የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክነት
ክፍል 1 “እርሱ በባሕርዩ አምላክ ሆኖ ሳለ፣ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን ሊለቀው እንደማይገባ አድርጎ አልቈጠረውም፤” ፊልጵስዩስ 2፥6 (አዲሱ መ.ት) አንድ አካል አምላክ ነው የሚባለው ወይም እንደ አምላክ ሊመለክ የሚገባው <አምላክ ነኝ> ብሎ ስለተናገረ ብቻ ወይም ብዙዎች አምላክነቱን ስላወጁለት አይደለም። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አምላክ ነኝ ብለው የተነሱ ነገስታት እንዳሉ እንመለከታለን። ለምሳሌ፦ የጢሮስ ንጉስ እኔ አምላክ ነኝ ማለቱን እንመለከታለን (ሕዝቅኤል 28፥2-9) ስለዚህ የጢሮስ ንጉስ እኔ አምላክ ነኝ ስላለ ብቻ አምላክ ነው ብሎ መፈረጅ አግባባዊ ሙግትና እና ከስነ አመክንዮ አንጻር ምክንዮአዊ ሐሳብ ፈጽሞ አይደለም። በሰውም አጀብ አንድ አካል አምላክ ስለተባለም አምላክ ሊሆን አይችልም ምክንያቱም የግሪክ ጣዖታት እንዲሁ ተብለው ምንነታዊ ለውጥ ስላላሳዩን። ክርስቶስ ኢየሱስ አምላክ ለመሆኑ የአምላክነት ግብሩን፤ ባህሪዎቱንና ሐልዎቱን በተለያየ መንገድ መጽሐፍ ቅዱስ ሲናገ፤ ሲተርክና ሲገልጽልን እንመለከተዋለን። የክርስቶስ ኢየሱስን አምላክነትና ዘላለማዊ መለኮታዊ ኑባሬ እንዳለው ከሚናገሩ እልፍ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ውስጥ አንደኛው የፊልጵስዩስ መልእክት ም2 ቁ6-7 ነው፦ ⁶ እርሱ በባሕርዩ አምላክ ሆኖ ሳለ፣ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን ሊለቀው እንደማይገባ አድርጎ አልቈጠረውም፤ ⁷ ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ፣ በሰውም አምሳል ተገኝቶ፣ ራሱን ባዶ አደረገ ፊልጵስዩስ 2 (አዲሱ መ.ት) <<ὃς ἐν μορφῇθεοῦ ὑπάρχων οὐχ ἁρπαγμὸν ἡγήσατο τὸ εἶναι ἴσα θεῷ,>>/Προς Φιλιππησιους 2:6 በጽርዑ ሞርፌ/μορφῇ የሚለው ቃል ኑባሬያዊ መገኘትን፣ ሁናቴን ወይም ባህሪዎተ መልክን የሚገልጽ ቃል ሲሆን ክርስቶስ ኢየሱስ (ወልድ) እም ቅድመ አለም በኑባሬው በባህሪዎተ መልኩ ራሱ አምላክ (ፈጣሪ) ሁኖ የሚኖር አካል እንደሆነ ይገልጻል። በተጨማሪም በባለቤትነት ሙያ (Nominative case) የመጣው ሁፓርኾን/ὑπάρχων የሚለው ቃል በአሁን ጊዜ አመልካች ግስ(Present participle tense) መምጣቱ ወልድ ከዘላለም ጀምሮ ከአብ ጋር አብሮ ህያው