Foundation

Soli Deo Gloria/ክብር ለእግዚአብሔር ብቻ

በቤተክርስቲያን ታሪክ ውስጥ ከተወገዙ የምንፍቅና መምህራን አንዱ ፔላጄዬስ ነው። እርሱም እግዚአብሔር በሰው ልጆች የድነት ስራ ላይ በብቸኛነት ያለውን ባለቤትነት ፈፅሞ ከወደቀው ሰው ነፃ ፈቃድ ጋር የጋራ ስለነበረ ነው በማለቱ ነው።(ይህን ታሪካዊ ምሳሌ ያነሳንበት የምንሞክርበት ምክንያት ለእግዚአብሔር ክብር ብቻ የሚለው ክርስቶስ ካደረገው የድነት ሥራ ጋር ስለሚገናኝ ነው።) ይህ ሰው የእግዚአብሔርንም ጸጋ ለሰው ልጆች ድነት አነሳሽ ብቻ እንጂ የድነት ምንጭ አይደለም ብሎ ያስተምራል። ይሄን ትምህርት ደሞ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ በክታቡ ከዚህ በተቃራኒው ሆኖ እንዲህ ይናገራል፦ “ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል፤”  — ሮሜ 3፥23 ክፍሉ የሰው ፈቃድና ባህሪይ በኃጢአት መበከል፣ ከእግዚአብሔር እንደለየው፣ የሰውም ፈቃዱም ወደ እግዚአብሔር ፈፅሞ ሊሆን እንደማይችልና እርሱንም ሚፈልግ ማንም እንደሌለ በክታቡ እንዲህ በማለት ይናገራል፦ “ጻድቅ የለም አንድ ስንኳ፤ አስተዋይም የለም፤ እግዚአብሔርንም የሚፈልግ የለም፤ ሁሉ ተሳስተዋል፥”  — ሮሜ 3፥11 ከዚህም መጽሐፍ እንደምንረዳው የሰው ድርሻ  በድነቱ ውስጥ ባዶ ቦታ እንዳለው ይናገራል። ስለዚህም ጻድቅ የሆነውን እግዚአብሔርን ሊመርጥ በሰውም በኩል ወደ እግዚአብሔር ልቡንም ወደ ፈጣሪው ሊመልስ ይህ ሙት ሰው አይቻለውም ምክንያቱም ሁሉ ኃጢአትን ሰርተዋልና። የሞተስ እንዴት ሕይወትን ይመርጥ ዘንድ ይቻለዋል? ነገር ግን በምህረቱ ባለፀጋ ስለሆነ ስለወደድን ሳይሆን ስለወደደን ብቻውን ለድነታችን ምክንያት፥ የድነታችንም ፍፃሜ ሆነልን። በቀደመው ኪዳን ተስፋ በእርሱ ላይ ባላቸው እምነት አባቶችን አዳነ፥ በዘመኑ መጨረሻ  በልጁ የቤዝዎት ስራ ህጉን መጠበቁን አውቀን በእርሱ ስላመንን ብቻ ጽድቁን ቆጠረልን። ደግሞም አለማትን በፈጠረበት በልጁ የጠፋውን ህዝብ ተቤዥቶ አለሙን አዳነ። በእርሱ ብቻ ተፈጠርን፣ በእርሱ ብቻ ዳንን ያዳነን እርሱ ይቀድሰናል፣ የቀደሰን እርሱ ራሱ ያጽናናል፣ ያጸናን እርሱ ደግሞ ያከብረናል። ወደ ፈጠረን ወደ አባታችንም እንፈፀማለን። በዚህ እንቅስቃሴ ነው የተሐድሶ አራማጆች በሮማ ካቶሊክ ያለውን የተሳሳተ ግንዛቤ ማጥራት መጀመራቸው የሚታወሰው። ታዲያ ለእኛ ምን ይሰራል? ለምን እስካሁን ተቃውሞ ታደርጋለህ? ቢባል መልሳችን እንደ ተሐድሶውያኑ መሠረት የሮማ ካቶሊክ ኢስተርን ሆነ ሌሎች ታሪካዊ ቤተክርስቲያን አማኞች በአብዛኛው ንግግራቸው ሆነ ፍለጋቸው ለእግዚአብሔር ክብር ብቻ የሚል ነው ይላሉ። ነገር ግን በሚያሳዝን ሁኔታ ግን በተሐድሶ ወቅት የካቶሊኩ ምልከታ ፖፑና ቅዱሳን በሚባሉት ላይ ነው። በሌሎቹ ቤተክርስቲያን የፖፑ አለመቀብልን እናም አይሳሳቴነትን ትተው የቅዱሳን ክብር ገኗል።