Soli Deo Gloria/ክብር ለእግዚአብሔር ብቻ

በቤተክርስቲያን ታሪክ ውስጥ ከተወገዙ የምንፍቅና መምህራን አንዱ ፔላጄዬስ ነው። እርሱም እግዚአብሔር በሰው ልጆች የድነት ስራ ላይ በብቸኛነት ያለውን ባለቤትነት ፈፅሞ ከወደቀው ሰው ነፃ ፈቃድ ጋር የጋራ ስለነበረ ነው በማለቱ ነው።(ይህን ታሪካዊ ምሳሌ ያነሳንበት የምንሞክርበት ምክንያት ለእግዚአብሔር ክብር ብቻ የሚለው ክርስቶስ ካደረገው የድነት ሥራ ጋር ስለሚገናኝ ነው።) ይህ ሰው የእግዚአብሔርንም ጸጋ ለሰው ልጆች ድነት አነሳሽ ብቻ እንጂ የድነት ምንጭ አይደለም ብሎ ያስተምራል። ይሄን ትምህርት ደሞ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ በክታቡ ከዚህ በተቃራኒው ሆኖ እንዲህ ይናገራል፦

“ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል፤”
  — ሮሜ 3፥23

ክፍሉ የሰው ፈቃድና ባህሪይ በኃጢአት መበከል፣ ከእግዚአብሔር እንደለየው፣ የሰውም ፈቃዱም ወደ እግዚአብሔር ፈፅሞ ሊሆን እንደማይችልና እርሱንም ሚፈልግ ማንም እንደሌለ በክታቡ እንዲህ በማለት ይናገራል፦

“ጻድቅ የለም አንድ ስንኳ፤ አስተዋይም የለም፤ እግዚአብሔርንም የሚፈልግ የለም፤ ሁሉ ተሳስተዋል፥”
  — ሮሜ 3፥11

ከዚህም መጽሐፍ እንደምንረዳው የሰው ድርሻ  በድነቱ ውስጥ ባዶ ቦታ እንዳለው ይናገራል። ስለዚህም ጻድቅ የሆነውን እግዚአብሔርን ሊመርጥ በሰውም በኩል ወደ እግዚአብሔር ልቡንም ወደ ፈጣሪው ሊመልስ ይህ ሙት ሰው አይቻለውም ምክንያቱም ሁሉ ኃጢአትን ሰርተዋልና። የሞተስ እንዴት ሕይወትን ይመርጥ ዘንድ ይቻለዋል? ነገር ግን በምህረቱ ባለፀጋ ስለሆነ ስለወደድን ሳይሆን ስለወደደን ብቻውን ለድነታችን ምክንያት፥ የድነታችንም ፍፃሜ ሆነልን። በቀደመው ኪዳን ተስፋ በእርሱ ላይ ባላቸው እምነት አባቶችን አዳነ፥ በዘመኑ መጨረሻ  በልጁ የቤዝዎት ስራ ህጉን መጠበቁን አውቀን በእርሱ ስላመንን ብቻ ጽድቁን ቆጠረልን። ደግሞም አለማትን በፈጠረበት በልጁ የጠፋውን ህዝብ ተቤዥቶ አለሙን አዳነ። በእርሱ ብቻ ተፈጠርን፣ በእርሱ ብቻ ዳንን ያዳነን እርሱ ይቀድሰናል፣ የቀደሰን እርሱ ራሱ ያጽናናል፣ ያጸናን እርሱ ደግሞ ያከብረናል። ወደ ፈጠረን ወደ አባታችንም እንፈፀማለን። በዚህ እንቅስቃሴ ነው የተሐድሶ አራማጆች በሮማ ካቶሊክ ያለውን የተሳሳተ ግንዛቤ ማጥራት መጀመራቸው የሚታወሰው። ታዲያ ለእኛ ምን ይሰራል? ለምን እስካሁን ተቃውሞ ታደርጋለህ? ቢባል መልሳችን እንደ ተሐድሶውያኑ መሠረት የሮማ ካቶሊክ ኢስተርን ሆነ ሌሎች ታሪካዊ ቤተክርስቲያን አማኞች በአብዛኛው ንግግራቸው ሆነ ፍለጋቸው ለእግዚአብሔር ክብር ብቻ የሚል ነው ይላሉ። ነገር ግን በሚያሳዝን ሁኔታ ግን በተሐድሶ ወቅት የካቶሊኩ ምልከታ ፖፑና ቅዱሳን በሚባሉት ላይ ነው። በሌሎቹ ቤተክርስቲያን የፖፑ አለመቀብልን እናም አይሳሳቴነትን ትተው የቅዱሳን ክብር ገኗል።(ይሄን ስንል እኛ ክላሲካል ፕሮቴስታንት ለቅዱሳን ክብር አይገባም ማለት አይደለም።) ይሄን የእኛን አቋም ለመረዳት አንድ ሰው እንዲህ ሲል የጠየቀንን ጥያቄ ማንሳት ይቻላል፦

ጥያቄ፦ ማርያም የድነታችን ምክንያት ናት ወይ?