አብሮ እኩል አብሮ ዘላለማዊ እንደሆነ በሚገልጽ መልኩ እንደመጣ የክፍሉን ሰዋሰዋዊ መዋቅር በተመለከትን ጊዜ በቀላሉ መረዳት ያስችለናል። ይህም ደግሞ ለወልድ ኑባሬ ጅማሮ አለው ፍጡር እንጂ ፈጣሪ አይደለም ለሚሉት አርዮሳውያን እና ኢብዮናውያን (Ebionite/Ἐβιωναῖοι) በተለምዶው አዶፕሽኒስቶች የሚባሉት የምን*ፍቅና የአስተምህሮቶችን መሰረታቸውን የሚንድ ክፍል ነው። ሙግታችንን ጠበቅ ለማድረግ ያክል ከተመለከትን ደግሞ ኢየሱስ ክርስቶስ (ወልድ) አምላካዊ ባህሪ(መልክ) ከጥንተ ዘላለም ጀምሮ በዚሁ ባህሪ ሲኖር የነበረው አምላክ ወደ ፈጠራት ጠባበ አለም የሰውን ወይም የባሪያን ባህሪ(መልክ) ይዞ መምጣቱ “ከእግዚአብሔር አብ ጋር መተካከልን ሊለቀው እንደማይገባ አድርጎ አልቈጠረውም” በማለት ብርሃነ አለም ቅዱስ ጳውሎስ ፍንትው አድርጎ የወልድን መለኮታዊ ባህሪዎት ከእግዚአብሔር አብ ጋር እኩል እንደሆነ ያሳየናል። ከአምላክ ጋር እኩል መሆን ወይም በጽርዑ ቶ ኢናይ ኢሳ ቴኦ/τὸ εἶναι ἴσα θεῷ የሚለው ሐረግ እግዚአብሔር ወልድ ከእግዚአብሔር አብ ጋር በባህሪው እኩል ወይም አንድ አይነት ሆሙስዮስ/ὁμοούσιος እንደሆነ በግልጽ ሁኔታ ሲነግረን የአርዮሳውያንን መርሆተ ቃል የሆነውን ተመሳሳይ ወይም ተቀራራቢ ባህሪዎት ሆሞዮስዮስ/ὁμοιούσιος የሚለውን ምንፍቅና አፈር ከመሬት የሚደባልቅ ክፍል እንደሆነ እንመለከታለን። በቁጥር ሰባትን አንድ በአንድ ስንመለከተው “የባሪያን መልክ ይዞ” የሚለው ሐረግ በፊት የተገለጠበት ቅድመ ኑባሬያዊ ባህሪዎት እንደነበረው ቁልጭ አድርጎ ያሳየናል፤ እርሱም በቁጥር 6 ላይ እንዳየነው የወልድ አምላካዊ መልክ (ባህሪ) ከጥንተ ዘላለም ጀምሮ ገንዘቡ የሆነ ምንነት ነው። “በሰውም ምሳሌ ሆኖ” የሚለው ሐይለ ቃል ደሞ ወደ ምድር በመጣ ጊዜ ፈጣሪ በፍጡራን ምሳሌ ሆኖ ሰዋዊ ባህሪዎትን እንደተላበሰ ያሳየናል። ቀጥሎም “ራሱን ባዶ አደረገ” የሚለው ደሞ አንድ ነገር ባዶ ሆነ የሚባለው ያ ነገር መጀመሪያውኑ የሆነ ነገር ሲኖረው ነው። ክርስቶስ ኢየሱስ ደግሞ <<ራሱን ባዶ አደረገ>> ሲባል አምላካዊሙሉነት የነበረው አካል ወደ ፈጠረው፣ ወዳዘጋጀው፣ ሰዋዊ ባህሪዎት ዝቅ ብሎ በመምጣቱ ነው። ስለዚህ ክርስቶስ ኢየሱስ ሰው ሁኖ ከመምጣቱ በፊት በአምላካዊሙሉነት የሚኖር አምጻኤ ኩሉ አምላክ እንደሆነ እንመለከታለን። በመጨረሻም የሙግት ኩረጃ የማይሰለቻቸው አብዱላዊ ኡስታዞች የጸረ ክርስቶሳውያንን ሐሳብ በማንጠልጠል <<ክርስቶስ ኢየሱስ (ወልድ) በእግዚአብሔር ወይም በአምላክ መልክ መኖሩ አዳም በእግዚአብሔር መአልክና ምሳሌ በተፈጠረበት ሒሳብና ቀመር ነው>> ብለው