናገረው ማንኛውም ነገር ከአለመኖር ወደ መኖር ከመምጣታቸው በፊት እግዚአብሔር አምላክ እንደነበር ይናገራል፦

“ተራሮች ሳይወለዱ፥ ምድርም ዓለምም ሳይሠሩ፥ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ አንተ ነህ።”
  መዝሙር 90፥2

ስለዚህ እግዚአብሔር አምላክ ዘላለማዊ ከሆነ ከጊዜ ውጭ የሆነ እና ጊዜ የሚባለውን መስፈሪያ አስገኚ ነው። የነገረ ምክንያትነት ህግ(Law of Causality) በጊዜ ውስጥ የተገደበ ማንኛውም ነገር ለመገኘቱ ምክንያት አለው ስለሚል ፍጥረታዊው አለም ደግሞ ለመገኘቱ  ጅማሮ እና ከጀርባው ከሳች ምክንያታዊ ሐይል እንዳለው የሚያሳይ ነው። በሌላ በኩል ከጊዜ ውጭ የሆነው ከሳች ሐይል ግን ለመገኘቱ ምክንያት ሊኖረው ፈጽሞ አይችልም። ምክንያቱም ስለ ከሳቹ ሐይል ስናወራ ዘላለም የሚባለው ገደብ የለሽ ጊዜ ስለሚነሳ እና ከጊዜ ውጭ ስለሆነ ራሱ ምክንያት የሌለው መንስኤያተ ምክንያት(Uncaused Cause) ነው እንላለን። ይሄም ክኑሳዊው ሙግት ያረጋግጥልናል።

ማጣቀሻዎች፦

[1] Craig, William Lane. The Kalam Cosmological Argument. Wipf and Stock Publishers, 2000. page 303
[2] “ከምንም ነገር ምንም ሊከሰት አይችልም/ex nihilo nihil fit”
[3] Alex Vilenkin (Many Worlds in One): Suggests that the universe could arise spontaneously from “nothing.” (Page 181-182)
[4] David Albert (Quantum Mechanics and Experience): Critiques modern redefinitions of “nothing” in scientific contexts. (Page 142-144)
[5] Swinburne, Richard, The Existence of God /Clarendon Press, 2004, Page 50-53, 138-140/
[6] Craig, William Lane. The Kalam Cosmological Argument. Wipf and Stock Publishers, 2000, page 182,87,228

ለሌሎች ያጋሩ

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top