የባሕርዩ ምሳሌ
በማህበራዊ ሚዲያ ላይ አንድ ሙግት መልስ ፈልጋለሁ በሚል ርዕስ አንድ ጥያቄ ተቀምጦ ነበር። ይኼም ሙግት ኢየሱስ ፍጡር ነው ከሚል ከአንድ አርዮሳዊ በተለምዶ የይሖዋ ምሥክሮች ቤተ ጎራ እንደሚመደብ ጥያቄውን ያነበበ ሰው ወዲያውኑ ያውቃል። ኢየሱስ ፍጡር ነው ያለውም ከዚህ ጥቅስ የተነሳ ነበር፦ “እርሱም የክብሩ መንጸባረቅና የባሕርዩ ምሳሌ ሆኖ፥ ሁሉን በስልጣኑ ቃል እየደገፈ፥ ኃጢአታችንን በራሱ ካነጻ በኋላ በሰማያት በግርማው ቀኝ ተቀመጠ፤” — ዕብራውያን 1፥3 ምሳሌ ሲባል ሰው በእግዚአብሔር ምሳሌ ተፈጥሯል እናም ኢየሱስ የእግዚአብሔር ምሳሌ ነው። ስለዚህ ፍጡር ነው የሚል ድምዳሜን አስቀምጦም ነበር። መልስ ምሳሌ የተባለበት ምክንያት ኢየሱስ በትክክል አብን የሚገልጥ መሆኑን ለማመልከት እንጂ ፍጡር መሆኑን ለማሳየት አይደለም፡፡ ኢየሱስ የእግዚአብሔር አብ ምሳሌ መኾኑ የተጠቀሰበት አምላክነቱን ለክርክር ሊቀርብ በማይችልበት ኹኔታ የሚገልጥ ሌላ ጥቅስ በዕብራውያን መልዕክት ውስጥ ይገኛል(ዕብራውያን 1፥2 ዕብራውያን 1፥8 እና ሌሎችም)። ከጠያቂያችን ጥቅስ ግን ተነስተን በአጭሩ መልስ እንስጥ፡- “እርሱም የክብሩ መንጸባረቅና የባሕርዩ ምሳሌ ሆኖ፥ ሁሉን በስልጣኑ ቃል እየደገፈ፥ ኃጢአታችንን በራሱ ካነጻ በኋላ በሰማያት በግርማው ቀኝ ተቀመጠ፤” — ዕብራውያን 1፥3 “የባሕርዩ ምሳሌ” ተብሎ የተተረጎመው “ሁፖስታሴዎስ ካራክቴር” የሚል የግሪክ ሐረግ ሲሆን ካራክቴር የአንድን ነገር ትክክለኛ፣ ያልተሸራረፈ፣ ከዚያኛው አካል ያላነሰ፣ እኩል የሆነ ማንነት የሚያሳይ ነው፡፡ ይህ “ምሳሌ” ከዚያኛው አካል ጋር በኹሉም ረገድ ፍጹም ተመሳሳይ ነው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሚነግረን ወልድ ከአብ ልዩ መኾኑን፤ ነገር ግን ደግሞ ከአብ ጋር ፍጹም እኩል መኾኑን ከምንም ዓይነት ጥርጣሬ በፀዳ ኹኔታ የሚገልጥ ክፍል ነው፡፡[፩] ስለዚህ ይሄ ክፍል ኢየሱስ ፍጡር ነው ተብሎ የቀረበው መለኮታዊ ባሕርዩን ገላጭ እና ይልቅም አምላክነቱን የሚያሳይ ሆኖ እናገኘዋለን። ማጣቀሻ [፩] Vines Complete Expository Dictionary of Old and New Testament Words, Thomas Nelson Publishers, Nashville Camden New York, 1984, P. 319.