Author name: admin

የባሕርዩ ምሳሌ

በማህበራዊ ሚዲያ ላይ አንድ ሙግት መልስ ፈልጋለሁ በሚል ርዕስ አንድ ጥያቄ ተቀምጦ ነበር። ይኼም ሙግት ኢየሱስ ፍጡር ነው ከሚል ከአንድ አርዮሳዊ በተለምዶ የይሖዋ ምሥክሮች ቤተ ጎራ እንደሚመደብ ጥያቄውን ያነበበ ሰው ወዲያውኑ ያውቃል። ኢየሱስ ፍጡር ነው ያለውም ከዚህ ጥቅስ የተነሳ ነበር፦ “እርሱም የክብሩ መንጸባረቅና የባሕርዩ ምሳሌ ሆኖ፥ ሁሉን በስልጣኑ ቃል እየደገፈ፥ ኃጢአታችንን በራሱ ካነጻ በኋላ በሰማያት በግርማው ቀኝ ተቀመጠ፤”  — ዕብራውያን 1፥3 ምሳሌ ሲባል ሰው በእግዚአብሔር ምሳሌ ተፈጥሯል እናም ኢየሱስ የእግዚአብሔር ምሳሌ ነው። ስለዚህ ፍጡር ነው የሚል ድምዳሜን አስቀምጦም ነበር። መልስ ምሳሌ የተባለበት ምክንያት ኢየሱስ በትክክል አብን የሚገልጥ መሆኑን ለማመልከት እንጂ ፍጡር መሆኑን ለማሳየት አይደለም፡፡ ኢየሱስ የእግዚአብሔር አብ ምሳሌ መኾኑ የተጠቀሰበት አምላክነቱን ለክርክር ሊቀርብ በማይችልበት ኹኔታ የሚገልጥ ሌላ ጥቅስ በዕብራውያን መልዕክት ውስጥ ይገኛል(ዕብራውያን 1፥2 ዕብራውያን 1፥8 እና ሌሎችም)። ከጠያቂያችን ጥቅስ ግን ተነስተን በአጭሩ መልስ እንስጥ፡- “እርሱም የክብሩ መንጸባረቅና የባሕርዩ ምሳሌ ሆኖ፥ ሁሉን በስልጣኑ ቃል እየደገፈ፥ ኃጢአታችንን በራሱ ካነጻ በኋላ በሰማያት በግርማው ቀኝ ተቀመጠ፤”  — ዕብራውያን 1፥3 “የባሕርዩ ምሳሌ” ተብሎ የተተረጎመው “ሁፖስታሴዎስ ካራክቴር” የሚል የግሪክ ሐረግ ሲሆን ካራክቴር የአንድን ነገር ትክክለኛ፣ ያልተሸራረፈ፣ ከዚያኛው አካል ያላነሰ፣ እኩል የሆነ ማንነት የሚያሳይ ነው፡፡ ይህ “ምሳሌ” ከዚያኛው አካል ጋር በኹሉም ረገድ ፍጹም ተመሳሳይ ነው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሚነግረን ወልድ ከአብ ልዩ መኾኑን፤ ነገር ግን ደግሞ ከአብ ጋር ፍጹም እኩል መኾኑን ከምንም ዓይነት ጥርጣሬ በፀዳ ኹኔታ የሚገልጥ ክፍል ነው፡፡[፩] ስለዚህ ይሄ ክፍል ኢየሱስ ፍጡር ነው ተብሎ የቀረበው መለኮታዊ ባሕርዩን ገላጭ እና ይልቅም አምላክነቱን የሚያሳይ ሆኖ እናገኘዋለን። ማጣቀሻ [፩] Vines Complete Expository Dictionary of Old and New Testament Words, Thomas Nelson Publishers, Nashville Camden New York, 1984, P. 319.

የባሕርዩ ምሳሌ Read More »

“አንድ ታሪክ ላውጋችሁ”

ከአዲስ አበባ ወጣ ብላ በምትገኝ በአንዲት ገጠራማ አካባቢ የሚኖሩ አነስተኛ ማህበረሰብ ነበሩ። አብዛኛዎቹ የአውራጃው ነዋሪዎች ጣዖት አምላኪያን የነበሩና ስለ እግዚአብሔር መኖር የማያቁ የሆኑ እንደዋዛ የሚታለፉም አይደሉም። በዛ መካከል እውነትን የሚያቁ ጥቂት ክርስቲያኖች ግን አልጠፉም ነበር፡፡ ያው ጭስ ባለበት ጥቂትም ቢሆን እሳት አይጠፋም እንደሚባለው ተረቱ አንዳንድ ቦታዎች ላይ ሰፍረው ነበር።(ከዛ በፊት ሚሶናውያን በስፍራው ተልከው ወንጌልን ያደረሱ የነበሩ ይመስላል።) በጥልቀት በማህበረሰቡ ጫና ምክንያት ግን ወንጌልን ባለማድረሳቸው ብርቱ ክርስቲያን እንቁጠር ብንል እንደ ቦዘና ሽሮ ጥቂት ሥጋ ጣል ጣል ይመስል በትግል ነው የምናገኘው፡፡ (ያው ቦዘና ስለምወድ ምሳሌ ተጠቀምኳት፤ የምትወዱ ሰዎች ካላችሁ ከአፍቃሬ ነኝ ለማለት ነው)። በአንድ ወቅት እኒያ ወንጌልን የሰሙት ሰዎች ላልሰሙ ሰዎች ለማድረስ ለሁለት ተከፍለው ለጣዖት አምላኪውና አንዱ ወገን ደሞ አምላክ የለም(እግዚአብሔርን ለማያቀው) ተበታትነው በአንድነት ማሰራጨት ጀመሩ። በማህበረሰቡ መካከል በብዙ ታወቁ፣ ክርስትና ከዛች መንደር አልፎ ቀያቸውን ሙሉ አጥለቀለቀው፡፡ የዚህ ሁሉ ብርታትና የአንድነታቸው ምክንያት ለቤተክርስቲያን ቀናኢ ሀሳብ አለን ማለታቸውና አንዱ በአንዱ ስራ ጣልቃ ሳይገባ፣ ሳይንቅ፣ የሚሰራውን አገልግሎት ሳያሰናክልና ክፉ ሳያስብ አንድነትን ስለመረጠ ነበር። የሆነው ሁሉ ግን በአንዲት ክፉ ቀን ይሄ አንድነት ብዙ ርቀው እንዳይሄዱና ተሰናክለው እንዲወድቁ አደረጋቸው፡፡ የሰላሟ መንደርም ሁከት ተጀመረ። ለዚህ ሁሉ ጉስቁልና መንስኤ ክፋት ማሰባቸው ነበር። በተጨማሪም ሐዋርያው ጴጥሮስ በክታቡ እንዲህ ያለውን መዘንጋታቸው ነበር፦ “እግዚአብሔርንም በመምሰል የወንድማማችን መዋደድ፥ በወንድማማችም መዋደድ ፍቅርን ጨምሩ።” 2ኛ ጴጥሮስ 1፥7 እግዚአብሔርን ምሰሉ በተባሉበት ቦታ ይልቅ የራስን ፍላጎትን በሰዉ ዘንድ መሳላቸው፣ ከአሻጥር ይልቅ መዋደድን ሳሉ በተባሉበት ቦታ ላይ የእኔ ወንጌል በላጭ የእግዚአብሔሩ ሀሳብም በእኔ ተገልጧልና ፍቅር እኔ ጋር ነው፤ የእርሱ ወንጌል እንዲህ…በማለት ለማህበረሰቡ አልባሌ ስብከት ማሰማት ጀመሩ። ይሄ ነበር የውድቀታቸው ምክንያቱ፡፡ ታሪኩ በዚህ አላበቃም ቢያበቃማ ጥሩ ነበር፤ እነዚያ ወንጌል የሰሙ ያመልኩበትም የነበረችው ቤት በዚህ ሽኩቻ ወደቀች፣ የመንደሪቷ ቤተክርስቲያን ፖለቲካ ስለያዛት ተናደች፣ የአንዱን ግለሰብ ትችት ለገሃዱ ዓለም መናገር የሚያመጣውን ጦስ ስላልተገነዘቡ ጣዖት አምላኪያኑ ወደ እጣናቸውና ደም ማፍሰስ፤ አምላክ የለሾቹ ወደ ቁዘማቸው ገቡ፡፡ ይሄን ሁሉ ታሪክ ያነበብክ አንባቢዬ የነገሩ መጎሳቆል ለምን የሆነ ይመስልሃል? እንዲያ እንዲህ ብለህ ልታብራራ ከቻልክ ጥያቄው ላንተ በዝርዝር ከታች ላስቀምጥልህ፦  ➞ የክርስቲያኖቹ እንዲያ መሆን መንስኤው ምንስ ይሆን? ➞ በዚህስ ዘመን ምን እየሰማህ ይሆን? ➞ በዚህ ታሪክ ላይ ቀይራለሁ ብለህ ምታስበው ነገር ይኖር ይሆን? ኦኦኦ….ጥያቄማ አላብዛ ይቅር፤ ይሄ አጭር ማስታወሻዬ ጽሑፍ ለካ ብዙ ጥያቄ ያግዳል..! ጽሑፏም ጣፍጣ ለአንባቢያን በአጭሩ አትቀርብ ይሆን በሚል አሳጥሬዋለሁ፡፡ አድማጬና አንባቢዬ ሆይ..! ስትመልሳቸው ሐዋሪያው ጨምሩ ማለት ምን ማለት ይሆን? የምትለዋን ነገር ባትረሳት ጥሩ ነው፡፡ ጨረስኩ እያልኩ ቀጠልኩ አይደል ጨርሻለሁ።[2] 1] ሰሞናዊውን የክርስቲያን ማህበረሰብ ሁኔታ ስንመለከት ይሄ ታሪክ ለመጻፍ ተነሳሁ። ከእግዚአብሔር አገልጋይ ሆነው ግን በእግዚአብሔር ዓለም ውስጥ የሌለን ማንነት ለማሳየት፣ ለማጉላት መሞከራቸውን ሳይ እግዜሩ ይፋረድ አልኩና ይሄን አጭር ታሪክ በአጭር ማስታወሻዬ አካተትኩላችሁ። 2] በመጨረሻም ይሄን የጽሑፍ ልጥፍ ለማለት የፈለገውና የተነገረው ሳይገባህ ቅርጫፉን ይዘህ በደፈናው የምትቆጣ፣ ምዕመኑን ጨፍላቂና እብሪተኛ መጋቢ ሆይ….! ቤተክርስቲያን ላይ መንግስት ለመሆን የምታስቡም ጭምር ካላችሁ…! ይቺ አጭር ፖስት ለእናተ ትቀርብልኝ ዘንድ አሳሰብኩ። እግዚአብሔር በዚህ ዘመን ከምንሰማው ነገር ሁሉ ይጠብቀን። አሜን።

