ወልድ የመጀመርያው ፍጡር ነውን?


ክፍል

አርዮሳውያን ወልድ ፍጡር ነው ብለው የሚጠቅሷቸውን ጥቅሶች መካከል አንዱ እንዲህ ይነበባል፦

“እግዚአብሔር የመንገዱ መጀመሪያ አደረገኝ፥ በቀድሞ ሥራው መጀመሪያ።”
  — ምሳሌ 8፥22

ይሄን ክፍል ነበር አርዮስ ኢየሱስ ፍጡር ነው ብሎ ሲሞግትበት የነበረው። በአስተውሎት ክፍሉን ላጠና ፍጡር መሆንን ይሆን የሚያወራው የሚለውን በስፋት እንይ። በመጀመሪያ በክፍሉ ላይ ያሉ ምልከታዎች ጥበብን አካል እንዳላት አድርጎ አቅርቧት እንጂ ኢየሱስ አይደለም ብለው የሚሞግቱ ሰዎች አሉ። ነገር ግን የተለያዩ የአበው ክታባትን ሆነ ኮሜንተሪዎችን ስናነብ በተጨማሪም በቋንቋዊ አገላለጽ ያለውን አገባብ ስንመለከት ይበልጡን ክፍሉ ወደ ክርስቶስ አቅንቶ እንደሚናገር እናያለን። እስቲ የግሪኩን የቃል አጠቃቀም እንመለከት፦

Κύριος ἔκτισέν με ἀρχὴν ὁδῶν αὐτοῦ εἰς ἔργα αὐτοῦ
PROVERBS 8.22

ብዙ ምሁራን የሚከራከሩት፣ አንዳንዶች ደሞ ጎራ ይዘው ኢየሱስን ፍጡር ለማለት የሚጠቅሷት ኤክቲሴን/ἔκτισέν የምትለው ቃል ነው። ቃሉም ብዙ ክርክሮችን በተለያዩ ሰዎች አስነስታለች። አንዱም ታላቁ መናፍቅ አርዮስ እንኳን ወልድ ፍጡር ነው ብሎ ሲሞግት ከሚጠቃቅሳቸው ክፍሎች ውስጥ አንዱ ይሄ ክፍል ነበር። እንደ እውነቱ ኤክቲሴን/ἔκτισέν የሚለው ቃል መፍጠር ማስገኘት ወዘተ የሚሉ ትርጉሞች አሏት። ነገር ግን በዚህ ክፍል ላይ መፍጠር በሚለው ትርጉም ሳይሆን ማስገኘት የሚለው እንደገባች አንዳንድ ሙህራን ያትታሉ። ወልድ ከአብ የተገኘ እንጂ በአብ የተፈጠረ ፈጽሞ አይደለም። መገኘት እና መፈጠር ለየቅል የሆኑ ናቸውና። ይሄም የሆነበት ምክንያት ኢየሱስ ከአብ የተገኘ ማለት ከዘላለማዊ መገኘት ከአብ ጋር አብሮ የሚኖር ወደ ምድርም በመጣ ጊዜ ከአብ ወጥቶ የመጣ አካል መሆኑን የሚገልጽ መሆኑ ነው። በኒቂያው ጉባኤ የተሰጠውን የእምነት መግለጫ ስንመለከት፦

“እርሱ ብቻ የአብ ልጅ በሚሆን፣ ዓለም ሳይፈጠር ከአብ በተወለደ፣ ከአምላክ በተገኘ አምላክ፣ ከብርሃን በተገኘ ብርሃን፣ ከእውነተኛ አምላክ በተገኘ እውነተኛ አምላክ፣ በህልውናው ከአብ ጋር አንድ የሆነ፣ በተፈጠረ ሳይሆን በተወለደ፣ ሁሉ በእርሱ በሆነ፣ ስለ እኛ ስለ ሰዎች ስለ ደህንነታችንም ከሰማይ በወረደ፣…”

ከአምላክ በተገኘ አምላክ፣ ከብርሃን በተገኘ ብርሃን፣ ከእውነተኛ አምላክ በተገኘ እውነተኛ አምላክ ካለ በኋላ በተፈጠረ ሳይሆን በተወለደ በማለት በአብና በወልድ መካከል ያለውን መስተጋብር እንደ ፍጥረት እንዳልሆነ ሲገልጹ እንመለከታለን። አስተውሉ መፈጠርና መወለድ ወይም መገኘት ሁለት የተለያየ ትርጉም ያላቸው ቃላት ናቸው።

የእብራይስጡን ቃል ስንመለከት ደሞ፦

כב  יְהוָה–קָנָנִי, רֵאשִׁית דַּרְכּוֹ:    קֶדֶם מִפְעָלָיו מֵאָז.