(ይሄን ስንል እኛ ክላሲካል ፕሮቴስታንት ለቅዱሳን ክብር አይገባም ማለት አይደለም።) ይሄን የእኛን አቋም ለመረዳት አንድ ሰው እንዲህ ሲል የጠየቀንን ጥያቄ ማንሳት ይቻላል፦ ጥያቄ፦ ማርያም የድነታችን ምክንያት ናት ወይ? መልስ፦ በሥጋዌ ምክንያት አዎ ናት እንላለን። በእርሷ በኩል ጌታ ተገኝቷል የሚለውን ነገር ብቻ ለመግለጽ ከሆነ። ለድነታችን ምክንያት ስንል(የአምላክ እናት፣ የብርሃን እናት..) ይህንን ጠቅልሎ ማለታችንም ነው። ጥያቄ፦ እና ታዲያ የምትቃወሙት ምንድነው? ኢየሱስን የድነቴ ምክንያት ብለህ እሷንም ማለትህ እኛ የተለየ ነገር አልን ወይ? ለምን ተቃወምክ? መልስ፦ በድጋሚ እኛ የተቃወምነው ድነታችንን ሆነ ወደ እግዚአብሔር መቅረባችን የራሱን ክብር በመግጡ እንጂ ሰዎች ባደረጉት ወይም በእነሱ በኩል መግባትን ወይ ያለ እነርሱ የሚልን ነገረ ድነታዊ ተፋልሶን ነው። ይሄንንም አጥብቀን ምንቃወመው ከእነዚህን ጋር ተያይዘው በCatechism of the Catholic Churchም ሆነ በሌሎች ቤተ ክርስቲያን ዘንድ የተቀመጡትን የተለጠጠ ግንዛቤዎችን እንቃወማለን፦ “By asking Mary to pray for us, we acknowledge ourselves to be poor sinners and we address ourselves to the ‘Mother of Mercy,’ the All-Holy One” (CCC 2677). “After speaking of the Church, her origin, mission, and destiny, we can find no better way to conclude than by looking to Mary” (CCC 972). ሌላም በእናተው መካከል በቀላሉ የማናልፈው ነገር፦ ” ለእኛ ድኅነት ብዙ መንገድ አለ” በማለት በየምስባኩ ሰው ሰራሽ ዶክትሪን በማሳየት፣ ይባስም ብሎ የእግዚአብሔርን የማዳን ክብሩን የሚነቅልና የሰውን የመገናኛ ድንኳን የሚተክል ትምህርት ስላለ ነው። እና ሌሎችም ነው። በድጋሚ እኛ ክላሲካል ፕሮቴስታንት ስንቃወም እየተቃወምን ያለውን ነገር አጥርቶ ማየት ያሻል። በዚህ ብርሃን መንገድ የተሐድሶ አበው ያሳደጉት ነገር አምስቱን ብቻዎችን ነው። ለዚህም መፍትሔው በቃለ እግዚአብሔር ላይ በተጨመሩ ትምህርቶች በአባቶች ትምህርት የሌሉትንና በታሪክ ዶግማ ተደርገው ያሉትን የእግዚአብሔርን ክብር የሸፈኑትን እነዚያን ተቃውመው ቆሙ። ➞ ስለዚህም ምክንያት ክብር ለእርሱ ብቻ ይገባዋል። ➞ ብቻውን የድኅነታችንን ስራ ሰርቶታልና። ➞ የማዳኑ ኪዳኑ መሰረት እርሱ ብቻ ላይ ብቻውንም አዳኝ  ስለሆነ ላዳነን ለእርሱ በብችኛነት ሌላ ሳይጨመር ሳይደመር አምልኮ ስግደት ይገባዋል። ➞ ብቻውን ሊደነቅ ሊመሰገንም የተገባው ነው እጅግ ድንቅ ግሩምም ነውና። ምክንያቱም እርሱ፦ እንደ እንቁ የተዋበ በኪሩቤልም ላይ የሚቀመጥ በመዞርም ጥላ የማይገኝበት ማንም ሊቀርበው በማይችል ብርሃን ተሰውሮ ለዘላለም ሚኖር ሰማያትን ያለ ምስሶ የዘረጋ ምድርንም በውኆች ላይ ያፀና የምድርም አህዛብ በፊቱ በገምቦ እንዳለች ጠብታ የሆኑለት በጽድቅ የሚፈርድ መሐሪ የአብርሃም የይስሃቅ የያእቆብ አምላክ  የዘላለም አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሄር ሚመስለው የለም!   