መልስ፦ በሥጋዌ ምክንያት አዎ ናት እንላለን። በእርሷ በኩል ጌታ ተገኝቷል የሚለውን ነገር ብቻ ለመግለጽ ከሆነ። ለድነታችን ምክንያት ስንል(የአምላክ እናት፣ የብርሃን እናት..) ይህንን ጠቅልሎ ማለታችንም ነው።

ጥያቄ፦ እና ታዲያ የምትቃወሙት ምንድነው? ኢየሱስን የድነቴ ምክንያት ብለህ እሷንም ማለትህ እኛ የተለየ ነገር አልን ወይ? ለምን ተቃወምክ?

መልስ፦ በድጋሚ እኛ የተቃወምነው ድነታችንን ሆነ ወደ እግዚአብሔር መቅረባችን የራሱን ክብር በመግጡ እንጂ ሰዎች ባደረጉት ወይም በእነሱ በኩል መግባትን ወይ ያለ እነርሱ የሚልን ነገረ ድነታዊ ተፋልሶን ነው። ይሄንንም አጥብቀን ምንቃወመው ከእነዚህን ጋር ተያይዘው በCatechism of the Catholic Churchም ሆነ በሌሎች ቤተ ክርስቲያን ዘንድ የተቀመጡትን የተለጠጠ ግንዛቤዎችን እንቃወማለን፦

“By asking Mary to pray for us, we acknowledge ourselves to be poor sinners and we address ourselves to the ‘Mother of Mercy,’ the All-Holy One” (CCC 2677).

“After speaking of the Church, her origin, mission, and destiny, we can find no better way to conclude than by looking to Mary” (CCC 972).

ሌላም በእናተው መካከል በቀላሉ የማናልፈው ነገር፦ ” ለእኛ ድኅነት ብዙ መንገድ አለ” በማለት በየምስባኩ ሰው ሰራሽ ዶክትሪን በማሳየት፣ ይባስም ብሎ የእግዚአብሔርን የማዳን ክብሩን የሚነቅልና የሰውን የመገናኛ ድንኳን የሚተክል ትምህርት ስላለ ነው።

እና ሌሎችም ነው። በድጋሚ እኛ ክላሲካል ፕሮቴስታንት ስንቃወም እየተቃወምን ያለውን ነገር አጥርቶ ማየት ያሻል። በዚህ ብርሃን መንገድ የተሐድሶ አበው ያሳደጉት ነገር አምስቱን ብቻዎችን ነው። ለዚህም መፍትሔው በቃለ እግዚአብሔር ላይ በተጨመሩ ትምህርቶች በአባቶች ትምህርት የሌሉትንና በታሪክ ዶግማ ተደርገው ያሉትን የእግዚአብሔርን ክብር የሸፈኑትን እነዚያን ተቃውመው ቆሙ።

➞ ስለዚህም ምክንያት ክብር ለእርሱ ብቻ ይገባዋል።

➞ ብቻውን የድኅነታችንን ስራ ሰርቶታልና።

➞ የማዳኑ ኪዳኑ መሰረት እርሱ ብቻ ላይ ብቻውንም አዳኝ  ስለሆነ ላዳነን ለእርሱ በብችኛነት ሌላ ሳይጨመር ሳይደመር አምልኮ ስግደት ይገባዋል።

➞ ብቻውን ሊደነቅ ሊመሰገንም የተገባው ነው እጅግ ድንቅ ግሩምም ነውና። ምክንያቱም እርሱ፦

እንደ እንቁ የተዋበ በኪሩቤልም ላይ የሚቀመጥ በመዞርም ጥላ የማይገኝበት ማንም ሊቀርበው በማይችል ብርሃን ተሰውሮ ለዘላለም ሚኖር ሰማያትን ያለ ምስሶ የዘረጋ ምድርንም በውኆች ላይ ያፀና የምድርም አህዛብ በፊቱ በገምቦ እንዳለች ጠብታ የሆኑለት በጽድቅ የሚፈርድ መሐሪ የአብርሃም የይስሃቅ የያእቆብ አምላክ  የዘላለም አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሄር ሚመስለው የለም!  

በዚህም መሠረት ደሞ እርሱም የተባረከ አምላክ ነው ሰውም መድኃኒት ይሆን ዘንድ አይቻለውምና። ይሄን ሐዳሲያኑም ሲሉም ሆነ እኛም ስንለው ቅዱሳንን ክብር አንሰጥም ማለት አይደም። እነሱን ምናከብረው ግን ድነትን መንገድ በመለጠጥ ከሆነና ወይ ደሞ ለእግዚአብሔር የቀረበውን የሚቀናጅ ከሆነ ግን በእግዚአብሔር ክብር ላይ አደጋ ነው። በታሪካዊ ፕሮቴስታንቱ ተሐድሶ ውስጥ ትልቅ ትኩረት የተሰጠውና የአስተምህሮቶች ሁሉ መጠቅለያ ነው።

“It is not sufficient for anyone, and it does him no good to recognize God in his glory and majesty, unless he recognizes him in the humility and shame of the cross.”
—Martin Luther
“We never truly glory in him until we have utterly discarded our own glory. . . . The elect are justified by the Lord, in order that they may glory in him, and in none else.”
—John Calvin

በድጋሚ እንጠየቅ እስኪ?why it still matters(በዚህ ዘመን ላለነው ምን ፋይዳ አለው?)