“አንድ ታሪክ ላውጋችሁ” Read More »

ይገርማል…ይደንቃል….!

ድንቅ ነው!! አምላክ ሥጋን ለብሶ ወደ ምድር መጣ የሃጥያት መከራችንንና የዲያቢሎስ የሹፈት ነጋሪት ዝም ለማስባልም ተገለጠ። ነገር ግን የእኛን መከታን ነፃ አውጪያችንን፦ በአክሊል ፋንታ የእሾህ ጉንጉን፣ በፍቅር ከማቀፍ ፋንታ ሰጠነው ጅራፍ፣ በእጆቻችን። እሱም አልበቃ ብሎ አዳኙን ራሱን ራስህን አድን አልነው፤ ሙሾ በሚመስል ቅላጼ እያላገድን አሾፍንበት፤ ከዛም ብሶ ሰቀልነውም በእንጨት በችንካር አድርገን። ይሄ ሁሉ ሆነና ጀንበርም ሳትጠልቅ፣ ፀሐይም ሳትገባ ሥራው ድንቅ ነው የሚል ድምጽ ሰማይ ምድር ሁሉ መወደስ ጀመረ። የጩኸቱ ድምድምታ ምን ይሆን? ብለን ተነሳን፤ እኛም ያኔ ጎኑን የተወጋው፣ እጆቹም ተቸነከሩ፣ ሄዷልና ሞቷል የተባለው አዳኙ ራሱ ያው መሢህ መሆኑን አወቅን። በፍርሃትም ያየነውን በመገረም ድንቅ ነው አልን። ከእላፋት ጋር አእላፋት ሆነን፥ ባሾፍንበት ከንፍራችን ከሙታን በኩር፣ የነገስታት ንጉስ፣ የጌቶች ጌታ፣ የምድር ሁሉ ባለቤት እርሱን አመሠገንን። ጨመር አድርገንም ተነስቷል በዚህ የለም መቃብሩ ባዶ ነው ተመልከቱ በዚህ የለም፤ በሚል ክብሩ ሁሉ በአርያም በምድር ይሁን ስንል ጣፋጭ መዓዛ ያለውን ዝማሬ ለታረደው በግ አቀረብን። ለአንባቢው መልዕክቴ በዚህ ወቅት ላይ የጥሞና ጊዜ ያጣህ እና ረፍት የሌለህ ሆይ “እርሱ ሰላም የሚሰጥ እረፍት ነውና በልብህ ታስገባው ዘንድ አሳሰብኩህ”። አሜን።[፩][፪][፫] መልካም የጥሞና ጊዜ ይሁንላችሁ…..! [፩] ከሚባለው በላይ ከደረሰበት መከራ አንጻር ይገርማል ጥቂት ሆና ትታየን ዘንድ አንባቢው ያስተውል። [፪] ይደንቃል ስንል ከእውነት የሆነ መደነቅ እንዲሆን ሰሚው ከንግግል ባለፈ ከልብ በኾነ ፍቅር ትል እንደሆን አሳሰብኩህ። [፫] ምንጭ፦ አጭር ማስታወሻ በወንድም David Yeshua, ያልታተመ በጽሑፍ ላይ ካለ መጣጥፍ የተወሰደ።

ይገርማል…ይደንቃል….! Read More »

ሆሣዕና <አሁን አድን….!>

ደጉ ጌታ መጣ ተገለጠ ሰዎችም ተቀበሉት። ከተቀበሉት መካከል ሰው ብቻ ሳይሆን ከምድር ፍጥረታት መካከል ያለች አንዲት ውርጭላ ከአህያይቱም ጋር ነበረች። አህያይቱም ተነሳች ክብሯን አየች፣ ንጉስም ተቀመጠባት፤ አምላክ ሥጋን ለብሶ መጣ ወደ ምድር አቤቱ ዛሬ አድን ሆ…ሆ ብለን ሆሣዕና[፩] እንድል። የቀደመው ተተንብዮ የነበረው ትንቢቱ ተፈፀመ ሆ…! እያልን ከተገኘው የዘንባባ ዝንጣፊ ከእግሩ ሥር እያቀረብን። ንጉሡም ተራመደ[፪] አለፈ የትንቢቶቹ ምጻሜ ሊቃረብ ሆነ…! ይኼን ለመረዳት ጥሞና መውሰዱ ሳያሻን አይቀርም ከበፊቱ ይልቅ ሆሣዕና እንድልን…[፫]   መልካም የጥሞና ቀን እና ምሽት…! [፩] ሆሣዕና|Hosanna፦ ዋሴ ና፣ አዳኜ ና፣ ጠባቂዬ ድረስ ማለት ነው። ‘ዋስ’ እና ‘ና’ ከሚሉ ቃላት የተመሠረተ ቃል ነው።[…አድነን፡ እባክኽ አድነን…መድኅኒትነት፤ መሆን ወይም መባል።] [፪] ጌታ ወደ ኢየሩሳሌም በገባ ጊዜ ህጻናት ካዜሙት ቃል፥ ሆሣዕና ፥ “…ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ በጌታ ስም የሚመጣ የተባከ ነው፤ ሆሣዕና በአርያም እያሉ ይጮኹ ነበር።” (ማቴ 21፡9) [፫] ሆሣዕና በአርያም ሆሳዕና በምድርይሁን ለዳዊት ልጅ ለመጣው በክብርይዘርጋ ዘንባባ ይነጠፍ ምንጣፉከዳዊት አምላክ ጋር በክብር እንዲያልፉይቻለዋል አምላክ ታሪክ ይለውጣልመራራውን ሕይወት እርሱ ያጣፍጣልጌታ አንዴ ከፈታን ከቶ ማን ያስረናልሆሳሣና እንበል ነጻነት ወጥተናል

ሆሣዕና <አሁን አድን….!> Read More »

“ጣዕመ ዜማ የሌለው እንቢተኛ ልብ…!”