በዚህም መሠረት ደሞ እርሱም የተባረከ አምላክ ነው ሰውም መድኃኒት ይሆን ዘንድ አይቻለውምና። ይሄን ሐዳሲያኑም ሲሉም ሆነ እኛም ስንለው ቅዱሳንን ክብር አንሰጥም ማለት አይደም። እነሱን ምናከብረው ግን ድነትን መንገድ በመለጠጥ ከሆነና ወይ ደሞ ለእግዚአብሔር የቀረበውን የሚቀናጅ ከሆነ ግን በእግዚአብሔር ክብር ላይ አደጋ ነው። በታሪካዊ ፕሮቴስታንቱ ተሐድሶ ውስጥ ትልቅ ትኩረት የተሰጠውና የአስተምህሮቶች ሁሉ መጠቅለያ ነው። በድጋሚ እንጠየቅ እስኪ?why it still matters(በዚህ ዘመን ላለነው ምን ፋይዳ አለው?) በአጭሩ እኛ ክላሲካል ፕሮቴስታንት በዚህ ዘመን ያለነው ይሄን ለምን እናምናለን የሚለውን ስንመልስ፦ ለእግዚአብሔር ክብር ብቻ የተሃድሶው መሠረታዊው አስተምህሮ የሁሉም ነገር የመጨረሻ ዓላማ ለእግዚአብሔር ክብርን ማስገኘት ነው የሚል ነበር። እነሱ ከመጽሐፍ ቅዱስ የወጣውንና ከቤተክርስቲያን የተገኘውን ያንን መሠረት ይህም የእግዚአብሔርንም ሉዓላዊነት አፅንተው በመጠበቅ፣ የሚሆነው ነገር ሁሉ ከሰው ወይም ከፖፑ(ካቶሊኮችን ነው) ይልቅ እንዴት ለእግዚአብሔር ክብር እንደሚሆን ያስተማሩትን ዛሬም እኛም ማስተማር ስላለብን። አንደ ተሐድሶውያኑ በዘመናቸው ለእግዚአብሔር የሚገባውን ያንን ክብር የወሰዱ አካላት ነበሩ ብለው ተቃውመዋል። በዚህ ዘመንም የእግዚአብሔርን ክብር የሸፈነ አለ። ሻገር ብንልም አምልኩ ቢባል ምን እንደሚጨመር እስከማይታወቅ ድረስ የሚሰጥ ክብር(ኤጲፋንዮስ ኮሊሪዲያንን የተቃወመውን አይነት ላቅ ያለ ክብር ለፍጥራን መስጠት) ብዙ መንገዶች አሉ፤ ለድነታችን ብዙ መፍትሔ አለ። በማለት የክርስቶስ የማዳንን ክብር ዝቅ እስከማድረግ ስለደረሱ ነው። በቀላሉ የማናልፈው ነገር ብዙ መንገድ አለ በማለት በየምስባኩ የእግዚአብሔርን የማዳን ክብሩን የሚነቅልና የሰውን የመገናኛ ድንኳን ስለሚተክል ነው። በመጨረሻም በ16ኛው ክ/ዘ የነበረው የፀጋ ልዩነቶች ነበር። ለእኛም በዚህ ዘመን ፋፍቶና በዝቶ ተቀምጧል። ስለዚህ እኛ ክላሲካል ፕሮቴስታንት ነገረ ድነት ይሁን ሌላ አሁን ላይ ከእነሱ በኋላ በብዙ አካላት መካከል በማደጉ አሁን ላይ የምንቃወምበት ብዙ መሠረታውያን ነጥቦች ይኖሩናል። እኛም እንደ ተሐድሶውያኑ Soli Deo Gloria/ክብር ለእግዚአብሔር ብቻ/ ስንል ይህንን ጽሑፍ በቅዱስ አውግስጢኖስ በኑዛዜ መጽሐፉ ክፍል.10 ምእ.27 ቁ.38 ጸሎት እንቋጫለን፦ “ምነው ዘግይቼ አንተን ማፍቀሬ! ኦ ጥንታዊም አዲስም የሆንክ ውበት፥ምነው ዘግይቼ አንተን ማፍቀሬ !እነሆ አንተ በውስጤ እያለህ በፈጠርካቸው ነገሮች መካከል ያለ ማስተዋል ስጣደፍ አንተ ከእኔ ጋር ነበርክ፤እኔ ግን ካንተ ጋር አልነበርኩም። እንዚህ ነገሮች ካንተ አርቀውኛል፥ ሆኖም እነርሱም ባንተ ባይሆኑ ኖሮ መኖር ባልቻሉ ነበር።ድምፅህን ከፍ አድርገህ ጮህክልኝ፤ጠራኸኝም። ድንቁርናዬን በሃይልህ ከፈትከው። ጸዳልህን ልከህ ሸፈነኝ፤ አበራህልኝም፤ አይነ ሥውርነቴንንም ገፈፍከው።መኣዛህን ለእኔ ተነፈስክ፤ተንፍሼም ሳብኩት፤ ተከትዬህም ቃተትኩ። ቀመስኩህ፤ ተራብኩ፤ ተጠማሁም። ዳሰስከኝ ለሰላምህ ተቃጠልኩ።” እግዚአብሔርን ብቻ ፊት አድርገን መጓዝ ይሁንልን። አሜን! ለተጨማሪ ንባብና ጥናት ➞ God’s glory alone— the majestic heart of Christian faith and life: what the reformers taught . . . and why it still matters / By David VanDrunen.