በአጭሩ እኛ ክላሲካል ፕሮቴስታንት በዚህ ዘመን ያለነው ይሄን ለምን እናምናለን የሚለውን ስንመልስ፦ ለእግዚአብሔር ክብር ብቻ የተሃድሶው መሠረታዊው አስተምህሮ የሁሉም ነገር የመጨረሻ ዓላማ ለእግዚአብሔር ክብርን ማስገኘት ነው የሚል ነበር። እነሱ ከመጽሐፍ ቅዱስ የወጣውንና ከቤተክርስቲያን የተገኘውን ያንን መሠረት ይህም የእግዚአብሔርንም ሉዓላዊነት አፅንተው በመጠበቅ፣ የሚሆነው ነገር ሁሉ ከሰው ወይም ከፖፑ(ካቶሊኮችን ነው) ይልቅ እንዴት ለእግዚአብሔር ክብር እንደሚሆን ያስተማሩትን ዛሬም እኛም ማስተማር ስላለብን። አንደ ተሐድሶውያኑ በዘመናቸው ለእግዚአብሔር የሚገባውን ያንን ክብር የወሰዱ አካላት ነበሩ ብለው ተቃውመዋል። በዚህ ዘመንም የእግዚአብሔርን ክብር የሸፈነ አለ። ሻገር ብንልም አምልኩ ቢባል ምን እንደሚጨመር እስከማይታወቅ ድረስ የሚሰጥ ክብር(ኤጲፋንዮስ ኮሊሪዲያንን የተቃወመውን አይነት ላቅ ያለ ክብር ለፍጥራን መስጠት) ብዙ መንገዶች አሉ፤ ለድነታችን ብዙ መፍትሔ አለ። በማለት የክርስቶስ የማዳንን ክብር ዝቅ እስከማድረግ ስለደረሱ ነው። በቀላሉ የማናልፈው ነገር ብዙ መንገድ አለ በማለት በየምስባኩ የእግዚአብሔርን የማዳን ክብሩን የሚነቅልና የሰውን የመገናኛ ድንኳን ስለሚተክል ነው።

በመጨረሻም በ16ኛው ክ/ዘ የነበረው የፀጋ ልዩነቶች ነበር። ለእኛም በዚህ ዘመን ፋፍቶና በዝቶ ተቀምጧል። ስለዚህ እኛ ክላሲካል ፕሮቴስታንት ነገረ ድነት ይሁን ሌላ አሁን ላይ ከእነሱ በኋላ በብዙ አካላት መካከል በማደጉ አሁን ላይ የምንቃወምበት ብዙ መሠረታውያን ነጥቦች ይኖሩናል። እኛም እንደ ተሐድሶውያኑ Soli Deo Gloria/ክብር ለእግዚአብሔር ብቻ/ ስንል ይህንን ጽሑፍ በቅዱስ አውግስጢኖስ በኑዛዜ መጽሐፉ ክፍል.10 ምእ.27 ቁ.38 ጸሎት እንቋጫለን፦

"ምነው ዘግይቼ አንተን ማፍቀሬ! ኦ ጥንታዊም አዲስም የሆንክ ውበት፥ምነው ዘግይቼ አንተን ማፍቀሬ !እነሆ አንተ በውስጤ እያለህ በፈጠርካቸው ነገሮች መካከል ያለ ማስተዋል ስጣደፍ አንተ ከእኔ ጋር ነበርክ፤እኔ ግን ካንተ ጋር አልነበርኩም። እንዚህ ነገሮች ካንተ አርቀውኛል፥ ሆኖም እነርሱም ባንተ ባይሆኑ ኖሮ መኖር ባልቻሉ ነበር።ድምፅህን ከፍ አድርገህ ጮህክልኝ፤ጠራኸኝም። ድንቁርናዬን በሃይልህ ከፈትከው። ጸዳልህን ልከህ ሸፈነኝ፤ አበራህልኝም፤ አይነ ሥውርነቴንንም ገፈፍከው።መኣዛህን ለእኔ ተነፈስክ፤ተንፍሼም ሳብኩት፤ ተከትዬህም ቃተትኩ። ቀመስኩህ፤ ተራብኩ፤ ተጠማሁም። ዳሰስከኝ ለሰላምህ ተቃጠልኩ።"

እግዚአብሔርን ብቻ ፊት አድርገን መጓዝ ይሁንልን። አሜን!

ለተጨማሪ ንባብና ጥናት

➞ God’s glory alone— the majestic heart of Christian faith and life: what the reformers taught . . . and why it still matters / By David VanDrunen.

ለሌሎች ያጋሩ

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top