ኢየሱስ አብ ነውን?
ክፍል ፩ ክርስትና በዘመናት ያሳልፈው ውጣ ውረድ የነገስታት እጃቸውን በመጫን ማሳደድ እና መገፋት፣ በጣዖት አምላኪያን መብዛት ብቻ ሳይሆን በዘመናት የተነሱ መናፍቃንም ጨምሮ ነው። ይሄ ደሞ ከተሰቀለ ጣዖት ይበልጥ ክፉ፣ ከሚያሳድድ ጠላት ይልቅ እጅግ ጨካኝ ትምህርት ነው። ከእነዚህም እንደ አንዱ የሆነው ሰባሊዮስ ይገኝበታል። ክርስቲያኖች የሥላሴን አስተምህሮ ታሪካዊነቱ የተመሠከረ፣ ቀጥተኛዋ ሐይማኖት የምታስተምረው እንደሆነ ቢናገሩም በዘመናችን ያሉ ሰባሊዮሳውያን(በተለምዶ Only Jesus በመባል የሚታወቁ) ይህን ትምህርት ለመቀበል ዝግጁ አይደሉም፤ ለምን ሲባል የቃላቶች ትርጉም ከትክክለኛው ቃል እና አውድ በማስወጣት መተርጎማቸው ለዚህ ትልቅ ችግርም ዳርጓቸዋል። ለክርስትናውም ዓለም ትልቅ ጠላትም የሆነው ጥቅሶችን በመቁረጥ የሚከናወን የአውድ ስንጠቃ ሥነ-አፈታት ነው። እኛም በተከታታይ ክፍል እነዚህ ወገኖቻችን ሥላሴን በመቃወም ኢየሱስ አብ ነው ብለው ከሚያነሷቸው ጥቅሶች በመነሳት መልስ እንሰጣለን። “እኔና አብ አንድ ነን” (ዮሐ 10:30) እኔ እና አብ አንድ ነን የሚለው የኢየሱስ ንግግር አንድ አካል ነን እያለ ነው በማለት በስፋት በእነዚህ ወገኖች ይጠቀሳል። ከመመለሳችን በፊት አንድ ማወቅ ያለብን ኢየሱስ በዚህ ቦታ ላይ እኔና አብ አንድ ነን አለ እንጂ እኔ አብ ነኝ አላለም። ስለዚህ በዚህ ጥቅስ ላይ ተንተርሰን ኢየሱስ አብ ነው ማለት አንችልም። እስኪ በዝርዝር እንመልከት፦ ዮሐ10፥30 ላይ የሚገኘው ክፍል ብቻውን ቆርጦ ማንበብ ሙሉ ትርጉም አይሰጥም፤ ኢየሱስ በዚህ ክፍል መልስ እየሰጠ ያለው አንተ ክርስቶስ ነህ ወይ? ለሚለው የአይሁድ ጥያቄ ነው። መልሱን ሲጀምር፦ “እኔ በአባቴ ስም የማደርገው ሥራ ይህ ስለ እኔ ይመሰክራል፤” እነዚህ ወገኖች ኢየሱስ አብ ነው ብለው ከጠቀሱት ክፍል ከፍ ስንል ኢየሱስ በአብ ስም ነው የምሰራው ማለት ምን ትርጉም ይሰጣል? ኢየሱስ በምድር ላይ ሲመላለስ የሰራውን ሁሉ የሰራው በአብ ስም ከሆነ እንዴት እርሱ አብ ነው እንለዋለን? አብስ እንዴት የራሱ ልጅ ይሆናል? እንዴትስ አብ ስራውን በአባቴ ስም ሰራሁት ይላል? በመቀጠል እዛው ምዕራፍ ላይ ኢየሱስ ስለ በጎቹ ማንነት ከተናገረ በኋላ እንዲህ ይላል፦ ” የሰጠኝ አባቴ ከሁሉ ይበልጣል፥ ከአባቴም እጅ ሊነጥቃቸው ማንም አይችልም።”