Soli Deo Gloria/ክብር ለእግዚአብሔር ብቻ Read More »

ተሐድሶ በአጭሩ

ጊዜው ኦክቶበር 31፣ 1517 ነበር። በዚህ ወቅት ነው አንድ መነኩሴ የተነሳው። ይህ ወቅት በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ውስጥ ትልቅ መንፈሳዊ ቀውስ የነበረበት፤ ሥልጣናዊነት በቤተክርስቲያን ላይ ትልቁን ለጳጳጻቱ አድርጎ፣ መጽሐፍትን የመተርጎም ስራ የእነርሱ መብት ብቻ የሆነበትና ትምህርተ ድነት መጽሃፍ ቅዱሳዊ ማንነቱን ያጣበት 16ኛው ክፍለ ዘመን ነበር። በዚህም በአንዲት ትንሽ የጀርመን ትምህርት ቤት ውስጥ ለመጽሐፍ ቅዱስ ሕልውና ሲል የቤተ ክርስትያን በሮች ላይ የተወሰኑ አንቀጾችን ለመለጠፍ በሕይወት ዘመኑም ለመጽሐፍ ቅዱስ ሕልውና ዘብ ለመቆም ሩቅ መንገድ የሄደበት ጊዜ የጀመረው። እነዚያ አናቅጾች የለጠፈበት ምክንያት በዚህ ዘመን እኛ ለሥራ መግለጫ ሥፍራ አሳደን ለማንበብ እንደምንታትረው የቤተክርስትያኒቱ በር ብዙዎች ቀልባቸውን ስበው የሚያነቡበት ሥፍራ ተደርጎ ስለሚወሰድ ነበር በዚያ የለጠፈው። ባስቀመጠው 95 አናቅጽ ውስጥ የኢንደልጀንስን “በጥምቀቱ ጊዜ እንደነበረው አይነት ንጽህና” ከመስጠቱም በላይ ሰዎች ለሞቱ ወገኖቻቸው ሳይቀር ይህንን ክፍያ ከፍለው ከስቃይ ሊያድኗቸው እንደሚችሉ ተሰበከ። በካቶሊኮቹም ዘንድ ፑርጋቶሪ ማለትም ነፍሳችን ወደ ገነትም ሆነ ሲዖል ከመጣሏ በፊት የምትሆንበት ስፍራ ውስጥና በሕይወት እንቅስቃሴዎቻችን እያለን ስላጠፋው ስለኃጢአቷ የሚቆይበትን ጊዜ (ወደ መንግስተ ሰማይ ከመግባቱ በፊት) በሚገዛው ኢንደልጀንስ ማቀናነስ ይችላል የሚል የኑፋቄ ትምህርት ነበር። እንግዲህ ይህ ክስተት ምን ያህል ትክክለኛውን የድህነት መንገድ እንዳጣመመ ለመረዳት የአዲሲ ኪዳናችንን መጽሐፍ ገለጥ አድርገን ብንመለከት ቅዱስ ዮሃንስ በወንጌሉ እንዲህ አለ፦ ዮሐንስ 1¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯¹¹ የእርሱ ወደ ሆነው መጣ፥ የገዛ ወገኖቹም አልተቀበሉትም።¹² ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤ በማለት የመሰከረለት ድነት ለሕንጻ ማስጨረሻ በጳጳሳቱ በተዘየደው መላ ሕያው የመዳኑ መንገድ ተሻረ፤ ይህም ጳጳሳቱ ያልተገደበ ስልጣንና ህጸጽ የለሽ ማንነትን ለራሳቸው እንደወሰዱ በግልጽ ያሳየና ቃሉን ለፈለጉት አላማ ለማዋል እንደሚደፍሩ ያመለከተ ነበር። ነገር ግን ይህ አይነቱ ኢ መጽሃፍ ቅዱሳዊ አካሄድ በሁሉም ዘንድ ይሁንታን አላገኘም፤ እንደ ሉተር አይነቶቹን በቤተክርስቲያኒቱ ውስጥ የነበሩ ምሁራን አስነስቷል። በርግጥ ወደ ቤተክርስቲያኒቱ የተወረወረው የመጀመሪያው የተሃድሶ ፍላጻ ከሉተርም ቀደም ይል ነበር። ውስጥ የተነሳው ጆን ዊክሊፍ የጳጳሱን ያልተገደበ ስልጣን በመቃወሙና መጽሃፍ ቅዱስን ማንኛውም ሰው እንዲያነበው ወደ እንግሊዘኛ በመተርጎሙ ምክንያት በኑፋቄ ተወግዟል፤ ተከታዮቹም ከስደት በቃጠሎ እስከመሞት ድረስ መከራ ተቀብለዋል። ታሪኩ ሰፊ ነው በዚህ ማያበቃ ቢሆንም እኛ ግን በዚህ እናብቃ፦ በዚህ ዘመን ያለነው ከቅዱሳት መጽሐፍትና ከአበው ትምህርት