መናፍቃን እና እንቢተኛ ልብ አንድ ናቸው። ሁለቱም ስተው ሳሉ ጭብጨባ ይሻሉ፤ መናፍቅ ሁሌ የሳተ ስለሆነ ከቅዱሳት መጽሐፍት መውጣቱ በቀላሉ ያሳብቅበታል። እንቢተኞቹ ግን ተበጥረው ከመናፍቃኑ መለየቱ የሰሚው ድርሻ ነው። በዚህች አጭር ጽሑፍ ግን የምታደምጥ እና የምትሰማ አንባቢ ሆይ ዕቡይ[፩] ልብ ያላቸውን ሰዎች በዚህ ለያቸው፦ “የቅዱሳት መጻሕፍት ትርጓሜ ቃናው ጠፍቶባቸው፤ አቃቢነ ክርስትና ዕቡይ ሰው ልሁን ልደመጥ ማለታቸው መሠረታዊ መለያቸው ነው። በመጨረሻም አንባቢ ሆይ..! ያው ዕቡይ ዕቡየ ልብ ነው። ዕቡየ መንፈስም።[፪] እኒህን ዕቡያን ከመናፍቃኑ ለመቆንጠር ቢያዳግትም…. ሥነ-ምግባራቸውን በሚያስተምሩት አስተምህሮ ከቅዱሳት መጽሓፍት እና ከቤተክርስቲያን ትምህርት አፈንግጦ ወጥ መሆናቸውን በጩኸቱ፣ በሥነ-ምግባሩ እና በሚያደርገው ክዋኔ ለክተህ ታውቅ እንደሆነ እወቅ።[፫] [፩] በቁሙ ትቢተኛ፣ ኵሩ፣ ልቡ ያበጠ፣ የተነፋ፡፡ ምንጭ፤ መጽሐፈ ሰዋሰው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ (ኪዳነ ወልድ ክፍሌ) [፪] ኦ ዘያነብብ!! በእለ ምግባሮሙ ወበስብከቶሙ እም ቅዳሳት መጻሕፍት ወ ትምህርተ ቤተክርስቲያን አእምር ከመ ለሊሆሙ ውጉዛን ውእቶሙ! [፫] Tertullian,De praescriptione haereticorum (On the prescription of heretics), Chap. 43፡ You can judge the quality of their faith from the way they behave. Discipline is an index to doctrine. [፬] Erasmus, Paraphrase On Matthew, Chap. 7፡ “If you observe their lives and character more attentively, you will find them to be self-pleasing, everywhere serving their own advantage, arrogant, vindictive, envious, disparaging, thirsting for glory, often both devoted to their bellies and acting completely in their own interests, rather than in the interest of the flock or of the gospel.”

“ጣዕመ ዜማ የሌለው እንቢተኛ ልብ…!” Read More »

ሑባል(هبل)

እስልምና እና የአረቡ ጣዖታት ክፍል 1 እንደሚታወቀው እስልምና ሲነሳ በአእምሯችን ፈጥኖ የሚሳለው የገሚሱ ጨረቃ እና ኮከብ አርማ ነው። በትላልቅ መስጂዶች አናት ላይ በሚናራዎች[¹] እንዲሁም እስላማዊ በሆኑ ኪነ ህንጻዎች ላይ የሚስተዋል ምልክት ነው። በሰባተኛው መቶ ክ/ዘ መጀመሪያዎቹ አካባቢ የእስላማዊ አገሮች መገበያያ የጨረቃ እና ኮከብ ምስል ያለው ሳንቲሞችን እንደሚጠቀሙ አርኪዎሎጂስቶች ያትታሉ።[²] በ11ኛው መቶ ክ/ዘ ግብጻውያን እና ሶርያውያን ይህንን ምልክት ለጌጣጌጣቸው ማስዋቢያነትም ይጠቀሙት ነበር።[³] በተጨማሪም አንዳንድ አገራት ማለትም እንደ አልጀሪያ፣ አዘርባጃን፣ ኮሞሮስ፣ ማሌዥያ፣ ሞሪታንያ፣ ፓኪስታን፣ ቱኒዚያ፣ ቱርክ፣ የቱርክ ሪፐብሊኳ ሰሜኒቷ ቆጵሮስ፣ ኡዝቤክስታ የምዕራብ ሰሐራ …ወዘተ  እስላማዊ አገራት ይህንኑ አርማ እንደ ሀገራዊ መለያ ሰንደቅ ማድረጋቸው ይታወቃል።[⁴] እስልምና ከጨረቃ እና ኮከብ ምልክት ጋር ምን ግንኙነት አለው? ይህንን ግንኙነት ለመረዳት ዲነል ኢስላም ከመጀመሩ በፊት ጥቂት አመታት እልፍ ብለን ስንመለከት በመካ ይመለኩ ከነበሩ ጣዖታት መካከል አንዱ ሑባል(هبل)  የጨረቃ እና የከዋክብት አምላክ እንደነበር የታሪክ መዛግብት ያትታሉ።[⁵] ሑባል(هبل) የአሏህ ቤት ተብሎ በሚጠራው በካዕባ ውስጥ ትልቅ ስፍራ የነበረው እና ለነገደ አረቡ ጣዖት አምላኪያን ሐያል አምላክ እና ታላቁ ጣዖታቸውም ነበር።[⁶] የሑባል ሌላኛው ስሙ “ሏህ” በመባል ይታወቅ ነበር። እንደ ሮበርት ሞሪ ያሉ ስኮላሮች ጥናት መሠረት ከአርኪዎሎጂስቱ ተመራማሪ ሁጎ ዊንክለር ጥናት በመነሳት “አሏህ” የሚለው ስም ለቅድመ እስላማዊ የአረብ ማህበረሰብ አፈታሪክ ውስጥ ለጨረቃ አምላካቸው ስያሜ እንደዋለ ይነግረናል።[⁷] ጁሊየስ ዌልሃውሰንም ጨምሮ የእስልምና ሐይማኖት ከማንሰራራቱ በፊት የአሏህ ቤት ተብሎ የሚጠራው ካዕባ በጣዖቱ ሑባል ሐውልቶች ቁሳቁሶችና ስዕላት ተሞልቶ እንደነበርና ሑባል የአሏህ የመጀመሪያ ስሙም እንደነበር ይናገራል።[⁸] ነገር ግን በእስልምናውም ላሉ ሊቃውንቶች ሆነ ለለዘብተኛ የታሪክ አጥኝዎች ጥያቄ የሆነው ክስተት አሏህ ስለዚህ ታላቅ የአረቦች ጣዖት በሐዲሱ ላይ አንድ ሱፍያን ኢብን ሀርብ የተባለ የቁረይሽ የጦር መሪ ከባድር ጦርነት በኋላ ድልን እንዲሰጣቸው እንደተጣራና ሑባልን እንዳመሰገነ[⁹] ከመጥቀሱ ባለፈ በቁርአኑ ውስጥ በስሙ ተጠቅሶ አለመነሳቱ ነው። እንደ እነ አል ላት አል ኡዛ እና እንደ እነ አል መናት ያሉ ጣዖቶች በቁርአኑ ውስጥ ተጠቅሰው ሳሉ ጣዖቱ ሑባል አለመጠቀሱ አጠያያቂ ጉዳይ ነው። እንደ አንዳዶች አባባል ቁርአን በካዕባ ስለነበሩ ሶስት መቶ ስልሳ ጣዖቶች እያንዳንዱን ስም እየጠቀሰ ግድ መናገር የለበትም ይላሉ። ነገር ግን ቁርአን በቁረይሾች ነገድ እንደ ሑባል በገነነ መልኩ የማይመለኩትን በስም ጠቅሶ ከገለጠ ስለ ሑባል አለማውራቱ አግራሞትን የሚያጭር ጉዳይ ሁኖ እናገኘዋለን። ይህ የሆነበት እንደምክንያት የሚነሳው የእስልምናው ሐይማኖት ቆርቋሪ እና መስራች የሆነው መሐመድ ከጣዖቱ ሑባል ጋር የተቆራኘ ታሪክ ስላለው ነው። ነብይ ተብዬው ከመወለዱ በፊት አያቱ አብዱል ሙጠሊብ የጣዖቱ ሑባል አምላኪ እንደነበር የእስልምና ታሪክ መዛግብት ይናገራሉ።[¹⁰] አብዱል ሙጠሊብ ከልጆቹ መኻል እጣው የወደቀበትን ልጅ በአሁኑ ጊዜ ቅዱስ ስፍራ ተብሎ በሚጠራው በካዕባ ለጣዖት ሑባል መስዋዕት አድርጎ ለማቅረብ በደጋን እጣ በልጆቹ ላይ ይጥላል። የደጋኑም ጫፍ የመሐመድ አባት በሆነው በአብደላህ ላይ ያመልክታል። የመሐመድም አያት ልጁን ለመሰዋት ማረጃ እንዳነሳና ነገር ግን ቁረይሾች፣ ከመኸዙም ጎሳ የሆነው አጎቱ እና ወንድሙ ልጁን እንዳይሰዋ አሳምነው አብዱል ሙጠሊብ በመሐመድ አባት አብደሏህ ምትክ የሚሆን የግመል መስዋዕት ለሑባል እንዳቀረበ እንመለከታለን።[¹¹] እንደውም እንደ ጠበሪ ዘገባ አብዱል ሙጠሊብ መሐመድ ጨቅላ እንደነበር ወደ ጣዖቱ ሑባል ፊት ያመጣው እንደነበር ይተርካል።[¹²] ይህ ሁሉ የታሪክ ማስረጃዎች የሚያሳዩን የቁርአኑ ደራሲ መሐመድ ከሑባል ጣዖት ጋር ገና ከመወለዱ ጀምሮ ህጻንም እያለ ጥብቅ ቁርኝት እንደነበረው ያሳያል። ምንም እንኳን መሐመድ በካዕባ የሚገኙትን የሑባልን ጣዖት እና መገልገያዎችን ለማጥፋት ቢሞክርም የሑባል ጣዖት የአምልኮ ስርአቶችን ለምሳሌ በካዕባ ዙሪያ ጠዋፍ ማድረግን(የቅድመ አረባውያን የጣዖት አምላኪዎች ልምምድ ነበር ለጣዖት ሑባልም ይህንኑ የአምልኮ ስርአት አምላኪዎቹ ይከውኑ ነበር) የጣዖቱ ስም ከአምላኩ ስም ጋር ማመሳሰሉ(ቀደምት እስልምና የጣዖት አምላኪያውያን አምላካቸውን ላህ ወይም ሑባል በማለት ይጠሩት እንደነበር እና የእስልምናው አምላክ ስም ከጣዖታውያኑ ጋር ጥልቅ ቁርኝት ነበረው) በተጨማሪም የአሁኑ የሙስሊም  ማህበረሰብ የሚጠቀምበት የእምነት መለያ አርማቸው ያደረጉት በጥንቱ የአረብ ጣዖት አምላኪያን ዘንድ ለሑባል የተሰጠ የጣዖታቸው መለያ መሆኑ ይህ ሁሉ የሚያሳየን እስልም የቅድመ አያቶቹን የአረብ ጣዖታውያንን የሐይማኖት ስርአት፣ ስያሜ የማምለኪያ ቦታ(ካዕባ) እና የመለያ ምልክቱን መኮረጁ ወልደ ጣዖታውያን የእምነት መሠረት መሆኑን በግልጽ ሁኔታ መረዳት የምንችለው የሐይማኖት ቡድን እንደሆነ ነው። መጽሐፍ ቅዱሳችን ግን፦ “እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝና ለእናንተ ጣዖት አታድርጉ፥ የተቀረጸም ምስል ወይም ሐውልት አታቁሙ፤ ትሰግዱለትም ዘንድ በምድራችሁ ላይ የተቀረጸ ድንጋይ አታኑሩ።”  — ዘሌዋውያን 26፥1 በማለት እንዳናመልክና እውነተኛውን ጌታ እንድንከተል ያደርገናል። እግዚአብሔር በዚህ መንገድ ይመራቸው ዘንድ ፀለይን አሜን። ማጣቀሻዎች [¹] International Federation of Red Cross & Crescent Societies [²] S. Album & T. Goodwin – Syllogue Of Islamic Coins In The Ashmolean – The Pre-Reform Coinage Of The Early Islamic Period – 2002, Volume I, Ashmolean Museum: Oxford (UK), pp. 6-7 [³] “Pendant (Egypt) (30.95.37)”. In Heilbrunn Timeline of Art History. New York: The Metropolitan Museum of Art, 2000–. (October 2006) [⁴] Islamic flags – Flags Of The World, October 18, 2008 [⁵] Karen Armstrong (2000,2002). Islam: A Short History. pp. 11 [⁶] ዝኒ ከማሁ [⁷] Morey, Robert(1994)The Moon-god Allah in Archeology of the Middle East. Newport, Research & Education Foundation. [⁸] Wellhausen, Julius. Reste Arabischen Heidenthum, pp. 75/ Hawting, Gerald R.(1999). The Idea of idolatry & the emergece of Islam: from polemic to History. pp. 112 [⁹] Winckler, Hugo(1901) Arabisch, Semitisch, Orientalisch: Kulturgeschichlich-Mythologische Untersuchung.Berlin:W. Peiser pp. 83 [¹⁰] Ibn Hisham 1/151-155; Rahmat-ul-lil’ alammeen 2/89, 90 [¹¹] ዝኒ ከማሁ [¹²] Mohammed ibn Jarir al-Tabari, The History of the Prophet & Kings,1:157