ይሞግታሉ። ነገር ግን የሁለቱን ክፍሎች የጽርዑን የቃላት አገባብ እና አውዳዊ ምልከታ ባደረግን ጊዜ ፈጽመው የየቅል ሐሳብ እንደሆነ እንረዳለን፦ እግዚአብሔርም አለ፦ ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር/καὶ εἶπεν ὁ θεός Ποιήσωμεν ἄνθρωπον κατ᾽ εἰκόνα ἡμετέραν καὶ καθ᾽ ὁμοίωσιν — ዘፍጥረት 1፥26 በዘፍጥረት 1፥26 መልክ ብሎ የገባው የግሪኩ ቃል ኤይኮና/εἰκόνα ሲሆን ምሳሌ የሚለው ደሞ ሆሞዮሲን/ὁμοίωσιν በሚለው የቃላት አገባብ እንደተሰደረ እንመለከታለን። ኤይኮና/εἰκόνα የሚለው ቃል ኤይኮን/εἰκών ማለትም ምስለ መልክን መመሳሰል ወይም መቀራረብ(በውጫዊ ማንነት መገለጫ) የሚል ትርጉም አለው። እግዚአብሔር አምላክ ሰውን እኛ መልክ(ኤይኮና ሄሜቴራን/εἰκόνα ἡμετέραν) እንፍጠር ሲል በጽድቅና ቅድስና(ኤር 4:24)፤ እንዲሁም በመገንዘብ ችሎታንና እውቀትን(ቆላ 3:10) የመሳሰሉትን የምስስሎሽ መገለጫዎች በሚገልጽ አገባብና አግባብ መምጣቱ ቅብል ነው። ነገር ግን የሰው ልጅ በእግዚአብሔር መልክና አምሳል መፈጠሩ በእርግጥ የሚካፈለው ባህሪ እንዳለው ሁሉ የማይካፈለው ባህሪ አለ። በዛው በፊልጵስዩስ መልእክት 1:7 እና 2ኛ ጴጥሮስ 1፥4 ላይ የእግዚአብሔር የባህሪው ተካፋዮች እንደሆንን ይናገራል፦ “ስለ ክፉ ምኞት በዓለም ካለው ጥፋት አምልጣችሁ ከመለኮት ባሕርይ ተካፋዮች(κοινωνοὶ φύσεως) በተስፋ ቃል እንድትሆኑ፥ በእነዚያ ክብርና በጎነት የተከበረና እጅግ ታላቅ የሆነ ተስፋን ሰጠን።”— 2ኛ ጴጥሮስ 1፥4 ተካፋይ ወይም በግሪኩ ኮይኖኖስ/κοινωνός የሚለው ቃል የሰው ልጅ ከእግዚአብሔር ፈጽሞ የማይካፈለው ወይም የቀረበት ነገር እንዳለ አመላካች ነው። ይህንን ሐሳብ በሌላ ክፍል በስፋት እንመለከተዋለን። ነገር ግን ክርስቶስ ኢየሱስ ከእግዚአብሔር አብ ጋር የማይጋራው ሆነ የማይካፈለው ባህሪ የለም። ከላይ በፊልጵስዩስ መልእክት 2:6 ከአብ ጋር በመለኮተ ባህሪዎት እኩል ወይም አንድ እንደሆነ ተመልክተናል። ስለዚህ አምላክ ክርስቶስ ኢየሱስ በአምሳለ ሰውነት መገለጡ (እንደ ሰው መብላት መጠጣቱ፤ መተኛት መነሳቱ፤ መወለድ ማደጉ ወዘተ) መለኮታዊ ክብር እንደሌለው የሚያሳየን ተግባር አይደለም። እርሱ ወደዚች ወደ ፈጠራት አለምና ሰውነት ከመገለጡ በፊት አምላካዊ ምንነት፤ ክብርና መለኮታዊ ኑባሬ ከጥንተ ዘላለም ጀምሮ ገንዘቡ ያደረገ ሐያል አምላክ ነው።
የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክነት Read More »