ላልተቀዱ ትምህርቶች ጎን ሳንቆም ቅዱሳት መጽሐፍትን የሁሉ የበላይ አድርገን እንድንቀጥልና የቫሌንቲነስ ኑፋቄ የሐዋርያትን ትምህርት ከአፍላጦን ፍልስፍና ጋር ያገናኘ፣ የመርቅያን ኑፋቄ የሐዋርያትን ትምህርት ከስቶይሲዝም ጋር በመቀየጥ የተገኘ ነው እንደሚለው  ዛሬም እንደ ሉተርና ተሐድሶ አበው የምንቃወማቸውን ነገሮች ከራሳችን ሳይሆን ከመጽሐፍ ቅዱስና ከአበው ክታባት እንዲሆን መሆን አለበት። ከቶ ጥለን መቀጠል የለብንም። “ከሕገ ቤተ ክርስቲያን ቅጽርና ክልል ወጥታችሁ፣ የሕግ ክልል የሥርዓት ወሰን በሌለው ሜዳዊ ሕግ አውታሯን እንደበጠሰች በቅሎ ፈቃደ ሥጋችሁ እንዳዘዛችሁ ስትፏልሉ ትታያላችሁ። የሚወስናችሁ የሥርዓት አጥር ቅጥር፣ የሚገታችሁ የሕግ ልጓም ከማጣታችሁ የተነሣ የማኅበራችሁና የባህላችሁ ቁጥር በየቀኑ እየበዛ ሲሔድ ይታያል።”[1] ለማስተማር የሚነሳ ሁሉ ግለሰብ ከሁሉም አስቀድሞ ሐዋርያት ያስተማራትን የሃይማኖት ትምህርት ጠንቅቆ ማወቅ ይገባዋል።[2] ልክ ማርቲን ሉተር An Assertion of All the Articles (1520) እንደጻፈው፦ “[ከእኔ በላይ] የተማሩትን እነዚያን አውጥቼ ልጥላቸው አልወድም፣ ነገር ግን መጽሃፍ ቅዱስ ብቻ እንዲነግስ፤ በራሴም ይሁን በሌላ በማንም መንፈስ እንዳልተረጉመው፤ በእርሱ በራሱ መንፈስም እንደረዳው እፈልጋለሁ”[3] ከቶ አባቶችን ጥለን የምንቀጥለው ተሐድሶ የለምና ከዚህ ትምህርት ጋር የተቆራኘውን ክላሲካል ፕሮቴስታንት መኾን ያሻልና አንዘንጋ! ማጣቀሻ [1] አድማሱ ጀንበሬ፣ ኰኲሐ ሃይማኖት፣ ገጽ 160 [2] ሔኖክ ኢሳያስ፣ በእንተ ኑፋቄ፣ ገጽ 24 [3] Martin Luther, Assertio omnium articulorum M. Lutheri per bullam Leonis X. novissimam damnatorum (1520), WA 7:98.40–99.2.

ተሐድሶ በአጭሩ Read More »

መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ/Sola scriptura/ – ክፍል 2

የማይሳሳቱትን መጽሐፍት ማን ሰጣችሁ? እንዴትስ አወቃችሁ? በጥንቷ ሆነ በአሁኗም ቤተክርስቲያን ውስጥ ምናልባትም ዋና አከራካሪው ርዕሰ ጉዳይ ሚባለው የቅዱሳት መጽሓፍት ቀኖና ነው። በታሪካዊው ፕሮቴስታንቱም ላይ በተደጋጋሚ ከሚነሱና ዋና ከሚባሉ ጥያቄዎች መካከል ትላልቆቹን ሁለቱን ከፍለን እናንሳ፦ 1) ያለ ቤተክርስቲያን ምስክርነት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉት መጽሐፍት ራሳቸው እንዴት ትክክለኛና ስህተት አልባ መሆናቸውን እናውቃለን? 2) በምንስ ስልጣን ነው የቅዱሳት መጽሐፍትን ቀኖና ምንወስነው? የማይሳሳቱትን መጽሐፍት የማይሳሳት አካል ነው የሰጧችሁ? በመጀመሪያ ይሄን ጥያቄ ለመመለስ ከኦርቶዶክሶች እና ከካቶሊካዊያን ጋር ምን ላይ እንስማማለን? 