ሑባል(هبل) Read More »

ኃልወተ መንፈስ ቅዱስ

“ብትወዱኝ ትእዛዜን ጠብቁ። እኔም አብን እለምናለሁ ለዘላለምም ከእናንተ ጋር እንዲኖር ሌላ አጽናኝ (ἄλλον παράκλητον) ይሰጣችኋል፤”  ዮሐንስ 14፥15-16 እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ኅልው አምላክ በራሱ የቆመ ማንነት ያለውና ከሥሉሳዊ አካላት መካከል አንዱ አካል ነው። ስለ መንፈስ ቅዱስ አካላዊ ማንነት ከማውራታችን በፊት በተወሰነ መጠን ስለ አካል ምንነት ለመመልከት እንሞክር፦ አካል የምንለው መጠሪያ በጣም ልም ከሆነ ብናኝና በጣም ረቂቅ ከሆነ ትናኝ እጅግ በጣም ረቂቅ ከሆነ አየር ጀምሮ የመጨረሻ ጥጥርነትና ጉልህነት እስካለው ውፍረት ደንዳናነትም ድረስ በዚያ በሚገኝ ዐቅምና ብቃት እንደየ መጠኑ እንደየ መልኩ ተወስኖ እንደሚታወቅ ሁሉ፤ በዓለም ግዘፍ አካል ተብሎ ይሰየማል። በሌላም አገላለጽ በሰማይ ያለው የሚዳሰስና የሚገሰስ የሚቋጠርና በአምስቱ የስሜት ህዋሳት ተደርሶበት የሚጨበት ነገር ሁሉ በዓለመ ግዘፍ አካልነት እንዳለ ያለ መሆኑ ይታወቃልና አካል በሚል ስያሜ መጠራት ገንዘቡ ነው።[1] ነገር ግን አካል የሚለው ስያሜ በአምስቱ ህዋሳት ብቻ ለሚታወቀው ነገር ብቻ ሳይሆን ለማይታይ ለማይዳሰስ፣ ለማይገሰስ፣ ለማይቋጠር ነገር ግን በህያውነት፤ በዓለመ ነፍስ የሚኖር እኔ የሚል ነባቢ ለባዊ አለሁ ባይ ሁሉ አካል አለው ተብሎ ሊጠራ ይችላል።[2] እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ የራሱ የሆነ አካል ያለው አምላክ ነው። መንፈስ ቅዱስ አካል አለው ስንል ከሌላው የስላሴ አካላት ራሱን ችሎ ለራሱ ብቁዕ የሆነ ዕውቀት ቀዋሚነት ያለው አለሁ ባይ ቁመና መሆኑን አመላካች መገለጫ ነው። ከአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ የተለያዩ የምንፍቅና አንጃዎች በመንፈስ ቅዱስ ላይ በተለያየ መንገድ አስተምህሮና ልምምዶች ተነስተው ነበር። በመንፈስ ቅዱስ ላይ ምንፍቅናዊ ዘመቻ የከፈቱትን ቡድኖች ኔውማቶማኪያውያን የሚልን ስያሜን ተሰጥተው ነበር። ኔውማቶማኪ(Pneumatomachi) ወይም በግሪኩ (Πνευματομάχοι) የሚለው ቃል ኔውማ(πνεῦμα) ማለትም መንፈስ እና ማኬ(μάχη) ውጊያ፤ በአንድ አካል ላይ በአሉታዊ ሁኔታ መነሳትን ወይም ጠበኛ መሆንን ሲገልጽ በአጠቃላይ የመንፈስ ቅዱስ ጠበኞች፣ ተቃዋሚዎች አልያም በመንፈስ ቅዱስ ማንነትና ምንነት ላይ በአሉታዊ ጎን የተነሱ ማለት ነው።[3] ለምሳሌ ያክል መቅዶናውያን (የመቅዶኒዮስን አስተምህሮተ ምንፍቅና የሚከተሉ)፣ አርዮሳውያንና ከፊል አርዮሳውያን፣ ሰባልዮሳውያ ወዘተ ተጠቃሽ ናቸው። አንዳንዶቹ የምንፍቅና ቡድኖች የመንፈስ ቅዱስን መለኮትነት ሲክዱ አንዳዶቹ ደግሞ ከነጭራሹን መንፈስ ቅዱስ ህልውና የሌለው ማለትም በራሱ የቆመ ወይም አካል የለውም ብለው ያምናሉ ያስተምራሉ። በዚህ ጽሑፍ መንፈስ ቅዱስን አካላዊ ማንነትን ለሚክዱት ቡድኖች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምላሽን ከሰዋስው እና ከአውዳዊ ዳሰሳ አንጻር አንዳንድ ነጥቦች ለመዳሰስ እንሞክራለን፦ መንፈስ ቅዱስ በራሱ ኃይል አይደለም ኃይልን ለባህሪው ገንዘብ ያደረገ አምላክ እንጂ መንፈስ ቅዱስ የራሱ የሆነ ማንነት የለውም “እርሱ የእግዚአብሔር ሐይል ብቻ ነው” ለሚሉ መናፍቃን መጽሐፍ ቅዱሳችን መልስ አለው፦ “ወንጌላችን በኃይልና በመንፈስ ቅዱስ በብዙ መረዳትም እንጂ በቃል ብቻ ወደ እናንተ አልመጣምና፤ በእናንተ ዘንድ ስለ እናንተ እንዴት እንደ ነበርን ታውቃላችሁ።”  — 1ኛ ተሰሎንቄ 1፥5 የተሰሎንቄን መልዕክት ጸሐፊ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ኃይልን(δυνάμει) እና መንፈስ ቅዱስን(πνεύματι ἁγίῳ) በማለያየት “እና(ካይ/καὶ)” በሚለው መስተጻምር ቃላቶቹን ሲሰነጥቃቸው እንመለከታለን። ይህም ማለት መንፈስ ቅዱስ ከኃይል የተለየ ማንነት እንደሆነ ያስረዳል። መንፈስ ቅዱስ በራሱ ኃይል ሳይሆን ኃይልን ባህሪው ያደረገ አምላክ ነው(ሉቃ 4፥14፣ ሐዋ 1፥18፣ ሮሜ 15፥13, 18-19)። በሐዋርያት ስራ ላይ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመንፈስ ቅዱስን መምጣት ሲናገር መንፈስ ቅዱስን እና ሐይልን ለያይቶ በመናገር እንጂ መንፈስ ቅዱስ ራሱ ሐይል ነው ወይም ሐይል በወረደባችሁ ጊዜ ፈጽሞ አላለም። እንዲያውም መንፈስ ቅዱስ በእነርሱ ላይ በወረደ ጊዜ ሐይልን እንደሚቀበሉ ያስረዳል። ይህም ማለት ሐይል ከመንፈስ ቅዱስ የሚወጣ ባህሪዎት ነው፦ “ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ፥ በኢየሩሳሌምም በይሁዳም ሁሉ በሰማርያም እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ አለ።”  — ሐዋርያት 1፥8 በሁለተኛ፦ መንፈስ ቅዱስ ከአብ እና ከወልድ የተለየ የራሱ የሆነ ማንነት ያለው አካል ነው “ብትወዱኝ ትእዛዜን ጠብቁ። እኔም አብን እለምናለሁ ለዘላለምም ከእናንተ ጋር እንዲኖር ሌላ አጽናኝ (ἄλλον παράκλητον) ይሰጣችኋል፤”  — ዮሐንስ 14፥15-16 “ሔቴሮስ/ἕτερος” የሚለው የጽርዕ(ግሪክ) ቃል የተለየ፣ ሌላ ወይም አንድ አይነት ያልሆነ የሚል ትርጉም ሲኖረው አብዛኛውን ጊዜ በአይነትም ሆነ በአካል የተለየን ነገር የሚያመለክት ነው።