ያህዌ ቃናኒ/יְהוָה–קָנָנִי የሚለው ሐረግ ውስጥ ቃናኒ/קָנָנִי ማለት ቃናህ/קָנָה ይህም ማለትም ማስገኘት፤ ማድረግ ማምጣት የሚል ትርጉም ነው ያለው።[1] ይሄ ማለት ደሞ ጥበብ በያህዌ ከዘላለም መገኘት የተገኘ ወይም የመጣ አካል እንደሆነ ያሳየናል። እንደ አርዮስ በዚህ ክፍል ላይ መፍጠር በሚለው አገባብ አልገባም ማለት ነው።

በመጨረሻም አርዮስ ከፍልስፍና ጋር በማዛመድ ከምሳሌ 8፥22 በተጨማሪ የሚመቸውን ጥቅስ በመጥቀስ ጥያቄ በመጠየቅ ሰጣ ገባ ውስጥ ሲገባ በክርክሩ ጊዜ ቅዱስ አትናቴዎስ ይህን አንሥቶ ነበር፤ ይኸውም አርዮስን ሲጠይቀው፦

“ወልደ አብ ኢየሱስ መድኃኒት ነው፤ አዳኛችን ነው፤ አዳኝ መሆኑን ካመንን የባህርይ አምላክነቱን ማመን አለብን። የሚያድን እግዚአብሔር ብቻ መሆኑን ቅዱሳት መጻሕፍት ይመሰክራሉ። በቅዱሳት መጻሕፍት ምስክርነት የወልድ አምላክነት ከሰው ልጆች የመዳንን ምሥጢር ጋር የተያያዘ ነው። ወልድ የባህርይ አምላክ ካልሆነ ግን እኛም አልዳንም ማለት ነው። በእርሱ መዳናችን ካመንን ግን ያዳነን እሱ አምላክ መሆኑን ማወቅና ማመን አለብን። ፍጡር ፍጡራንን ማዳን አይችልምና። ብሎ አትናቴዎስ ሲከራከር የሰሙት አብዛኛዎቹ የጉባኤው አባላት በደስታ ተዋጡ።[2]

አርዮስም፦ “ወልድ በምድር ሕይወቱ ታላቅ ትሕትናንና ተጋድሎ በማሳየቱ በባሕርይ ሳይሆን በጸጋ የአምላክነትን ክብር ስላገኘ ስግደት ይገባዋል” አለ።

ቅዱስ አትናቴዎስ ሲመልስ “ክርስቶስ ከባሕርይ አባቱ ከአብ ጋር አንድ ነው። ነገር ግን ወልድ ፍጡር ነው ካልን ለእርሱ የአምልኮ ስግደት ማቅረብ አምልኮ ባዕድ ነዋ!” ሲለው መናፍቁ አርዮስ መልስ አላገኘም።[3][4] ምክንያቱም፦

“ወልድ በራሱ እሱ በስጦታ ያገኘውን አምላክነት ለሌላ ሊቸረው ሊለግሰው አይችልም፤ ከራሱ አይተርፍምና፡፡ ስለዚህ ወደ እኛ ወርዶ ራሱን ያሻሻለ አይደለም፤ ይልቁንስ መሻሻል የሚያስፈልገውን ሰው አሻሻለ እንጂ”

እግዚአብሔር አምላክ የቃሉን መረዳት በሙላት ይግለጥልን አሜን።

ይቀጥላል

1] ENGLISH-HEBREW LEXICON BEING A COMPLETE VERBAL INDEX TO GESENIUS’ HEBREW LEXICON, JOSEPH LEWIS POTTER, A.M, pp 132

2] የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በዓለም መድረክ፣ በአቡነ ጎርጎርዮስ ገጽ 111-112

3] ዝኒ ከማሁ ገጽ 112

4] ዶ/ር ምክረ ሥላሴ የእግዚአብሔር መንግስት ታሪክ 292-293

ለሌሎች ያጋሩ

Leave a Comment

ኢ-ፖስታ አድራሻወ ይፋ አይደረግም። መሞላት ያለባቸው መስኮች * ምልክት አላቸው

Scroll to Top