1) እስትንፋሰ መለኮት እንዳለባቸው 2) ቤተክርስቲያን ለቅዱሳት መጽሓፍት ምስክር ነች፥ ቤተክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስን ተቀብላለች። ስለዚህ ቤተክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስን የማስተማር፣ የመጠበቅና፣ የመለየት ሃላፊነትና ስልጣን አላት። Post reformation reformed dogmatics vol 2 ለማይሳሳት(infalliable) ለሆነ ነገር ምስክር ለመሆን የማይሳሳት(infalliable) መሆን ይጠበቅበታል ማለት አይደለም። ወይም አንድ አካል የማይሳሳት ነው(infalliable ነው) ተብለን ለመቀበል የእርሱ ምስክር ግዴታ የማይሳሳት (infalliable) መሆን የለበትም። ለምሳሌ፦ ነቢያት የእግዚአብሔርን ድምጽ ይሰሙ ነበር ታዲያ ሊሳሳት ማይችለውን የእግዚአብሔርን ቃል ሊሳሳት በሚችል አእምሮአቸው ተቀብለውታል። ክላሲካል ፕሮቴስታንት ይሄንን ጨመር አድርገው ሲያስረዱ እንዲሁ ቤተክርስቲያን በቀኖና ጊዜ ለመጽሐፍቱን የስልጣን ምንጭ እየሆነች ወይም ሊሳሳት የማይችል ነገር እያደረገች አይደለም። ይልቁንም የእውነትን አስተምህሮ እያስተማረችና እየጠበቀች እንጂ። ይህ የእኛ የክላሲካል/ታሪካዊው/ ፕሮቴስታንት መሠረቶቻችን ናቸው። ታሪካዊ ሙግታችን ደግሞ ቤተክርስቲያን ታሪክ ውስጥ የመጽሐፍትን አይሳሳቴነት እንዴት እንደምንረዳ እንይ በተለይ ከቀኖና አንፃር፦ 2.1 አዲስ ኪዳን መጽሐፍት ቀኖና በአዲስ ኪዳን መጽሐፍት ቀኖና ጊዜ ቤተክርስቲያን እንደ መስፈርት አድርጋ ከተጠቀመቻቸው ነጥቦች ውስጥ፦ በዚህ ሁሉ ግን ለመጽሐፍቱ ቀኖና የቤተክርስቲያን አይሳሳቴነት በየትኛውም ጉባኤያት ላይ ለቀኖና መስፈርት ሆኖ አያውቅም። የሚገርመውም ደሞ ጉባኤያቱ ራሳቸው Local እንጂ አለም አቀፍ አይደሉም። ታሪካዊ ነን በሚሉ ቤተክርስቲያን በመካከላቸው የቆየ አለመግባባት ስለነበር ለብዙ አመታት የተዋቀረና ስሙንሙነት ያለው ቀኖና አልነበራቸውም። 2.2 የብሉይ ኪዳን ቀኖና ብሉይ ኪዳን መጻሕፍትን የተቀበሉት አይሁዳዊያን  ቢያንስ በ1ኛው ክፍለዘመን ጊዜ የተዘጋና የቆመ የመጻሕፍት ቀኖና ነበራቸው። ኢየሱስ ክርስቶስም በ ዮሐ5፥39 እና በሉቃ24፥44 ላይ ካለው ንግግሩ የታውቁ የህግና የነቢያት እንደነበሩ መናገር ይቻላል። ይሁንና እነዚህ አይሁዳዊያን መጽሐፍቱን እንደ የማይሳሳቱ አድርጎ ለመቀበል(infallible accept) ለማድረግ ምንም አይነት የማይሳሳት(infalliable) ሥልጣን ያለው አካል ሲጠቀሙ አናይም። እንደሙግቱ ከሆነ እነዚህ አይሁዳዊያን infallible የሆኑ የብሉይ መጽሐፍትን ስለተቀበሉ እነሱም የማይሳሳቱ(infallible) መሆን አለባቸው? ይሄ እንኳን ቀርቶ ሻገር ብለን ስናይ እኛ ሁላችን ጌታን ለማመን የማይሳሳት እውቀት(infalliable knowledge) እንኳን የለንም። ሊኖረንም አይገባም። ይሄ አጠቃላይ ሙግታችን ሥነ አመክንዮን እና ታሪካዊውን ክርስትና የሚጠብቅ ሙግት ነው። ስለዚህ የማይሳሳቱ መጻሕፍት ለመቀበል ሌላ የማይሳሳት ነገር(infallible) መሆን የለበትም። ይልቅ(Falliable list of infallible books) ማለታችን ታሪካዊ ሃቅ ነው። እኛም ይህንን ለመቀበላችን ምክንያት ብዙ ማለት ይቻላል። በአጭሩ ከክላሲካል ፕሮቴስታንት መሠረቶች መጽሐፍ ቅዱስን ብቻ ከመቀበል ውጪ ሌላ አማራጭ የለም። እግዚአብሔር ይርዳን!

መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ/Sola scriptura/ – ክፍል 2 Read More »

መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ/Sola scriptura/ – ክፍል 1

መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ማለት የቤተክርስቲያን ብቸኛው የማይሳሳተው ባለሥልጣን መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ነው። ይህን ስንል ግን ብዙዎች ተሳስተው የሚወስዱት ብቸኛ ባለስልጣን ነው ብለን ይመስላቸዋል። ይሄ ግን ስህተት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ የማይሳሳት ብቸኛ ባለሥልጣንና ዳኛ ማለታችን መሆኑን ይዘነጉታል። ይሄን ልዩነት እንዴት ተቀመጠ ቢባል በቤተክርስቲያን የተለያዩ ሊሳሳቱ የሚችሉ ነገር ግን ሥልጣናት አሉ ከነዚህም ለምሳሌነት፦ ክሪዶች፣ ካታኪዝም፣ ኮንፌሽኖች፣ ጉባኤያት አንዳንዶቹ ናቸው። እነዚህም ደግሞ ሊሳሳቱ የሚችሉና በመጽሐፍ ቅዱስ መታረም ሚችሉ ናቸው።(የቤተክርስቲያን አባቶች ይሄን መስፈርት ሲጠቀሙ እንደነበር በብዙዎቹ ዘንድ የታወቀ ነው።) ስለዚህ እኛ ክላሲካል ፕሮቴስታንት ከማንላቸውና ሶላ ስክሪፕቹራን በተሳሳተ መልኩ ተረድተው የሚተቹ ሰዎች ሁሉም አስተምህሮ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ግልጽ በግልጽ መቀመጥ አለበት የሚል አስተምህሮ ነው። ስለዚህ ሌሎች ጉባኤያት ሆኑ አበው አያስፈልጉም የሚሉ ናቸው ይሉናል። እኛ ግን የምንለው ከሐዋርያት በኋላ ያሉትን ጉባኤያት ሆነ አባቶች እንቀበላለን።[1] መቀበላችን እነሱንም ጨምሮ በቤተክርስቲያን ያሉ ባለሥልጣን አካላት ሊሳሳቱ የሚችሉ ናቸው። ስለዚህ በሚሳሳቱና በሚያስተምሩት በመጽሐፍ ቅዱስ ሥልጣን መታረም አለባቸው የሚል እንጂ። በዚህ ምክንያት ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ የሁሉም ዳኛና የሁሉም መሠረትና መዛኝ ማለት ነው። ታሪካዊው ፕሮቴስታንት መጽሐፍ ቅዱስ ብቻን ስናነሳ ሁለት ዋና ዋና ነገሮችን ስለመፅሃፍ ቅዱስ እናነሳለን፦ 1) የመጽሐፍ ቅዱስ ባህርይ መጽሐፍ ቅዱስ እስትንፋሰ መለኮት የሆነ የጌታ ቃል ነው። ከእግዚአብሔር መሆኑ ደግሞ በባሕሪው  የተለየ ያደርገዋል(ontologically unique) ይህንንም በ 2ጴጥ 1፥21 እና በ1ጢሞ 3፥16 ተገልፆ እናገኛለን። መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ንግግርና የእግዚአብሔር ቃል ነው። ሮሜ 3፥2 ማቴ19፥4-5 ላይ ተገልፆ እናገኛለን።የእግዚአብሔር ቃል ስለሆነ ፈጽሞ ሊሻር እንደማይችል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐንስ 10፥35 ላይ፦ “መጽሐፉ ሊሻር አይቻልምና እነዚያን የእግዚአብሔር ቃል የመጣላቸውን አማልክት ካላቸው” በማለት እንደማይሻር አጥብቆ ይናገራል። እግዚአብሔር ሊሳሳት አይችልም መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ የእግዚአብሔር ቃል ነው ስለዚህ መጽሃፍ ቅዱስ ሊሳሳት አይችልም። ይህንን ሐሳብ ቅዱስ አውግስጢኖስ ዘሒፖ(Augustine of Hipo) በመደገፍ መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ዝንፈተ እውነት የሌለበት እንደሆነ ይናገራል፦ I have learned to yield this respect & honour #only to the scripture, of these #alone do I most firmly believe that completely #inerrant (free from error)—-Letters, 82:3 ትውፊትም, የአምልኮ ሥርዓቶች ሆኑ ጉባኤያት ስህተት ሊገኝባቸው ይችላል። ምክንያቱም የትውፊት አስተላለፋቸውን በተመለከትን ጊዜ በሰዋዊ አተረጓጎም, በተፈጥሮዋቸው የሚሳሳቱ ስለሆኑ እና በባህል ጫና ውስጥ የታሰረ በመሆኑ ትክክለኛውን መልዕክቱ የተበላሸ ሊሆን ይችላል። በተለይም ትውፊት እና የቤተክርስቲያን ሥርዓቶች በዘመናት መሐል የተለያየ ብርዘት እና