[4] “አሎስ/ἄλλος” የሚለው የጽርዕ (ግሪክ) ቃል ደግሞ በአይነታቸው ተመሳሳይ የሆኑ ነገሮችን ነገር ግን በአካል ወይም በቁጥር የተለያዩ መሆናቸውን የሚገልጽ ቃል ነው።[4]ለምሳሌ፦ “በክርስቶስ ጸጋ እናንተን ከጠራችሁ ከእርሱ ወደ ልዩ ወንጌል( #ἕτερον εὐαγγέλιον) እንዲህ ፈጥናችሁ እንዴት እንዳለፋችሁ እደነቃለሁ፤” — ገላትያ 1፥6 ሔቴሮን ኢዋንጌሊዮን(ἕτερον εὐαγγέλιον) የሚለው ሐረግ በአይነቱም ሆነ በይዘቱ ለገላትያ ሰዎች ከተሰበከላቸው ከቀድሞው ከእውነተኛው እና ከቀጥተኛው ወንጌል ፍጹም ሌላ (ሔቴሮስ/ἕτερος) ወይም የተለየ መሆኑን የሚገልጽ ነው። “ስምዖን ጴጥሮስም ሌላውም ደቀ መዝሙር(አሎስ ማቴቴስ/ἄλλος μαθητής) ኢየሱስን ተከተሉ። ያም ደቀ መዝሙር በሊቀ ካህናቱ ዘንድ የታወቀ ነበረ፥ ወደ ሊቀ ካህናቱም ግቢ ከኢየሱስ ጋር ገባ፤”— ዮሐንስ 18፥15 በግሪኩ “አሎስ/ἄλλος” የሚለው ቃል ከስምዖን ጴጥሮስ የተለየ ማንነት እንዳለ ወይም በማንነታዊ መገለጫ ፈጽመው የተለያዩ አካላቶች እንደሆኑ የሚያሳይ ቃል ነው። ይህም ማለት ደግሞ ሁለት በአገልግሎታቸው፣ በምንነታዊ ባህሪዎታቸው(ሰው በመሆናቸው) እና የመጠሪያ ማዕረጋቸው አንድ አይነት የሆኑ ነገር ግን በአካል ሆነ በማንነታቸው ደግሞ የተለያዩ ሁለት ሰዎች መሆናቸውን ይገልጻል። የሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስን የጽሑፎቹን የሰዋሰው አወቃቀርና የቃላት አጠቃቀም በተመለከትን ጊዜ ምን ያክል ለቋንቋ ህግጋት ጥንቃቄዎችን እንደሚያደርግ እናስተውላለን። በዮሐ 14፥15-16 ላይ ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ ከእኛ ጋር ለዘላለም የሚኖረው አጽናኙ በአካል ከአብ እና ከወልድ የተለየ፤ በባህሪዎቱ እና በምንነቱ ደግሞ ከአብ እና ከወልድ ጋር ተስተካክሎተ ኑባሬ ያለው አካል መሆኑን ለመግለጽ “አሎስ/ἄλλος” የሚለው የጽርዕ (ግሪክ) ቃል እንደተጠቀመ እንመለከታለን። በተጨማሪም ቁጥር 17ን ስንመለከት፦ “ እርሱም(αὐτὸ) ዓለም የማያየውና የማያውቀው ስለ ሆነ ሊቀበለው የማይቻለው የእውነት መንፈስ ነው፤ ነገር ግን ከእናንተ ዘንድ ስለሚኖር በውሥጣችሁም ስለሚሆን እናንተ ታውቃላችሁ።”  — ዮሐንስ 14፥17 በዚህ ክፍል ላይ የእውነት መንፈስ(τὸ πνεῦμα τῆς ἀληθείας/ቶ ኒውማ ቴስ አሌቴያስ) የተባለው አካል እርሱ(αὐτὸ) ሊባል የሚችል ማንነታዊ ቅዋሜ ያለው አካል እንደሆነ በግልጽ ሁኔታ ያስረዳል።[5] በተጨማሪም “..ከእናንተ ዘንድ ስለሚኖር/ὅτι παρ’ ὑμῖν μένει…” በሚለው ሐረግ ውስጥ “ስለሚኖር” ማለትም በግሪኩ ሜኔይ/μένει በሚለው ግሳዊ ቃል በተባእታይ ጾታ የመጣ እርሱ/He የሚል ውስጠ ተውላጠ ስም እንዳለ እንመለከታለን። በተለያዩ የዮሐንስ ወንጌል ክፍሎች ላይ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መንፈስ ቅዱስን እርሱ እያለ በተባዕታይ ጾታ ሲጠራው እንመለከታለን። ይሄ ደግሞ የመንፈስ ቅዱስን አካላዊ ማንነት የሚያስረዳ ነው። መንፈስ ቅዱስ በኑባሬያዊ ማንነቱ በግዑዝ ጾታ አለመጥራቱ የራሱ የሆነ ማንነት እንዳለው አስረጂ እና አመላካች ነጥብ ነው።[6] ቀጥሎ በዮሐንስ ወንጌል ላይ መንፈስ ቅዱስ እርሱ እየተባለ በተባዕታይ ጾታ የተጠራባቸውን ክፍሎች እንመልከት፦ በዮሐንስ 14፥26 እና 15፥26 ላይ መንፈስ ቅዱስ በሶስተኛ መደብ ሰብአዊ ተውላጠ ስም ኤኬይኖስ/ἐκεῖνος “እርሱ” ተብሎ ተጠርቷል። በተጨማሪም አጽናኝ በግሪኩ ፓራክሌቶስ/παράκλητος የሚለው ስም በባለቤት ሙያ በተባዕታይ ጾታ የመጣ ስም ነው፦ “አብ በስሜ የሚልከው ግን መንፈስ ቅዱስ የሆነው አጽናኝ (ፓራክሌቶስ/παράκλητος) እርሱ (ኤኬይኖስ/ἐκεῖνος) ሁሉን ያስተምራችኋል እኔም የነገርኋችሁን ሁሉ ያሳስባችኋል።”  — ዮሐንስ 14፥26 “ዳሩ ግን እኔ ከአብ ዘንድ የምልክላችሁ አጽናኝ (ፓራክሌቶስ/παράκλητος) እርሱም ከአብ የሚወጣ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ፥ እርሱ (ኤኬይኖስ/ἐκεῖνος) ስለ እኔ ይመሰክራል፤”  — ዮሐንስ 15፥26 በተጨማሪም በዮሐንስ ወንጌል በምዕራፍ 16 ቁጥር 7 ላይ የሚላከው አካል “እርሱን” አውቶን/αὐτὸν በማለት በሶስተኛ መደብ ሰብአዊ አገናዛቢ ተውላጠ ስም ተባዕታይ ጾታ ሲጠራው እንመለከታለን፦ ⁷ እኔ ግን እውነት እነግራችኋለሁ፤ እኔ እንድሄድ ይሻላችኋል። እኔ ባልሄድ አጽናኙ ወደ እናንተ አይመጣምና፤ እኔ ብሄድ ግን እርሱን (አውቶን/αὐτὸν) እልክላችኋለሁ።… ¹³ ግን እርሱ ἐκεῖνος የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል(ሆዴጌሴይ/ὁδηγήσει)፤ የሚሰማውን (አኩሴይ/ἀκούσει) ሁሉ ይናገራል (ላሌሴይ/λαλήσει) እንጂ ከራሱ (ሄአውቱ/ἑαυτοῦ) አይነግርምና፤ የሚመጣውንም ይነግራችኋል (አናንጌሌይ/ἀναγγελεῖ)።¹⁴ እርሱ (ኤኬይኖስ/ἐκεῖνος) ያከብረኛል፥ ለእኔ ካለኝ ወስዶλήμψεται ይነግራችኋልና።— ዮሐንስ 16፥7፣13፣14 በቁጥር 13 እና 14 ላይ ያሉት ግሶች ስንመለከት(ይመራችኋል፣ የሚሰማውን፣ ይናገራል፣ ይነግራችኋል …ወዘተ) “እርሱ”