(የዮሐንስ ወንጌል 10፥29) የሚገርመው እዚህ ጋር ኢየሱስ የበጎቹ ተቀባይ አብ ደግሞ በጎቹን ለኢየሱስ ሰጪ ሆነው በቃሉ ላይ ተገልጠዋል። መስጠት እና መቀበል መሀል ቢያንስ ሶስት አካላት መኖር አለባቸው፤ ሰጪ ተቀባይና ሁለቱ የሚቀባበሉት ሌላ ሶስተኛ አካል። በቁጥር 29 የምናየው ይህንኑ ስለሆነ ነው፤ ሰጪው አብና ተቀባዩ ኢየሱስ የተለያዩ ሁለት አካላት ናቸው። እንዲህ ካልሆነ ግን አብ በጎቹን ለራሱ ሰጠ ልንል ነው?እንግዲህ ከዚህ ሁሉ በኋላ ነው ኢየሱስ ለጥያቄያቸው መደምደሚያ መልስ የሆነውን “እኔና አብ አንድ ነን” የሚል መልስ የሰጠው። ቃሉን ቀረብ ብለን ስንመለከተው ጌታ ኢየሱስ አብንና እርሱን አንድ ነን በሚል የብዙ ቁጥር መቋጫ መግለጡን እንመለከታለን። ይህንን በየትኛውም ቋንቋ በጽርዑ(በግሪኩ) ቢሆንም ብንመለከተው ተመሳሳይ ውጤት እናገኛለን። ለምሳሌ፦ ” I and my Father are one. “ἐγὼ καὶ ὁ πατὴρ ἕν ἐσμεν.ኤጎ ካይ ሆ ፓቴር ሄን ኤስሜን ከላይ ባሉት በየትኛውም ቋንቋ ኢየሱስ ራሱንና አብን ያስቀመጠው ከአንድ በላይ አካል በሚገለጽበት የብዙ ቁጥር መግለጫ ነው። ይህ ደሞ የጽርዑ ἐσμέν(esmen) የሚለው ቃል εἰμί(eimi) ለሚለው የነጠላ ቁጥር ገላጭ አበዢ ሆኖ የሚያገለግል first person plural indicative (አንደኛ መደብ ብዙ ቁጥር አመልካች) ነው። ስለዚህ አብና ወልድ አንድ ናቸው በሌላ አባባል We are one ማለቱ እንረዳለን እንጂ አብ ወልድ ነው እንድንል የሚያንደረድር እሳቤ አያሰጠንም። ስለዚህ በዚህ በዮሐንስ 10፥30 ላይ ኢየሱስ እየተናገረ ያለው፦ በጎቹን ከእርሱም ሆነ ከአብ እጅ ማንም መንጠቅ እንደ ማይችል እርሱና አብ አንድ እንደሆኑ በማሳወቅ በባሕርይ እኩል መሆናቸውን ግልፅ አድርጓል (ዮሐ. 10፡30)፡፡ ይህ አንድነት የኃይል አንድነትን የሚገልፅ ነው፡፡ አብና ኢየሱስ በኃይል አንድ ናቸው፡፡ ለዚህ ነው ማንም በጎቹን ከአብ እጅ መንጠቅ እንደማይችል ሁሉ ከኢየሱስም እጅ መንጠቅ የማይችለው እንጂ ስለ አካላት አንድ ወደ መሆን እና ነጠላነት መቀየራቸውን ክፍሉ አያወራም። ለዚህ ክፍል የመጨረሻ ለሰባሊዮሳውያን ምላሻችን ይህ ነው፦ “ቃሉን ክደህ ቃሉንስ ሽረህአባትም እራሱ ልጅም እራሱ ነውየሚለው አባባል ምን አይነት ብሂል ነውትመልስ እንደሆነ የቱ ሐዋርያ እንዲ ብሎ ፃፈያልተባለን ሚያነብ ቃሉን ተላለፈ…” ቸር ቆዩኑ