ለውጥ ሊገባባቸው የሚችሉ ናቸው። ለምሳሌ ያክል በካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የጳጳሳቱ መብት እያደገ እየተሻሻለ በመምጣት ወደ ፖፑ አይሳሳቴነት በመጨረሻም ወደ ስህተት መምጣታቸው የሚዘነጋ አይደለም። በተጨማሪም በነገረ ማሪያም ያላቸውን ዶክትሪን እጅጉን እየለጠጡ በመምጣታቸው ወደ Immaculate conception(አንዳንድ ኦርቶዶሳውያንም ይህንኑ አስተምሮ ይቀበላሉ) እንዳመሩ እንመለከታለን። የፑርጋቶሪ ጽንሰ ሐሳብ ሌላው የሚጠቀሱ ጉዳዮች ናቸው። በኦርቶዶክሱም ሆነ በካቶሊኩም የሚስተዋለው የመጽሐፍ ቅዱስ የቀኖና ችግር ስንመለከት ትውፊት በዘመናት መካከል ሊቀያየር እና ሊበከል የሚችል ጉዳይ ሁኖ እናገኘዋለን። መጽሐፍ ቅዱስ በባህሪው  ልዩ መሆኑ ስልጣኑ ደግሞ ከሌሎቹ የተለየ እንዲሆን ያደርጋል። ይህንን በቀጣዩ ነጥብ ላይ እንመለከተዋለን። 2) ሁለተኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ሚና ነው። መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል ስለሆነ  በቤተክርስቲያን ካሉ ከሁሉም ባለስልጣናት በላይ ስልጣን አለው። በማር 7፥ 9-13 ና በማቴ 23፥2-3 ኢየሱስ ከአይሁድ ትውፊት በላይ ቅዱሳን መጽሐፍት ስልጣን እንዳላቸው ይናገራል። እንዲያው ለምን ቅዱሳት መጻሕፍት ከትውፊቶቻችን መብለጣቸው በመፅሃፍት ውስጥ በግልፅ አልተነገረንም ሚል ጥያቄ ቢነሳ መልሱ ሚሆነው ሁሉም ነገር ቃል በቃል ሊጻፍ አይገባውም ነው። ይልቁኑ ጳውሎስ ለገላቲያ ቤተክርስቲያን በጻፈው መልእክት ከተነገረን ወንጌል ሚለይ የትኛውም አይደለም ምድራዊ ሰማያዊ አካል እንኳን ቢሆን የተረገመ ይሁን ይላል። ይህም መጽሐፍ ቅዱስ በሁሉም ላይ ባለሥልጣን ሚሆነው እግዚአብሔር በሁሉም ላይ ባለሥልጣን ስለሆነ መሆኑን ያስረዳናል። ስለዚህ በጳውሎስ ስብከት መሰረት የትኛውም ስብከት በመጽሐፍ ቅዱስ ተመዝኖ ነው ተቀባይነት ሊኖረው ሚገባው። ቤተክርስቲያን ልትሳሳት ማትችል ነችን? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በ1ቆሮ 11፥2 ና በ2ጢሞ 2፥15 ላይ ሐዋሪያት በቃላቸው እንዳሰተማሩ ተፅፏል። ይህን ትውፊት ከሌላው ትውፊት ልዩ ሚያደርገው ሐዋሪያት በህይወት በነበሩበት ዘመን የተነገረ መሆኑ ነው። ምንም እንኳ ሐዋሪያት በቃላቸው ያስተማሩት ሊሳሳት ማይችል ትምህርትም ቢሆንም ነገር ግን በተነገረው ትውፊት infallibility እና ያ ትውፊት በተላለፈበት መንገድ መካከል ልዩነት አለ። ትውፊቱ የተላለፈበት መንገድ infallible አይደለምና። አዲስ ኪዳን መጻሕፍት ውስጥ ስለቤተክርስቲያን ሥልጣን ስራ ባህሪ በግልፅና በጥልቀት ተጽፎ ብናገኝም ቤተክርስቲያን ልትሳሳት ማትችል መሆኗን ሚናገር ክፍል አንድም የለም። ይሄም ብቻ ሳይሆን የቤተክርስቲያንን infallibility አገናኝተን ልንተረጉምበት የምንችለው አንዳች የሐዋሪያት ጽሑፍ የለንም። ይልቁኑ እነዚህ ትምህርቶች በቤተክርስቲያን ታሪክ አርፍደው የመጡ ናቸው።(ቤተክርስቲያን በዘመናት ተሳስታለች ማለት ግን በፍጹም ጠፍታ ነበር ማለታችን አይደለም። በዚህ ርዕስ ላይ ወደፊት የምንላችሁ ነገር ይኖራል) ስለዚህ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጪ ድህረ ሐዋሪያዊ የሆነ ሊሳሳት የማይችል ምንም አይነት ሥልጣን ያለው አካል የለም። ስናጠቃልል Sola scriptura/መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ/ ፍፁም እምነታችንን ሊሳሳት በሚችል ምድራዊ አካል ሳይሆን ሊሳሳት በማይችለው ፍፁም በሆነው በእግዚአብሄር ላይ እንድናደርግ ሚያመለክት ትምህርት ነው። ማጣቀሻ 1] 39 Articles of Religion, v 8 ለተጨማሪ ንባብ 1] Gavin Ortlund, What it means to be Protestant. 2] Keith A. Mathison, The shape of Sola Scriptura

መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ/Sola scriptura/ – ክፍል 1 Read More »

Scroll to Top