ኃልወተ መንፈስ ቅዱስ Read More »

ዘላለማዊ ቃል ወልድ ከአብ በኑባሬው ያነሰ እና ለአብ የሚገዛ ነውን?

“…በዚያን ጊዜ ልጁ ራሱ ደግሞ ሁሉን ላስገዛለት ይገዛል።”1ኛ ቆሮንቶስ 15፥28 “…τότε καὶ αὐτὸς ὁ υἱὸς ὑποταγήσεται τῷ…”1Cor 15:28 ሃይፖታጌሴታይ/ὑποταγήσεται የሚለው ቃል ሃይፖታሶ/ὑποτάσσω ከሚለው ስርወ ቃል የመጣ ሲሆን መታዘዝ፣ መተናነስ ወይም ደግሞ መገዛትን የሚያመለክት ነው። አንዳንድ ሐያስያንና የክርስቶስን አምላክነት የሚክዱ(ሙስሊሞችንም ያጠቃልላል) መናፍቃን በ1 በቆሮንጦስ ምእራፍ 15 ላይ አብ ሁሉን ነገር ለወልድ ካስገዛለት በኋላ ወልድ ራሱ ደግሞ ሁሉን ላስገዛለት ለእርሱ እንደሚገዛ የሚናገረውን ክፍል በመጎንተል ክርስቶስ ኢየሱስ አምላክ አይደለም ለማለት ይዳዳቸዋል። መገዛት ወይም መተናነስ (subordination) የሚለው ቃል በምን አግባብና አገባብ እንደሚውል ከማየታችን በፊት ስለ ነባቤ እንሰተ ቃል (subordination view) በትንሹ እንመለከታለን። በSubordinationism ዙርያ እስከ 4 መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ ብዙ ሀሳቦችንና አስተምህሮቶች ተሰንዝረውበታ። በዚህም ዙሪያ የሁለት ጎራዎችን ምድብ ነጥብ በነጥብ እንመልከት፦ አንደኛው፦ ሆሞዮስዮስ/ὁμοιούσιος ሆሞዮስዮስ የሚለው የግሪክ ቃል“ሆሞዮስ/ὅμοιος” “ተመሳሳይ” ወይም “ተቀራራቢ” ከሚለውና “ኡሲያ/οὐσία” “ኑባሬ” ወይም “ባህሪ” ከሚሉት ጥምር ቃላቶች የተገኘ ሲሆን ኢንግሊዘኛው ontological subordination ሲለው የአማርኛው የቁም ፍቺው ደግሞ “ኑባሬያዊ እንሰት” ወይም “በባህሪ መተናነስን” ያመላክታል። በዚህ መርሆተ ቃል በነገረ ክርስቶስ(christology) ዙሪያ ብዙ የኑፋቄ ትምህርቶች ተነስተዋል። ከእነዚህም መካከል እውቁ የኑፋቄ መምህር የአሌክሳንድሪያው ጳጳስ አርዮስ ከክርስትናውና ከቅዱሱ መጽሐፍ ያፈነገጠ አስተምህሮ በመለኮታዊ በኑባሬ ወይም በባህሪ አንጻር ያለን መተናነስን ወይም መበላለጥን (ontological subordination) አስተማረ። በአሁኑ ጊዜ ለተነሱት የኑፋቄ ትምህርቶች ለጅሖቫ ምስክሮች ለኢብዮኒዝም(Ebionism) አስተምህሮ እንደውም ለመሐመዳውያን ለእስልምና መነሳሳት ትልቅ ጠባሳ ጭሮ ያለፈ እንደሆነ ይገመታል። ሁለተኛው፦ ሆሙስዮስ/ὁμοούσιος ሆሙስዮስ ማለት “ኡሲያ/οὐσία” “በኑባሬ” ወይም “በባህሪ” አንድ አይነት ወይም እኩል መሆንን ያሳያል። በ325 አ.ም በኒቂያው ጉባኤ ላይ በተደረገው ጉባኤ የአርዮስን የተሳሳተ የሰቦርዲኔሽናል ፈርጅ ማለትም የወልድን ለአባቱ መገዛቱ  ontological subordination ወይም “ኑባሬያዊ እንሰት” በማውገዝ የክርስቶስ ለአባቱ መገዛቱ ግብራዊ እንሰት/functional subordination ያመላክታል በማለት ወልድ ከአብ ጋር በባህርዮቱና በኑባሬው ከአባቱ ጋር እኩል ወይም አንድ አይነት (ሆሙስዮን ቶ ፓትሪ/ὁμοούσιον τῷ Πατρί) መሆኑን ገልጸውልናል። በመጨረሻም ወልድ ለአባቱ መገዛቱ፤ መታዘዙ እና ያባቱን ፈቃድ ማገልገሉ በአባትና በልጅ መካከል ያለውን የማንነትና በባህሪም ሆነ በኑባሬ መተናነስን ሆነ መበላለጥን ፈጽሞ አያመለክትም። ቅዱስ ባስልዮስ በክታቡ፦ “…አብ ከወልድ ከመንፈስ ቅዱስ ተለይቶ አንዲት ሰዓት እንደ ዓይን ጥቅሻ ያህል ስንኳ አልነበረም ሁል ጊዜ ከነርሱ ጋር የነበረ የሚኖር ነው እንጂ።…”[1] በማለት በሥላሴ መካከል አንዳች ብልጫ ወይ መተናነስ እንደሌለ ይሄ አባት ያስቀምጠዋል። የቆሮንቶስን መጽሐፍ ለመረዳት ከቅዱሳት መጽሐፍት ምሳሌ እንጠቀም። በሉቃስ ወንጌል ምእራፍ 2 በቁጥር 51 ላይ ጌታችን ክርስቶስ ኢየሱስ በናዝሬት ከተማ ለቤተሰቡ ይታዘዛቸው እንደ ነበር ቅዱስ ቃሉ ይነግረናል። በዚህ ክፍል ላይ ይታዘዝላቸዋል የሚለው የግሪክ ቃል ከ1ኛ ቆሮንቶስ 15፥28 ወልድ ለአባቱ እንደሚገዛ በሚናገረው ክፍል ጋር ተመሳሳይ ቃልን ነው የተጠቀመው፦ (ሃይፖታሶ/ὑποτάσσω) “ከእነርሱም ጋር ወርዶ ወደ ናዝሬት መጣ፥ ይታዘዝላቸውም (ὑποτασσόμενος) ነበር። እናቱም ይህን ነገር ሁሉ በልብዋ ትጠብቀው ነበር።” ሉቃስ 2፥51 ከዚህም የምንረዳው ክርስቶስ ኢየሱስ ለቤተሰቡ ሲታዘዝ ከእነርሱ በማንነት፤ በባህሪዎትና በኑባሬ ተናንሶ ወይም ዝቅ ማለቱን ሳይሆን በልጅና በወላጅ መካከል ያለውን መታዘዝ ወይም የመከባበር መስተጋብር በሚያሳይ ረገድ መሆኑ እውቅና ቅቡል ነው። በሌላ በኩል ደግሞ በኤፌሶን ምእራፍ 5 በቁጥር 21-22 ሐዋርያው ጳውሎስ “…ለባሎቻችሁ ተገዙ(ሃይፖታሶ/ὑποτάσσω)…”  ብሎ ሲል ሴቶች ከወንዶች እንደሚያንሱ እየገለፀ እንዳልሆነ ለገላትያ የጻፈውን መልእክት በምእራፍ 3 በቁጥር 28 ላይ ባለው በቀላሉ እንረዳለን፦ “አይሁዳዊ ወይም የግሪክ ሰው የለም፥ ባሪያ ወይም ጨዋ ሰው የለም፥ ወንድም ሴትም የለም፤ ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናችሁና።”— ገላትያ 3፥28 በሴትና በወንድ መካከል ያለው መተናነስ ኑባሬያዊ(ontological) ሳይሆን ግብራዊ መተናነስን(functional subordination) ነው የሚያመለክተው። ስለዚህ በቆሮንቶስ 15፥28 ጥቅስ መሠረት ወልድ ከአብ ያንሳል ማለት በፍፁም አይቻልም ማለት ነው። ጸጋ ሰላም ይብዛላችሁ። ዋቢ ምንጭ 1] ሐይማኖት አበው ምዕራፍ ፴፫ ክፍል ፭

ዘላለማዊ ቃል ወልድ ከአብ በኑባሬው ያነሰ እና ለአብ የሚገዛ ነውን? Read More »

ማቴዎስ 28፥19 እና ሰዋሰዋዊ ሙግት

በማቴዎስ 28:19 በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም የሚለው ሐረግ የአካል ሦስትነትን አያሳይም የሚሉ መናፍቃን ሙግት የሚንድ ሆኖ የሚቀጥ ነው። ምክንያቱም ከስም ባሻገር የአካላዊ ሶስትነትን ያሳያል። በአንደኛው መቶ ክፍለ ዘመን ውስጥ እንደተጻፈ የሚታመነው ዲዳኬ (ትምህርተ ሐዋርያት) ጽሑፍ ላይ ስለ ጥምቀት ስርአት በማቴዎስ ወንጌል ላይ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተላለፈውን ትእዛዝና ሐዋርያት በዛ ዘመን እንዴት እንደሚያጠምቁ ሲያብራራ እንመለከታለን፦ “…ስለ ጥምቀትም ረገድ እንዲህ አጥምቁ፤ ይህን ሁሉ በመጀመሪያ ከተናገርክ በኋላ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም በሕያው ውኃ አጠምቁ (“…βαπτίσατε εἰς τὸ ὄνομα τοῦ πατρὸς καὶ τοῦ υἱοῦ καὶ τοῦ ἁγίου πνεύματος…”)…….በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም ራስ ላይ ሦስት ጊዜ ውኃ አፍስሱ…” [ትምህርተ ሐዋርያት ስለ ጥምቀት ህግጋት][1] አንዳንድ ጸረ ስላሴያውያን የማቴዎስ ወንጌል 28:19 የስላሴን አስተምህሮ አያሳይም በማለት ክፉኛ ሲሞግቱ እንመለከታለን። ነገር ግን ይሄ አካሄዳቸው የበኩረ ጽሑፋቱን ቋንቋ ያማከለ ሙግት ፈጽሞ አይደለም። ይሄም የሚያሳየው የሰዋሰው ሙግት ላይ ምን ያህል ደካማ መሆናቸውን ነው። ይባሱን ብሎ ጽሑፉ በጥንታውያን ክታባት ላይ አይገኙም የሚሉም መጥተዋል። ለዛሬ እኛ በማቴዎስ ወንጌል 28:19 ያለው ጽሑፍ ላይ እናተኩር። ጥንታዊ ሰነድ የሆነው ዲዳኬ (ትምህርተ ሐዋርያት) የጥምቀት ስርዓትን በተመለከተ የአብ የወልድና የመንፈስ ቅዱስ ስም ከመጠቀሱም ባሻገር አካላዊ ልዩነቶች (Personal Distinction) እንዳላቸው በግልጽ ያሳያል። ይህም ማለት አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ እያንዳንዱ አካል እኔነት እንዳለው የሚያሳይ ክፍል ነው። የክፍሉን የሰዋሰው መዋቅር ከመመልከታችን በፊት አንድ ወሳኝ ህግ እንመልከት፦ በ1735-1813 ይኖር የነበረው የግሪክ ቋንቋ ሊቅ እንዲሁም ባለ ብዙ ዘርፈ ሙያ ባለቤት የሆነው ግራንቪል ሻርፕ ስለ ውስን መስተኣምር አገባብ እና የአረፍተ ነገሩን አተረጓጎም ሒደት ላይ ባስቀመጠው ስድስት ህጎች መካከል በስድስተኛው ነጥብ ላይ እንዲህ የሚል መርህ እናገኛለን፦ “ሁለት ወይም ከዛ በላይ ተመሳሳይ ሙያ(case) ያላቸው ስሞች(የማዕረግ )፤ በ ‘እና/ካይ (καὶ)’ ተያይዘው፤ በስሞቹ መጀመሪያ ላይ ውስን መስተኣምር ካለ አረፍተ ነገሩ ስለ ተለያየ አካል(person) የሚናገር ነው”[2] “πορευθέντες οὖν μαθητεύσατε πάντα τὰ ἔθνη, βαπτίζοντες αὐτοὺς εἰς τὸ ὄνομα τοῦ πατρὸς καὶ τοῦ υἱοῦ καὶ τοῦ ἁγίου πνεύματος”[Κατα Μαθθαιον 28:19] በዚህ ህግ መሰረት የማቴዎስ ወንጌል 28፥19 ያለው ክፍል ይሄንኑ ህግ አሟልቶ እንመለከታለን። አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ የሚሉት የማዕረግ ስሞች ተመሳሳይ ሙያ ያላቸው ነጠላ ስሞች(የቃል ክፍሉ Noun, የሙያ መደቡ Genitive case, የብዜት ቁጥሩ Singular) ስለሆኑ አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ የተለያዩ ማንነቶች እንደሆኑና ያልተጨፈለቁ አካላቶች መጠቀሳቸው በግልጽ ህጉ ይደግፍልናል። ይህ ደግሞ ስም ብቻ መጠቀሱን አይተን በቀላሉ እንድናልፍ የሰዋሰው ውቅረ ህጉ አይፈቅድልንም። በዚህም መስፈርት ከሄድን ከማቴዎስ ወንጌል በተጨማሪ በ2ኛ ቆሮንቶስ ም.13 ቁ.14 የሰዋሰው አወቃቀሩ ተመሳሳይ ነው የህጉን መስፈርት ያሟላል። ጸጋ ሰላም ይብዛላችሁ! ዋቢ ምንጮች [¹] Didache-ΔΙΔΑΧΗ ΤΩΝ ΔΩΔΕΚΑ ΑΠΟΣΤΟΛΩΝ 6:1 [²] W. D. McBrayer, ed., Granville Sharp’s Remarks on the Uses of the Definitive Article in the Greek New Testament (Atlanta: The Original Word, 1995), p.25. Once More, Matthew 28:19 and the Trinity, Robert M. Bowman, Jr

ማቴዎስ 28፥19 እና ሰዋሰዋዊ ሙግት Read More »

ቅድመ ኒቂያ አበው ትምህርተ ሥላሴ እና የቤተ ክርስቲያን ታሪክ

ሰላም እንደምን ቆያችሁን በባለፈው ልጥፍ ማለትም በመጽሐፍ ዳሰሳችን የትምህርተ ሥላሴ ቀዳማይ አመንጪ ጉባኤ ኒቂያ አለመሆኑን በአጭሩም ቢሆንም አይተናል። ይህ አይነት አስተሳሰብ ላላቸው(ቅድመ ኒቂያ ጉባኤ ያሉት የቤተ ክርስቲያን አበው ሥላሴን  የሚገልጽ ነገር ፈጽሞ አላስተማሩም) ለሚሉት ትችት ታሪክን ካለማንበብ የመነጨ እንደሆነ እናስተውላለን። ይህንን ማሳያ ከሌሎች አበው አንጻር በማቅረብ እንዘልቃለን። የቤተ ክርስቲያን አበው ስለ ሥላሴ የነበራቸውን መረዳት እዚህ ጋር አምጥቶ መጻፍ እጅጉን ብዙ ነው። ከእነዚህም መካከል ጥቂቱን እናጋራችሁ፦ 1)Clement of the Rome(30-95) ቅዱስ ቀለሜንጦስ የሐዋርያውን ቅዱስ ጳውሎስን ኤፌሶን ላሉት ምእመናን በጻፈው መልእክት ላይ በምዕራፍ 4 ከቁጥር 4 እስከ 6 ባለው ሐሳብ ተሞርክዞ የስላሴን አንድነትና ሶስትነት ሲገልጽ እንመለከተዋለን፦ “….አንድ አምላክ፤ አንድ ክርስቶስ፣ በእኛ ላይ የፈሰሰው አንድስ የጸጋው መንፈስ ያለን አይደለንምን? [1] ኤፌሶን 4፥4-6″…⁴ በመጠራታችሁ በአንድ ተስፋ እንደ ተጠራችሁ አንድ አካልና አንድ መንፈስ አለ፤ ⁵ አንድ ጌታ አንድ ሃይማኖት አንዲት ጥምቀት፤ ⁶ ከሁሉ በላይ የሚሆን በሁሉም የሚሠራ በሁሉም የሚኖር አንድ አምላክ የሁሉም አባት አለ።(——ኤፌሶን 4፥4-6) 2)Hippolytus of Rome(3rd ce. earlier)፦ በ3ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ የሮሙ ሂፖሊተስ ኖተስ(Noetus) ለተባለ የሰምርኔስ ክርስቲያን(Christian from Smyrna) ሂፖሊተስ ምንፍቅና ነው ብሎ ያመነበትን የፓትሪፓሻውያንን አመለካከት ሲያራምድ ለነበረው መናፍቅ ምላሽ በኖተስ ላይ የጻፈው ጽሑፍ ስለ አስተምህሮተ ስላሴ እንዲህ ብሎ ሲሞግት እንመለከታለን፦ “…እንግዲህ የአብን መስተጋብራዊ ግንኙነትን፤ ፈቃዱንና አብም ከዚህ መንገድ ውጭ ሊመለክ እንደማይፈልግ አውቆ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀመዛሙርቱ ይሄንን ትእዛዝ ሰጣቸው፦’እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው…'(— ማቴዎስ 28፥19-20) ከእነዚህም አንዱን ያጎደለ ሰው እግዚአብሔርን ፍጹም በሆነ መንገድ እንዳላከበረ ጭምር አሳይቶናል። ምክንያቱም እግዚአብሔር የሚከብረው በስላሴ በኩል ነው። አብ ፈቅዷልና ወልድ አደረገ መንፈስ ቅዱስም ተገለጠ ይቺም የአብ ቃል ናትና…”[2] 3) ጠርጡሊያኖስ ወይም ተርቱሊያኖስ (Tertullian 160-215) ፦ የጥንቷ የቤተ ክርስቲያን አባት የሆነው ጠርጡሊያኖስ በስላሴያዊ አስተምህሮት ላይ ለሚነሱ ኑፋቄዎች መልስ በመስጠትና ቤተክርስቲያን እምነት ላይ ከሚሰሩ አቃብያነ አባቶች መካከል አንዱ ነው። ለምሳሌ በመናፍቃን ሙግት ላይ ባነሳው በፕራክሲየስ (against praxeas) ለሞዳሊስት አራማጅ የሆነው የፓትሪፓሺያን(Patripassian) ሐሳብ አንስቶ እንዲህ ሲል በሙግቱ ላይ ጽፏል፡- “…ሶስቱ አብ፣ ወልድና መንፈሱ ናቸው። ሶስት ናቸው ነገር ግን በሁናቴ አይደለም በግብር እንጂ፤ በኑባሬም አይደለም በአካል እንጂ፤ በስልጣን ወይም በሐይል አይደለም በአይነት እንጂ ሆኖም ግን እግዚአብሔር አምላክ አንድ ኑባሬ፣ ስልጣን፣ ሐይል አለው ምክንያቱም በአካል፣ በግብርና በአይነት በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ የተገለጠ አንድ አምላክ ነውና…”[3] 4)አርጌንስ (Origen 185-254) ፦ አርጌንስ የተባለው አባት ከጠርጡሊያኖስ ትምህርት በመነሳት ከእርሱ ጋር በተመሳሰለ ሁኔታ ስለ አስተምህሮተ ስላሴን ሲደግፍ እንመለከታለን። ነገር ግን አርጌንስ በስላሴ አካላት መካከል እንደ ጠርጡልያኖስ በደረጃ (ወይም በsubordination) ረገድ ልዩነት መኖሩን እንደሚያምን ከጽሑፋቱ እንመለከታለን። ሆኖም ግን ኦሪገን የጻፈው የመጀመሪያው መርህ (De Principiis or Peri Archon) እጅግ ጥንታዊ የሆነ የስነ መለኮት ትምህርት ግኝት እንደሆነ ሊቃውንት ያትታሉ። በጽሑፉም ላይ በስላሴ ማመን እንዴት አስፈላጊ እንደሆነ አትቶልን እናገኛለን፦ “…ስላሴ ዘላለማዊ ነው……….በእርግጥ ከስላሴ ውጭ ያሉ ነገሮች ሁሉ በጊዜና በእድሜ ሊለኩ ይችላሉ። ደግሞም ማንም ሰው ለመዳን ወይም “እንደገና ከእግዚአብሔር ለመወለድ” አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ እንደሚያስፈልገውና ከሥላሴ እምነት ውጪ ደህነትን የማያገኝበትን እንዲሁም ያለ መንፈስ ቅዱስ የአብ ወይም የወልድ ተካፋይ መሆንን የማይችልበትን ምክንያት ለምን እንደሆነ መጠየቁ ተገቢ ይመስለኛል። በእነዚህ ነጥቦች ላይ በመወያየት ለመንፈስ ቅዱስ፣ ለአብ እና ለወልድ ልዩ የሆነውን ተግባር(አስተምህሮ) መግለጽ እንደሚያስፈልግ አያጠራጥርም።”[4] 5)Gregory Thaumaturgus-Wonder worker/ጎርጎርዮስ ገባሬ ተአምራት ወመንክራት/(205–270)፦ “ሁሉም(አካላቶች) አንድ ምንነት፤ አንድ ባህሪዎት እና አንድ ፈቃድ አላቸው። ይህ ደግሞ “ቅድስት ስላሴ” ተብሎ ይጠራል። እንዲሁም እግዚአብሔር በንዑሳን ስሞች፣ በአንድ ምንነት ሶስት አካላት እና በአንድ አይነት ዘር (አካላቶቹ በባህሪ ደረጃ) የተገለጠ አምላክ ነው።”[5] ይሄን ካየን ከሁሉ በፊት የሌለ በኒቂያ ነው የሥላሴ ትምህርት የተጀመረው የሚልን ነገር በፍፁም እንደሙግት አንድም ሰው በክርስቲያኖች ላይ ሊያቀርብ በፍፁም አይችልም ማለት ነው። ሌሎች ተጨማሪ የቤተክርስቲያን አበው ላይ የሚነሳውን ተቃውሞ በባለፈው ልጥፋችን ጠርጡሊያኖስ በመቀጠል እንደምናስቀምጥ ነግረናችሁ ነበር። የሌሎቹንም አባቶች በክፍል በክፍል አደራጅተን የምናቀርብ ይሆናል። ጸጋ ሰላም ከሁላችን ጋር ይሁን ማጣቀሻ 1] /1Clement 46:6/ 2] /—Against Noetus Ch. 14./ 3] /Against Paraxeas 2/ 4] /De Principiis, book 1, chapter 3The Trinity according to Origen/ 5] Gregory Thaumaturgus, On the Trinity. ANF, VI:48

ቅድመ ኒቂያ አበው ትምህርተ ሥላሴ እና የቤተ ክርስቲያን ታሪክ Read More »

Scroll to Top